የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማሕበር ከተመሰረተ ሰላሳ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በየዓመቱም ጉባኤውን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ያካሂዳል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በበርካታ ቁጥር ባላቸው ተሳታፊዎች ጉባኤውን ማካሄድ አልቻለም።
ዘንድሮም 33ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን በውስን ሰው ለሶስት ቀናት ከሰሞኑ በአዲስ አበባ አካሂዷል። በአካል ከተገኙ ተሳታፊዎች ባለፈ ግን በአስራ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የማሕበሩ አባላቱ በየዩኒቨርሲቲዎቹ በተዘጋጁ አዳራሾች በኦን ላይን ጉባኤውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።
የማሕበሩ የዘንድሮ ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳም በዋናነት በአገሪቱ የተከሰተው የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ቀውስ ላይ ያተኮረ ነበር። በተለይ ደግሞ በግጭት ጊዜ ምን አይነት የጤና አጠባበቅ አገልግሎት መሰጠት እንዳለበትና እንዴትስ አገልግሎቱ ሊሰጥ እንደሚችል፤ በቀጣይም እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ግጭቶች ሲያጋጥሙ ለእነዚህ ግጭቶች የማይበገር የጤና ሥርዓት እንዴት መፍጠር እንደሚቻል በጉባኤው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ተመክሮበታል፤ ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበዋል።
የጠቅላላ ጉባኤ አባላት/የጤና ባለሙያዎች/፣ የቦርድ አባላት፣ የየክልሉ ሙያ ማሕበራት አባላትና ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች በጥቅሉ 120 የሚጠጉ ሰዎች በተሳተፉበት በዚህ ጉባኤ፣ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትና ተጽዕኗቸው አንድ የጉባኤው አጀንዳ ነበር።
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማሕበር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን በዚህ ጉባኤ ላይ እንደሚገልጹት ደግሞ፤ በግጭቱ ምክንያት በተለይ ደግሞ በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ የጤና ተቋማት ወድመዋል። ይህም የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ቀውስ አስከትሏል። ጤና ተቋም ከሌለ የጤና ሥርዓት አይኖርምና በርካታ የጤና ተቋማት በግጭቱ ምክንያት አገልግሎት ለመስጠት አልቻሉም። በተሟላ ቁመና ላይም አይደሉም።
አንዳንዶቹ ግን በተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች በመጠኑ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። አብዛኛዎቹ ጤና ተቋማት በግጭቱ ምክንያት በውስጣቸው ያሉ የህክምና መሳሪያዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መድሃኒቶች እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች ወድመውባቸዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በከፊል የወደሙ ጤና ተቋማት አሉ።
ሆኖም በአብዛዎቹ የጤና ተቋማት ላይ ከደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመት አንፃር ገና ብዙ መስራትን ይጠይቃል። ዶክተር አለማየሁ እንደሚሉት፤ እንደ ጤና አጠባበቅ ማሕበር ካለው የአቅም ውስንነትና ከሚሰራው ሥራ አንፃር በአብዛኛው ትኩረቱ መንግሥትን መደገፍ ነው።
በዚሁ መሰረትም ልክ በኮቪድ ጊዜ ማሕሩ እንዳደረገው አሁንም የወደሙ የጤና ተቋማትን ለመገንባት የቅስቀሳ ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል። ሆኖም ችግሩ ሰፊ ከመሆኑ አኳያ የቅስቀሳ ሥራ ብቻ በቂ ባለመሆኑ በግጭቱ የወደሙ የተወሰኑ የጤና ተቋማት መሰረታዊ የሚባሉ የጤና አገልግሎቶችን እንዲጀምሩ የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረግ ጀምሯል።
ከዚህ ባሻገር የጤና ሥርዓቱ ምሶሶ ናቸው የሚባሉት የጤና ባለሙያዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ተፅእኖ ደርሶባቸዋል፤ ብዙዎቹም ሸሽተዋል። ንብረታቸውም ተዘርፏል፤ የሞራል ስብራትም አጋጥሟቸዋል።
ከዚህ አንፃር እነዚህን የጤና ባለሙያዎችን ሞራላቸውን አነሳስቶ፤ የደረሰባቸውንም የአዕምሮ መሸበር አክሞ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማሕበሩ እያነቃቃና አነስተኛ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።
በተለይ ደግሞ በሰሜን ወሎ አካባቢና በአፋር ክልል ድጋፍ እያደረገ ነው። ጤና ሚኒስቴር በአብዛኛው ከማዕከልና ከክልሎች ጋር በማቀናጀት ሆስፒታሎችን እደገፈ ነው። ለሆስፒታሎች ህመምተኞችን የሚያቀብሉት ደግሞ ጤና ጣቢያዎች በመሆናቸውና በርካታ አገልግሎቶችንም የሚሰጡት እነሱ በመሆናቸው ማሕበሩ ጤና ጣቢያዎቹን በቁሳቁስና የጤና ባለሙያዎቹን ደግሞ በሥነ ልቦና እና በአዕምሮ ሥልጠና ያግዛል።
ወደ ሥራ ሊያስገባቸው የሚችሉ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። እንደ ሙያ ማሕበርም የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማሕበር ከመሰል የጤና ማሕበራትና ተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ የሲቪክ ማሕበራት ጋር በመሆን በግጭቱ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት፣ የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
ማሕበሩ በግጭቱ ምክንያት የተቆራረጠውን የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለማስቀጠል እስካሁን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህ በኋላም የማሕበሩ እንቅስቃሴ በይበልጥ ስልታዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ጉባኤም ማሕበሩ እስካሁን ያላያቸውን አዳዲስ ነገሮች፣ አሰራሮችና እውቀቶችን አግኝቷል። ከጤና ዘርፍ ባሻገር ሌሎች ሴክተሮችም እንዲሳተፉና በጋራ ሥራዎች እንዲሰሩም ይደረጋል ብለዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014