አከራካሪው – “አገር ማለት ሰው ነው!”
በ2007 ዓ.ም ለዘጠነኛ ጊዜ በቤኒሻንጉል ክልል ለተከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ድምቀት እንዲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴያትር ጥበባት ክፍል ተማሪዎች አንድ ሙዚቃዊ ድራማ ተዘጋጅቶ የአሶሳን ከተማ በምሽት አድምቆ ነበር።
ለትርዒቱ የተሰጠው ርዕስም ሆነ ጭብጡ፤ “አገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ነው አገር ማለት” የሚል ነበር። ይህ ትርዒት ከቀረበበት ዕለት ጀምሮ ዛሬም ድረስ “አገር ማለት ሰው ነው” የሚለው ፍልስፍናዊ ሃሳብ በተለያዩ ጽንፎች አቧድኖ ዜጎችን እንዳከራከረ ዛሬም ድረስ ዘልቋል።
“አገር ማለት ሰው ብቻ አይደለም። መልክዓ ምድሩ፣ የብሔረሰቦች ታሪክ፣ ባህላቸውና ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸውና ማሕበራዊ ተራክቧቸው ወዘተ. የአገር አካል እንደሆነ እስካልታመነ ድረስ ‘አገር ማለት ሰው ብቻ ከሆነ’ ትርጉሙ ይዛባል።
የፖለቲካዊ መዘዙም ተመዝዞ አያልቅም” የሚል መከራከሪያ ይቀርብበታል። እርግጥ ነው ያለሰው ተራራና ወንዙ፣ ሸለቆና ሜዳው ወይንም ውበቱ የሚያማልለው መልክዓ ምድራዊ ገጽታ ብቻውን ትርጉም ላይኖረው ይችላል።
ቢሆንም ግን አገር ማለት ሰው ብቻ ከሆነ፤ ሰው ማለትም አገር ብቻ ከሆነ ስደተኝነት ቃሉና ተግባሩ ለምን የዓለማችን ፈተና ሆነ? ሰው በሰውነቱ ብቻ ያለምንም ተጨማሪ መስፈርት ክብሩ የሚጠበቅለት ከሆነ እንደምን ከሠፈሬ ውጣ፣ ክልሌን ልቀቅ፣ እኔ መንደር አትድረስ እየተባለ ሰው ሰውን ሊያፈናቅል ሊገልና ሊያደማ ቻለ፤ የሞራል ብርታትንስ ከየት አገኘ? ‘አገር ማለት ሰው ከሆነ’ ማንም ሰው ባህር ተሻግሮና ውቂያኖስ አቋርጦ በመፍለስ ያለምንም ፈተና የፈለገበት አገር ለመኖር ስለምን አልቻለም? ፖለቲከኞች ለድብቅ ዓላማ የሚያስተጋቡት የተጣመመ ፍልስፍና እንጂ እውነታነት የለውም። ” የሚሉት ሃሳቦች የመከራከሪያው መርቻ ብቻ ሳይሆኑ የመጨረሻው የጡዘቱ ማጠቃለያ ሃሳቦች ጭምር ናቸው።
“ይህን ድብቅ አጀንዳ የተላበሰ ፍልስፍና በብሔር ብሔረሰቦች በዓል ላይ እንዲናኝ የተፈለገበት ምሥጢራዊ ተልዕኮ የሕዝብ ቁጣ እንደ “ጥንጣን” አመንዥኮ የገነደሰው ሕወሓት/ኢህአዴግ አንዳንዶቹን የአገሪቱን ወሰኖች እያዛባ ሊያስፈጽም የፈለገበትን ሴራና ሸር ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ዘዴ ነበር። ” እየተባለም ታምቷል። መከራከሪያው ደመቅ ብሎና ጎልቶ ዛሬም ድረስ መደመጡ ጉዳዩ በግልጽና ተከታታይ ውይይቶች እልባት ባለማግኘቱ ይመስላል።
ይህ እንዳለ ሆኖ “አገር ማለት ሰው ነው ፍልስፍና” በትውልዱም ውስጥ በሚገባ ሰርጾ እንዲገባ በማስፈለጉ ይመስላል በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር የመማሪያ መጻሕፍት (ከ5ኛ – 12ኛ ክፍሎች) በተለይም “የአገር ፍቅር – Patriotism” በሚለው ምዕራፍ ውስጥ እንዲካተት ተድበስብሶም ቢሆን ሙከራ ተደርጓል። ከመጻሕፍቱ አዘጋጆች መካከል አንዱ ይህ ጸሐፊ ስለነበር ሴራውን ለማክሸፍ በጥቂቱም ቢሆን መፍጨርጨሩ አልቀረም ነበር።
ለማንኛውም አገርን አገር የሚያሰኙት ሰውና ተያያዥ የፍልስፍና ጉዳዮች ይህንን ያህል ካንደረደሩን ዘንዳ ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ሃሳባችን ሰብሰብ አድርገን እንደተባለው “ሰው ማለት አገር” ይሁንም አይሁን ልክ እንደ ሰው አገርም መታመሟ ግን እውነትነቱ የገዘፈ ስለሆነ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህም…።
አገራችን ታማለች፤ ፈውስም ትፈልጋለች፤
በዕድሜ የገፉ አዛውንት እናቶች ታመው የአልጋ ቁራኛ በሚሆኑበት አጋጣሚ ያልጠየቃቸውን ሰው የሚቀየሙት፤ “እከሌ ሕመሜን ሰምቶ እንዴት እግዜር ይግደለሽ ብሎ ሳይጠይቀኝ ቀረ?” በሚል የምሬት ቃል ነው። ምፀታዊው አባባላቸው ምን መልዕክት “አገር ታማለች፤ የሚያክማት ሕዝብ ነው” እንደሚያስተላልፍ ግልጽ ነው።
ኢትዮጵያም ታማለች። ሕመሟም ጽኑ ነው። ብዙኃኑ ልጆቿ በነጋ በጠባ በጸሎትና በእግዚኦታ የእናትነት ፍቅሯ ግድ እያላቸው ውሎ አዳሯን የሚከታተሉት ክፉውን እንዲያርቅላት “እግዜር ይማርሽ!” የሚለውን ምኞቶቻቸውን በመግለጽ ነው።
በአንጻሩ ሕመሙ ጸንቶባት ከሞት አፈፋ ብትደርስ ደስታቸው ገደብ ጥሶ የሚቦርቁ የራሷ ውላጆች በተለይም የሽብር ሱስ ተጸናውቷቸው፣ የክፋት ኃይላት እየነዷቸው፣ በሽምቅና በደባ ለሞቷ የሚካድሙና ለውድቀቷም የሚሳሉ ብዙዎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ግማሹ ተጋላቢ፣ ግማሹ ተቀላቢ፣ ከፊሉ ተደጓሚ እንደሆነ ተግባራቸው እየመሰከረ ነው። “አገሬ ሕመምሽ ምንድን ነው?” ተብላ ብትጠየቅ ከእግሯ እስከ አናቷ የምትዘረዝራቸው የበሽታ ዓይነቶችና ለደዌዋ በምክንያትነት የሚጠቀሱት የተሕዋሲያን ብዛት እጅግ ብዙ እንደሚሆኑ ለመገመት አይከብድም።
ተሕዋሲያኑ የበቀሉት ደግሞ ከውስጥም ከውጭም ነው። “ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነው፤ አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው” እንዲል ቀረርቶኛው፤ አገሬን ቢቻል “የሚቻለውን ሁሉ ሊያደርጉባት” ባይቻል ደግሞ በደዌዋ አልጋ ላይ ሊያሰነብቷት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማያጠነጥኑት ሴራ፣ የማይቆፍሩላት ጉድጓድ የለም ማለት ይቻላል። የበሽታዋን ዝርዝር እንጠቋቁም ብንል አናቷ አካባቢ የሚያዞሯት፣ በጀርባዋ በኩል የሚያቆስሏት፣ በደረቷ በኩል ውጋት ሆነው የቀሰፏት፣ ቀና እንዳትል ወገቧን ያጎበጡ ወዘተ. ቫይረሶችና ተሕዋስያን ባህርያቸውም ሆነ ዓይነታቸው በርከት ያለ ነው።
አገርን በመወለድ ከዕትብታችን ጋር የምንቆራኛት፤ ስንሞት የበድናችን ማረፊያ ሆና በሰላም የምታሳርፈን መሆኗ እየተዘነጋ እሷን ራሷን መልሶ ለመግደል ሲሞከር ማስተዋል እንቆቅልሹን ይበልጥ ያወሳስበዋል። ለማንኛውም የአገርን ሕመም ይበልጥ አግዝፎ ከመናገር ይልቅ በፈዋሽ ባለመድኃኒተኞች ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይሆናል።
ባለመድኃኒቶቹ አድራሻቸው ሩቅ አይደለም። “ባለ መድኃኒት ሆይ ወዴት ነህ?” አሰኝቶ የሚያስጨንቅም አይደለም። ለአገር ሕመም ዋነኞቹ ባለመድኃኒቶች ፖለቲከኞች፣ አንቂ ተብዬዎች ወይንም ነቅናቂ ነን ባዮች አይደሉም። የፈዋሽነት ምሥጢሩ ያለው በራሷ ልጆች ዘንድ ነው፤ በሕዝቧ እጅ ማለትም ይቻላል። እንዴት? አንዳንድ የመፍትሔ ጉዳዮችን እየጠቋቆምን ጥቂት እናመላክት። “በቃ!”
“No More!”
ይህ እንቅስቃሴ በዲያስፖራው ዘንድ ተጋግሎ የሰነበተው የባዕዳን አገራትንና መንግሥታትን ጣልቃ ገብነት ለማውገዝና ለማስቆም የዘመቻ መልክ ይዞ አደባባይ በመዋል እንደነበር አይዘነጋም።
የዘመቻው መልዕክት ሲጠቃለል “እስከ ዛሬ ታግሰናል፤ ወደረኞቻችን ወደ ቀልባቸው ይመለሳሉ በማለትም ባለመናወጥ ድርጊታቸውን በቅርበት እየተከታተልን ጨዋ ባህላችንን በማክበር ለጥሞና ጊዜ ሰጥተናቸው ነበር። ጥረታችንንና ትዕግሥታችን ቁብ አልሰጣቸውም። ስለዚህም በቃን! በዕለት ጉርሻ እያስፈራራችሁ አትጎትጉቱን። የልማት አጋርነታችሁን የመቅጫ በትር አድርጋችሁ ልትገርፉን አትሞክሩ።
ከጠላቶቻችን ጋር በማበር ለጥፋታችን አትስሩ ወዘተ.” የሚል ነበር። ዓለም አቀፉ “የበቃ!” አንቅስቃሴ መልእክቶች እነዚህና እነዚህን በመሳሰሉት ይዘቶች ዙሪያ በመላው ዓለም በተበተኑት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተስተጋባው በተባበረ ድምጽ ነበር። ግሩም ትብብር! ዘመቻው ብዙዎችን አስደንግጦ፣ አንዳንዶችንም አስደንብሮ የተወሰነ ውጤት ማስገኘቱ አይካድም።
ይህ ዓለም አቀፍ ዘመቻ በርቀት ላሉትና ለወደረኞቻችን ብቻ መሆን ያለበት ግን አይመስለንም። ዘመቻው ወደ ራሳችን ዞሮ በራሳችንና በኢትዮጵያ የበሽታ ጉዳይ ላይ ተባብረን “በቃ!” በማለት ለዘመቻ መንቀሳቀስ ያለብን ይመስለናል። ለምሳሌ፡-
የዘረኝነት ልክፍት በቃ!
የብሔርና የጎጥ ጥብቅናችንና አምልኮታችን ወደ ከፋ ጫፍ አስፈንጥሮ አገራችንን እንደጎዳ በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል። አእምሯችንን ከበከለው ከዚህ ክፉ ደዌ ራሳችንን ነፃ አውጥተን ሕመምተኛዋ ኢትዮጵያ ልትፈወስ ይገባል።
የበሽታዋ መንስኤ የሆኑት ቡድኖችና ግለሰቦች ማስተዋላቸውን የጋረደውን ዐይነ ርግብ አውልቀው በቅድሚያ ራሳችውን እንዲፈውሱ፤ ከዚያም ለአገራቸው ሕመም የፈዋሽነት ሚናቸውን እንዲወጡ የአገራዊ “በቃን!” እንቅስቃሴው ሊጀመር ጫፍ ላይ የደረሰ ይመስላል።
የበቃ! ዘመቻው መተግበር ያለበት ሕመሟን በሚያባብሱና ግርሻ እየሆኑ በሚያውኳት “ፖለቲከኞች” ላይ እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ ሊገለጽላቸው ይገባል። “መስሎንና አጅበን እያጨበጨብን ተከትለናችሁ ነበር “አገር ታማለች፤ የሚያክማት ሕዝብ ነው”አሁን ግን በቃን! የሞት ድግሳችሁ፣ የሴራ መንገዳችሁ አንገፈገፈን። ለአገራችንም ሕመም ዋና ሰበብ ሆነ – ስለዚህም በቃን! እናንተም በቃችሁን!” ብለን በድፍረት ልንነግራቸው ይገባል።
ምክራችንን መስማት ካልፈለጉም በእምቢታችን ልንቀጣቸው፣ ስለ እብሪታቸው ልናገልላቸው ይገባል። በፈጣሪ ፀጋ እንጂ በወላጆቻችን ወይንም በራሳችን ዕቅድ ያልተገኘንበትን የዘር ሀረግ እየመዘዝን ወይንም ለጠብ መቆስቆሻነትና ለመከፋፈል እንድናውል ሲቀሰቅሱን አጀንዳቸው ክፋት ብቻም ሳይሆን እርኩሰት ጭምር እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ እንንገራቸው። “ሕዝባችን” እያሉ ራሳቸውን በሕዝብ ስም ሸፍነው መዝለል ሲጀምሩም ቁልቁል ስበን ከትዕቢታቸው ተራራ ላይ እናውርዳቸው።
በብሔር ስም ለጠብና ለሞት ጭዳ ላለመሆንም በቃን! እንበላቸው። የሚፈሰው የንጹሐን ደም መከራችንን እያከበደ፣ የስደተኞችና የተፈናቃዮች እምባ እሳት ሆኖ አገራችንንም ሆነ ሕዝባችንን እየለበለበ ብዙ መጓዝ ስለማንችል በቃን! ለማለት እንጨክን። ብሔሬ፣ ጎጤ፣ ምንትሴ እያሉ እርስ በእርስ መሰያየፉ አከሰረን እንጂ አላበለጸገንም። አናከሰን እንጂ አላስተቃቀፈንም – ስለዚህም በቃን! ይህንን የበቃን መርህ በተባበረ ድምጽና መደማመጥ ወደ ተግባር የምንለውጥ ከሆነ እኛም ሆንን ኢትዮጵያ ፈጥነንና ፈጥና የማንፈወስበት ምክንያት አይኖርም።
ለፖለቲካ ሴራና ለፖለቲከኞች ሽንገላ በቃን!
ከላይ የዘረዘርናቸው ሃሳቦች ብዙውን ጊዜ ነፍስ ዘርተው መናፈስ የሚጀምሩት በፖለቲካ መነባንብ ታጅለው እንደሆነ አልጠፋንም። ስለዚህም ይሄኛው ንዑስ ርዕስም ከላይኛው ሃሳብ ጋር የሚጣቀስ መሆኑ ባይጠፋንም አጽንኦት ለመስጠትና ጫን ብሎ ነገሮችን ለማየት ስለሚረዳን አንዳንድ ሃሳቦችን በተለየ አመለካከት ለማየት ግድ ይላል። ረቡዕ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ ላይ “ፖለቲካና ኪነ ጥበብ” በሚል ርዕስ ባስነበብኩት ጽሑፍ ውስጥ ስለ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ዘርዘር ያሉ ሃሳቦችን ለማሳየት ስለሞከርኩ አንባቢያን መለስ ብለው እንዲያነቡት እጋብዛለሁ።
አንዳንድ ፖለቲከኞች በሚያራምዱት ሴራና ሽንገላ ተቀስፋ እያቃሰተች ላለችው አገራችን ፈውስ እንዲሆን በመመኘት በቃን! ብለን ሕዝባዊ ድምጻችንን የምናሰማባቸው ብዙ ጉዳዮች ስለመኖራቸውም ደጋግመን ለማሳየት ሞክረናል።
ፖለቲካና የሽመና ጥበብ ባይመሳሰሉም በአተገባበር ግን የመቀራረብ ባህርይ ይስተዋልባቸዋል። ሽመና በድርና በማግ፣ ልዩ ልዩ ቀለማት ባላቸው ክሮችና የካሎስ ጥለቶች ተሰላስሎና ተቀናብሮ በጠቢቡ ሸማኔ የሚከወን እጅግ ድንቅ የእጅ ሙያ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ጥረትና ልፋት ተሸምኖ ከለባሾች ዘንድ የሚደርሰው “የአገር ልብስ” ነዎሩ አሰኝቶ ያስከብራል፤ ያደምቃልም።
በፖለቲከኞች የሚሸመነው “የአይዲዮሎጂ ልብስ” ግን ከቁሳዊው ልብስ በእጅጉ የተለየ ነው። ብዙውን ጊዜ በሴራ ድርና ማግ፣ በአማላይ የቅስቀሳና የመሸንገያ ቀለማት ተለብጦ ሕዝብ እንዲደርበው የሚሰጠው የተስፋ “ልብስ” ሸማኔዎቹን ፖለቲከኞች ራሳቸውን የሥልጣን መጎናጸፊያ ይደርብላቸው ካልሆነ በስተቀር ብዙውን ጊዜ ለብዙኃኑ ሲበጅ አይስተዋልም – በተለይም በእኛ አገር ዐውድ ስንፈትሸው።
አገራችንን ከሚያምሱት ጋር በስውርና በድብቅ ጤና እየነሱን ያሉት የሃሳብ ድንክዬ ፖለቲከኞች ነን ባይ “አንቋራሪዎች” እና በየዋህነት ወይንም አድርጉ ስለተባልን ብቻ የምርጫ ካርዳችንን አዘናግተውን ያባከንባቸው አንዳንድ “የበግ ቆዳ ለባሽ ተኩላዎችን” ቆም ብለን እንድንፈትሻቸው ሕዝባዊ ሥልጣናችን ግድ የሚለን ወቅት ላይ ደርሰናል።
መፈተሽ ብቻም ሳይሆን ተኩላዊ ባህርያቸውን በማጋለጥ ጭምር በቃን! No More! በማለት “እናት ዓለም” የውጥር ከተያዘችበት ክፉ ደዌ ነፃ እንድትወጣ “ሐኪም” በመሆን የፈዋሽነቱን ሚና ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ለመወጣት ልናመር ይገባል። የአገራችንን የበሽታ ቁጥር ካበራከቱት ችግሮች መካከል ሌላው የተጠላለፈው መንግሥታዊ ቢሮክራሲም ከበቃን በላይ ሕዝባዊ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ይመስለናል። ዜጎችን ለሚያስለቅሰው፣ በሙስና ለተዘፈቀው፣ በተገልጋዮች እንግልትና ብሶት ለደለበው፣ እምባና እዮታ ሲያስተናግድ ለሚውለው የአገሪቱ ቢሮክራሲ እኛ ብዙኃን ዜጎች “በቃን!” ብለን የተሸበብንበትን ልጓም ከአንደበታችን ላይ በማውለቅ ዘመቻውን ልናጋግል ይገባል።
“መንግሥት ሆይ!” እያልን ማላዘኑ ኢትዮጵያን ከደዌ አልጋዋ ላይ ቀና ሊያደርጋት ስላልቻለ እኛው ለራሳችን በራሳችን “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ብለን ልንጨክን ይገባል። የመንግሥትን ተራዳዒነት እየጠበቅን ብቻ ማላዘኑ አልቅሰን ኖረን አልቅሰን የመሞት ያህል እየሆነብን ስለሆነ በሕዝባዊ ድምጻችን “በቃን!” ልንል ይገባል።
እየሰማ እንዳልሰማ፣ እየተመከረ እንዳልተመከረ፣ እያየ እንዳላየ ጩኸታችንን ለመመለስ ፈቃድ ለነሳን መንግሥታችን ወደ ቀልቡ ተመልሶ ይታደገን ከሆነ በሕግ አምላክ ሕጉን ያስጠብቅልን። ጉልበት ስላለውም በጉልበትህ አምላክ ከጉልበተኞችና ከሙሰኞች አፍ አስጥለን።
ካልሆነም በቅዱሳት መጻሕፍት አምላክ እንማጠናለን ቢሮክራሲህ ላይ ዱላህንና ሰይፍህን አንስተህ ኢትዮጵያን ከጽኑ በሽታ፣ ሕዝቡን ከፍትሕ ርሃብና ጥማት ታደግ” – በበቃን ከሚያስጮኹን መከራዎቻችን መካከል በጣም ጥቂቶቹ እነዚህን ይመስላሉ። መንግሥት ሆይ ሰማኸን!? ሀገሬ ሆይ ፈጣሪ ይማርሽ።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014