ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ከተመሠረተ ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን ጉባኤውን ሰሞኑን አካሂዷል፤ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት እና ምክትሎቻቸውን እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።
ከስብሰባው በኋላ የተለያዩ ስሜቶች የተንጸባረቁ ሲሆን፣ ትኩረቴን የሳበው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እንዲሁም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ያስተላለፉት መልዕክት ነው።
አቶ ሙስጠፌ በፌስቡክ ገጻቸው በእንግሊዝኛ ያሰፈሩትን ወደ አማርኛ ሲመለስ ፡- “የፓርቲውን ምክትል ፕሬዚዳንትነት ወንበር ፤ ሶስት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ወንበር ፤ 23 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ወንበር፤ ሶስት የሚኒስትሮች እና ሶስት የሚኒስትር ዴኤታዎች ወንበሮች በመያዛችን ፖለቲካችን ስኬታማ ሆኗል።
አሁን ዳር ተመልካች አይደለንም ፤ ማዕከላዊ ተሳታፊ ነን”፤ የሚል ነው። ከንግግሩ መረዳት እንደሚቻለው ፤ ርዕሰ መስተዳድሩ የድል ስሜት ተሰምቷቸዋል። ቢሰማቸውም ትክክል ነው። ምክንያቱም የሶማሌ ክልል ሕዝብ ለዓመታት ከማዕከላዊው መንግሥት ፖለቲካ ተገልሎ ፤ ክልሉን የሚመራው ገዢ ፓርቲ አጋር ፓርቲ እየተባለ ለአስርት ዓመታት የዳር ተመልካች ሆኖ ቆይቷል።
የብዙው የክልሉ ልሂቃን የፖለቲካ ትግልም ወደ ማዕከሉ በመጠጋት እና ወሳኝ ቦታ በመያዝ ላይ ያጠነጠነ ነበር። ይህ ግን በዘመነ ኢሕአዴግ ቀላል አልነበረም። ከሶማሌ ሕዝብ በቁጥር የማይተናነሰውን የትግራይ ሕዝብን የሚወክለው ሕወሐት ሥልጣኑን እና ሀብቱን በሙሉ ተቆጣጥሮ እነ ሶሕዴፓ ፤ አብዴፓ በመናጆነት እንዲያገለግሉት ብቻ ነበር የፈቀደላቸው። ለውጥ ተከስቶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት ካስተካከላቸው ነገሮች መካከልም አንዱ ይሄን ነው። ገዢ እና አጋር ፓርቲ የሚባል ነገር የለም ተባለ። ፓርቲውም እንደ አዲስ ራሱን አደራጀ። ይሄኔ የቀድሞዎቹ አጋር ፓርቲዎች ወደ ማዕከላዊው መንግስት ስልጣን ተሳቡ። ነገሩ ቀላል የሚባል እርምጃ አልነበረም። ይህ የብልጽግና ፓርቲ እርምጃም ነበር ከሕወሐት ጋር መሠረታዊ መለያየት እንዲከሰት ምክንያት የሆነው። አሁን ብልጽግና ፓርቲም ሆነ አቶ ሙስጠፌ
እና መሰሎቻቸው የቀድሞ አጋር ፓርቲ አባላት ደስተኛ የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሁንና ቀጣዩ እና መሠረታዊው ጥያቄ መሆን ያለበት ሁሉም የገዢው ፓርቲ አባላት፣ ሁሉም ባለድርሻዎች ወደ ማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን የተሳቡትን ያህል አጀንዳዎቻቸውንስ ወደ ማዕከላዊ ነጥብ መሳብ ችለዋል ወይ የሚለው ነው። አሁን እንደሚታየው ከሆነ አጀንዳዎችን ወደ መሐል በማምጣት እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ በመመራት ረገድ ብዙ ሥራ ይቀራል። የአገሪቱ ፖለቲካ አሁንም ጽንፍና ጽንፍ እንደረገጠ ነው። ለማቻቻል እና ለማመቻመች ጥረት ከሚያደርገው ይልቅ ገመዱን የሚወጥረው አካል ይበዛል። የሕወሓት መገለጫ የሆነው እና ብዙ ጣጣ ውስጥ የከተተን ይህ የጽንፈኝነት ባህሪ ነው። አሁንም ብዙዎች ይህንን መስመር ይከተላሉ። ላለመስማማት የመስማማት ስምምነት ላይ የደረሱ ይመስላሉ። ሰጥቶ መቀበል እንደ ከሀዲነት መቆጠር ጀምሯል። ማመቻመች አድር ባይነት ነው ተብሏል። ይህን ሁኔታ የአብን አመራር የሆነው ጋሻው መርሻ በፌስቡክ ገጹ ሰሞኑን ባሰፈረው ጽሑፍ በሚገባ ገልጾታል። ጋሻው ፤- “ወያኔ የፈጠረችልን ጠላት አንሶን ተጨማሪ ጠላት ፍለጋ መባዘን፣ እንደ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጋር እንድንጋጭ ጥላቻን መጥመቅ፣ ዘለፋ እና ስድብ፣ ጩኸትና መደናቆርን እንደ ፖለቲካ አዋቂነት መቁጠር፤ ተው እንረጋጋ ማለትን እንደ ተላላኪነት መፈረጅ፣ ስክነትን እንደ ተንበርካኪነት፣ መረጋጋትን እንደ ሽንፈት መረዳት የበዛበት፣ ፖለቲካችን የአልፎ ሂያጅ እጅ ገብቶ የሚወጣበት ሆኖ ተቸግረናል።›› ሲል ይገልጻል።
አያይዞም ‹‹ትልቅ አጀንዳ ይዘህ በዋናው መንገድ ስትራመድ መናኛ አጀንዳ ይዞ ከውስጥ ለውስጥ መንገድ በመውጣት ጃም መፍጠር እየተለመደ መጥቶ ባህል ሊመስል ጫፍ ደርሷል። ተው ባይ ሽማግሌ የማይከበርበት፣ አስታራቂ የሚወገዝበት ክፉ ጊዜ ላይ እንገኛለን። ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎች ባላዋቂ ኩታራ የሚዘለፉበት ምን አይነት ጉድ እንደገጠመን አላውቅም። ብቻ ልቦና ይስጠን።” ይለናል።
ጋሻው ይህን የጻፈው ስለ አማራ ፖለቲካ በሰጠው ሂስ ላይ ቢሆንም፣ ተግባራዊነቱ ግን በሁሉም ክልሎች ፖለቲካ ላይ የሚታይ ነው። ይህ ችግር ገዢው ፓርቲንም አይመለከትም ማለት አይቻልም።
ጠርዘኝነት በፓርቲው ውስጥ እንዳለ የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ። ፓርቲው እንደ መርሕ ጽንፈኝነትን እቃወማለሁ ቢልም እንኳ የጽንፈንነት ውጤት የሆኑ ተግባራት ፓርቲው ስልጣን ከያዘበት እለት አንስቶ በሚመራት አገር ላይ ቀን በቀን የሚታዩ ችግሮች ናቸው። አሁን እየተስተዋለ ያለው ማመቻመች (compromise) አላስፈላጊ ማመቻመች ነው።
አንዱ የአንዱን ሌባ ላለመንካት ፤ አንዱ የአንዱን ብልግና ላለማንሳት የተማማሉ ይመስላሉ። ማመቻመች እየተካሄደ ያለው በመሠረታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ሳይሆን ፍጹም ማመቻመች ሊደረግባቸው በማይችሉ የሰው ልጅ በሕይወት የመኖር መብት ላይ ፤ ሙስናን በመታገል ላይ ፤ ልማትን በማምጣት ላይ ወዘተ ..ነው።
ክልሎች ወደ አዲስ አበባ እየላኩ ያሉት ለሰጥቶ መቀበል የሚሆን አጀንዳን ሳይሆን ስልጣን የሚሻማ ሹመኛን ነው። ይህ እውነታ እስካለ ድረስ ለውጥ ሩቅ ነው የሚሆነው።
ስለዚህም አሁን ብልጽግና ፓርቲ አገሪቱን አንደኛ ዜጋ እና ሁለተኛ ዜጋ የሚባል መደብ ሳይኖራት ሁሉንም እኩል አንደኛ ደረጃ ዜጋ አድርጌያለሁ ሲል በዚያው ልክ የአንድ ቡድን አጀንዳ ሁሌም የማዕከል አጀንዳ ሆኖ የሌሎች አጀንዳ ሁሌም እየተደፈነ የሚሄድ መሆን የለበትም።
ሁሉም አጀንዳ ፊትለፊት በጠረጴዛው ላይ መቅረብ አለበት። ብልጽግና አካታች ሆኛለሁ ሲል አካታችነቱ የፌደራል መንግሥት ስልጣን ላይ ያልነበሩ ቡድኖችን ወደ ስልጣን በማምጣት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አጀንዳዎች ማስተናገድ የሚችል አካታች ምህዳር በመፍጠር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል።
አካታች አጀንዳዎች ደግሞ ሰጥቶ መቀበልን የሚፈልጉ እና ጠርዘኝነትን የሚቃወሙ መሆን አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርቲቸው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ለአዲስ ተመራጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት የስራ ስምሪት ላይ ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስብራቶች አግላይነት ፤ ጽንፈኝነት ፤ መገፋፋት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም መፍትሔው አካታችነት ፤ ሚዛናዊነት እና ወንድማማችነት እንደሆነም ገልጸዋል። ትክክል ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ግን ሁሉም ቡድኖች ወደ ስልጣን እንዲመጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም አጀንዳዎች ወደ መሐል መጥተው ጠረጴዛው ላይ እንዲቀመጡ ማድረግ ይገባል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014