‹‹ማንም ቢሆን ወዶ ጠብ ውስጥ አይገባም›› ብሎ መደምደም አይቻልም። ምክንያቱም አንዳንዶች ጥጋብ መድረሻ አሳጥቷቸው ጠብ ውስጥ ይገባሉ። ይሄኔ ‹‹ማዘን ለተራበ ሳይሆን ለጠገበ ነው።›› ያስብላል። አንዳንዱ ከጎረቤቱ ጋር ይጣላል። አንዳንዱ ከቤተሰቡ፤ አንዳንዱ ደግሞ ከራሱ አልፎ ተርፎ ከፈጣሪው ጋር የሚጣላ አይጠፋም። ነገሩ ከማንም ጋር የተጣላ ያው ከፈጣሪው እንደተጣላ ይታመናል። እርግጥ ነው መጣላት ገዝፎ አንዱ ሌላው ላይ ግፍ ሲፈፀም ያየ ከፈጣሪው ቢጣላ ‹‹እርሱ የተረገመ እና አጥፊ ነው›› ብሎ ለማሰብ ያዳግታል።
ዋናው ጉዳይ ‹‹እከሌን እጠላዋለሁ›› ብሎ ምንም ሳያደርግ ወይም ‹‹የእከሌ ብሔር፣ የእከሌ ጎሳ›› አልያም የሆነ አካባቢ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ፤ ጭራሽ ምንም በማያውቅ ሰው ላይ ግፍ ሲፈፅም የታየ ሰው መጨረሻው ይናፍቃል። በእርግጠኝነት ጥጋበኛ ግፍ ፈፃሚ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ማንም አያውቅም። ነገር ግን ለፈፀመው ግፍ ዋጋ መክፈሉ የማይቀር ነው።
ግፍ ባይፈፅሙ እንኳ በቅርብ የሚያውቁት ወዳጅ ዘመድ በመንደር እና በጎጥ አስተሳሰብ ራሱን ተብትቦ ሰው ሲገፋ እያዩ ዝም ማለት፤ የሌላውን ሰው ጉዳት እኔ በሆንኩ ብሎ አለማሰብ እጅግ ያሳዝናል። ታሪክ ሆኖ ሲፃፍ ደግሞ ለትውልድ ያሳፍራል። እርግጥ ነው፤ እኔ ብሆን ብሎ አስቦ ግፍ ለሚፈፀምበት አካል ቆሞ መከራከር አለመቻል እንደየሁኔታው የሚያስወቅስ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ማንንም ለማይጠቅም ይልቁኑም ብዙዎችን ሊያሳዝን፣ ሊያስቆጭ እና አደጋ ውስጥ ሊጨምር በሚችል የግፍ ተግባር ውስጥ መሳተፍ ነገን ጨለማ እንደሚያደርገው አያጠያይቅም።
ልብሱ ፀድቶ አዕምሮ ያልፀዳ፤ ሰው የማያከብር ማንም ቢሆን በእርግጠኝነት ራሱን አያከብርም። ምንም እንኳ ላዩ ቢፀዳ ውስጡ ቆሻሻ ከሆነ፤ ራሱን ያላከበረ ቆሻሻ ደግሞ መጣሉ ስለማይቀር ቢዘገይም መውደቁ አጠያያቂ አይሆንም። ጨው ድንጋይ ነው ተብሎ እንደሚወረወረው፤ ቆሻሻ የሆነ ሰው መጣል ብቻ ሳይሆን የክፋቱን ዋጋ የሚቀበልበት ቀን ይደርሳል።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ ሰሞኑን ጉባ አካባቢ ተቃጠሉ ስለተባሉት ሰዎች ላይ የተፈጸመው እጅግ ዘግናኝ ተግባር ነው። ምናልባት አጥፍተው ነው ቢባል እንኳን ፍርድ የሚሰጠው በፍርድ ቤት ተመርምሮ እና ተረጋግጦ ሊሆን ሲገባ በዚህ መልክ በአገሪቱ ካለው ባህል ውጪ የሰው አስክሬን ማቃጠል፤ አልፎ ተርፎ ሰው ከነነፍሱ እያየ እንዲቃጠል ማድረግ ለማየት ቀርቶ ለመስማት የሚዘገንን ነው። በትንሹ ተግባር ስንበሳጭ አሁን ደግሞ ከበድ ያለው እየተሰማ ነው። ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንደሚባለው ሆኗል።
እጅግ አበሳጭተውኝ ካለፉ አጋጣሚዎች መካከል አንደኛው ከሰዎች ጋር በሰላም ውሎ ማደር ሲቻል እየተስገበገቡ የሰውን የልፋት ውጤት መውሰድ፣ መዝረፍ፣ አልፎ ተርፎ ማሳበድ እና መግደል ላይ የሚሳተፉ ሰዎች መኖራቸው ነው። በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ አንዳንዴ አሁንም ድረስ እያጋጠሙ ካሉ ሁነቶች መካከል አንዱን ለአንባቢዬ ማጋራትን መርጫለሁ። በነገራችን ላይ ይህንን ሥራዬ ብለው የተያያዙ የሆኑ ሰዎች አሉ ብዬ አምናለሁ።
