አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልትጥለው ላሰበችው ማዕቀብ HR 6600 ፤”የኢትዮጵያ መረጋጋት ፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሕግ፤”(“Ethiopia Stabilization, Peace and Democracy Act”) የሚል መላዕካዊ ስም ሰጥታዋለች። ለኢትዮጵያ ሰላምን ፣ መረጋጋትንና ዴሞክራሲ የሚያመጣ ማዕቀብ ቢኖርማ እኛ ዜጎች እንጥለው ነበር። አዎ ምን ደም አፋሰሰን በታሪካዊ ጠላቾቻችንም ሆነ በታማኝ ቡችሎቻቸው በእነ ሕወሓት፣ ሸኔና ሌሎች ላይ፤ “የኢትዮጵያ መረጋጋት ፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሕግ፤” የሚል ማዕቀብ እንጥል ነበር ። አሜሪካስ ለምን “ትቸገራለች” መረጋጋት ፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚያመጣ ማዕቀብ ብናገኝማ እኛ ዜጎቹ “የመንግሥታችንን ጀርባ የሚያጎብጥ” ማዕቀብ እንጥልበት ነበር።
HR 6600 ረቂቅ ከጸደቀ በሁሉም ዘርፍ ማለትም በአገራችን ህልውና ፣ ሉዓላዊነት ፣ ከእነ ውስንነቶቹ ተስፋ በጣልነበት ለውጥ ላይ አደጋ የሚደቅን ከመሆኑ ባሻገር አገራችንን እንደነ ራሽያ ፣ ኢራን ፣ ሶሪያ ፣ ቬንዙዌላ ፣ ሰሜን ኮሪያና በርማ (ማይነማር) ከተቀረው ዓለም ነጥሎ ብቻ የሚያስቀር ነው። ከተቀረው ዓለም ጋር በሚኖራት የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ ሞግዚት የሚያስቀምጥ ሌላው የ2014 የውጫሌ ውል ረቂቅ ነው ማለት ይቻላል።
የአገራችንን የውጭ ንግድ ከማሽመድመድ አልፎ ከወገኖቻችን የሚላክን የውጭ ምንዛሬ(ሬሚታንስ) ሳይቀር በመወሰን አሁን የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማባባስ መንግሥት መድሃኒትን ጨምሮ መሠረታዊ ሸቀጦችን ማስገባት እንዳይችል በማድረግ የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን በማባባስ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ በማድረግ አሜሪካ በእነ ሕወሓትና ሸኔ ማሳካት ያልቻለችውን ኢትዮጵያን የመበተንንና የመንግሥት ለውጥ አድርጎ አሻንጉሊቷን ሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ የተቀየሰ ሌላ ዕቅድ (ፕላን B ) ነው። በመሆኑም ሉዓላዊነቱንና ነጻነቱን ሳያስደፍር ለኖረ ሕዝብ ይህ እጅ አዙር አዲስ ቅኝ ግዛት በፍጹም ተቀባይነት የለውም።
በኒውጀርሲው ሴናተር በቶም ማሊኖውስኪ መሪነት ተረቆ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው ሕግ ፤ ከዚህ በፊት ከተጣሉ ማዕቀቦች እና ከፕሬዚዳንት ባይደን ውሳኔ ማለትም ከጦር መሳሪያ ግዥ ፤ የደህንነትና የወታደራዊ ስምምነትን ከማቋረጥ ፤ ኢትዮጵያ ምርቶቿን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ ለመላክ የተሰጣትን ዕድል (አግዋ) ከማንሳት በላይ የከፋ የማዕቀብ ረቂቅ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ጦርነት በተፈጸሙ የሰብዓዊ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግና በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ያለመ ነው ቢባልም፤ ዓላማው አንድና አንድ ነው ። ኢትዮጵያን ማንበርከክ ፡፡ በቅኝ ግዛት ያልጫኑብንን የባርነትና የጭቆና ቀንበር በእጅ አዙር መጫን ነው ግቡ።
በረቂቅ ሕጉ ክፍል ዘጠኝ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር (Treasury Department) አማካሪ በ180 ቀናት ውስጥ በትግራይ ክልል ጦርነት የተካፈሉ ኃይሎች ሚናን አጣርተው ያቅርቡ የሚል አንቀጽ ይገኛል፡፡ በዚህ አንቀጽም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፤ የኤርትራ ሠራዊትና የሕወሓት ኃይል በጦርነቱ ምን ዓይነት የሰብዓዊ ወይም የጦር ወንጀል እንደፈጸሙ በዝርዝር ለአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ እንዲቀርብ የሚያዝ ንዑስ አንቀጽም ይገኛል፡፡
በክፍል አሥር ላይ ደግሞ በትግራይ ክልል ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎችን አጣርቶና ለይቶ ለማቅረብ የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ይሰጣል፡፡ በትግራይ ክልል ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎች የዘር ማጥፋት ፣ የጦር ወንጀል ወይም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች መሆን አለመሆናቸው ተለይተው እንዲቀርቡ ረቂቅ ሕጉ ግዴታ የሚጥል ነው፡፡
የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ሲል ተቋማት (ቡድኖችን) ብቻም ሳይሆን የግለሰቦች የወንጀል ተሳትፎ (በተለይ የባለሥልጣናት) በዝርዝር መቅረብ እንዳለበትም የሚያዝ ንዑስ አንቀጽ ይዟል ፡፡ ይህ በተዘዋዋሪ የመንግሥታቱ ድርጅትና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኖች በጋራ ያቀረቡትን ጥናትና ዘገባ ዋጋ የሚያሳጣና በምትኩ ኢትዮጵያን በጦር ወንጀለኝነት ፤ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በሚፈጸም ወንጀል እና በዘር ማጥፋት በመወንጀል በትግራይ ነጻ የአየር ክልልን ለመፍጠርና ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጥርጊያውን የሚያመቻች አደገኛ ረቂቅ ሕግ ስለሆነ ነው በማር የተለወሰ መርዝ ያልሁት።
HR 6600 የኢትዮጵያን በተለይ የትግራይ ክልልን ጉዳይ የተመለከተ ቢሆንም፤ በጦርነቱ ተሳትፋለች የሚላትን ኤርትራንም ይመለከታል፡፡ ሕጉ የኤርትራና የኢትዮጵያ ፀጥታ ተቋማትን ባለሥልጣናትንና የመንግሥት አካላትን በየደረጃው ለመቅጣት ያለመም ነው ፡፡ “በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍ ፤” የሚል ሽፋን የተሰጠው የማሊኖውስኪ ረቂቅ ሕግ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማዕቀብ በማሽመድመድ ቀጣናውን ለለየለት ቀውስና ትርምስ የሚዳርግ አደገኛ ሰነድ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማጤን ይገባል ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ ትግራይ ክልል እንዳይገባ በመወሰን ለሰላም ዝግጁነቱን ባሳየበት፤ የሕወሓትን የጡት አባት አቦይ ስብሀትንና ሌሎች አመራሮችን ጭምር ከእስር በመፍታት፣ ሁሉን አካታች አገራዊ ምክክር ለማድረግ ኮሚሽን አቋቁሞ ኮሚሸነሮችን በሰየመበት ፤ በመንግሥታቱ ድርጅትና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኖች የተሰጠን ምክረ ሃሳብ የሚያስፈጽም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አቋቁሞ እየሰራ ባለበት ፤ ይህ አደገኛ ረቂቅ ሕግ ወደፊት መምጣቱ የአሜሪካ መንግሥት ፍላጎት ሌላ መሆኑን ያረጋግጣል። ላለፉት 27 አመታት ከሕወሓት/ኢህአዴግ ጋር ድርና ማግ ሆኖ ሲሰራ የኖረ መንግሥት ዛሬ በሕዝብ ከተመረጠ መንግሥት ጋር ተቀራርቦ ከመስራት ይልቅ ለውድቀቱ ጉድጓድ የሚምስ መሆኑና የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑት ጋር መቆሙ ግብሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አደባባይ እያሰጣው ነው።
ቶም ማሊኖውስኪ እና ግሪጎሪ ሚክስ አርቅቀው ያቀረቡት ይህ ሕግ የኢትዮጵያና የኤርትራ እንዲሁም የሕወሓት ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ዕገዳ የመጣል ፤ ማዕቀቡ ከግለሰቦች ባለፈም በትግራይ ክልል ጦርነት እጃቸው አለበት ያላቸውን ተቋማትና ድርጅቶች ያካትታል። ማዕቀቡን ከሁሉም በላይ አደገኛ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ማለትም ከዓለም ባንክና ከአይኤምኤፍ ብድር እንዳታገኝ እገዳ ይጥላል ። የ HR 6600 ረቂቅ ሕግ በትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ እጃቸው አለበት ብለው ባመኑትና አጥፊ ነው ባሉት አካል ላይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማዕቀብ እንዲጥሉ ሥልጣን ይሰጣል ። በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን የማይተባበር አካል ቅጣት እንደሚጠብቀው እና በክልሉ ሰላም እንዲወርድ መንግሥትና ሕወሓት ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር መግባት እንደሚኖርባቸው ያስገድዳል። በአጭሩ የኢፌዴሪ መንግሥት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ሕወሓትና ሸኔ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለድርድር እንዲቀመጥ የሚያስገደድ ፍርደ ገምድል ሕግ ነው።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚያ ሰሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት መግለጫ ፤ ሕጉ ከጅምሩ መቅረብ ያልነበረበት ፤ አሁንም በሒደት ላይ ያለ ቢሆንም የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡ በተሳሳተ መረጃ ተመርኩዞ የቀረበ ብለውታል። እናም ይህን የማዕቀብ ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ሊቃወመው ይገባል፡፡
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በበኩላቸው በቲዊተር ገጻቸው ፤ ሕጉ በቅርቡ በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ፤ ማንም አገር በሌላ አገር ላይ የሚወስዳቸውን የተናጠል ዕርምጃዎች እንደሚቃወም ግልጽ ማድረጉን አስታውሰዋል። በተመሳሳይ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ፤ “ለኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማምጣት ተብሎ የተረቀቀው ሕግ እንደሚለው ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ለ30 ዓመታት የነገሠውን ውድመትና ቀውስ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ፡፡ ሕጉ የቀውስ ምንጭ የሆነው የሕወሓት ቡድን ምሥራቅ አፍሪካን ዳግም እንዲያወድም የሚያበረታታ ነው፤” ይለዋል።
ከዚህ አኳያ ይሄ አደገኛ ማዕቀብ ከመጽደቁ በፊት በውጭም በአገር ቤት ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ሊቃወሙት ይገባል ። መንግሥትም በማዕቀቡ አደገኝነት ልክ ወዳጆቹንና አጋሮቹን አስተባብሮና አቀናጅቶ ሌት ተቀን ሊሰራ ይገባል። ከዚህ በፊት ግን የገናው ስህተት በይቅርታ መታረም አለበት። ጥሎት ያለፈውም ሀንጎቨር መታከም አለበት።
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊባል በሚችል ሁኔታ በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች ለአገራቸው ህልውናና የግዛት አንድነት ሲሉ ልዩነታቸውን አቆይተው በአንድነት ከመንግሥት ጎን በቆሙበት ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ታላቁን የ 1 ሚሊዮን ለገና ወደ አገር ቤት ግቡ ጥሪ ተቀብለው በከፍተኛ ቁጥር እየገቡ ባለበት፤ በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ለመከላከያ ሰራዊት አቅማቸውን የፈቀደውን ባደረጉበት፤ በቀጣይም በጦርነቱ የተፈተነውን ኢኮኖሚም ሆነ በአሜሪካና በምዕራባውያን የተከፈተብንን የተቀናጀና የተናበበ የዲፕሎማሲ የሚዲያና የኢኮኖሚ አሻጥርና ሴራ ለመቀልበስ ከአገራቸውና ከሕዝባቸው ጎን ቆመው ለመመከት በተዘጋጁበት ቀውጢ ሰዓት በአንድም በሌላ በኩልም አገራችን ለገባችበት ቀውስ ተጠያቂ የሆኑት የእነ አቦይ ስብሀት ክስ ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ በዲያስፖራም ሆነ በአገር ቤት ተፈጥሮ የነበረውን አንድነት ክፉኛ ጉድቶታል።
መንግሥት ሰላምን ለማምጣት ረጅም እርቀት መሔዱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የሕዝብን አንድነት ከሚጎዱ እርምጃዎች ግን ሊታቀብ ይገባል። የእነ አቦይ ስብሀት ክስ ተቋርጦ መፈታት ለመላው ኢትዮጵያውያን አስደንጋጭ ዱብ እዳ ነበር። ለሕዝብ ግልጽ ማብራሪያና መረጃ ሳይሰጥ ፤ የተገለጸበት ሰዓትም ትክክለኛ ስላልነበር ፤ ሁሉንም ዳር እስከ ዳር ከማስደንገጡ ባሻገር ተፈጥሮ የነበረውን አንድነት ክፉኛ ከመጉዳቱ ባሻገር ለመንግሥት የነበረውን ድጋፍ ሸርሽሮታል። ዛሬ HR 6600 መቃወም ላይ የተስተዋለው መቀዛቀዝ የእነ አቦይ ስብሀት መፈታት የፈጠረው ሀንጎቨር ውጤት ነው ።
ስለሆነም ይህን ሀንጎቨር ማከም ያሻል። ለዘላቂ አገራዊ ጥቅምና ሰላም ሲባል መፈታታቸው የአካሄድ ችግር የነበረበት ቢሆንም በመርህ ደረጃ ግን እንደ ኮሶ ቢመርም ውሉ አድሮ ሕዝብ ውሳኔውን ለመቀበል አይቸገር ። ይሁንና ውሳኔው የተገለጸበት timing እና ሕዝብ ሳይመክርበት በድንገት መሆኑ ስህተት ነበር። ስለሆነም መንግሥት ይሄን ስህተቱን አምኖ ዲያስፖራውንም ሆነ መላ ኢትዮጵያውያንን ይቅርታ ጠይቆ HR 6600 ለመቃወምም ሆነ በቀጣይ ለሚገጥሙን ፈተናዎች ሕዝብን ከጎኑ ማሰለፍ አለበት። መቼም ሕወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ለፈጸመው ግፍና ዘረፋ በፓርላማ ይቅርታ የጠየቀ መንግሥት ሕዝብን በአካሄድ ላይ ስለተፈጸመ ክፍተት ይቅርታ ለመጠየቅ ይከብደዋል ብዬ አላስብም።
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም