የሚኒስቴሩንና የማህበራቱን በጋራ የመሥራት ፍላጎት ያመላከቱ መድረኮች

በቅርቡ የቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ የሥራ ርክክብ ካደረጉ በኋላ መደበኛ ሥራቸውን መጀመራቸው የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቹ አሳውቋል። ሚኒስትሯ ከሰሞኑ ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይት ማድረጋቸውንም ይሄው መረጃ ያመለክታል። ውይይቱ ዘርፉ የሚጠበቅበትን እድገት እንዲያመጣ ከሁሉም ባለድርሻ ጋር በቅንጅት መሥራት በሚችልባቸው እንዲሁም የማህበራቱና የባለድርሻ አካላቱ በሥራ ወቅት የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመለየትና መፍትሔ ለመስጠት ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ መግለጫ ከሚኒስትሯ ጋር ውይይት ካደረጉት ባለድርሻዎች መካከል የአስጎብኚ ማህበራት አንዱ ነው። በመድረኩም ማህበሩን ወክለው የተገኙ የሥራ ኃላፊዎች መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ከዋና ዋና የኢኮኖሚው ዘርፎች ውስጥ እንዲካተት ከማድረግ ባሻገር አዳዲስ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በማልማት እያከናወነ ያለው ተግባር ከምንጊዜውም በተለየ ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሊያከናውናቸው ይገባል ባሏቸው፤ በተለይ ከክልሎች እና የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር የሚስተዋለው ቅንጅታዊ አሰራር ውስንነት፣ በመስህብ ስፍራዎች አካባቢ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እና አገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ያሉ ችግሮችን ማንሳታቸውን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

መረጃው እንዳመለክተው፣ ሚኒስትሯ የአስጎብኚ ማህበራት ኃላፊዎች እና ተወካዮችን ባወያዩበት ወቅት፤ ከቱሪዝም ኢንቨስትመንት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ትብብር፣ በዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ጥምረቶች፤ የንግድ ትርዒት እና ባዛሮች፤ በሀገራዊ የቱሪዝም መለያ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ከቱሪዝም ገበያ ልማት አንጻር ከግሉ ዘርፍ ጋር መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየት ዘርፉ የተጣለበትን ሀገራዊ ፋይዳ እንዲያበረክት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከአስራር ጋር በተያያዘ ከማህበራቱ አባላት በተነሱ ጉዳዮች ላይም ሚኒስትሯ በመሥሪያ ቤቱ በኩል መከናወን ያለባቸውን ተግባራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚከናወኑ መናገራቸውን ገልጸዋል። የዘርፉ ባላድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ሚኒስትሯ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መረጃው እንደሚያመለክተው፤ የቱሪዝም ሚኒስትሯ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ምክክር ለማድረግ ከመረጧቸው ባለድርሻዎች መካከል የሆቴል ፌዴሬሽኖችና የቱሪዝም የሙያ ማህበራት ኃላፊዎች እንዲሁም ተወካዮች ይገኙበታል። ሁለቱም አካላት በዚህኛው መድረክ ላይ በቅንጅት መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡ በዚህም የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው የዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እና ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብ መንግሥት አስቻይ የሆኑ የማበረታቻ ስልቶችን የዘረጋ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ በጥምረት በመሥራት፤ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በመወያየት ዘርፉ የተጣለበትን ሀገራዊ ፋይዳ እንዲያበረክት ለማድረግ ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የማህበራቱ ተወካዮቹ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረትና የሳተላይት አካውንት ማስጀመሩን በማወደስ አሉብን ያሏቸውን ችግሮች ለሚኒስትሯ ማንሳታቸውን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ጠቅሷል፡፡ በተለይ ከሆቴል የኮኮብ ከደረጃ ምደባ አንጻር፣ ለእሳት አደጋ መከላከል የሚጠየቁ ፋሲሊቲዎችን በተመለከተ፣ የቀረጥ ነፃ የአንድ ጊዜ ፈቃድ ብቻ መሆን፤ በኮቪድ ምክንያት ገበያው የተቀዛቀዘው የሆቴል ኢንዱስትሪ በዳግም የደረጃ ምደባ ቁሳቁስ መቀየር ባለመቻላቸው ደረጃቸው ዝቅ ሊያደርግ ስለሚችል ከግምት ውስጥ ቢገባ የሚል እና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በተለይ ዘርፉ ችግር ላይ በወደቀበት ወቅት የ6 ወር እፎይታ ቢሰጥም አመርቂ አለመሆኑን፣ ከውጭ የሚመጡ ባለሙያዎች የቆይታ ጊዜ እና ያበቁት የሰው ኃይል እና ዓይነት የሚለይበት አግባብ መፍጠር ላይ ዘርዘር ያሉ ሃሳቦችን ማንሳታቸውን የሚኒስቴር መረጃው አመልክቷል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳም ለባለድርሻ አካላቱ ወሳኝ ጥያቄዎች በቀጣዩ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ከሰው ኃይል ስልጠና አንጻር፣ ከትብብር እና ድጋፍ እንዲሁም የሚታዩ ክፍተቶችን በጋራ የሚፈቱበትን አግባብ እና የግንኙነት ጊዜ በተመለከተ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተገልጿል።

በተከታታይ ከተደረጉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ውይይቶች መካከል ከሁነት አዘጋጆች ጋር የተካሄደው አንዱ ነው። ሚኒስትሯ በቱሪዝም ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የትብብር እድሎች፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች እና ኢትዮጵያን ዋና የማይስ መዳረሻ ለማድረግ በሚበጁ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከአዘጋጆቹ ጋር መምከራቸውን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ገልጾልናል።

ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ የማይስ ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን መጥቀሳቸውን መረጃው ጠቁሞ፣ የዳበረ የኩነት ኢንዱስትሪ እንዲሆን መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት በአጽኖት ማስታወቃቸውን መረጃ አብራርቷል።

መረጃው እንደጠቆመው፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ መገንባት ዋና ሥራው በመሆኑ የዘርፉን እድገት የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን መመሪያዎችን በማዘጋጀት እና ወደ ተግባር እንዲገቡ በማድረግ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻ መደበኛ የሆነ የግንኙነት አግባብ በመፍጠር አጋርነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ መግለፃቸውን ጠቅሶ፣ የሁነት አዘጋጅ ድርጅት ተወካዮች በኢንዱስትሪው ፍላጎቶች ላይ ያላቸውን አጠቃላይ ግንዛቤ በማካፈል በአፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመውጣት አንጻር በተግዳሮትነት የሚነሱ ጉዳዮችን ማንሳታቸውን አመልክቷል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ ባሕል እና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበራት እና የሀይኪንግ ኦርጋናይዘር አሶሴሽን ተወካዮች ጋርም እንዲሁ መክረዋል። ከእነዚህ ማህበራት ጋርም ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው መምከራቸውን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ አስታውቆ፣ በውይይቱ ወቅት ማህበራቱ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲስፋፋ ከሚጫወቱት ሚና ባሻገር እርስ በርስ መተዋወቅን በማስፋት ረገድ ቱሪዝም ለሀገራዊ አንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያመጣ በአጽንኦት መግለጻቸውንም አብራርቷል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ መሰል መድረኮች የእርስበርስ ትብብር መንፈስ የበለጠ እንደሚጨምሩ መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የማህበራቱ ተወካዮች ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ሙያቸው በሚፈቅደው አግባብ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከተቋሙ ጋር ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን መረጃው ጠቁሟል። በዚህም ለሚፈለገውና ለተገቢው ውጤትም በጋራ ለመሥራት ፍቃደኛ መሆናቸውን ማሳወቃቸውንም ገልጿል።

የዝግጅት ክፍላችን በውይይቶቹ ላይ ከተሳተፉ ማህበራት መካከል የኢትዮጵያ የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነውን ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩምን አነጋግሯል። ጋዜጠኛ ሄኖክ እንደሚለው፤ በውይይቱ ላይ ባለፉት 15 እና16 ዓመታት የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጦች ክበብ፣ ፎረም እንዲሁም ማህበር በየደረጃው በማቋቋም ኢንዱስትሪውን ለማገዝ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በዝርዝር እንዳስረዱ ገልጿል። በተለይ የመገናኛ ብዙሃን እና የቱሪዝም ግንኙነት በቂ ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን ጠቅሶ፣ በተለያየ ቋንቋ ቱሪዝምን የሚመለከቱ ዘገባዎች አለመኖራቸውን የሚያሳዩ ውስንነቶች በመጥቀስ በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ርምጃዎች የመፍትሔ ሃሳብ ማመላከታቸውን አስረድቷል።

ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም እነዚህን ተግዳሮቶች ለማለፍ የክህሎትና የአቅም ግንባታ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡ መንግሥትም ይህንንም ጉዳይ በተለይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲረዳው በምክክሩ ላይ ትኩረት በመስጠት ማቅረባቸውን ይናገራል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውጤታማ እንዲሆን በቀጣናው፣ በአህጉሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የቱሪዝም ሚዲያ ሊኖር እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ይገልፃል። ይህንን ለማሳካት እስካሁን የተነፈገውን ትኩረት ማስተካከልና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለእቅዱ እውን መሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው መወያየታቸውንም ገልጾልናል።

‹‹ከዚህ ቀደም በዘርፉ ላይ በቅንጅት የመሥራት ባሕል ደካማ ነበር። በተለይ በፌዴራሉና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት ላልቶ ነበር›› የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልሉ ቢሮዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረውና በቅንጀት መሥራት እንደሚኖርበት ምክረ ሃሳብ ማንሳታቸውን ገልጿል።

እንደ ማህበሩ ፕሬዚዳንት ገለፃ፤ ሀገሪቱ የምትከተለው የአስጎብኚዎች ፍቃድ አሰጣጥ ሕግ (በተለይ ፍቃዱ የሚሰጠው መኪና ላሟላ ብቻ መሆኑን የሚገልጸው) ክፍተት እንዳለበትና መታረም እንደሚኖርበት በውይይቱ ተነስቷል። ይህ የፍቃድ አሰጣጥ ሕግ በኢንዱስትሪው ላይ ለመሥራት ፍላጎት የሌለውን ሰው መኪና ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ብቻ ምቹ አጋጣሚን እንዲያገኝ ክፍተት እንደሚፈጥር ማንሳታቸውን አስረድቷል። በዚህም ማህበራቱ የአስጎብኚነት ፈቃድ ሙያንና እውቀትን ገንዛቤ ውስጥ አስገብቶ መሰጠት እንዳለበት (መኪና ተከራይተው ሥራውን መሥራት የሚችሉበትን አማራጭም የሚጨምር) የሚገልፅ ሃሳብ ለሚኒስትሯ አቅርበዋል።

እንደ ማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖከ ሰዩም ፤ በውይይቱ ላይ የእግር ጉዞ ጉብኝት አዘጋጆች ማህበር የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማነቃቃት ላይ በርካታ ሥራዎች መሥራታቸውን ማንሳቱንም ይናገራል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በየሳምንቱ ከአካባቢያቸው ራቅ ወዳሉ መዳረሻዎች እየወጡ ሀገራቸውን እንዲያውቁ ማድረጋቸውን ጠቅሶ የተጠናከረና ቀጣይነት ያለው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት እንዲመዘገብ በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸውን ይገልፃል። ይህንን ወደ መሬት ለማውረድም ለሥራቸው የሕግ ማሕቀፍ ተዘጋጅቶ በፋይናንስና በፖሊሲ የሚደገፉበት እቅድ ተግባራዊ እንዲደረግ ለሚኒስትሯ ጥያቄ አቅርበዋል።

‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለድርሻ አካላትን በተናጠል ጠርቶ በዚህ መልኩ ካወያየ ረጅም ጊዜ ሆኖታል›› የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ከዚህ ቀደም የባለድርሻ አካላቱን ችግርና በጋራ አብሮ ለመሥራት የሚገድብ እንቅፋት እንደነበር አስታውሶ፣ መንስኤው ምን ነበር ተብሎ ተጠይቆ እንደማያውቅ ይናገራል። አሁን በዚህ መልኩ እድል መሰጠቱና የጋራና የትብብር ሥራዎችን በቅንጅት ለመሥራት የተጀመረው ጥረት ሊደነቅ የሚገባው በጎ ጀምር መሆኑንም ያነሳል።

ይህንን ለማላቅ የኢትዮጵያ የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ሌሎች ማህበራትን በማስተባበር አንድ ማሕቀፍ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጿል። ይህንን ስኬታማ ማድረግ ከተቻለ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቅንጅት ለመሥራት መድረኮችን ክፍት ከማድረጉ ጋር ተደምሮ በኢንዱስትሪው ተስፋ ሰጪ ውጤት በቅርቡ እንደሚመዘገብ አስረድቷል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You