የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ጎንደር ክፍለ ሀገር ሰሜን አውራጃ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ትምህርት ሥርዓት መሰረት የድቁና ትምህርት ጀምረው እስከ ፆመ-ድጓ ደርሰዋል።
በመቀጠልም ድልይብዛ እና ጎርጎራ በተባሉ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ወቅቱ ግርግር እና ብሔራዊ ውትድርና ዘመቻ የተፋፋመበት ስለነበር ሸሸተው ደባርቅ ከተማ በመሄድ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመደቡ።
ሆኖም ባልመረጡት የትምህርት ዘርፍ መመደባቸው ቅር አሰኛቸውና ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር አቀረቡ። ይሁንና አጥጋቢ መልስ በማጣታቸው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሰርተክፊታቸውን ተቀብለው ወደቀያቸው ተመለሱ። ገና በለጋ እድሜያቸው ስለመብታቸው መታገል የጀመሩት እኚሁ ሰው ሃኪም የመሆን የልጅነት ህልማቸውን ለማሳካት ሲሉ ዳግመኛ የ12ኛ ክፍል ፈተና በመውሰድ ውጤታቸውን አሻሻሉ።
አሁንም ያመጡት ከፍተኛ ውጤት ቢሆንም በግል ለተፈተነ ሰው በህክምና መማር አይቻልም ተባለና አሁንም የመማር ፍላጎታቸው ሳይሳካላቸው ቆዩ። በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ ለሶስተኛ ጊዜ ተፈትነው ውጤታቸውን 3 ነጥብ6 አደረሱ።
ካሰቡት ቦታ ለመድረስ ጠንካራ ሥነ-ልቦና እና እልህ ይዘው የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆዩ። በኋላም በነበራቸው ብርቱ ተሳትፎ በአካባቢያቸው በዳኝነት ትምህርት የመሰልጠን እድሉን አገኙ። ሥልጠናቸውን እንዳጠናቀቁም በዳኝነት ለሰባት ዓመታት ባህርዳር ከተማ አገለገሉ።
እንዲሁም በዳኝነት አስተዳደርና በአሰልጣኝነት ለተጨማሪ ሰባት ዓመታት ሰርተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ገብተው በመማር ዲፕሎማቸውን ተቀብለዋል፤ ቀጥለውም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዚያው የትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ። ዲግሪያቸውን እንደያዙ ግን የዳኝነቱን ሥራ በመተው በግላቸው ፈቃድ አውጥተው የጥብቅና ሥራ ጀመሩ። ለትምህርት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጡት እንግዳችን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዓለምአቀፍ ሰብአዊ መብት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡
ገና ከተማሪነታቸው ጀምሮ ለመብታው መታገል የጀመሩት እኚሁ ሰው በኋላም አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸውን በሰብአዊ መብት ለማስከበር ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በዚህም የሰብአዊ መብት ተከራካሪነታቸው በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ይህም ለሰብአዊ መብት መከበር የሚያርጉትን ጥረት የበለጠ አጠናክረው ለመሄድ አቅም ፈጠረላቸው። በተለይ በ2008 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም ላይ በተፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ተሟግተዋል።
በማዕከላዊ እስር ቤት ሲሰቃዩ የነበሩ በአሸባሪነት ያለፍርድ ለቆዩ 350 ሰዎች ነፃ አገልግሎት ሰጥተዋል። አሁንም ድረስ በሰብአዊ መብት ተከራካሪነታቸው የቀጠሉት የዛሬው የዘመን እንግዳችን በተለይ በሕገ-መንግሥቱ እና በአጠቃላይ የመሬት ሊዝ ሕግ ዙሪያ ሁለት መጻሕፍትን አሳትመው ለአንባቢያን አድርሰዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በጥብቅና እና በሕግ ማማከር ሥራ ላይ ይገኛሉ፤ እንግዳችን አቶ አለልኝ ምህረቱ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ እንግዳ አድርጎ ይዞ ቀርቧል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ለንባብ ስላበቋቸው ሁለት መጻሕፍት ጥቂት በሉንና ውይይታችንን እንጀምር? አቶ አለልኝ፡- በመጀመሪያ ያሳተምኩት መጽሐፍ ርዕስ ‹‹የሊዝ ሕግ መዘዝ›› ነው የሚለው። ይህም ሲባል የኢትዮጵያ የሊዝ ሕግ ከሌሎች ከዓለም ከተሞች የሊዝ ሕግ ጋር ሲነፃፀር በጣም የወረደና የሰውን ልጅ መብት የሚጥስ መሆኑን የሚተነትን ነው።
የአውሮፓን፤ የአሜሪካን፤ የቻይናን፤ የህንድን የሊዝ ሕግ በመዳሰስና ጥልቅ ጥናት በማካሄድ ነው የተዘጋጀው። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው 2009 ዓ.ም ነበር፤ በወቅቱ ለናሙና ያወጣኋቸው ሃሳቦች ለምክር ቤት አባላት እንዲያኙትና የሕጉን ጉድለቶች እንዲያዩ አድርጌ ነበር። የኢትዮጵያ የሊዝ ሕግ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ፤ በተለይ ሰብአዊ መብትን ጭምር የሚፃረር መሆኑን ለማሳየት ሞክሬ ነበር። ሰብአዊ መብት ሕጉ ከሚሰጣቸው መብቶች መካከል አንዱ መጠለያ ማግኘት ነው፤ ሆኖም የሊዝ ሕጉ ይህንን መጠለያ እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሆነ ለማሳየት ሞክሪያለሁ።
ከዚያም አልፎ ትልቁ ጉድለቱ የተሰራ ከተማን እንደገና ባድማ ማድረግ የሚያስችል አንቀፅ አለው። ሕጉ ልማት ያለማ ሰው ለ60 ዓመት ውል ተሰጥቶት ከሆነ ሁለት ዓመት ሲቀረው ውሉ እንዲታደስለት እንደሚጠይቅ ይደነግጋል።
በዚያ ሁለት ዓመት ውስጥ አስተዳደሩ ውሉን ካላደሰለት ግን የሰራውን አፍርሶ ይለቃል ነው የሚለው። እንግዲህ አንድ ከተማ ገንብተሸ ሳለ አስተዳደሩ ፈቅዶ ካላደሰልሽ ያንን ከተማ እንድታፈርሺ እድል ይሰጥሻል ማለት ነው። ሌላው ጉድለት ደግሞ አልሚው በተባለው ጊዜ ካላፈረሰ መንግሥት ያለምንም ካሳ ይወርሰዋል፤ በሚል በሕጉ ተቀምጧል።
ያ አልሚ ስንት ወጪ አውጥቶ እና ደክሞ የገነባውን ከተማ ያለምንም ካሳ ተወርሶ እንደሚባረር መደንገጉ መብትን የሚፃረር ሆኖ ነው ያገኘሁት። በተለይ ከአውሮፓ የሊዝ ሕግ ጋር ሲነፃፀር ፍፁም የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጽም በመሆኑ ይህ ሕግ እንዴትና ለምን መሻሻል እንደሚገባ የሚያትት መጽሐፍ ነው።
በአጋጣሚ ግን ይህ መጽሐፍ ከደህንነቶች እጅ ገባና ወዲያውኑ አታሚው መጽሐፉን እንዳያስረክበኝ ከለከሉት። እናም መስከረም 2009 ዓ.ም የታተመ መጽሐፍ አታሚው በደህንነት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል አላስረክብም ብሎኝ በዓመቱ የመንግሥት ለውጥ ከተካሄደ በኋላ ነሃሴ ወር ላይ ነው ያስረከበኝ። አሁንም ቢሆን እየተጠቀሙበት አይደለም እንጂ ሥራ ላይ ቢያውሉት ወይም ቢያሻሽሉ ብዙ ጠቀሜታ ያመጣ ነበር ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የሊዝ ሕግ መልሶ ማፍረስን የሚያበረታታ ስለሆነ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን የሕግ ክፍተት ለሕግ አውጪው አካል ለማሳየት ያደረጉት ጥረት ለምን ሊሳካ አልቻለም? አቶ አለልኝ፡- እንዳነሳሁልሽ ለምክር ቤት አባላት ክፍተቱን ለማሳየት ሞክሪያለሁ። መጽሐፌን ለብዙዎቹ ሰጥቻቸዋለሁ። ግን ያንብቡት፤ አያንብቡት እርግጠኛ መሆን አልችልም። አሁንም ቢሆን ብዙ ለማንበብና ሃሳብ ለመቀበል የሚሻ አባል አለ ብዬ በግሌ አላምንም።
ሃሳብ አንስቶ ለመከራከርም የሚሻ እሳካሁን ስላላየሁ በዚህ በኩል ብዙም ተስፋ አላደርግም። በእኔ በኩል ግን የሚገባኝን ያህል ጥረት አድርጌያለሁ። በደብዳቤም ጭምር ጠይቄያለሁ። የሚገርምሽ በውጭ ሆኜ ከምታገል ውስጥ ሆኜ መታገል አለብኝ ብዬ ፓርላማ ለመግባት ስል ብቻ ከአንድ ፓርቲ ዓርማ ተውሼ በምርጫ ተወዳድሬ ነበር። ግን በአንዳንድ ምክንያቶች ሳልገባ ቀርቻለሁ። በዚህ ጉዳይ ግን ብዙ መናገር አልፈልግም። ሁለተኛውም መጽሐፍ ተፅፎ ያለቀው በ2009 ዓ.ም ነበር።
ግን በወቅቱ ይህንን መጽሐፍ ማሳተም አደገኛ ነበር። ምክንያቱም መጽሐፉ የሚያጠነጥነው የሕገ-መንግሥት ጉድለቶች እና መንግሥታዊ አሸባሪነት በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል ነው የሚያሳየው። በዚያ ወቅት ታዲያ መንግሥታዊ አሸባሪነት ብሎ መናገር ብዙ ችግር ያመጣል። በዚያ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ሳላሳትመው አቆየሁት።
ግን ማቆየቴ ጠቅሞኛል፤ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰጦች እየተጨመሩ ስለመጡ መጽሐፉ ብዙ ሃሳብ ታክሎበት ዳጎስ እንዲል አድርጎታል። ዞሮ ዞሮ ይህም መጽሐፍ የሚያጠነጥነው ሕገመንግሥቱ ላይ ይሁን እንጂ ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኩራል። መሰረታዊ ዓላማውም ከሰብአዊ መብት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን ማሳየት ነው። መጽሐፉ መነሻ አሁን ያለውን የሕገ-መንግሥት ጉድለቶች ከአንቀፅ 1 እስከ 105 ድረስ ጉድለቱን ይተነትናል።
እነዚያ ጉድለቶች በምን መልኩ ቢሻሻሉ ጥሩ ነው? የሰብአዊ መብት የሚጥሱት በምን መንገድ ነው? ለሚሉትን ነገሮች ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል፡፡ አሁን ያለውም ሕገመንግሥት እንኳን ሥራ እንዳይሰራ ሌሎች አዋጆች ሕገ-መንግሥቱን የሚጥሱ በጣም በርካታ አዋጆች አሉ። ለምሳሌ በዋናነት የሚጠቀሰው ምስክሮችና የጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አለ።
ሕገ-መንግሥቱ ማንኛውም በወንጀል የተከሰሰ ሰው በአቃቤ ሕግ የሚቀርበብትን ማስረጃ የማየት፤ የመርመር ሥልጣን አለው ይላል። ይህም ማለት ከሁሉ የሰፋ መብት ይሰጣል። አሁን የጠቀስኩልሽ የምስክሮች እና የጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ግን ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚጣረስ ነው። አሁን ላይ እንደምናየው ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጡ ምስክርነቶች የተከሳሹን መብት ይጥሳል። ምስክሮች የሚደረግላቸውን ጥቅም ስም እስከመለወጥ፤ መልክ እስከመቀየር ድረስ አዋጁ መብት የሚሰጥ መሆኑ ተከሳሹ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ናቸው።
ለምሳሌ አንድ ምስክር በቀዶ ጥገና መልኩን ቢቀይር አልያም በመጋረጃ ጀርባ የሚናገረውን ሰው ማንነት ሳያውቅ የሚሰጥ ምስክርነትም መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ አያመችም። ይህም በሕገመንግሥት የተሰጠውን መሰረታዊ መብት ያሳጣል። በዚህ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የራሴን ትችት መጽሐፉ ላይ አስቀምጫለሁ። በሌላ በኩልም አሸባሪነት በሶስቱ የመንግሥት አካላት ሲፈጸም እንደነበረ ጠቅሼያለሁ። እንደሚታወቀው ሶስቱ የመንግሥት አካላት ሕግ አውጪው፤ ሕግ ተርጓሚውና አስፈፃሚው ናቸው።
በእነዚህ አካላት እንዴት አሸባሪነት እንደሚፈጸም በዝርዝር በመጽሐፉ ላይ ተቀምጧል። ግን በዋናነት ማንሳት የምፈልገው አሸባሪነት ማለት ሰው ማረድ፤ ሰው መግደል ፤ ወይም የሰው ቤት ማቃጠል ብቻ አይደለም። አሸባሪነት ዓለምአቀፍ ትርጉሙ ሰውን በፍርሃት ውስጥ ማድረግም ነው። ሰውን በፍርሃት ውስጥ ሆኖ መብቱን እንዳይጠይቅ ማድረግ ነው።
ያ ማለት የመንግሥት ተቋማት ስለመብቱ የጠየቀውን የሚቀጡት ከሆነ ሁለተኛውም ሰው መብቱን አይጠይቅም። ምክንያቱም ያኛው ሰው መብቱን ስለጠየቀ ከተቀጣ እኔስ ለምን እየጠይቃለሁ? ብሎ ተሸብቦ ዝም ይላል ማለት ነው። ይህም በሕግ ሰበብ ወይም ሕግን ተገን አድርጎ የሚፈጸም መንግሥታዊ አሸባሪነት ይባላል። ይህ በተለየ ሁኔታ በመንግሥት ነው የሚፈጸመው። ሌሎች አሸባሪዎች ሕግ ኖረ አልኖረ አይገዳቸውም፤ ዋና ስራቸው ማሸበር ስለሆነ የፈለጉትን ያደርጋሉ።
በሁለተኛ ደረጃ መንግሥት ቡድን በማደራጀትም ሰዎችን በማሸማቀቅ አሸባሪነትን ይፈጽማል። በተጨባጭነትም ሲታይ የነበረው ያ ነው። መጽሐፉ በተጨማሪም ከለውጡ በኋላ ይህ ነገር ቆሟል? ወይስ አልቆመም? ብሎ ጥያቄ ያነሳል። ይህ መጽሐፍ ተችቶ ወይም ጠይቆ ብቻ አይተውም፤ የወደፊቱ ሕገመንግሥት በምን መልኩ መቀረፅ እንዳለበት የሕገመንግሥት ንድፍ 100 አንቀፆች ያሉት መጽሐፉ መጨረሻ ላይ አስቀምጫለሁ። ያ ማለት እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት ማለቴ ሳይሆን የራሴን ሃሳብ ለማቅረብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሕግ፤ ፍትሕና የሕግ የበላይነት ያለመከበሩ አሁን ላለው አገራዊ ሰላም እጦት የነበረው ሚና ምንድነው ይላሉ?
አቶ አለልኝ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ስለሕጉ አወጣጥ ካየን ብዙ ጊዜ የአገራችን ሕግ የሚወጣው በተወሰነ ቡድን ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው። ለሕዝብና ለአገር ይጠቅማል ተብሎ ተመክሮበት አይወጣም። ወደ ኋላ ተመልሰን በ1936 ዓ.ም ጀምሮ ነው ኢትዮጵያ ሕግና አዋጅ ማሳተም የጀመረችው።
የ1950ዎቹን ሕጎች ስናያቸው አሁንም ድረስ በስራ ላይ ናቸው። ሕጎቹ ሲረቀቁ ከዓለምአቀፍ እይታ፤ የሥነልቦና እይታ፤ የማሕበረሰብ ባህል እይታ እየተጠኑ ነው የተሰሩት። ያ ስለሆነ በቀላሉ መፍረስ አልቻሉም፤ አሁንም ድረስ እየተጠቀምንባቸው ናቸው። ካለፈው 30 ዓመት ወዲህ የሚወጣው ሕግ ግን ገና ሲወጣ የፖለቲካውን አቅጣጫ ብቻ ነው የሚከተለው እንጂ በማሕበረሰብ ላይ የሚያመጣው ጣጣ አይታይም። ከወጣም በኋላ ሕጉ አይተገበርም።
የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አሁን ባለው ደረጃ ጉድለት አለበት እየተባለ ሥራ ላይ በአግባቡ አልዋለም። ከዚያ ይልቅም ሥራ ላይ የሚውለው የባለሥልጣናት ውሳኔ ፤ ወይም የፖለቲካ ውሳኔ ነው። ለምሳሌ የክልሎች አከላለልን ብናይ፤ እንዴት? ከየት? እና የት? መከለል እንዳለባቸው የሚደነግግ አንድም ሕግ የለም።
በሕገ-መንግሥቱም ሆነ ክልሎችን ለማዋቀር የወጣ አዋጅ የለም። በ1985 ዓ.ም የወጣው አዋጅ በተወሰነ መልኩ ስለክልሎች የሚያነሳውም ቢሆን ስራ ላይ አልዋለም። ከዚያ በኋላ የወጣ አዋጅ የለም። የክልሎችን ወሰን የሚያሳይ አንድም አዋጅ ወይም ሕግ የለም። ያለ ሕግ ነው የምንተዳደረው። ያለውንም ሕግ ቢሆን ለማስፈራሪያ ብቻ ነው የምንጠቀምበት። በመሰረቱ ሕጉ የሚወጣው በግብታዊነት ነው።
እኔ በአንድ ቀን የተሻረ ሕግ አውቃለሁ። መመሪያዎችማ ጠዋት ወጥተው ከሰዓት የሚሻሩበት አጋጣሚ በርካታ ናቸው። ሕጎቹን ብናነፃፅር ከ1923 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ አዋጅ ማሳተም ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1966 ንጉሡ እስካለፉበት ጊዜ ድረስ ያሉትን አዋጆችና እና ያለፉትን 20 ዓመታት የወጡትን አዋጆች ብናይ በአምስት በስድስት እጥፍ ይበልጣል የአሁኑ አዋጅ። ግን አንድ ዓመት ሞልቶ የቆየ የለም። ለምሳሌ የአስፈፃሚውን አካል ሥልጣን ለመወሰን በ20 ዓመት ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ ተሻሽሏል።
ሌሎቹም እንዲሁ ተሻሽለዋል። በአጠቃላይ የሚወጡ ሕጎች አይሰራባቸውም፤ ሲወጣም በጥንቃቄ አይወጣም። ቢያንስ ቢያንስ የወጣውን ሕግ በአግባቡ ተከታትለን የምንሰራበት ቢሆን አሁን የምናያቸው ችግሮች ላይከሰቱ ይችሉ ነበር። በየቀኑ ይታወጃል ዞሮ የሚያየው ሳይኖር ነገ
ሌላ ሃሳብ ይመጣል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በአገሪቱ የተከሰተው የዋጋ ንረት የሕግ በአግባቡ ካለመተግበር ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆን? አቶ አለልኝ፡- ልክ ነው። መነሻው ሕግን ካለማክበር የመነጨ ነው። አሁንም ሕጉ ሥራ ላይ ቢውል ዋጋን ማረጋጋት እንችላለን። ምክንያቱም ለዚህ ሕግ ወጥቷል። ለዚህ ታስቦ የወጣ የገበያ ውድድር ሕግ አለ። ያ ሕግ ተጥሶ ሲገኝ ቅጣት ሊታከል ይገባል። ግን አልተሰራበትም፤ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ሕጉ ሼልፍ ላይ ነው የተቀመጠው። ያ ሕግ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ግን በየመጋዘኑ የተደበቀው ዘይት፤ ጤፍና የመሳሰሉት ምርቶች ይወጣሉ፤ የደበቀው ሰው እርምጃ በተወሰደበት ነበር።
