በ2010 ዓ.ም በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በብሔር ብሔረሰቦች ስም ጽንፈኝነትን እየበጠበጡ ሲግቱን የነበሩት የጽንፈኝነት መምህሮቻችን “አፈር ነህ እና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ሆኖ ቃሉ ከእነጽንፈኝነታቸው ወደመጡበት ሰፈራቸው ተመለሱ።
ጽንፈኝነት ያንገሸገሸው ሕዝብም የለውጡን መንግሥት ያለምንም ልዩነት በአደባባይ በመውጣት ደገፈ። ይህን ተከትሎም ጽንፈኝነት እና ጎጠኝነትን ያስተማረን ወያኔ በቆሻሻ እንደተሞላ “ዳይፐር” ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ ከላያችን ላይ አውልቀን የጣልነው መስሎኝ ነበር።
የሆነው ግን በግሪስ የተጨማለቀ የመካኒክ ልብስ ለመኝታ ሲሄድ አውልቆ እንደሚያስቀምጠው እና ከመኝታ መለስ ወደ ሥራ ሲገባ እንደሚለብሰው አይነት ነው።ምክንያቱም በለውጡ ማግስት በወያኔ የጥፋት ፈረሶች አማካኝነት ዘረኝነት በየሰፈሩ ተቦካ፤ ተጋገረ፤ የማንነትን ጥቃት ተከትሎ ሚሊዮኖች ለመፈናቀል፤ ሺዎች ደግሞ ለሞት ተዳረጉ።
ኮሜዲያን ተስፋየ ካሳ፡-
«እኔስ ብዬ ነበር ፍርድ ቤት መረጡኝ ፣
እኔስ ብዬ ነበር ቀበሌ መረጡኝ ፣
እድሜ ለስካሬ ከዕድርም አስወጡኝ።» ማለቱም የጠበቀው ቀርቶ ያልጠበቀው ቢመጣበት ነበር። ከእነሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ላይቤሪያ ወዘተ መሰል አገራት ታሪክ ባለፈ ጽንፈኝነት የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ በእራሳችን አገር ከወያኔ ጋር ባደረገነው እልህ አስጨራሽ ውጊያ በተግባር ተመልክተናል።
ሴቶች(ከሕጻን እስከ አዛውንት) በመደፈራቸው አለቀስን፤ ከአንድ ቤተሰብ አባላት እስከ ስድስት ሰው ሞቶ ለመቅበር እንኳን ተቸግረን አየን፤ ሰው ከሞተ በኋላ መቅበር የድሎት እስኪመስለን ድረስ ስንት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሳይቀበሩ የጅብ እና የአሞራ ሲሳይ ሲሆኑ ተመለከትን፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆች ያለአሳዳጊ፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው አረጋውያን ደግሞ ያለ ጧሪ ቀባሪ ሜዳ ላይ ሲቀሩ አየን፤ ከድሃ ቤት ሽሮ እና ሊጥ እስከ ሀብታም ድርጅቶች ያሉ የሕዝብ ጥሪቶች ተዘረፉ፤ ተቃጠሉ።
በአጠቃላይ ከውጊያው ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ አሰቃቂ ክስተቶችን ያየ ማንም ሰው ዘረኝነት ማለት እራስን በፈላ ዘይት ውስጥ ከመጨመር በብዙ እጥፍ የሚልቅ አሰቃቂ ውጤትን የሚያስከትል ስለመሆኑ በደንብ አድርገን በተግባር ተመለከተን።
ከዚህ በላይ ዘረኝነትን ለመጸየፍ የሚያስችል በራሳችን የተፈተነ ማስተማሪያ እና ማስረጃ እንዴትስ ልናገኝ እንችላለን? ብልህ ከሰው ይማራል፤ ሞኝ በእራሱ ይማራል እንዲሉ ብልህ ሆነን ከእነሩዋንዳ፣ ብሩንዲ ፣ላይቤሪያ ወዘተ ከመሰሉ አገራት ታሪክ መማር አልችል ብለን ወደ ጦርነት ገባን። ሞኝ በመሆናችን በራሳችን ሞክረን አየነው። አስከፊነቱንም ከራሳችን አልፎ ለሰው ማስተማር የሚያስችል ተሞክሮ ወሰድን።
ነገር ግን አሁንም ጨርሰን ከእነአካቴው ባለመጥፋታችን የበገኑ ኃይሎች ዘረኝነትን እያቦኩ የጋገሩትን ጥፋት ለመብላት የቋመጡ ብዙ ናቸው። አሁን ላይ ያለው የጽንፈኞችን የክፋት ንፍር ውሃ የሚመለከት ማንም ሰው የብርጋዴል ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ንግግር ማስታወሱ የማይቀር ነው። «ቤት ሲሰራ በር እና መስኮት ይሰራለታል።
መቃብር ሲሰራ ግን በርም መስኮትም አይሰራለትም።» የእኛ አካሄድም ለመጠፋፋትና በሰራነው የመቃብር ቤት ለመቀመጥ እንጂ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል አይመስልም። በዚህ ወቅት እየሠራነው ላለው ጥፋት ተጠያቂዎቹ ራሳችን ነን። በምዕራባውያን እና መሰል አካላት ማመካኘት አይቻልም።
ምክንያቱም ምዕራባውያን አገራችንን ለማፍረስ እየጣሩ መሆኑን ካወቅን ስለምን ምዕራባውያን እና ምዕራባውያን የሚጋልቧቸውን የጥፋት ባንዳዎች አንድ ሆነን መመከት ተሳነን? በዓድዋም ሆነ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ባንዳዎች ነበሩ። ነገር ግን አባቶቻችን ተባብረው በአንድ ላይ ቆመው ስለነበር የጣሊያንን አገር የማተራመስ ሴራ ፉርሽ ማድረግ ችለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ግን ጣቱን ምዕራባውያን ላይ ይቀስር እንጂ የምዕራባውያንን የጥፋት ድግስ ለማክሸፍ ከመጣር ይልቅ ምዕራባውያን በሚቀዱለት የጥፋት ቦይ መፍሰስ ይቀናዋል።
ስለእውነት እኛ ኢትዮጵያውያን እነዘይት እና መስል ኑሮ ውድነት ከፈጠሩብን ጭንቀት በላይ ሌላ አጀንዳ ከፍተን መነታረክ ነበረብን?
ስለእውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ዘይት ወይስ በዘረኝነት አረንቋ ገብቶ የአጥፍቶ መጥፋት ሥራ መሥራት? እውነት እኛ በዓድዋ በአንድ ላይ ቆመው ነጭን ድል ያደረጉ ጀግኖች ልጆች ነን? እውነት እኛ አፍሪካውያን በነጻነት ምሳሌ የሚጠቅሱን ሕዝቦች ነን? በአባቶቻችን የአንድነት ልክና ጥቁር አፍሪካውያን የነጻነት ምሳሌ አድርገው የሚያዩን ምሳሌ እየሆንን የኖርን ሕዝቦች ነን?
ምሳሌ እየሆንን የኖርን ሕዝቦች ነን? ከሁሉም በላይ ለአገራችን እድገት እና መረጋጋት ከፍተኛ ስጋት ሆነው የሚታዩት እና ለትልቋ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትንሽ አጀንዳ እየሰጡ የሚያናክሱን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባንዳ አመራሮች ናቸው። በዘረኝነት ልክፍት ያበዳችሁ አመራሮች ስርቆታችሁ እና ኃጢያታችሁ እንዳይጋለጥ የጽንፈኝነት ድራማ ድርሰት እየደረሳችሁ ራሳችሁን ተመልካች፤ ሕዝቡን ተዋናይ አድርጋችሁ በሕዝብ ደም፣ ለቅሶ፣ ችግርና ሰቆቃ ለመደሰት መሞከር የዋህነት ነው። በሐሰት የደረሳችሁት የዘረኝት ድራማ የሚያመጣው ዳፋ ወይም ማዕበል ከእነሰረቃችሁት ሀብት ጠራርጎ እንደሚበላችሁ አትርሱ!። ዛሬ ላይ ትክከል የመሰላችሁ ነገር ቆይታችሁ ስታጡት ስህተት እንደሆነ በደንብ ትገነዘባላችሁ። ይህንን አሁን ላይ ትክከል መስሎን በዘረኝነት በሽታ ያጣነው ሀብታችንን ወደፊት ለሚመጣው ተተኪ ትውልድ በእኛ ስህተት የጠፋውን ሀብት ለመመለስ አላስፈላጊ የቤት ሥራ እየተውንለት ነው። ለዚህ ሁለት መሳሪያዎችን እንመለከት። አንደኛ፣ ከ1960ዎቹ ትውልድ ጋር ተያይዞ በአገራችን ላይ የተከሰተውን ችግር ማስታወስ ይገባል። የ1960ዎቹ ትውልድ የኢትዮጵያን ችግር እንዲቀርፉ በማሰብ ስልጣኔ እና ቀለም ከዘለቃቸው አውሮፓ እና አሜሪካ ሄደው ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ፣ የተለያዩ ዘመናዊ መሣሪያዎች አመራረት፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ አሠራር፣ ወዘተ. እንዲማሩ ተላኩ። ነገር ግን የተላኩበትን መልዕክት ጭራሽኑ ረስተው ነጭ ጥቁርን ለማጥፋት የቀመመውን የዘረኝነት መርዝ ተግተው ተመለሱ።
በአገራችንም የዘረኝነት መርዛቸውን ያለማንም ከልካይ ረጩ። በተለያዩ አካባቢዎች እና መድረኮች በሚደሰኩሯቸው የፖለቲካ ዲስኩሮች እንደአዋቂ ተቆጥረው ይጨበጭብላቸው ነበር። እነኝህ አላዋቂዎችንም ከተራራ በላይ አገዘፍናቸው። የዘረኝነት መርዛቸውንም ያለምንም መሸማቀቅ እንደፈለጉ ተፉት። ሕዝቡንም በጥፋት መርዛቸው በከሉት። ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የውስጥ አንድነቷን እና ፈሪሐ እግዚአብሔር እንደምስጥ ቦርቡረው በሉ።
የአሁኑ ትውልድም እነዚያ ኃይሎች በፈጠሩት ችግር ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። ሁለተኛ፣ አቤ ጉበኛ አልወለድም በተባለው መጽሐፉ ከገለጸው አንድ ሃሰብ ተውሰን እንመለከት። አቤ በመጽሐፉ «እኛ ደን ቆርጠን እና መንጥረን ባለማነው የእርሻ መሬት ባለአባቶች መሬቱ የእኛ ስለሆነ ልቀቁ አሉን ።
መጀመሪያ ላይ ደኑን ቆርጠን እናልማ ብለን ስንጠይቅ ምንም ምላሽ የሰጠን አካል አልነበረም። አሁን ደን ቆርጠን እና መንጥረን መሬቱን ስናለማ ግን የኔ ነው ባዩ በዛ፤» ይላል።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ብሎም አለም ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት አንድ ነገር ስህተት ሆኖ እናገኘዋለን። የአሁኑ ትውልድም ቀድሞ በነበሩ አባቶች ዋጋ እየከፈሉ እንዳሉም እንረዳለን።
አባቶቻችን ትክክል ነው ብለው የተከሉትን፤ በዚያ ዘመን ደግሞ በልማት ስም በቆረጡት ደን አሁን ላይ መሬት ልብስ አጥታ በድርቅ እየተጎዳች በመሆኗ የአሁኑ ትውልድ ጊዜውን በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማድረግ ሲገባው አረንጓዴ አሻራ እያለን ሀብት እና ጉልበታችንን በከፍተኛ ደረጃ እያወጣን እንመለከታለን።
ለማጠቃለል ያህልም አሁን ላይ እየሄድንበት ያለው የጽንፈኝነት ጥግ መስመሩን ትቶ ወደፊት የሚመጡት ተተኪ ትውልዶች በእኛ ስህተት ዋጋ እንዳይከፍል ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፤ መልዕክቴ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014