. ብሄር ብሄረሰብ በሚለው መጠይቅ ስር ”ኢትዮጵያዊ” የሚል የለም።
በአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ሆነው እንደሚቆጠሩ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት አበራሽ ታሪኩ የህዝብና ቤት ቆጠራውን ለማከናወን እየተደረገ ስላለ ቅድመ ዝግጅት እና ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለህዝብና ቤት ቆጠራው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ወደማጠናቀቁ እየተቃረብን ነው ብለዋል።
በሰው ሀይል፣ በጀት፣ ስልጠና፣ ሎጅስቲክስ እና መሠል ዘርፎች ቅድመ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው ያሉት ወ/ሪት አበራሽ የካርታ ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ታብሌቶች የመጫን ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በስልጠና በኩል እስካሁን ለተለያዩ ባለድርሻዎች እና የአሰልጣኞች ስልጠና በሶስት ዙር መሰጠቱን የገለፁ ሲሆን አራተኛውና የመጨረሻው ዙር ስልጠና ለቆጣሪዎችና ተቆጣጣሪዎች በቅርቡ እንደሚሰጥም ም/ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ለአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ የዝግጅት ስራውን ጨምሮ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡ በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ብር በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለክልሎች ተልኳል ተብሏል፤ ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መቅረቡም ተገልጿል ።
ለቆጠራው አገልግሎት የሚሰጡ 180 ሺህ ታብሌቶች ተዘጋጅተው 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ላይ መተግበሪያዎችን ሙሉ በሙሉ የመጫን ስራ ተሰርቷል።
በህዝብና ቤት ቆጠራው ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዴት ይስተናገዳኑ ተብለው ለተጠየቁት ወ/ሪት አበራሽ ሲመልሱ ተፈናቃዮቹ ባሉበት ሆነው ይቆጠራሉ ለዚህም ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
80 ከሚሆኑ መጠይቆች አንዱ የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄን በተመለከተ መላሾች ብሄር ብሄረሰባቸውን በትክክል እንዲናገሩ የግንዛቤ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያዊ የሚለው የዜግነት እንጂ የብሄር ብሄረሰብ መገለጫ ባለመሆኑ በዚህ ስር አለመካተቱ ተነግሯል።
ለህዝብና ቤት ቆጠራው ስኬት መላው ህብረተሰብ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ወ/ሪት አበራሽ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29- ሚያዚያ 20/2011 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ ይካሄዳል።
በድልነሳ ምንውየለት