በአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትና የጋራ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት መገንባት አስፈላጊ ነው። የአገራዊ ዕድገትና ብልጽግና ጉዞም አልጋ በአልጋ አይደለም። በከፍታና ዝቅታ፣ በውጣ ውረዶች የተሞላ፣ ጋሬጣ የበዛበትና በእልህ አስጨራሽ እንቅፋቶች የታጀበ ነው። በዚህ ረገድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውና በርካታ መራጮች ድምፅ የሰጡበት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ መንግሥት ለመመስረትና አገር ለማስተዳደር የሚያስችለውን ድምፅ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲም፣ የማይለዋወጥና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት ከባድ ኃላፊነትን ተቀብሏል።
ይህን እውን ለማድረግም የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውንና ሲያስመለክት የቆየው ፓርቲው፣ ‹‹ከፈተና ወደ ልዕልና›› በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያ ጉባዔውን አካሂዷል። የጉባኤውን በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎም ፓርቲው ባወጣው የአቋም መግለጫ ከተካተቱ ስድስት ጉዳዮች መካከል ‹‹የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በማስፋትና በማጽናት የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ የፓርቲያችን ቀዳሚ አጀንዳ ነው›› የሚል ነው።
ፓርቲውም፣ ይህንንም ለማረጋገጥ የውስጠ ፓርቲ ጤንነታችንን መጠበቅ ከሌብነትና ከተደራጀ ስርቆት አንጻራዊ ነፃነቱን የጠበቀ የአመራር ስምሪት ማረጋገጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የአገልጋይ አመራር ስብዕናን የተላበሰ ጠንካራ የፓርቲ መስተጋብር ለመፍጠር ወስነናል፤ ሲል በመግለጫው ተደምጧል።
ሰላምን በጽኑ መሠረት ላይ ለማስቀመጥ መድረኩ የሚጠይቀውንና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነም እወቁልኝ ብሏል። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ገልጾ፤ እርስ በእርስ አለመከባበር፣ መዘላለፍ፣ በአደባባይ ላይ ሳይቀር ጸያፍ ድርጊት መፈጸም፣ ለኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና ለእህትማማችነት የማይመጥን ጸረ አንድነት የሆነ ከፋፋይ ድርጊት መፈጸም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጸር መሆኑንም አረጋግጦ ይህንን ችግር ለመፍታት አመራሩ ቀን ከሌት እንደሚሠራ አሳውቋል።
«የሕዝባችንን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ በአጠቃላይ የሕዝባችንን ኑሮ አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ ማሻሻል አለብን» ያለው ፓርቲው፤ አፋጣኝ መፍትሄ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቁሟል። በተመሳሳይ «የአገራችንን ሉአላዊነት እንደወትሮው ሁሉ ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን» ያለው የፓርቲው አቋም፤ «ማንኛውንም ጥቃት መቋቋም የሚችል የውስጥ አቅም ለመፍጠር እየተረባረብን እንገኛለን» ሲልም ጠቁሟል። አገራዊ አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያጎለብት፣ አገር በቀል እሴቶቻችንን ለላቀ ጥቅም የሚያውል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን የሚያቀል እንዲሆን መሥራት ይኖርብናል ብሏል።
ይሁንና ፓርቲው እስከዛሬ ከሠራቸው ሥራዎችና ካመጣቸው ለውጦች ይልቅ ገና ወገብ የሚያጎብጡ ተሻጋሪ ሥራዎች ከፊቱ እንደሚጠብቁት ይታመናል። የትናንት ስህተት ጥፋቱን ያላመነ ወይንም ተነግሮት ያልተቀበለ ሰው ነገም ያንኑ ለመድገም የተዘጋጀ ነው እንዲሉ አበው፤ ገዢው ፓርቲ ብልፅግናም የዚህ ታሪክ ምሳሌ ላለመሆንና በተለዋዋጭ ፈተናዎች እያለፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ጉዞዋን እንድትቀጥል ከትናንት ታሪክና ከዛሬ እውነት ተምሮ ሊያስቀጥላቸው የሚገቡ ድሎች እንዳሉት ሁሉ የተሠሩና መደገም የማይገባቸውን ስህተቶችንም ነገን አስልቶ ሊያርም የግድ ይለዋል።
እንደሚታወቀው የዘመነ ኢህአዴግ 27 አመታት ልዩነትን የሚያሰፉና ማንነት ላይ ያተኮሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሴራዎች መዋቅራዊና ተቋማዊ ሊባል በሚችል ሁኔታ ተሠርቷል። ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ በተደረገው ለውጥ ድል፣ ፈተናና ተስፋ ተፈራርቀዋል። በተለይ በኢትዮጵያ እድገት የሚከስሩ፣ በውድቀቷ የሚያተርፉ የዘመናት የሕዝቦች ጥያቄና ፍላጎት የሆነውን ዴሞክራሲን የመትከልና የማጽናት ትግልን ለመቀልበስ ሲጥሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እየጣሩ ይገኛሉ።
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እገዛ ከማድረግ ይልቅ ከውስጥም ከውጭም በባዕዳን ነዋይ ተደልለው በገዛ አገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የጸረ አንድነት መፈክር በማሰማት ሕዝብ የሚፈልገውን አገራዊ ዕድገት የሚያስተጋቡ ከንቱዎች አሁንም የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግላቸውን ቀጥለዋል።
ከውስጥ ባንዳዎች እስከ ውጭ ጠላቶች ብዙ ቢዘመትም፣ ፈተናን ወደ ጥንካሬ፣ ተግዳሮትን ወደ መልካም ዕድል የሚያሸጋግር ዝግጁነትና ፈጣን ምላሽ የሰጠ አመራር በመፈጠሩና ሕዝቡን ከጎን ማሰለፍ በመቻሉ አገርንና ሕዝብን የማዳንና የማበልፀግ አኩሪ ተግባር መፈፀም ተችሏል። ይሁንና በለውጡ የተመዘገቡ ድሎች በበሳል አመራሮች ውሳኔ፣ አብሮነትና ትጋት የመጡትን ያክል፤ በለውጡ ውስጥ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችና ተግዳሮቶችም በአመራሩ ድክመትና ቸልተኝነት የተፈጠሩ መሆናቸው ሊካድ አይገባም።
ፓርቲ የግለሰቦች ስብስብ ነው። ፓርቲ ጥንካሬም ሆነ ድክመት፣ በጎም ሆነ መጥፎ ዋነኛ መሠረትም የግለሰቦቹ አስተሳሰብ እምነትና ፍላጎት ውጤት ነው። ጠንካራ ፓርቲ መሆን የሚቻለው ጠንካራ አመራር ሲኖር መሆኑም የሚያከራክር አይደለም። ባሳለፍነው የለውጥ ሂደት ምንም እንኳን በአብዛኛው በሚባል መልኩ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ተልዕኮን ጠንቅቆ በመረዳት ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በማሳየት በቁርጠኝነት ቢሠሩም፤ በጎራ መደበላለቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡና ከጥፋት ኃይሎች ጋር የተባበሩ በየደረጃው ያሉ መኖራቸው አይካድም። የሕግ በላይነትን ያላከበሩ፤ የሥልጣን ጥም የተንጸባረቀባቸው፣ ለአብሮ መሥራት እንቅፋት የሆኑና በሁለት ቢላ ለመብላት የቋመጡ አመራሮች ቁጥር ጥቂት የሚባል አልነበረም።
ይሁንና በኢትዮጵያ ለውጥን እውን በማድረግ ሂደት ከአዲስ የለውጥ አስተሳሰብ ጋር ለማራመድ አቅምና ፍላጎት የጎደላቸው አመራሮችን መለማመጥና መታገስ አይገባም። አዲሱን አስተሳሰብ ለማራመድ አቅምና ፍላጎት የጎደላቸው ተቋማት፣ መዋቅሮችና አሠራሮች ማደስ አሊያም መተካት የግድ ይላል። በእርግጥ በፓርቲው ቅድመ ጉባኤ ግምገማ 108 ሺህ 258 አመራሮች ተገምግመው በ10 ሺህ 658 አመራሮች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው እርምጃ መውሰዱንና 2 ሺህ 574 አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን አስታውቋል። ይበል የሚሰኝ ጅምር ነው። ይሁንና በቀጣይም የአንድ ጀንበር ሳይሆን ተከታታይ የሆነ የአመራር ማጥራት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
የፓርቲ አባልና አመራሮችም ኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የተቃና ለማድረግ የሚችል ዝግጁነት አቅምና ቆራጥነት እንዲሁም ከፍተኛ የማስፈጸም ብቃት ያላቸው ከሁሉም በላይ የሕዝብ ምሬት መነሾ ከሆነው ሌብነት የጸዱ መሆናቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ ግድ ይለዋል። ምክንያቱም ፓርቲው የተሻለች ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ዜጎቹን የሚያከብር፣ ዝቅ ብሎ የሚያገለግል፣ አድሎአዊ አሠራርን የሚጸየፍና ሁሉንም በእኩል መመልከት የሚችል አመራር መፍጠርና ማስተዋወቅም ይጠበቅበታል።
ለምን ቢባል፣ ለራሱ ዜጎች ክብር የማይጨነቅ ሥርዓተ መንግሥት በመንበሩ ሊፀና አይችልም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም ኢትዮጵያ የቀደሙት ሳይፈቱ አዲስ እየተጫኑባት በመጡ ጉዳዮች ተወጥራለች። ይህ እንደመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ በሰላምና ጸጥታ ረገድ ጠረጴዛ ላይ ተደርድረው የሚጠብቁት መዝገቦች ቀላል እንዳልሆኑ ሊያስብ ይገባል።
ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ ይበቃዋል። ፈተና ይበቃዋል። ይህ የሚሆነው ግን በምኞት አይደለም። በሥራ ነው። እያንዳንዱ አመራር አባል ይህን ኃላፊነት መውሰድ አለበት። በዚህ የሚገመገምበት፣ ማድረግ ካልቻለም ወንበሩን የሚያስረክብበት አሠራርን መተግበር ያስፈልጋል። የተጀመረው ለውጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል፣ አስተማማኝ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ የግድ ነው። በእውር ድንብር እየተንቀሳቀሰ ካለው የሕወሓት የሽብር ቡድን ጋር እያደረግነው ያለው ትግል ወደ መጨረሻ ምዕራፉ እየተጠጋ መሆኑ ለማንም የተደበቀ ባይሆንም ገና ያልተጠናቀቁ የቤት ሥራዎች እንዳሉብንም መርሳት የለበትም።
አሸባሪው ሕወሓት ከስህተት የመማር ልምድም ይሁን ፍላት የሌለው በመሆኑ እስካሁን ከደረሰበት ሽንፈትና ውርደት እንኳን ሳይማር በጦርነት ዕድሜውን ለመግፋት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሆነም መገንዘብ አይከብድም። ሰላም ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም፤ ከዚህ ጥረት ባሻገር የሮማው ጄነራል ፍላቢየስ ቬጂተስ ሰላም ከፈለግህ ለጦርነት ተዘጋጅ ፣‹‹if you want peace, prepare for war›› ያለውን ማሰብ አዋጭ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት ነጋዴዎች አሉ። ግጭትን በማነሳሳትና በማፋፋም ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚታትሩም በርካታ ናቸው። በዚህ ረገድ በቂ የሆነ የክትትልና የግምገማ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ሸኔ በቅርብ ርቀት የጥፋት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የዚህ ቡድን ራስ ምታትነት ፈጣን እልባት ሊሰጠው ይገባል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታን በማስከበር ረገድ ልዩ ትኩረት የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት ትብብርና መናበብ ብሎም ጠንካራ የሆነ የሕግ አስከባሪ ሰራዊት የመገንባት ተግባር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።
ከእንግዲህ በሕግ አፈጻጸም ረገድ ግለሰቦች ተገምግመው ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ የብሔር መታወቂያቸውን የሚያወጡና የሚሸሸጉበት አካሄድ ገደብ ሊበጅለት ይገባል። ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደህንነት ሲባል በተለያዩ ክልሎቹ ኢ መደበኛ በሆነ መልኩ የታጠቁና የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን አደብ ማስገዛት አለበት።
ከዚህ ባሻገር የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በሰላም የመኖር፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ መብት በተጨባጭ ማረጋገጥ ይገባል። ግጭት ጠንሳሽና ጠማቂዎች በፈጠሯቸው ችግሮች የተጎዱና የተፈናቀሉ ሕዝቦችን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በሚያጠናክር መንገድ በዘላቂነት ዳግም የሚቋቋሙበትና ከችግር ወጥተው ወደቀድሞ ሕይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ መዘርጋት ይገባል። የሰማዕታቱን ቤተሰቦችም በቋሚነት በማገዝ ጉዳታቸውን መካፈል ያስፈልጋል።
ኢኮኖሚውም ቢሆን ለሁሉም ነገር መሠረት ነው። ኢኮኖሚ ካደገ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል። ሥራ አጥነት ይቀንሳል። ፖለቲካዊ መረጋጋት ይመጣል። የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቀንሳል። ከውጭ ተጽእኖ መላቀቅና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው ኢኮኖሚን ማሳደግ ሲቻል ነው። ጠላት የሚፈታተነን የኢኮኖሚያዊ አቅማችን የደከመና የእርስ በእርስ ትስስራችን መድከሙን ሲታዘብ ነው። ስለሆነም በሁለንተናዊ መልኩ የኢኮኖሚ አቅማችን ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር መሆን አለበት።
ፓርቲው በተደጋጋሚ ሲገልፅ እንደሚሰማው የኢትዮጵያ ብልፅግና ማለት የጥቂቶች ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ነው። ብልፅግናም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊጎናጸፈው የሚገባ ነው። አንዳንዶች ከዳር ቆመው የሚመለከቱበትና ጥቂቶች ብቻ የሚጠቀሙበት ሳይሆን መላው ኢትዮጵያውያን ያለአንዳች ገደብ በእኩልነት ተሳትፎ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው። በዚህ ረገድ ትግሉ የአንድ ጀንበርና ቀላል ባይሆን በአሁኑ ወቅት መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይህን እያስመለከተ አይደለም። በተለይ ከታች እስከ ላይ መዋቅር የተንሰራፋው ሌብነት በዜጎች መካከል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ልዩነት ፈጥሯል። ይህም አፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት አደጋው የከፋ ይሆናል።
ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ቢኖረውም በተለይ ሕዝቡን ያለ ልዩነት ቀስፈው በመያዝ እያሰቃዩ ለሚገኙት የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕድል መጥበብ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዕጥረት ከአጭር ጊዜ አኳያም ቢሆን ፈጣን መፍትሄ መስጠት የግድ ይላል። በተለይ ሕገ ወጦችን በመቆጣጠርና ለሕግ በማቅረብ ረገድ ፓርቲው መሽኮርመሙን ማቆም አለበት።
ለምሳሌ፣ በአሁኑ ወቅት፣ በተለያዩ ከተማና ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መልኩ የተደበቀ ዘይት በቁጥጥር ስር ዋለ ሲባል በዜና እንሰማለን። እናያለን። ይሁንና ዘይቱን የደበቀው ማነው፣ ፍርድ ቤት መቼ ቀረበ፣ ክስ ተመስርቶበትስ ምን ውሳኔ ተላለፈበት የሚል ዜና አይሰማም። አይታይም። ይህን መሰል አካሄድ ሳይውል ሳያድር መታረም አለበት። ሕዝብ ከእንግዲህ ለፍርድ የቀረበና የተፈረደበት ሕገ ወጥና ስግብግብ ነጋዴን መመልከት ይፈልጋል። ፓርቲው ሕግን በአግባቡ ለመተግበርና ለማስፈፀም ቁርጠኛ ከሆነ መሰል አስተማሪ ውሳኔዎችንም በግልፅ በአደባባይ ሊያሳውቅ ይገባል።
ኢኮኖሚን ለማጎልበት ሕገ ወጥነትን ከመከላከል አስፈላጊነት ባሻገር የሕዝብን የሥራ ባህል መለወጥ የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራትም ይገባዋል። ከአገራት ጋር የምናደርገው የኢኮኖሚ ትብብር ግንኙነቶችን ማስፋትና ማጠናከርም የግድ ነው። ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ የግብይት ሰንሰለቱን ማስተካከል፤ ሕገወጦችና ዘራፊዎችን መከላከል የግድ ነው። ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ በብልሹ አሠራር ምክንያት የተጓተቱ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች በነቃ የአመራር ክትትል ማጠናቀቅም ያስፈልጋል። በተለይ በጦርነት ውስጥ ሆነን ያሳለፍናቸውን ጊዜያት ለማሳካት በልማታዊ ሥራዎቻችን ላይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
ኢትዮጵያዊ እሴቶች ላይ መሥራትም የፓርቲው ቀጣይ ወሳኝ የቤት ሥራ ሊሆን የግድ ይላል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸውን ባህልና እሴት ከመጠበቅና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የጋራቸው የሆኑ ባህሎችንና እሴቶችን እያዳበሩ በመቻቻልና በመተሳሰብ ኖሩ እንጂ የተለያየ ቋንቋዎች ተናጋሪ መሆናቸውም ከመግባባት አላገዳቸውም። የተለያዩ ሃይማኖቶችንና እምነቶችን ቢከተሉም በፍቅርና በመተሳሰብ ከመኖር አልገደባቸውም። ብዝሀነትን አክብራ በምትኖር እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገርም የእርስ በእርስ መስተጋብር በእጅጉ ጠቃሚና ወሳኝ ነው። ይሁንና ባለፉት 27 ዓመታት ብሔርን መሠረት ባደረገ አክራሪ አስተሳሰብ፣ ‹‹የእኛ’ እና ‘የእነሱ›› በሚል ከፋፋይ ሃሳብ፣ በበቀልና በጥላቻ ስሜት ማንነት ተገንብቷል። የዚህ ማንነት ሰለባዎች ደግሞ አዲሱን ማንነትን መቀበል ሲተናነቃቸው እያስተዋልን እንገኛለን።
በእርግጥ በአንድ አገር ውስጥ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ኖሮም አያውቅም፤ ሊኖርም አይችልም። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ምልከታና ግምት አለውና በሁሉም ነገር መግባባት ከቶም አይቻልም። እንኳን በአገር ደረጃ በአንድ ቤተሰብ ውስጥም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አይኖርም። ሕዝብም በሁሉም ነገር ላይ ይግባባል ማለት አይቻልም። ይሁንና ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ባለችበት በዚህ ዘመን ከወንድማማችነት ይልቅ ልዩነትን የሚያቀነቅኑ፣ አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርጉ ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን የሚሰብኩ ግለሰቦች ለሕዝብ አንድነት ጠር እየሆኑ በመምጣታቸው አደብ ማስያዝ የግድ ይላል።
በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያው በሕዝቦች ዘንድ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ምቾትና እንቅልፍ ማሳጣት ዓላማቸው ያደረጉና በመርዛማ ብዕራቸው የሚረጩ የጥፋት ጥቅመኞች በግልፅ እየተመለከትን እንገኛለን። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ በዓላት ላይ መሰል እኩይ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ማነሳሳትና ግጭቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሲሆኑ ይስተዋላል። ሆኖም እንደ አገር መቀጠል የምንችለው በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት ስንችልና ለተግባባንባቸው ምሰሶዎች ዘብ መሆን ስንችል ብቻ ነው።
ብልፅግና ፓርቲ ደግሞ እርስ በእርስ መተሳሰብን፣ መተጋገዝን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን የመሰሉ የቆዩ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ለማስቀጠል የሚሠራ ወቅቱን የዋጀ ፓርቲ መሆኑ ተነግሮናል። ይህ እስከሆነ በሕዝቦች ዘንድ የወንድማማችነት መቻቻል፣ አንድነት፣ ፍቅርና መተሳሰብን እሴትን ይበልጥ ማስረፅ ከተፈለገ ታዲያ ፓርቲው ብዙ ርቀት መሄድ ሳያስፈልግ የከፋፋይና መሰል ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በጽናት መታገልና አደብ ማስገዛት፤ ሲያጠፉም ለሕግ ማቅረብ የግድ ይለዋል።
ማንኛውም ትልም በተናጠል ጉዞ አይሳካም። የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናም የሚረጋገጠው እንደ አንድ ነጋችንን ታሳቢ በማድረግ በምንጽፈው ታሪክ፤ በምንወረውራት እያንዳንዷ ጠጠር ነው። በሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር፣ መተማመን፣ መግባባት፣ ወንድማማችነት ከሁሉም በላይ በአገር ባለቤትነት ስሜት ነው። ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን ህልሙን ማሳካት አይቻለውም። በመሆኑም አሉኝ ከሚላቸው አባላቱም በላይ ከሕዝብ ጋር ይበልጥ እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርበታል። የምንዘራውም በጋራ፤ የምናጭደውም በጋራ፤ የምንቋደሰውም በጋራ ሲሆን ሁሉ ያማረ ይሆናል።
በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ብትለወጥ በጋራ ጥረት የመጣ ለውጥ ነው ብሎ ማመን እንጂ የድል አጥቢያ አርበኛ እሳቤም ብዙ ርቀት አያስኬድም። እንደ አንድ አገር ሕዝብ ለአገር ልዕልና ግድ የሚለን ከሆነ ከእኛ እና ከእነሱ ከሚል የመገፋፋትና የመፈራራጅ ፖለቲካ መቆራረጥ ይኖርብናል። ከሁሉ በላይ ለእኔ፣ ከእኔ በእኔ የሚሉ የግለኝነትና የራስ ወዳድነት አስተሳሰቦችን መላቀቅ አለብን።
ከተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ ሰዓት ሳንቆጥር፣ ድካማችንን ሳናስተውል፣ ልዩነቶቻችን ለአገር ልማት እንቅፋት ሳይሆን፣ ካለፈው ታሪካችን ተምረን ለትውልድ የምናወርሰው ሥራ ለመስራትና ለዚሁ የሚሆን መሠረት ለማስቀመጥ እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርብናል። ተመካክረንና ተደማምጠን ከሠራን፣ ተወያይተንና ተከራክረን ከተጓዝን፣ ተባብረንና ተጋግዘን፣ ተቻችለንና ተፈቃቅረን ወደፊት ከገሰገስን፣ ኢትዮጵያን ከፈተና ወደ ልዕልና ከፍ ማድረግ ቀላል ይሆናል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋት 9 ቀን 2014 ዓ.ም