ከፈተና ወደ ልዕልና የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ መሪ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን አሁን ላለችው ኢትዮጵያም መሪ ሀሳብ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።
እንደአገር ተንከባለው በመጡና ፖለቲካው በወለዳቸው ሳንካዎች በብዙ ችግሮች ስንታመስ ከርመናል ይሄ ሁላችንንም የሚያግባባ የፈተና ጊዜ ነው።
ከትላንት ተምረን፣ በችግሮቻችን ላይ የበላይ ሆነን፣ በሀሳብና በመሰል ተግባቦት ላይ አንድ አይነት አቋምን በመያዝ፣ በመለያየትና በመነጣጠል እንደ አሳደጅና ተሳዳጅ መተያየታችንን ትተን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናን የፈጠሩብንን ተግዳሮቶች ተቆጣጥረን፣ያደፈውን ፖለቲካ ወለድ ችግሮቻችንን የምናጠራበት መጪ ጊዜ ከፊታችን ያለ ይመስለኛል።
መንግሥት ከያዘው የማይናወጥ አቋምና ተስፋና ከፍታ ከናፈቀው ሕዝብ ጋር በጋራ አብረን የምንፈጥረው የመታደስ ዘመን ያለ ይመስለኛል።
አገራዊ ምክክሩ ፍሬ አፍርቶ፣ አንድ ኢትዮጵያን በአንድ ሀሳብ የምናቆምበት ጊዜ ሩቅ ይሆናል ብዬ አላስብም። ከዚህ እውነት በመነሳትም መጪውን ጊዜ የድል እና የልዕልና ብለን ልንፈርጀው እንችላለን።
በዚህ ከፈተና ወደ ልዕልና እሳቤ በዲሞክራሲ እሳቤ፣ በኢኮኖሚ መስክ፣ በፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም ደግሞ በውጪ ግንኙነታችን ላይ መንግሥት እየወሰደው ያለውና ወደፊትም ሊወስደው ያቀደው የሥርዓት ለውጥ አለ።
እኚህ የሥርዓት ለውጦች ደግሞ ለብዝኃነትና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ደግሞ በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት የአገርንና የዜጎችን ክብርና ፍላጎት ቅድሚያ በሰጠ መልኩ መስተናገዱ የላቀ ድርሻ አላቸው።
በተለይ ደግሞ ከአባላቱ ቁጥርና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ ፌደራላዊ ሥርዓት የዘረጋ በመሆኑ ወደ ልዕልና የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥነዋል ባይ ነኝ። ጉዞው ትልቅ አገርና ትልቅ ማኅበረሰብ እንደፈጠሩ ስኬታማ አገራት በፈተና ውስጥ ማለፉ ግድ ነው። ታሪኮቻችን መነሳትና እንደ አዲስ ማበብ የሚጀምሩት ከዚህ ፈተና በኋላ ባለው የመነሳት ጊዜ ውስጥ ነው። እስከዛው ግን የምናልፍባቸው እንቅፋታማ መንገዶች ይኖራሉ።
እንቅፋቱን ከመንገዳችን ላይ ዞር እያደረግን አሊያም ደግሞ ሌላ አመቺ መንገድ እየፈጠርን ወደ ፊት ለመሄድ ከእኛና ትልቅ ሀሳብ ካነገበው ብልጽግና ፓርቲ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ፈተናና ልዕልና የአንድ ሳንቲም ጥንድ መልኮች ናቸው። ልዕልና እንዲመጣ ፈተና ግድ ነው።
ብርሃን ከጨለማ ቀጥሎ እንደሚመጣ ሁሉ የእኛም ተስፋና ከፍታ እስከዛሬ ባጣናቸውና በተንገላታንባቸው ፈተናዎቻችን በኩል የሚመጣ እንደሆነ ስነግራችሁ ከልቤ ነው። ብዙ ጥያቄዎች ባሏት ድሀ አገር ላይ ይቅርና ብዙ ነገሮቻቸው ልክ በመጣ አገራት ውስጥም ችግሮች ይፈጠራሉ። የእኛ ከነሱ የሚለየው የነሱ ችግር ከዛሬ ወደ ነገ የሚሄድ አይደለም።
አገርና ሕዝብ እስኪጎዳ ዝም ብለው አያዩም ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለመስጠት የሚተጉ ናቸው። እኛ ጋ ሲሆን ግን ሌላ ነው..ችግሮቻችን እስኪጎዱን፣ እስኪያፈርሱን፣ ታሪክ እስኪያበላሹ የምንጠብቅ ነን። አገርና ሕዝብ ላይ ጥቁር ጠባሳ እስኪያደርሱ ዝምታን የምንመርጥ ነን። ለመወያየት የምንፈልገውም ብዙ ጉዳት ካደረሱ በኋላ መሆኑ ነው። እስካሁንም ዋጋ ሲያስከፍለን ያለውም ይሄ ልምድ ነው።
የጋራ ታሪክ ለመሥራት ባለፈው የፖለቲካ ሥርዓት የተበላሹ ችግሮቻችንን ማስተካከል ይኖርብናል። የጋራ አገር ለመገንባት አንድ የሚያደርገንን የአስተሳሰብና ዓላማ መር ፖለቲካ መገንባት ግድ ይለናል። በአብሮነት ለመቆም እንደ አገር ተነጋግሮ መግባባት ይጠበቅብናል። እነዚህ ሁሉ የበረከት ፍሬዎች ደግሞ ዝም ብለው አይመጡም።
ፖለቲካችንን ብናየው፣ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ብናየው በውሸትና በማስመሰል ድራማ የተቀመረ ነው። ይሄን እውነት ሳይሆን እውነት መስሎ በትውልድ ልብ ውስጥ የተቀበረውን የማስመሰል ድራማ ለመቀየር ደግሞ መልፋት ይጠይቃል። አሁን ላይ እየተፈጠሩብን ያሉና እንደ ፈተና የምናያቸው ችግሮቻችን እነዛን የማስመሰል ድራማ በእውነት ለመቀየር መንግሥት እየሄደባቸው ያሉ መንገዶች የፈጠሩት እንጂ አካሄዱ በራሱ ችግር ሆኖ አይደለም።
የሥርዓቱ ወደ ልክ መምጣት የፈጠረው ነው። አንድ የተሳሳተ ነገር ልክነትን ሲያገኝ ዝም ብሎ አይደለም..የሚፈርሱ፣ ቁጣ የሚያስነሱ፣ ተቃውሞ የሚጭሩ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ምክንያቱም የዚያን ነገር እንደዚያ መሆን የሚፈልጉ ኃይሎች ስላሉ ዝምታን አይመርጡም። ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ ጊዜው የልዕልና ነው።
አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትመጣ፣ ኢትዮጵያ ልትፈጠር ምጥ ላይ ናት። ከፊታችን የምናያቸውና የምንሰማቸው አገራዊ ችግሮች ኢትዮጵያን ሊፈጥሩ የመጡ ምጦች ናቸው። የምጥ መጀመሪያ እንደሆኑም ልናስባቸው ይገባል። እርግጥ ነው በነዚህ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙ ነገር አጥተናል፣ ብዙ ነገር ሰምተን ባይሆኑ የምንላቸው ብዙ ነገር ሆነዋል ግን ሊነጋ ሲል እንደሚጨልም ሁሉ ከፍ ልንል ዝቅ ያልን እንደሆነ ልናስብ ይገባል። መንግሥት ከፈተና ወደ ልዕልና ብሎ የእያንዳንዳችን ነገ በሚያሳይ ትልቅ ሀሳብ መነሳቱ የማይታበል ሐቅ ነው።
ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የዚህን ሀሳብ እውነትነት የሚያረጋግጡ በርካታ ለውጦችንና በዛው ልክ ወደ ልዕልና እየሄድን እንደሆኑ የሚያመላክቱ ተስፋ ሰጪ ለውጦችንና ይሄንኑ የሚገዳደሩ ነውጦችን አይተናል። በነዚህ ሁለት እውነቶች ላይ ተረማምደን ነው አዲስ የምትፈጠረውን ኢትዮጵያ የምንጠብቀው። ችግሮቻችን ወደ ከፍታ የምንሄድባቸው የልዕልና ድሮቻችን ናቸው። እነኚህ የልዕልና ድሮች እንዳይበጠሱና እንዳይላሉ ደግሞ የፈተና መኖር ግድ ይላል።
አሁናዊ ፈተናዎቻችን ነገን ለመሥራት፣ መጪውን ጊዜ አርቆ ለማየት መንገድ ጠራጊዎቻችን እንጂ ሌላ ምንም አይደሉም። መንግሥት ከፈተና ወጥቶ መጪውን ጊዜ የልዕልና ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ እንደሆነ የሚያጠራጠር አይደለም። ያለፉት ጊዜያቶች መንግሥት ራሱን ፈትሾ በአዲስ ኃይልና አብዮት እንዲነሳ ያደረጉት እንደሆኑም አምናለሁ።
እየወሰዳቸው ያሉ ዕውቀትንና አመክንዮን መሠረት ያደረጉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፍተሻዎቹ መጪውን ጊዜ በብርሃን እንድናይ ያደረጉ ናቸው።
በጀመርናቸው የጋራ ሀሳቦችና ለውጦች፣ በጀመርናቸው የአንድነት መንፈስና ኃይል ፈተናን ተቋቁመን ወደ ፊት ከመሄድ የሚያግደን አይኖርም። እስከዛው ግን የሚያደክሙና ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎችን ልናስተውል እንችላለን በነዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ወደፊት ለመሄድ ኃይል እያገኘን እንደሆነና የጋራ ታሪክ እየጻፍን እንደሆነ ቢታወስ መልካም ነው። ፈተናን እየሸሸን መለወጥ አንችልም። ዝቅታን እየጠላን ከፍ ማለት አይታሰብም።
የተፈጥሮ ቀመር በሁለት ተቃራኒ እውነቶች ውስጥ የቆመ ነው። ከፈተና ወደ ልዕልና የሚለው ሀሳብ ደግሞ ይሄን የተፈጥሮ እውነት ሸጋ አድርጎ ይገልጸዋል። አሁናዊውን የአገራችንን ሁኔታ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ገላጭ ሀሳብ አለ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም በፈተና ውስጥ ወደ ድል እየሄድን እንደሆነ ስለማምን፡ ተግዳሮታችን ብዙ መንስኤዎች አሏቸው።
አሁን በአሁን የሆኑ ወይም ደግሞ ቅርብ ጊዜ የፈጠራቸው አይደሉም። ከትላንት ይዘናቸው የመጣናቸው ብዙ ችግሮች አሉ። እኔነት የወለዳቸው የራስ ወዳድነት ችግሮችም አሉብን። ፖለቲካውና ፖለቲከኞቻችን የፈጠሯቸው፣ ተነጋግሮ ባለመግባባት ያመጣናቸው በርካታ ችግሮች አሉብን።
እነኚህ ብቻ አይደሉም አገር ለማፍረስ የተማሩ ምሑራን የፈጠሯቸው፣ ልዩነትን ለማስፋት ለዚህ ዘመን በማይመጥን አካሄድ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የፈበረኳቸው ችግሮች አሉብን። እነኚህ ብቻ አይደሉም ታሪክ ለማበላሸት፣ ወንድማማችነትን ለማጠልሸት ውጪ አገር ተቀምጠው በኮምፒውተር ቁልፍ የሐሰት ወሬ የሚነዙ፣ ቀለብ እየተሰፈረላቸውና
ረብጣ ዶላር እየፈሰሰላቸው የአገራቸውን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ከጠላት ቡድን ጋር የተሰለፉ እኚህ ሁሉ አሉብን ። በነዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ ተነጋግሮ አለመግባባት፣ በሀሳብ የበላይነት አለማመን፣ ከሳይንሳዊ እውነት ይልቅ በይሆናል መጓዝና የደቦ ፍርድ ሲታከልበት የአገራችንን ስቃይ አስቡት።
መንግሥት ከነዚህ ሁሉ ጋር ነው ግብ ግብ የገጠመው። ጠንካራና ራስ ገዝ አገር ለመፍጠር ከላይ የጠቀስኩላችሁ ስቃይ ፈጣሪ አካሄዶች ሁሉ መፍረስ አለባቸው። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ የምንፈጥረው ተዓምር የለም።
አሁን ላይ መንግሥት እነዚህን የአገር ጠንቆች በመዋጋት ላይ ነው፣ እነዚህን ለዘመናት አሳንሰውን ያሉ የጋራ ጠላቶች በማውደም ላይ ነው። ይሄ ሲሆን ደግሞ ፈተና የሚኖር ሲሆን ጊዜ መፍጀቱም አይቀሬ ነው። ከነዚህ መከራና ስቃዮች በኋላ፣ ከነዚህ የአገር ጠንቆች መፍረስ በኋላ ያለው ጊዜ ነው የልዕልና ጊዜ። መንግሥት ከፈተና ወደ ልዕልና ሲል የብልጽግና ፓርቲን አንደኛ ጉባኤ የጀመረው በዚህ ምክረ ሀሳብ እንደሚሆን አምናለሁ።
ወደ ልዕልና ለመሄድ ጎዳናችንን ያጠበቡ፣ መንገዳችን ላይ የተቀመጡ እንቅፋቶችን ገለል ማድረግ አለብን። የሁላችንንም የጋራ አገር ለመፍጠር የጋራ ችግሮቻችን እልባት ማግኘት አለባቸው። የጋራ ችግሮቻችን እልባት የሚያገኙት ደግሞ በጋራ ስናስብና በጋራ ስንቆም ነው። አንዳችን ችግር ፈጣሪ ሌላችን ችግር ፈቺ በመሆን የምናመጣው ለውጥ የለም። ነውጥና ለውጥ እጅግ የተራራቁ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው።
እኛ አገር ብዙ ነገሮች ተምታተዋል..በነውጥ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የምንሞክር ብዙዎች ነን። በጦርነት ውስጥ ሰላም ለማምጣት ለዘመናት ተጉዘናል። በመገፋፋት ውስጥ አብረን ለመቆም ብዙ መክረናል፣ ብዙ ዘክረናል። አሁንም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ነን። ከዚህ ኋላ ቀር አስተሳሰብ እስካልወጣን ድረስ ልዕልናችን ይዘገያል እንጂ አይፈጥንም።
ልዕልናችን እንዲፈጥን፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ እንዲመጣ የሰላም ስፍራው መነጋገር መደማመጥና ሰላም ብቻ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል። የተራመድንባቸውን እኩይ ጎዳናዎች መድገም የለብንም። ከዘርና ከጎሳ አድሎ የጸዳ ትውልዱ የሚሄድበትን አዲስና አይነተኛ መንገድ ልናሳየው ይገባል። እንደመንግሥት ደግሞ እኚህን የልዕልና ጎዳናዎች እየጠረገ ነው እላለሁ። በፈተናዎቻችን ላይ ተረማምደን ከፍ የምንልባቸው የድል ማማዎች እየተፈጠሩ ነው።
ተስፋችንን የሚነግሩ፣ ከፍታችንን የሚያበስሩ ምልክቶች እየታዩ ነው። እዛም እዚም የምንሰማቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ችግሮች በድላችን ዋዜማ የተከሰቱ እንደሆኑ በማሰብ ወደ ፊት መራመድ እንጂ ተስፋ ለመቁረጥ እድል መስጠት የለብንም። ከሁሉም በፊት አንቀው ከያዙን አፍራሽ አስተሳሰቦች መውጣት አለብን። በትላንት አስተሳሰብ ዛሬን መኖር አንችልም።
ዛሬ ለራሱ የሚሆን አዲስ አስተሳሰብ ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ላይ ከአንድነትና ተነጋግሮ ከመግባባት ውጪ አገራት አርነት የላቸውም። ችግሮቻችን በምንም ይምጡ እንዴትም ይከሰቱ መንግሥትና የሚመለከተው አካል ተነጋግሮ አንድ መሆንን መልመድ ያስፈልገዋል።
ታሪኮቻንን ብንገልጣቸው ከጦርነትና ከኃይለኝነት ውጪ ሌላ ነገር የላቸውም። አሁን የናፈቀን በሀሳብ ማሸነፍ ነው። አሁን ላይ አገሬ የናፈቃት ተነጋግሮ መግባባት ነው። ስለሆነም መጪው ትውልድ ሲገልጠው የሚያገኘውን ደስ የሚል ነገር እንዲያገኝ በመነጋገር የሚያሸንፍ አዲስ ታሪክ እንጻፍ።
ጦርነት እኮ ማንም የሚያደርገው ተራ ነገር ነው። መግደል፣ ማሰቃየት ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ናቸው። አሁን ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የምንሰጥበት፣ ከኃይል ይልቅ ለድርድር በራችን የሚከፈትበት ጊዜ ነው።
አሁን የሚያስፈልገን ይሄ ነው። በአገራችን ውስጥ ያልሞከርንው ነገር ይሄ ነው..ሁሉንም ሞክረን አይተነዋል እስኪ አሁን ደግሞ በዚህ አዲስ መንገድ እንጓዝ። በፈተና ውስጥ ከፍ ወደሚያደርገን ትብብር እናቅና። ከፈተና ወደ ልዕልና ማለት ይሄው ነውና! ሰላም
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014