ጥንታዊ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እንዲሁም መስጂዶች እውቀትን እየሰፈሩ ትውልድን በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከርክመው የቀረጹ ዩኒቨርሲቲዎች ስለመሆናቸው አያጠያይቅም። እነኚህ ተቋማት ከዩኒቨርሲቲነት ባለፈም የአገር ሀብት የሆኑ ቅርሶችን እና ታሪካዊ ሰነዶችን ዘንደው በማስቀመጥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየሞች ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። አሁንም እያገለገሉ ነው። ለዚህ ደግሞ አያሌ ማሳያዎችን ማቅረብ ይችላል።
የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ፣ ገዳማት እና መስጂዶች በሰው ልጅ ስለመሰራታቸው ለማመን የሚከብዱ እና ከአዕምሮ በላይ የሆኑ ቅርስችን ተሸክመው ይገኛሉ። እነኚህን ቅርሶች በማስጎብኘት ለአገራችን ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት ይቻል ነበር። ይሁን እንጂ ያሉንን ወይም የተሰጡንን ሀብቶች ማወቅ እና መጠቀም ተስኖን እርዳታ ስናሳድድ ፣ የውጭ እና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን የአገራችንን አንጡራ ሀብት በዝቅተኛ ዋጋ እንደፈለጉ ተጠቅመው ፋብሪካ እንዲከፍቱልን ስንማጸን፣ እና ከዓለም አበዳሪ አገራት ብድር በመፈለግ የሀብታም አገራትን ደጅ ስንጠና ፤ አንዳንድ ጊዜም ሉዓላዊ ክብራችንን ጭምር ዝቅ እያደረግን አበዳሪዎችን ስንለማመጥ እንታያለን።
በኢትዮጵያ ገዳማት ፣ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጂዶች ውስጥ ያሉንን ቅርሶቻችንን ለዓለም ሕዝቦች ብናስተዋውቅ እና ብናስጎበኝ በእርግጠኝንት ለኢንቨስተሮች ብድር እየሰጠን ፣ ያሉንን የተፈጥሮ ሀብቶች በትንሽ ገንዘብ እየሸጥን ከምንፈጥራቸው የሥራ እድሎች እና አይነቶች እጅጉን የተሻለ ገቢ ለአገራችን ማስገኘት ይቻላል። ብዙ አገራት እዚህ ግባ የማይባሉ ቁሳቁሶቻቸውን በቅርስነት ስም እያስመዘገቡ የሚያገኙት ገንዘብ የሚታወቅ ነው። አውሮፓውያን ከአፍሪካውያን የዘረፏቸው ቅርሶች ብቻ በማስጎብኘት የሚያገኙት ገቢ እንኳን የትየለሌ ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻችን በሚፈጥሩልን ተራ አሉባልታዎች አጀንዳዎችን እየፈጠርን እርስ በእርሳችን እየተጎሻሸምን እና እየተጓተትን ያለንን ማየት ተስኖን፤ የተሰጠንን መጠቀም አቅቶን ውድ የሆኑ እና በሌሎች ዓለማት የማይገኙ ቅርሶቻችንን እንዲሁ እያባከን ድሕነትን አፍቅረን ለመኖር ቆርጠን የተነሳን ይመስላል።
ወቀሳውን እዚህ ላይ ገታ ላድርገውና ካወቅንበት በቀጣይ የገቢ ምንጭ የቱሪዝም መዳረሻ የሚሆኑ ኢትየጵያውያን እስከመኖራቸው የማናውቃቸው ነገር ግን በአገራችን ከሚገኙ የአስገራሚ ቅርሶች መካከል አንዳንዶቹን በወፍ በረር ማስቃኘት ወድጃለሁ ።
ከሰሞኑ እግር ጥሎኝ ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን ሂጄ ነበር። በደቡብ ጎንደር ዞን በሄድኩበት አጋጣሚዎች እና ሁኔታዎች ፈቅደውልኝ በዞኑ የሚገኙ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ለማየት ቻልኩ። በዞኑ በሚገኙ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት የተመለከትኳቸው ቅርሶች እና የቱሪስት መዳረሻዎች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ ቁልጭ እና ቅልብጭ አድርገው የሚያሳዩ ከመሆናቸውም ባለፈ የዓለም ሕዝብ ቢያውቃቸው እና ቢጎበኛቸው ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ መሆን የሚችሉ ናቸው። ከእነዚህ አስደናቂ ገዳማት መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ የሚገኘው የዙር አምባ አቡነ አረጋዊ ገዳም አንዱ ነው።
የዙር አምባ አቡነ አረጋዊ ገዳም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ገብረመስቀል፣ ቅዱስ ያሬድ እና አቡነ አረጋዊ እንደተመሰረተች የገዳሟ የዜማ መዋሲት ማስመስከሪያ መምህር እና የቅዱስ ያሬድ 46ኛ ተተኪ መምህር መጋቢ ብርሃናት ፋንታ አፈወርቅ ይናገራሉ። ይች ገዳም የዜማ መዋሲት እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርሰቲያን የትምህርት አይነት ብቸኛው ማስመስከሪያ ገዳም ነው። የመጀመሪያው የዜማ መዋሲት መምህሩ ቅዱስ ያሬድ ነው። ዛሬ ላይ 46ኛው የዜማ መዋሲት መምህር በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚች ገዳም የተመለከትኳቸው ቅርሶች እና የቱሪስት መስህቦች በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉንም ቅርሶች እና የቱሪስት መስህቦች በዚህ ዝግጅት ላይ ብቻ በአይነት እና ብዛት መግለጽ የማይሞከር ነው። ግን ለቅምሻ ያህል በእነኚህ ገዳማት የሚገኙትን ከብዙዎቹ በጥቂቱ የተመለከትኳቸውን ጀባ ልበላችሁ።
የዙር አምባ ገዳም የቦታ አቀማመጥ
በዙር አምባ አቡነ አረጋዊ ገዳም በርካታ ቅርሶች ቢኖሩም ገዳሟ የተገደመችበት ስፍራ በራሱ እጅግ ልዩ እና ማራኪ ነው። የቦታ አቀማመጡ ደብረ ዳሞን ይመስላል። ልዩነቱ ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ለመግባት የምንጠቀመው መንጠላጠያ ገመድ ሲሆን ዙር አምባን ዳገት ለመውጣት የምንጠቀመው አጅግ ፈታኝ የሆነችን ቀጭን መንገድ ነው። ዳገቱ በእግር ይወጣ እንጂ በመንገዱ ግራ እና ቀኝ ያለውን የገደሉን ጫፍ ወደ ታች ማየት አይቻልም። ወደ ገዳሟ ለመግባት አንድ መንገድ ብቻ አለች። ከዚች መንገድ ውጭ ወደ ገዳሟ ለመግባት መሞከር እጅግ ሰፊ የሆነ የበቆሎ ማሳ በጸጉር መላጫ ሸበር ለማጨድ እንደመሞከር ነው ።
ገዳሟ ዙር አምባ የሚለውን የአካባቢውን መጠሪያ ያገኘችው በምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። ይሄውም ገዳሟ ከመቋቋሟ በፊት አቡነ አረጋዊ እና ቅዱስ ያሬድ በተራራው ጫፍ ለመውጣት ፈልገው መውጫ ያጣሉ። ይጨነቃሉም። አንድ ቀን በተኙበት በህልማቸው አቡ አረጋዊን አንድ አካል «አባ ወደ ምስራቅ ዙር» ይላቸዋል። አባም ወደ ምስራቅ ዞሩ ። ወደ ዳገቱ መውጫ መንገድም አገኙ። ከዚያ በኋላ የቦታው መጠሪያ «ዙር አምባ ወይም ዙር አባ» እየተባለ ለመጠራት መብቃቱን የዜማ መዋሲት መምህሩ ይናገራሉ።
የዙር አምባ ገዳም አቡነ አረጋዊ ገዳም እጅግ በርካታ ለአይን ማራኪ ቀልብን ሰራቂ የሆኑ ቅርሶች መገኛ ናት ። ከእኚህ መካከል የተወሰኑትን እንመልከት ።
የቅዱስ ያሬድ መቋሚያ ዘንግ እና ጸናጽን
በጥንታዊቷ ዙር አምባ ገዳም ከብረት የተሰራ የቅዱስ ያሬድ መቋሚያ ዘንግ እና ጸናጽን ይገኛል። የቅዱስ ያሬድ የመቋሚያ ዘንግ እና የጸናጽን አሰራር አይንን ከመማረክ ባለፈ በዚያ ዘመን የነበሩ አባቶቻችን የብረት ጥበብ ሥልጣኔአቸው በከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እንደነበር አመላካችም ናቸው። ከዚህም ባሻገር የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ሥልጣኔ ማስቀጠል እንዴት እንዳልቻለ ጥያቄም የሚያስነሳ ሆኖ እናገኘዋለን።
የቅዱስ ያሬድን መቋሚያ ዘንግ እና ጸናጽን የሚመለከት ማንም ሰው የያሬድ ዜማ መፈጠሪያ መሳሪዎችን እንደተመለከተ ለአፍታም አይዘነጋም ። እነኚህን የዜማ መፍጠሪያ መሳሪያዎች ስንመለከት ደግሞ ከእነሞዛርት እና ቪቶቭን በፊት ሙዚቃ በአገራችን መፈጠሩን መገንዘብ እንችላለን። ስንቶቻችንስ በቅኝት የታገዘ ሙዚቃን ከአውሮፓውያን በፊት እንደጀመርን እንገነዘብ ይሆን?
ከመቋሚያ ዘንግ እና ጽናጽን ባለፈ ቅዱስ ያሬድ ሲያስተምሩባት የነበረች አንዲት ገራሚ ተፈጥሮ ያላት ዛፍ ትገኛለች። ይች ዛፍ አንዳንዴ ትደርቃለች። አበቃላት ደረቀች ስትባል መልሳ አረንጓዴ ሆና እንደምትታይ የገዳሟ አባቶች ይናገራሉ። አሁን ላይ ዛፏ ደርቃ ትገኛለች። በቀጣይ ለአይን ማራኪ ሆና ታብባለች እና በቅርበት ለሚያውቃት ደረቀች ተብሎ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም።
የአቡነ አረጋዊ ዘንግ እና ጭራ
በዙር አምባ ከሚገኙ እጅግ የከበሩ ቅርሶች መካከል ክርስትናን በኢትዮጵያ ካስፋፉ ዘጠኙ ቅዱሳኖች መካከል አንዱ የሆኑት የአቡነ አረጋዊ ከብረት የተሰራ ዘንግ እና ጭራ ይገኛል። የአቡነ አረጋዊ ዘንግ በተወሰነ መልኩ ከቅዱስ ያሬድ ዘንግ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ከመቋሚያ ዘንጎቹ በላይ እንደእኔ ሁሉም ሰው ቢያየው ብየ የምመኘው ከአዕምሮየ ሊጠፋ የማይችለው የአቡ አረጋዊ ጭራ ነው። በእርግጥ ጭራው የተሰራው እንደማንኛውም ጭራ ከፈረስ ጭራ ነው ። እርዝማኔው እና የጭራው ቀለም ግን ከፈረስ በተገኘ ጭራ ነው ቢባል ለማመን ትንሽ ያስቸግራል። ይህንን ጭራ የሚመለከት ማንም ሰው እርግጠኛ ነኝ እጅጉን በሃሴት ይሞላል። ለብዙ ቀናትም በደስታ ውስጥ የሚኖር ይመስለኛል። የጭራውን ውበት በቃላት ለመግለጽ መሞከር ያዳግታል። ስለሆነም በአካል በቦታው ተገኝታችሁ ጎብኙ ብዬ ለመጋበዝ እገደዳለሁ።
ከአጼ ቴዎድሮስ እና ገብርዬ ለገዳሙ የተበረከቱ ንብረቶች
በገዳሙ ከሚገኙ አስደናቂ ቅርሶች መካከል ግዙፉ የአጼ ቴዎድሮስ ጠጅ መጠጫ ብርሌ ፣ የጄኔራላቸው ግብርዬ ቆመጥ (ዱላ) እና ሰይፍ ይገኛሉ። የአጼ ቴዎድሮስ ጄኔራል ነበሩትን ገብረዬ ቆመጥ (ዱላ) እና ሰይፍ የሚያይ ማንም ሰው ስለ አጼ ቴዎድሮስ እና ገብርዬ ጀግንነት የሚሰማውን ዝና በተግባር የሚመለከት ይመስለኛል።
ስጋቶች
በየገዳማቱና መስጂዶች የሚገኙ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ቅርሶች የቱሪስት መስህብ መሆን ይችላሉ ፤ ገቢ ያስገኛሉ ሲባል ግን ቅርሶቹ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ናቸው ብሎ ማንሳትና ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ ይገባል። ቅርሶቹ በሥርዓቱ ተመዝግበው ሙዚየም ተሰርቶላቸው በእንክብካቤ መቀመጥ አለባቸው። ይሄ ካልተደረገ ግን ወደፊት ቅርሶችን በነበሩበት ማግኘት አይቻልም። አሁን ላይ በገዳሟ የሚገኙ ቅርሶች ተገቢውን እንክብካቤ ባለማግኘታቸው በተለይም ካባዎች እና ለምዶች «ብል» በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃቸው እና እየተቀዳዱ ይገኛሉ። ስለሆነም የሚመለከተው አካል ተቢውን ትኩረት ለቅርስች ቢሰጥ መልካም ነው።
ቅርሶቹን በተገቢው አቀማመጥ ማስቀመጥ ከተቻለ ወደ ፊት ቅርሶቹ ጊዜ ተወስዶባቸው ለአገር ውስጥ እና ለዓለም ማስተዋወቅ ቢቻል ለአካባቢው ማሕበረሰብ ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በእጅጉ ማሳደግ ያስችላል።
እንደ መልዕክት
በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ቅርሶቻችንን ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለዓለም ሕዝብ በማሳወቅ ለዜጎቻችን የሥራ እድል ለመፍጠር እና ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰበት ያለውን የቅርሶች የፎቶ አውደ ርዕይ እንዲሳካ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል! መልዕክቴ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም