በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ለኩ ከተማ ተወልደው አድገዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በለኩ ከተማ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በይርጋለም ከተማ ተምረዋል።
ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅም የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርታቸውን በመከታተል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በትምህርት ዓለም እያሉ ትዳር መስርተው ሁለት ልጆችን ያፈሩ በመሆኑ የኑሮ ጫናው እየበረታ ሲመጣ ገቢያቸውን ለማሻሻል ሲሉ የሆቴል ንግድ ሥራን ተቀላቅለዋል፡፡ ከሆቴል ሥራቸው ጎን ለጎን የሠርግና የተለያዩ የድግስ ሥራዎችን ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በመሥራት ልጆቻቸውን አሳድገው አስተምረዋል።
በግላቸው የከፈቱት የሆቴል ሥራ አላዋጣ ብሏቸው ከሥራ ውጭ የነበሩበትን ወቅት ያስታውሳሉ። ያም ሆኖ ግን ከሆቴል ሥራ ውጭ ማንኛውንም የድግስ ሥራዎች በመሥራት በከፍተኛ ጥረትና ትጋት ውጤታማ መሆን ችለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በዋናነት በባልትና እንዲሁም በሆቴል ሥራ ተሰማርተው ከ20 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ወይዘሮ ሳራ ዱኮ ይባላሉ፡፡
እንግዳችን ወይዘሮ ሳራ፤ በሲዳማ ክልል አፖስቶ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ማሰልጠኛ 700 ለሚደርሱ ፖሊሶች ምግብ በማቅረብ የጀመሩት የመጀመሪያው የግል ሥራቸው ከሶስት መቶ ሺ ብር በላይ ለኪሳራ ዳርጓቸው ከሥራ ውጭ ሆነዋል። በዚህ ጊዜ ታዲያ ልጆቻቸው የደረሱና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በመሆናቸው ተመልሰው ወደ ሆቴል ሥራ እንዳይገቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
የልጆቻቸውን ተቃውሞ ተቀብለው ከቤት የዋሉት ወይዘሮ ሳራ ያለ ሥራ መቀመጥ አልተዋጠላቸውም ነበርና የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም እንዲያስችላቸው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ። አዲስ አበባ በገቡበት ወቅትም ለልጃቸው የሥራ ማስታወቂያ ለመመልከት በወጡበት አጋጣሚ ለእርሳቸው የሚመጥን የሆቴል ሥራዎች ከአንድም ሶስት ቦታ በማግኘታቸው የሆቴል ሥራ አትስሪ ብለው ለሚቃወሟቸው ልጆቻቸው ሳይነግሩ ተመዝግበው፣ ተፈትነውና ፈተናውንም አልፈው ለሥራ ዝግጁ ሆኑ። በሶስቱም ቦታ ማለፍ የቻሉት ወይዘሮ ሳራ፤ ምንም እንኳን ከአዲስ አበባ ውጭ ያገኙት ሥራ ከፍ ያለ ደምወዝ ቢኖረውም የልጆቻቸው ምርጫ አዲስ አበባ በመሆኑ በዝቅተኛ ደምወዝ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የማህበረ ቅዱሳን ሆቴልን በኃላፊነት ወስደው የመምራቱን ሥራ ተቀጥረው ሰሩ ፡፡
በ1600 ብር የወር ደምወዝ 51 ሠራተኞችን በማስተዳደር የማህበረ ቅዱሳን ሆቴልን የመሩት ወይዘሮ ሳራ፤ ለሥራ በነበራቸው ተነሳሽነትና ትጋት እንዲሁም የመምራት ብቃት በየጊዜው የሆቴሉን ደረጃ ከፍ በማድረግ ውጤታማ ሆነዋል።
በወቅቱ ቆሎን ጨምረው ደረቅ እንጀራና ቆጮ ሳይቀር ወደ ውጭ አገር በመላክ ገበያውን መቆጣጠር ችለዋል። ወደ ውጭ ከሚልኳቸው ምግቦች በተጨማሪም ሰዎች ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚፈልጓቸውን ድፎ ዳቦ በማስጋገር ጭምር የቤቱን ገበያ በውጤት መርተዋል።
በቆይታቸው ከሠራተኞች ጋር የነበራቸው የሥራ ግንኙነት ቤተሰባዊና በመከባበር ነበር ፤ ከመደበኛው የሆቴሉ ሥራ በተጨማሪ በርካታ የድግስ ሥራዎችን ተቀብለው ማታም ጭምር ትርፍ ሰዓት በማሰራት ሠራተኞቹ ተጨማሪ ክፍያ እንዲያገኙ አድርገው የስራን ክቡርነት ባለው ጊዜ ሁሉ ሰርቶ ማግኘት እንደሚቻል አሳይተዋል። ይህም ከ51 ሠራተኞቻቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ቤተሰባዊ አድርጎታል።
የማስተባበርና የመምራት ልዩ ችሎታ ያላቸው ወይዘሮ ሳራ፤ ችሎታውን ከቤተሰባቸው በተለይም ከወላጅ እናታቸው የተማሩት መሆኑን ያነሳሉ። ወላጅ እናታቸው በአካባቢው ማሕበረሰብ የተወደዱና የተከበሩ ከመሆናቸው ባለፈ በሥራቸው ሁሉም የሚወዳቸውና በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ አንቱ ሳይባሉ ማለፋቸውንም አጫውተውናል።
ለሥራ ትልቅ ግምት የሚሰጡት ወይዘሮ ሳራ፤ በማሕበረ ቅዱሳን ሆቴል ውስጥ በኃላፊነት ባገለገሉበት ወቅት ውጤታማ ሥራን ሠርተው ማለፍ በመቻላቸው ከገንዘብ በላይ ብዙ ልምድና በረከት ማግኘት እንደቻሉና በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከአምስት ዓመታት የሆቴል ሥራ አስኪያጅነት አገልግሎት በኋላ የራሳቸውን ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ያመኑት ወይዘሮ ሳራ፤ በወቅቱ በገጠማቸው ግጭት የማሕበረ ቅዱሳን ሆቴልን ትተው ወጥተዋል።
ወደ ግል ሥራቸው ሲገቡም ከሚያውቁት ሥራ በመነሳት ሽሮና በርበሬን ጨምሮ 45 የሚደርሱ የባልትና ምርቶችን በማዘጋጀት ወደ ንግዱ ዓለም ተመልሰው ገብተዋል። ምርቶቹን ሲያዘጋጁ በዋናነት የገበያ መዳረሻቸው በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ወንደላጤዎች የነበሩ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን ምርቶቻቸውን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ አገር ድረስ የመላክ ዕድል አጋጥሟቸዋል፡፡
ከወንደላጤው በተጨማሪ ማንኛውም የቤተሰብ ኃላፊ ቤተሰቡን ከሚያስተዳድርበት መደበኛ ሥራ በተጨማሪ ሽሮ በርበሬ ለማዘጋጀት የሚተርፍ ጊዜ የሌለው በመሆኑ በርካቶች ጋር ተደራሽ መሆን እንደቻሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ሳራ፤ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ስለመሆናቸው ሲያነሱ ታዲያ እያንዳንዱ የሚያዘጋጁት የባልትና ውጤቶች ጥራታቸው የተጠበቀና ለጤና ተስማሚ በመሆናቸውን ነው። በእርሳቸው ቤት ምንም ዓይነት የባልትና ውጤት በጥራት ተዘጋጅቶ ከመታሸግ ውጭ ከገበያ ተገዝቶ የሚታሸግ ዕድል የለውም።
በእርሳቸው ክትትልና ምጠና የሚዘጋጀው 45 ዓይነት የሚደርሱ የባልትና ውጤቶችና ቅመማ ቅመሞች ታዲያ ከጋራ መኖሪያ ቤት አልፎ በሱፐርማርኬቶችም የሚገኙ እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ ሳራ፤ በተለይም ሀዲያ ሱፐርማርኬትና ሸዋ ሱፐርማርኬትም ለረጅም ጊዜ እያቀረቡ መሆኑን ይናገራሉ።
ባላቸው የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት በነጋዴ ሴቶች ማሕበር አማካኝነት የውጭ አገር ገበያን የመተዋወቅ እድልም አግኝተው ዱባይ ተጉዘዋል። ዱባይ በነበራቸው ቆይታም ማሳያ ሱቆች ምን መምሰል እንዳለባቸውና ሌሎች ሥልጠናዎችን በመውሰድ የውጭው ዓለም ንግድ ምን እንደሚመስል አውቀውና ተረድተው ተመልሰዋል፡፡ ዱባይ አገር ያዩትንና ያገኙትን ልምድ መሰረት በማድረግ ጊዜ ሳይፈጁ ሁለት መቶ ሺ ብር ወጪ በማድረግ የባልትና መሸጫ ሱቃቸውን ቀይረዋል።
በመሆኑም ባማረና በተዋበ የመሸጫ ሱቅ ውስጥ ማሳያዎች ብቻ እንዲታዩ ሆነ። የውጭው ዓለም የንግድ ሂደት የሳባቸውና ይበልጥ ተነሳሽነታቸውን የጨመረላቸው እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ሳራ፤ ከውጭው ዓለም ያገኙትን የተለያዩ ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ማሻሻል በመቻላቸው ተጨማሪ ዕድል በነጋዴ ሴቶች ማሕበር በኩል ዱባይ ላይ በተዘጋጀው የዓለም ገበያ የተለያዩ የባልትና ውጤቶችና ቅመማ ቅመሞችን የማቅረብ ዕድልም አግኝተዋል።
ለዱባይ ላይ ለተዘጋጀው የዓለም ገበያ የባልትና ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ለማቅረብ ሲሰናዱ ታዲያ ግብዓቶቹን ለማግኘት ጅንአድ ከተባለው ጅምላ አቅራቢ የአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ ብር ግብዓት ለመግዛት ባመሩበት አጋጣሚ ከባልትና ሥራቸው በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የሆቴል ሥራቸውን እየሰሩ ያሉበትን የጅንአድ የሠራተኞች ክበብን ለሥራ አጭተው እንደነበር ያስታውሳሉ።
የሆቴል ሥራቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው ታዲያ ከጅንአድ ያገኙትን የባልትና ግብዓቶች እና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን እሴት በመጨመር ሁሉንም በየፈርጁ አዘጋጅተው ከአንድ ሺ ኪሎ ግራም በላይ የባልትና ውጤቶችና ቅመማ ቅመሞችን ዱባይ ላይ በተዘጋጀው የዓለም ገበያ አቅርበዋል። ለዱባይ ካቀረቡት ምርቶች መካከልም በሌላው ዓለም የማይገኙ ከተለያዩ ውህዶች የሚዘጋጁ ምርቶች ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪ የማር ምርት በማቅረብ የዓለም ገበያን መሳተፍ ችለዋል፡፡ በባልትና ሥራቸው ከአገር ውስጥ አልፈው የዓለም ገበያን መቀላቀል የቻሉት ወይዘሮ ሳራ፤ ከዱባይ ንግዳቸው በኋላም በጅንአድ ጊቢ ውስጥ ጭር ብሎ በተመለከቱት የሠራተኞች ክበብ ለመሥራት አስፈላጊ የተባሉ መረጃዎችን አሟልተው የሆቴል ሥራቸውን ጀምረዋል። ከባልትና ሥራቸው ጎን ለጎን ለማስኬድ የጀመሩት የሆቴል ሥራም እንዳሰቡት አዋጭና ተመራጭ ሆኖላቸዋል።
ለዚህም ምክንያቱ በጊቢ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ግብዓቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ነው። ለአብነትም አገር እየጮኸበት ያለውን ዘይት ጨምሮ ስኳር፣ ጤፍ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ሳሙና እንዲሁም ሌሎች ምርቶችንም ከጅንአድ ያገኛሉ። ከጊቢ ውጭ የሚገዙት አትክልት ብቻ ነው።
በእነዚህ ጥቅማጥቅሞች ምክንያት በጊቢ ውስጥ ለሚገኙ ሠራተኞች ምግብ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ። የውጭ ተጠቃሚዎችም መግባት የሚችሉ ሲሆን ከጠዋት ጀምሮ እስከ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ሁሉ ጠዋት ላይ ብዙ ፈላጊ ያለውና ከበሶና ከተልባ የሚዘጋጀውን የቤቱን ጁስ ጨምሮ የተለያዩ ምግቦችን ያቀርባሉ።
በመሆኑም ፓስታ ፣ መኮረኒ እና ሌሎች ምግቦችን ሳይጨምር በትንሹ በቀን ከ150 እንጀራ በላይ ይሸጣሉ፡፡ ለሆቴል ቤት ሥራው ለ15 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን በባልትናው ደግሞ ወፍጮ ቤት የሚሄዱትን ጨምሮ አምስት ሠራተኞች በድምሩ ለ20 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት ወይዘሮ ሳራ፤ በዋናነት ከሚሰሯቸው የባልትና ውጤቶች ዝግጅት እና የሆቴል ሥራቸው በተጨማሪ ሙሉ የድግስ ዕቃዎች ያሏቸው በመሆኑ የተለያዩ ድግሶች ላይ ተንቀሳቅሰው ይሠራሉ። እንዲሁም አገልግል በትዕዛዝ ያዘጋጃሉ።