ለአንዱ ላብ አደር ዳቦ ሸጡለት፤ ከሸጡለት በኋላ ዳቦውን ሊበላው ሲል ከፋቸው። መልሰው የሸጡለትን አካፍለን ያለበለዚያ እንቀማሃለን ብለው አስፈራሩት። የሸጣችሁልኝ እናንተው ናችሁ ብሎ ሊሞግታቸው ቢሞክርም ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም። እንዲያውም ዳቦውን እኛም አንበላም፤ አንተም አትበላም መሬት ላይ ጥለን ከአፈር ጋር እንደባልቀዋለን አሉ። ላባደሩ ተበሳጨ። ርቦት ነበር። አካፍሏቸው ግማሹንም ቢሆን ለመብላት አሰበ። ነገር ግን ከርሃቡ በላይ ክብሩ በለጠበት። ‹‹ወንድ ናችሁ አትነጥቁኝም ብሎ ታገለ።›› ታግሎ ዳቦውን ማስመለጥ አልቻለም።
ብዙ እና ጉልበተኞች በመሆናቸው ነጥቀው ጣሉበት። አልፈው ተርፈው ደበደቡት። ቆሻሻን የማይጠየፉ ቆሻሻዎች በመሆናቸው የወደቀውን ዳቦ አንስተው ከላይ ያለውን በሉ። በእርግጥ እንደሰማሁት ላባደሩ ምንም ማድረግ አልቻለም። አፈር ላይ ተደፍቶ ሰማዩን እያየ እንባውን አፈሰሰ። እንግዲህ ይህ ሰው ለፈጣሪው ፍርድ ይጠይቃል። ፈራጅ በዙፋኑ ላይ ሆኖ ይፈርዳል።
ነገር ግን እንዴት ሰው በምንም መልኩ የሸጠውን ዕቃ መልሶ እስከመካድ የደረሰ ክሕደት እና ራስን የማዋረድ ሞራል ሊኖረው ይችላል? እንዲህ ዓይነት የሞራል ውድቀት ላይ መድረስ በእጅጉ ያሳዝናል። ሰው እንዴት ራሱን ማክበር አቃተው? ራሱን ያላከበረ ማንኛውም ሰው ሌላ ሰው ምንም ባይለውም ምንም ባያደርገውም ተደናቅፎ መውደቁ አይቀርም። ግፈኛ በመሆኑ ተደናቅፎ ሲወድቅ ደግሞ የሚያነሳው አያገኝም። ያን ጊዜ የሠሩትን ግፍ ማስታወስ ይከተላል።
ራቁቱን ተወልዶ ራሱን በእንቁ ተሽቆጥቁጦ እንደተወለደ የተለየ ፍጡር ከሁሉም በላይ እንደሆነ እያየ ሌላውን ማንኳሰስ ጠቅሞ አያውቅም። የተለያዩ ሰዎች ብሔራቸውን ሳይጠያየቁ ተጋብተው ብዙ ወልደው ልጅ እና የልጅ ልጅ ሲያዩ በኖሩበት አገር እኔ የተለየሁ ዘር ነኝ በማለት አጉል መመፃደቅ ያሳቅቃል። ይህ ተግባር በጊዜ እንዲቆም ማድረግ ካልተቻለ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ከዚህም የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም ሰው ከሆዱ በላይ ክብሩን ያስበልጣል። ለእዚያውም ኢትዮጵያዊ በክብሩ ሲመጡበት እልሁ እስኪያንፈራፍረው ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ እስክታልፍ ይተናነቃል። ስለዚህ ክብረነክ ነገሮች ቢቆሙ መልካም ነው።
ኢትዮጵያውያን ለብዙ ጊዜ በትምህርት ቤትም ሆነ በሃይማኖት ተቋማት ብሔራቸውን አይጠያየቁም ነበር። ተማሪው ዓላማው ትምህርቱን ማጠናቀቅ ብቻ ነው። ትምህርት ቤት ግፋ ቢል ሰው እንደሰው እኩል መታየት አለበት ከሚል ሃሳብ ውጪ ብሔር እየመረጡ መቀጣቀጥ እየተማርኩ ነው ከሚል ትውልድ የሚጠበቅ አይደለም። ብሔር ጠርቶ መሳደብ ያስነውራል። ይህ ለአገር የሚበጅ ሳይሆን አገር የሚያጠፋ ተግባር ነው።
ተማሪ በአዲስ አስተሳሰብ ውስጥ ራሱን እያሻሻለ ከሌሎች በተሻለ ፍጥነት ከመራመድ ውጪ ራሱን በጎሳ እና በብሔር ውስጥ ወትፎ ከተራ የቤተሰብ ሙግት በማያልፍ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማጥፋት የተማሪውን አላዋቂነት የሚያሳብቅ ነው። ራስን አልቆ ሌላውን አሸማቆ ያላቅም እየተንጠራሩ መመፃድቅ ብዙ ርቀት አያስጉዝም።
ሰዎች በሰላም ወጥቶ መግባት ፈተና ሲሆንባቸው ለተወሰኑ ጊዜያት በትዕግስት ሊያልፉት ይችላሉ። እየባሰ ሲመጣ እና ትዕግስታቸው ሲሟጠጥ ግን የተበደሉት ይብሳሉ። የዚያን ጊዜ መግቢያ እንዳይጠፋ ሁሉም ቢሆን መሠረቱን በእኩልነት እና በእውነተኛነት ላይ ቢያደርገው መልካም ነው።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም