ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ድርጊት ተፈጽሟል። በማሕበራዊ ትስስር ገፆች በተንቀሳቃሽ ምስል ሲዘዋወር በቆየው እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ሰው በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞቱት ሲደረግ ታይቷል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ልብ በእጅጉ እንዲሰበር አድርጓል።
ይህ ድርጊት ከኢትዮጵያዊነት ባህል፣ እሴትና ከማንኛውም የሰብአዊነት እሳቤ ያፈነገጠና እጅግ አሰቃቂ ተግባርም ነው። ይህ እኩይ ድርጊት መጠፋፋትን ያፋጥን ይሆናል እንጂ ሰላምንም ሆነ ፍትህን እውን ሊያደርግ አይችልም። ሊኮነንም ሊወገዝም የሚገባው እኩይ ተግባር ነው። መነሻቸውም ሆነ ማንነታቸው ምንም ይሁን ምን መንግሥት ይህን አይነት ፍጹም ከሰብአዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈጸሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባውም ምንም ጥያቄና መልስ የማያሻው ጉዳይ ነው።
ይህ እኩይ ተግባርና ድርጊት በእውነት ይህ የሆነው በእኛ በኢትዮጵያውያኑ አገርና ሕዝብ ላይ ነው? የሚለው ደግሞ እጅጉን ያሳዘነ ሁላችንንም ግራ ያጋባ ሆኗል። ሌላው ትልቁ ግራ የሚያጋባው ነገር ደግሞ ገዳዩም ተገዳዩም በዚህች አገረ እግዚአብሔር እየተባለች በምትጠራው ምድር ላይ የምንኖር እኛው መሆናችን ነው።
አሁን በደረስንበት ደረጃ እራሳችንን እንለካ ብንል እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊ ተብሎ ለመጠራት ወርደናል፣ አንሰናል፤ አንሰንም ሌሎችን ለማሳነስ የራሳችንን ጥረት በማድረግ ላይ ነን። በሳይንሱም ቢሆን የተማርነው ሰው ከእንስሳ የሚለየው በማሰቡ፣ በማመዛዘኑና ክፉና ደጉን በመለየት አቅሙ ነው። ነገር ግን እኛ ከእንስሳቶቹም አንሰን ከሰብአዊነት ደረጃም ከወረድን ሰነባበትን። እርስ በእርስ ከመባላት አልፈን መጋደላችን አልበቃ አላረካ ብሎን ዛሬ ላይ ደግሞ የአረመኔያዊ አገዳደል ፉክክር ውስጥ ገብተን ቁጭ ብለናል።
በጨካኞች ከራሳቸው በላይ ስለሌላው ወገን ደንታ በማይሰጣቸው ስግብግቦች ምክንያት ዜጎች በየቦታው ለስደትና ለእንግልት የመዳረጋቸው ዜና የየእለት ቀለል ያለ ተግባራችን ሁሉ መስሏል። የጅምላ ግድያና መቃብርንም እስኪበቃን አይተናል። በእነዚህ ነብሰ በላዎች ብዙዎች ያለ ጥፋታቸው በጅምላ ሲፈረድባቸውና ሕይወታቸው ሲነጠቀም አይተናል። ነፍሰ ጡር ሴት የምትወልደው ልጅ ብሔር ይኖረዋል ተብሎ ሞት ሲፈረድበትም ያየነው በዚህችው አገራችን ላይ ነው።
ከዚህ ሁሉ አረመኔያዊ ተግባር የጭካኔ አገዳደል በኋላ ያላየነው ወይም ደግሞ የምንሰማው አይኖርም ብለን ቁጭ ባልንበት፤ እጅግ የሚዘገንን እውነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ነው የተፈጸመው የሚያሰኝ ዜጎች ከነህይወታቸው እንደ ችቦ ተደምረው እሳት በላያቸው እንዲነድ ሆኖ ሲገደሉ አየን፤ ሰማን። ይህ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የጥቂቶችን አኩይ ተግባር ለማስፈጸም የሚውል አሰቃቂ ግድያ ግን ምን ዓይነት ውጤት ነው ሊያመጣ የሚችለው? የሚለው ጥያቄ ደግሞ የሁላችንም ነው። መንግሥትስ እውነት ይህንን ተግባር ዓላማው ምንም ይሁን ምን በዝምታ በሆደ ሰፊነት ነው የሚያልፈው ወይንስ እንዳለው አረመኔዎቹን ለፍርድ አደባባይ አውጥቶ ያሳየናል ? እንጃ ብቻ ሁሉም ጥያቄ ነው፤ እንደውም መልስ የሌለው።
ሌላው እጅግ የሚያሳስበኝ ነገር ደግሞ እስከ አሁን በአገሬ ላይ ያላየሁት ያልሰማሁት የግድያ አይነት ይኖር ይሆን የሚለው ነው። አዎ፣ ጭካኔያችን በዝቷል፤ ስግብግብነታችን መስመሩን ስቶ የማናውቀው ነገር ውስጥ ጨምሮናል። ኢትዮጵያዊ ባህል ወግ ርህራሄ ምናምን እያልን የምንላቸው የእኛነታችን መገለጫዎች በሙሉ አሁን ላይ ከእኛ ርቀው በምትኩ እኩይ ሃሳብ ሰይጣናዊ ተግባር የመጠፋፋት መንገድን መርጠናል፤ ግን የትኛውም ሥልጣን ጥመኛ ወይንም ደግሞ ነጻ ያልወጣ ነጻ አውጪ ቢሆን እንጂ በዜጎቻችን ሕይወት ላይ ቁማር ሲጫወት ዝም ብሎ ማየት ከአጥፊዎቹ ተርታ የሚያስመድብ እንዳይሆን መጠንቀቅም ይገባል።
እንደ እኔ በእነዚህና መሰል ኢሰብዓዊ ተግባሮቻችን ምክንያት ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያዊ ነን ብለን ለመኩራት ሰብዓዊ ፍጡር ነን ብለን እንደ ሰው ለመቆጠር የሚያስችለን ደረጃ ላይ ነን ብዬ አላምንም። ገዳዩም ተገዳዩም እኛው በመሆናችን ለዚህ ሁሉ ወንጀል ይጠየቅልን የምንለው አካልስ ማነው? ተጠያቂነቱም ጉዳቱም ኀዘኑም እልፍ ሲልም ሀፍረቱም የእኛው ብቻ ነው። እንደ ዜጋም ሆነ እንደሰው የገደለውም ሆነ የሞተው ማንም ሳይሆን እራሳችን ነን። በብሔር ማንነቱም ከገዳይም ሆነ ከተገዳይነት ያመለጠም የለም።
ይህ እኩይ ተግባር አሁንም ማነጋገሩን ብሎም የዜጎችን ልብ መስበሩን የወደፊቱን ጊዜ በፍርሃትና በሽብር የመጠበቅ ያህል ማስፈራራቱን ቀጥሏል። ዜጎች እንዲረጋጉ ይህ መሰሉ ክስተትም ዳግም በአገራችን ላይ የማናይበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ደግሞ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ሕገወጥነት ለመቆጣጠርና በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልም ከክልሉና ከመላው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ስለመሆኑ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል። የንጹሃን ዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን መንግሥት ከዚህ በኋላ አልታገስምም ብሏል።
ስለዚህ እነዚህ በወንጀል ስራ ላይ የተሰማሩና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት በጥብቅ አሳስቧል። በዚህ እጅግ አሰቃቂና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ድርጊት የፈጸሙ አካላትን አጣርቶ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ተናግሯል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ነገር ቢሆንም፤ ሕይወታቸውን ያለአግባብ የተነጠቁ ዜጎች ደም ግን ከመግለጫ የዘለለ እርምጃን ትፈልጋለች። በሕይወት ላሉትም የመኖር ዋስትና ሊሰጣቸው የግድ ነው። በመሆኑም መንግሥት በጉዳዩ ላይ የሰጠው መግለጫ እንዳለ ሆኖ እርምጃው ግን ያፈጠነ የተበዳዮችን ብሎም የመላውን ዜጋ ልብ ስለ ፍትህ ያለውን መተማመን ከፍ በሚያደርግ መልኩ ሊፈጸም ይገባል። አበቃሁ፤ ቸር ያቆየን!
በእምነት
አዲስ ዘመን መጋት 9 ቀን 2014 ዓ.ም