የሆቴል ሥራ እጅግ አድካሚና ልፋት የሚጠይቅ ቢሆንም የአሠራር ሥርዓት ከተዘረጋለትና በአግባቡ መምራት ከተቻለ ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም የሚሉት ወይዘሮ ሳራ፤ ሠራተኞችን በአግባቡ በመያዝ እራሳቸውን ችለው መስራት እንዲችሉ በማብቃት ኃላፊነት እንደሚሰጡ ይናገራሉ። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከእርሳቸው ጋር የሚሰሩ ሠራተኞች በአብዛኛው የእርሳቸውን መንገድ ተከትሎ የሚሠራ በመሆኑ ጥለው ቢሄዱም ሥራው የማይበላሽ መሆኑን አጫውተውናል። በባልትና ማቀነባበር ሥራቸው የዋንጫ ተሸላሚ እንደነበሩ ያጫወቱን ወይዘሮ ሳራ፤ በርካታ ደንበኞች ያሏቸው መሆኑን እና ደንበኞቹን የሚያገኟቸው በማስታወቂያ ሳይሆን ተጠቃሚ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት እንደሆነም ነግረውናል።
ሰዎች ምርቶቹን ተጠቅመው እርካታን ሲያገኙ ለሌሎች ሰዎች በመንገር በርካታ ደንበኞችን አፍርተዋል። የሚያዘጋጇቸው የባልትና ውጤቶችም ሆኑ በሆቴል ሥራቸው የሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች ሁልጊዜ ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑ ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ማሕበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም ቢሆን ወይዘሮ ሳራ፤ ለበርካቶች እንጀራ መሆን የቻሉ በጎ ሰው ናቸው። ከትውልድ አካባቢያቸው ጀምረው አቅም የሌላቸውን ሕጻናት እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ ያገኟቸውን ልጆች ያስተምራሉ። በበዓላት ወቅትም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ አቅመ ደካሞችን ያግዛሉ።
ለ20 ሰራተኞች ከፈጠሩት የሥራ ዕድል በተጨማሪም ሥራ ለመሥራት የሚፈልጉና መነሻ ካፒታል ለሌላቸው ሰዎች የባልትና ምርቶችን በቅናሽ በማስረከብ መሸጥ እንዲችሉና ድርሻቸውን እንዲወስዱ ያደርጋሉ። በዚህ ሂደት ጥሩ ደረጃ ደርሰው የራሳቸውን ምርት አዘጋጅተው የሚሰሩም ስለመኖራቸውም ወይዘሮ ሳራ አጫውተውናል፡፡
የባልትና ሥራዬ እጅጉን ይስበኛል የሚሉት ወይዘሮ ሳራ፤ በቀጣይም በስፋት ለመሥራት የሚያስቡት የባልትና ሥራውን በመሆኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ። የውጭውን ገበያ መቀላቀል የቻሉ በመሆናቸውም በስፋት በማዘጋጀት ከአገር ውስጥ አልፈው በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።
ከፍላጎት ባለፈም ወደ ውጭ መላክ ከሚፈልጉ ደንበኞቻቸው ጋር በመቀናጀት እየላኩ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም የእንጀራ ድርቆሽ ወደ ኮሪያ አገር ለመላክ በዝግጅት ላይ ሲሆኑ በሳምንት እስከ አንድ ሺ እንጀራ አድርቀው ለመላክ ተስማምተዋል። ታዲያ ይህ ሥራ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ እንዲመጣ በጠየቁት መሰረት ሕጋዊ ሲሆንላቸው ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሥራውን በማሕበር ለመሥራት አቅደዋል፡፡
ድርቆሽ እንጀራ ወደ ኮሪያ አገር ለመላክ በዝግጅት ላይ ያሉት ወይዘሮ ሳራ ‹‹ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ፍላጎትና ተነሳሽነቱ ካለ ውጤታማ ለመሆን ይቻላል። ማንም ሰው ምንም ነገር ከእናቱ ሆድ አልተማረም›› በማለት በተለይም ሴቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መሥራት ከቻሉ ዓለምን መለወጥ የሚችሉ ናቸው ይላሉ። እኛም የእርሳቸውን ሃሳብ በመጋራት ሰርተን ለመለወጥ እንትጋ በማለት አበቃን ። ሰላም!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014