ይህ ከሆነም ገበያው ይረጋጋል፤ ረሃብ አይኖርም። አሁን ሰው በእግዚአብሔር ጥበቃና ፈቃድ እንጂ ያለው ኑሮው የሚያቆየው ሆኖ አይደለም። ረሃብ በተጨባጭ በአገሪቱ ውስጥ አለ። ለእዚህ ራሴ ያጋጠመኝን ልንገርሽ፤ ረሃብ አዙሯቸው ቤተክርስቲያን ላይ የሚወድቁ እናቶች አይቻለሁ። ይህም የሕጉ ሥራ ላይ አለመዋል በተለይ ደግሞ የጉቦ መስፋፋት ምክንያት ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል ባይ ነኝ። ሕጎቹ ሥራ ላይ እንዳይውሉ የሚፈልጉ ባለሥልጣናት ቁጥር ቀላል አይመስለኝም። ምክንያቱም በሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ ከሄዱ የሚፈልጉትን አያገኙም።
እነሱ በልተው፤ የእነሱ ልጆች በልተው ሌላው ጦም ሲያድር የህሊና እረፍት ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ስርቆት መጥፎ ነው፤ ህሊና አያሳርፍም፡፡ ከሰው ጋር ብትጣዪ ሰው ሊያስታርቅሽ ይችላል፤ ከህሊናሽ ጋር ብትጣዬ አስታራቂ አታገኚም። ሁልጊዜ በፍጭት ውስጥ ነው የምትኖሪው። የረባ እንቅልፍ አይተኛም፤ ሠላም የለም፤ ምክንያቱም ጠቡ ከራስሽ ጋር ስለሆነ ነው።
ከራሱ ጋር የተጣላ ሰው መቼውንም ጊዜ ቢሆን አይታረቅም። ምንአልባት ሊታረቅ የሚችለው ከራሱ ጋር ያጣላውን ነገር እርግፍ አድርጎ ሲተው ብቻ ነው። እናም እነዚህ ሰዎች ሀብት ቢያካብቱም ከራሳቸው ጋር ተጣልተው ነው የሚኖሩት። ኮሽ ባለ ቁጥር ይደነግጣሉ፤ ሰው ካልከበባቸው አይሄዱም።
ድሮ አፄ ኃይለሥላሤ በዚህ ያልፋሉ ከተባለ በደል የደረሰባቸው ገበሬዎች መንገድ ላይ ጨርቅ ያነጥፋሉ፤ ንጉሡም ከበቅሏቸው ወርደው የተበደለው ሰው ሃሳቡን እንዲናገር በማድረግ ችግሩን ፈትተውና ፍርድ ሰጥተው ነው ወደ ጉዳያቸው የሚሄዱት። ዛሬ መንገድ ብትዘጊ በስናይፐር ግንባርሽን ነው የምትባዪው።
በደቂቃ እንኳን ፍትህ ፈልጋ ነው ብሎ የሚያስብ አታገኚም። ይህም የሚያሳየው ምን ያህል ወደ ድንቁርና እንደተመለስን ነው። ድሮ ግን መንገድ ላይ ጨርቅ በማንጠፍ ሕዝብና መንግሥት ይግባባ ነበር።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ እውነተኛ ታሪክ ልንገርሽ። ንጉሥ ኃይለሥላሴ በአንድ ወቅት በጌምድር ላይ ከባድ ግብር ጣሉ። በኋላ ላይ ግን ግብሩ መክበዱን ተረዱ፤ ስለዚህ ሕዝቡ ምን ይላል? ብለው መልዕክተኛ ልከው አስጠኑ። ሊያጠኑ የሄዱት ሰዎች ሶስት ወር ተቀምጠው ሕዝቡ ግብሩን ሳይከፍል ዝም ብሎ መቀመጡን ይነግሯቸዋል።
የሕዝቡ ሃሜትና እንጉርጎሮ አለመሰማቱና ዝምታን መምረጡ ያስጨነቃቸው ንጉሡ ‹‹በሉ ዝምታ ካለ የሚፈነዳ ነገር ስላለ ቶሎ ብላችሁ ግብሩን አንሱት›› ብለው ነው ትዕዛዝ የሰጡት። አሁን አፍ አውጥተሸ ብትናገሪም የሚከተለው ዱላ ነው፤ ዝም ብትይም የበለጠ ጭቆናው ነው የሚቀጥለው። ከዚህ አንፃር አገራችንን ወደ አለመረጋጋት እና ወደ ችግር ያመጣት የአስተዳደር ችግር ወይም ብልሹነት ነው ባይ ነኝ።
ሙሉ ለሙሉ አስተዳደሩ ወድቋል ማለት ይቻላል። የከሸፈ ሥርዓት ወደመሆን እየተቃረብን ነው። ምክንያቱም መንግሥት ከሰሜን እስከደቡብ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ ማስተዳደር አልቻለም። ይህ ደግሞ ወደ ወደቀ መንግሥት የመሄድ አቅጣጫ ላይ መሆኑን ነው የሚያሳየው። የሚታዩት ምልክቶች ሁሉ የሚያስረዱት ይህንን ነው። መንግሥት ቶሎ ካልነቃና አፋጣኝ ማስተካከያዎችን ካላደረገ አደጋው ከፍ ያለ ይሆናል የሚል ስጋት አለኝ። ግጭቱም ራሱ ለረሃቡ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ባይ ነኝ። ግጭት ባይኖር ምርት በበቂ ሁኔታ ይመረታል፤ የተመረተውም በሚገባ ሸማች ጋር ይደርሳል።
አሁን ግጭት ብቻ ሳይሆን ምርቶችም የሚቃጠሉበት ሁኔታ መኖሩ ለዋጋ መናገር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ዘርፎ የሚያከማችም አለ። እነዚህ ችግሮች ከአገሪቱ ሥርዓት ማጣት የተነሳ የተፈጠሩ በመሆኑ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማዳን ጊዜው አሁን ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ከዚህ በላይ መዘግየት ያለበት አይመስለኝም። መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ከዚህ በላይ ከዘገየ ወደበለጠ አደጋ ውስጥ ልንገባ እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- የሙስናው መስፋፋት ለዋጋ ንረቱ ያበረከተው አስተዋፅኦ ይኖረው ይሆን?
አቶ አለልኝ፡- ይህንን ጥያቄ በግሌ ካጋጠመኝ የሥራ ተሞክሮ አጣቅሼ ልንገርሽ። የጥብቅና ሙያ ከብዙ ሰዎች ጋር ያገናኛል፤ ብዙ ተቋም ጋር የመሄድ እድሉ ይኖርሻል። እኔ አንድ ደበኛዬ የሰጠኝን ውክልና ሕጋዊና ምንም አይነት ግድፈት የሌለበት ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤት ስሄድ አንቀበለውም ፤ ሌላ ውክልና አምጣ አሉኝ። ሌሎች ክፍተቶች ስልተገኙብኝ በዚህ ነገሩን ማጓተት ፈልገው ነበር።
ይህም በነገሩ መጓተት ምክንያት ተከሳሹ አካል እንዲጠቀም የተፈለገ ይመስለኛል። መጨረሻ ላይ እነሱ ባሉኝ መሰረት የአስተዳደር ውክልና ይዤ ደግሞ ቀረብኩም። ይሄንንም አንቀበለውም ብለው መዝገቡን ዘጉት። በኋላ ግን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቤ በሚገርም ሁኔታ ትንታኔ ሰጥቶ የታችኛው ፍርድቤት ያበላሸውን ነገር አስተካክሎ መለሰኝ።
ይህ እንግዲህ የሚያሳይሽ ‹‹ነጩ ጥቁር ነው›› ብሎ እስከመካድ ድረስ ሙሰኝነቱ አይን አፍጥጦ እንደመጣ ነው። ይህንን እንደምሳሌ አነሳሁልሽ እንጂ በየቢሮው ሲኬድ ጉቦ ለመቀበል ሲባል ብቻ በየቀኑ ምክንያት እየተፈጠረ ተገልጋይ የሚንገላታበት ሁኔታ ነው ያለው። የተሟላ ሰነድ እያለው አሟላ እየተባለ የሚመላለስበት፤ ጊዜ እያለ ጊዜ አልፎብሃል ይባላል። የሙስናው ነገር ተቆጥሮ የማያልቅ ነው። ከላይ እስከታች ያለ ችግር መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ከዚህ በላይ ከዘገየ ወደበለጠ አደጋ ውስጥ ልንገባ እንችላለን ነው።
እኔ እንዳውም መንግሥትም አምኖ የተቀበለው ነው የሚመስለኝ። በዚያ ላይ አቤቱታ ስታቀርቢ የላይኛው አካል ከሌላው አካል ጋር ተሞዳምዶ ነው አጥጋቢ መልስ ሳይሰጥሽ የሚያባርርሽ። ክሰሽ የቱንም ያህል ትክክል ቢሆንም አመራሩ ራሱ በጥቅም የተሳሰረ ስለሆነ አቤት ብትዪም መፍትሄ አታገኚም። አብዛኛው በሌብነት የተዘፈቀ አመራር ያለበት እንደመሆኑ አንዱ ሌላውን ለመንካት ወይም ለመንቀፍ አይደፍርም።
አሁን እኮ ጥቂት የማይባለው የመንግሥት አመራር ባለፎቅ ቤት ነው። ይህንን ስታዪ መቼም በደመወዝ ፎቅ እንደማይሰራ ግልፅ ነው። የመንግሥት ደመወዝ እየበላ አለ የተባለ መኪና የሚያሽከርክር ሞልቷል። ምንጩ የትነው? ብሎ የሚጠይቅ የለም። እንዳውም ፀረ-ሙስና ኮምሽን ባለሥልጣናት ሀብት አላስመዘግብለት ብለው ማስታወቂያ ሁሉ አውጥቶ ነበር።
ይህም የሚያሳይሽ ቢያስመዘግቡ ከየት አመጣችሁ የሚል ጥያቄ ለመሽሸ ይመስለኛል። ይህንን ለመቆጣጠር የወጣ ሕግ ቢኖርም ሥራ ላይ እየዋለ አይደለም። በአጠቃላይ አሁን ላይ የተፈቀደ ጉቦ በየተቋሙ ተስፋፍቶ ነው የሚገኘው።
ይህም ፍትህ እንዲዛባ፤ ጉበኞች አገሪቱን እንዲቆጣጠሩ ምክንያት እየሆነ ነው ያለው። በነገራችን ላይ በሙስና የጠፉ የአፍሪካ አገሮች አሉ። ዩጋንዳና ኬንያ ላይ ጉቦ ከመብዛቱ የተነሳ ግሽበት አስከትሎባቸዋል። ኢትዮጵያም ወደዚያ እያመራች ይመስለኛል።
የሙስና መስፋፋት ሕዝቡን ከመበደሉ ባሻገር ግሽበት ያስከትላል። በሙስና ሀብት ያካባተ ሰው የፈለገውን የመግዛት አቅም አለው፤ ምክንያቱም አልደከመበትም። በመሆኑም መንግሥት ሌብነትን ካልተቆጣጠረ ለራሱም አደጋ ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዝምድና እና በጎጠኝነት የሚፈጸም ሙስና በተለይም ከተሞች አካባቢ መጨመሩ አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያነሳሉ። ለመሆኑ እንዲህ አይነቱ ሙስና ከኢኮኖሚው ባሻገር በፖለቲካው ዘርፍ የሚያስከትለው ቀውስ እንዴት ይገለፃል?
አቶ አለልኝ፡- እንዳልሽው ጎጥን ወይም ዝምድናን ተገን በማድረግ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች በተለይ በከተሞች ላይ በጣም እየተበራከተና ስር እየሰደደ ነው ያለው።
ይህ ችግር ደግሞ ከዋና ከተማዋ ጀምሮ በሁሉም የክልል ከተሞች ተንሰራፍቶ ነው እያየን ያለነው። የጎሳ ፖለቲካ በኢኮኖሚውም ዘርፍ ተደራጅቶ የማጥቃት ባህል አምጥቷል። ለዚህ መነሻው ደግሞ በጎሳ የተደራጀው ሕገ-መንግሥት ነው። ይህንን ችግር በዋናነት መቅረፍ የሚቻለው ሕገመንግሥቱን በማሻሻል ይመስለኛል። ይህ ሕገመንግሥት ከመውጣቱ በፊት ሰው በሰውነቱ ብቻ ነበር የሚታየው። ‹‹እገሌ ከየት መጣህ? ከየትኛው ጎሳ ነህ ?›› ተብሎ አይጠየቅም ነበር።
ለሙስናውም ሆነ ለሌሎች ችግሮች በር ከፋች የሆነው ይኸው የጎሳ ፖለቲካ በመሆኑ ችግሩ እንዲቀረፍ ከፈለግን ከኢትዮጵያ ላይ ልናጠፋው ነው የሚገባው። በዝምድና ተጠቃቅሶ መሬት ይዘረፋል፤ ቤት ይወረሳል፤ ያለአግባብ ጥቅማ ጥቅም ይወሰዳል፤ እድገት ይሰጣል። ይህንን የምልሽ ለሃሜት ሳይሆን በሥራ ገጠመኜ ያየሁትና በተጨባጭ ማስረጃ ብጠየቅ የማሳየው በመሆኑ ነው። በአጠቃላይም ጎሳን ተገን አድርጎ የሚደረገውን ሌብነት በአፋጣኝ ማስቆም መቻል ያለብን ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ በአስቸኳይ ሊሰራቸው ይገባል የሚሏቸውን ነገሮች ካለ ቢጠቅሱልን?
አቶ አለልኝ፡– በመጀመሪያ ደረጃ መላውን ኢትዮጵያዊ በማማከር ሕገመንግሥቱን ማሻሻል እና ከጎሳ ፖለቲካ መላቀቅ ነው። ይህ ካልተቀየረ የፈለገውን ያህል ብናስተካክለው ችግሩ እየተመላለሰ ነው የሚያመረቅዘው።
አሁን ላለው የውድቀታችን መሰረቱ ይህ የጎሳ ፖለቲካ ነው። የርዕዮተ ዓለም ፖለቲካ ሥርዓት ከተከተልን ሰው እርስበርስ አይባላም፤ በዜግነቱ ብቻ ሁሉንም አገልግሎት ያገኛል። ሁለተኛው ጉዳይ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ወደ ነበረው ኢትዮጵያዊ አብሮነት መመለስ ነው። ለዚህ ደግሞ አሁን የተጀመረው አይነት ሕዝባዊ ምክክር በቀጣይነት ሊሰራ ይገባል።
ምክክሩ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ መካሄድ አለበት። ፖለቲከኞች የሚመካከሩ ከሆነ አሁንም ጥቅም የለውም። ለውጥ አናመጣም። ምክንያቱም ፖለቲከኞቹ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ብቻ ነው የሚያሳኩት። መመካከር ያለበት ሕዝብ ነው።
ፀቡ ያለው በሕዝብና በሕዝብ መካከል ሳይሆን በፖለቲከኞቹ ዘንድ ስለሆነ ሕዝብ አሁንም ቢወያይ የማይፈታው ችግር አይኖርም። በመሆኑም ፖለቲከኞቹ ከሕዝባዊ ምክክሩ ገለል ማለት አለባቸው። ፖለቲከኞቹ የማስተባበር ሥራ ነው መስራት ያለባቸው። ሕዝቡ ከተነጋገረ ፖለቲከኞቹን ከዚህ በኋላ ጣልቃ እንዳትገቡ ማለት ይችላል።
በአጠቃላይ ሕዝባዊ ምክክሩን ቅንነት ባለበት እውነተኛ ኢትዮጵውያን ወደነበሩበት ሊመልስ በሚችል መንገድ ማካሄድ ይገባል። በሶስተኛ ደረጃ የማየው በ30 ዓመታት ውስጥ በተዛባ ትርክት ቋሚ ጥላቻ የሚፈጥሩ ነገሮች አሉ።
በታዛባ ታሪክ ሃውልት አቁሞ ዛሬም ድረስ ሕዝብ የሚባላበት ሁኔታ አለ። እነዚህን የመሳሰሉ ጠብ የሚያጭሩ ትርክቶች በአስቸኳይ መነሳት አለባቸው። ምክንያቱም ለትውልዱ በጣም መጥፎ ስዕል የሚስሉ በመሆኑ ነው። እኛ ባልነበርንበት ዘመን ተደረገ ለተባለ ነገር ሃውልት ከማቆም ለዛሬ ጥሩ መስራት ነው የሚጠቅመው።
ዛሬን እያበላሸን ያለፈውን ሥርዓት ልንኮንን አንችልም። የእኛ ጊዜ ዛሬ ነው። ዛሬ ነው ጥሩ መስራት ያለብን። ዛሬ ጥሩ ሳንሰራ ወደኋላ ሄደን እንዲህ ነበር ብንል ምንም ጥቅም የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ እምነት የዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ገደብ የት ድረስ ነው?
አቶ አለልኝ፡- ለሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚሰጥ ሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲያዊ መብት አለው። ሰብአዊ መብቶች በየትኛው መለኪያ አይገረሰሱም።
ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ያገኘውን መብት ማንም ሊጥስበት አይገባም። የዴሞክራሲ መብት የምንለው ሰዎች ተመካክረው የፈጠሩት ነው። የሰው ልጅ ቁጥር እየበዛ በሄደ ጊዜ መብቶች መጣስ ሲጀምሩ በምክክር የመጣ ነው። የፖለቲካ አመራሮቻን ዴሞክራሲ የመጣው የሚመስላቸው ግን የዛሬ 30 ዓመት ነው።
ዴሞክራሲ ግን አዳም እንደተፈጠረ ነው የተጀመረው። ምክንያቱም አትብላ፤ ከበላህ ግን ትሞታለህ ተብሎ በፈጣሪ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ ነው ለሰው ልጅ ዴሞክራሲያዊ መብት የተሰጠው። የዴሞክራሲ መብቶች ገደብ አላቸው፤ ገደቡ ከታለፈ ያስጠይቃሉ።
መንግሥትም ገደቡን ማለፍ የለበትም፤ ማሕበረሰቡም እንዲሁ። በተለይ የማሕበረሰብ አንቂዎች ከመጠን በላይ ገደባቸውን ሲያልፉ ይታያሉ። ሲዋሹ፤ ያልተፈረደበትን ሰው ሌባ ሲያደርጉ ይታያሉ። በየትኛውም ዓለም ዴሞክራሲ ያለገደብ አይሰጥም።
በእኛ አገር ሥልጣኑን በበላይነት የያዘው አካል ሥልጣኑን ከአቅም በላይ ሲለጥጠው ይታያል፤ ራሱ ሲጥሰው ምንም የማይመስለው አመራር የሌላውን መብት ለመርገጥ ማንም አይቀድመውም። ሌሎችን ሲቀጣ ምህረት የለውም። ሌላው ማሕበረሰብም እንዲሁ በዴሞክራሲ ሰበብ የሌላውን መብት አልያም ሕግ የሚጥስበት ሁኔታ አለ። መብት ልቅ አይደለም። ሁሉም በገደቡ ልክ ነው መንቀሳቀስ ያለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡ አቶ አለልኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014