ለኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚበረከት እውቅናና ሽልማት ለጥበብ ሥራ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። የኪነ ጥበብ ባለሙያው ለኅብረተሰቡ የሚያቀርበውን ጥበባዊ ሥራ ማህበረሰቡ አይቶ ሙያዊ አስተያየት ሲሰጠው፤ ብሎም በሠራው እውቅናና ሽልማት በተገቢው አካል ሲበረከትለት ለቀጣይ ሥራው ጥሩ የሞራል ስንቅ ያገኛል። በዚህም በቀጣይ ሥራዎቹ ቀድሞ ከሠራቸው የተሻለ ኪነጥበባዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎችን መሥራት ያስችለዋል።
ለዚህም ነው፤ በተለያዩ ዓለማት ለኪነጥበብ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት የሚበረከትላቸው። በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዕድገት ውስጥ የጎላ ሚና ላላቸው የኪነጥበብ ሥራዎች በአገር ደረጃ እውቅናና ሽልማት ሲበረከት ቆይቷል።
ነገር ግን ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ በአገር ውስጥ ሌሎች ቋንቋዎች የሚሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎች በይዘትና በጥራት የተሻሉ ሆነው ማህበረሰቡ ዘንድ እንዲደርሱ ለማስቻል ብሎም የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ለማበረታታት ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ለኪነጥበብ ሥራዎች እውቅና መስጠት ብዙም አልተለመደም።
ኦዳ ሽልማት ይህንን ክፍተት ለመሙላት ብቅ ያለ ነው፤ ድርጅቱ በጥቂት አመታት ባከናወናቸው ለኦሮምኛ ኪነጥበብ መነቃቃት መፍጠር ችሏል። ላለፉት አምስት አመታት በአፋን ኦሮሞ (በኦሮሚኛ ቋንቋ) የተሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎችን በመምረጥ እና በመሸለም በቋንቋው ለሚሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎች ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል።
ለኪነ ጥበብ ሥራዎች እውቅናና ሽልማት መስጠት ኪነጥበባዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። ጥበበኛ ለሚሠራቸው ሥራዎች የተሻለ እውቅና ሲቸረው እውቅናው እና ሽልማቱ አቅም ሆኖት በቀጣይ በሚሠራቸው ሥራዎቹ የተሻለ አቅም የሚፈጥርለት ሞራል ይገነባል። ኦዳ ሽልማት በአፋን ኦሮሞ ኪነ ነጥብ ውስጥ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ በተለያየ ዘርፍ በሥራቸው ለተመረጡ አርቲስቶች በየአመቱ ሽልማትና እውቅናን ይሰጣል።
በበሻቱ ቶለማሪያም መልቲ ሚዲያ እና በኦሮሚያ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት የሚዘጋጀው ኦዳ ሽልማት ዘንድሮም 5ኛውን ዙር ሽልማት የካቲት 29ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በደማቅ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።
«ኦዳ አዋርድ» የአገራችንን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች በማበረታታት የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበብ በአገር ደረጃ በማሳደጉ ሂደት ላይ በጎ ሚና መጫወት ላይ አላማው አድርጎ የሚዘጋጅ መሆኑን ጋዜጠኛ በሻቱ ቶለማሪያም የኦዳ አዋርድ መስራች ትገልፃለች። በዘንድሮው ሽልማት በዓመቱ ውስጥ የላቁ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን መርጦ በ20 ዘርፍ መሸለሙን ገልፃ፣ ወደፊት ዘርፎቹ በማስፋት መሰል ሽልማቶችን ለምርጥ ሥራዎች ማቅረቡን እንደሚቀጥል ትጠቁማለች።
በበሻቱ ቶለማሪያም መልቲሚዲያና በኦሮሚያ ባህል ቱሪዝም ቢሮ ተባባሪነት በዘንድሮው የኦዳ ሽልማት ከ65 በላይ ሥራዎች በዕጩነት ቀርበዋል፤ ከዚህ ውስጥ በዓመቱ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉና ሥራዎቻቸው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ሆነው በሙያተኞች የተመረጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተሸልመውበታል።
ባለፉት 4 አመታት በተካሄዱት ደማቅ ዝግጅቶች ሲካሄድ የቆየው ኦዳ አዋርድ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ባለሞያዎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል። ይህም በአፋን ኦሮሞ የሚሰሩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች በብዛትም በጥራትም ከፍ እያሉ እንዲሄዱ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል፣ ከሽልማቱ በኋላ የኪነጥበብ ሥራዎች በይዘትና በጥራት ከፍ ማለታቸውን ነው የምታስረዳው።
በዘንድሮው ደማቅ ሽልማት መርሀ ግብር በተለያዩ ዘርፎች ከ65 በላይ ዕጩዎች ቀርበው አሸናፊዎች ተለይተው መድረክ ላይ በሥራዎቻቸው የክብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ከሌላው ጊዜ በተለየ በሁለት ተጨማሪ ቋንቋዎች የኪነጥበብ ሰዎች መሸለማቸው ለሽልማቱ ድምቀት ሆኗል።
በዓመቱ ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ከተሠሩ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ተመርጠው ለሽልማት የቀረቡ ሥራዎች በተለያየ ሙያዊ መስፈርት የተለዩ መሆኑን የምትገልፀው የኦዳ ሽልማት መስራች ጋዜጠኛ በሻቱ፣ 70 በመቶው በዳኞች የተሰበሰበ ውጤትና 30 በመቶ ከሕዝብ በተሰበሰበ ድምፅ ምርጫ መካሄዱና ተገቢው የምርጫ መስፈርት ባሟላ መልኩ እንደተካሄደ አስረድታለች። በሸራተን አዲስ ሆቴል የካቲት 29 ቀን በተካሄደው በዚህ 5ኛው ዙር የኦዳ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ተሸላሚ የሆኑ አርቲስቶች ስምንቱ በሙዚቃ፣ ሰባቱ በፊልም እንዲሁም ሁለቱ ደግሞ በሥነ ጽሑፍ ዘርፎችና ሌሎች በሕይወት ዘመንና በሥነፅሑፍ አስተዋፅኦ የተዘጋጁ ሽልማቶች ተበርክተውበታል።
የሽልማት ዘርፎችና አሸናፊዎች
ለሽልማት ከቀረቡ ዘርፎች መካከል የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ የአመቱ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ አልበም፣ የአመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፣ የአመቱ ምርጥ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ጥምረት፣ የአመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊት፣ የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ ፣ የአመቱ ምርጥ ፊልም፣ የአመቱ ምርጥ ሴት ተዋናይ፣ የአመቱ ምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ የአመቱ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር ይገኙበታል።
በተጨማሪም የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ ኤዲተር፣ የአመቱ ምርጥ ፊልም ጽሑፍ፣ የአመቱ ምርጥ ዳይሬክተር፣ የአመቱ ምርጥ ግጥም መጽሐፍ፣ የአመቱ ምርጥ ልቦለድ መጽሐፍ፣ በአፋን ኦሮሞ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ፣ በአፋርኛ የሕይወት ዘመን ተሸላሚና በሲዳምኛ የሕይወት ዘመን ተሸላሚም ይገኙበታል።
በሙዚቃ ዘርፍ
ላለፉት አምስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ሽልማት ለሙዚቃና ለፊልም ኢንዱስትሪው ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን የምትናገረው የኦዳ የሽልማቱ መስራች በሻቱ ቶለማሪያም፤ በዚህ አመት ብቻ ከ460 በላይ የሙዚቃ ሥራዎች በአፋን ኦሮሞ ለሕዝብ እንደቀረቡ ጠቅሳለች። ከእነዚህም መካከል በይዘትና በሥራ የተሻሉ ሥራዎች ለውድድር መቅረባቸውን ጠቁማለች። በመሆኑም በሙዚቃ ዘርፍ ብርቱ ፉክክር የታየበት መሆኑንም ትገልፃለች።
በዚህ ዘርፍ በዓመቱ ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ከተሠሩ ሙዚቃዎች በአልበም በነጠላ ዜማ በሙዚቃ ክሊፕና በጥምር ሙዚቃ ዘርፍ የተመረጡ አርቲስቶች በሥራቸው የተሸለሙ ሲሆን፤ በዓመቱ ውስጥ ከተሠሩት የሙዚቃ አልበሞች የሀጫሉ ሁንዴሳ ማልመሊሳ አልበምና፣ የጂሬኛ ሺፈራው አልበሞች የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፤ የሀጫሉ ሁንዴሳ ሽልማት ባለቤቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ተረክባለች። የአመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ደግሞ ኤልሳ ኑጉሴ፣ ኤቢሴ ብርሀኑ እና መርጊቱ ወርቅነህ ናቸው፤ በዚህ ዘርፍም መርጊቱ ወርቅነህ አሸናፊ በመሆን ሽልማትን ተቀዳጅታለች።
በዚሁ ዘርፍ በምርጥ ጥምር ድምፃውያን እጮች ተጣምረው በሰሩት የሙዚቃ ሥራ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዲቾ ሀዊና ጌታሁን፣ ሎንጮና ኤልሞ፣ ተካና ሞኢካ ሲሆኑ ኤሌሞ እና ሌንጮ የጥምር ድምፃውያን አሸናፊዎች በመሆን ተሸልመዋል። በምርጥ ዘመናዊ ሙዚቃ ዘርፍም ምርጥ ዘመናዊ ሙዚቃ ሱራ፤ ኢቢዶ፤ ሮቤካ እና ጂቦ አሸናፊ በመሆን ሽልማታቸውን ተረክበዋል። የአመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ በመሆን ያሸነፈው ደግሞ አዱኛ አመንቴ ነው።
በምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ አምስት ተወዳዳሪዎች ዕጩ ሆነው ቀርበዋል፤ እነሱም ገላና ጋሩምሳ፣ ሌንጮ ገመቹ፣ መርጊቱ ወርቅነህ፣ ተፈሪ አባቡና ገዳ ሀምዳ ሲሆኑ፣ ሌንጮ ገመቹ አሸናፊ በመሆን የዓመቱ ምርት የሙዚቃ ክሊፕ አሸናፊነት ሽልማት ተበርክቶለታል። በምርጥ ነጠላ ዜማ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ገላናህ ጋሩምሳ ሌንጮ ገመቹ፣ አመዷለም ጎሳ፣ ሻኪሶ አወልና ጆርጅ አቦ ሲሆኑ በዚህ ዘርፍ በሠራው ምርጥ ነጠላ ዜማ አንዷለም ጎሳ ተሸላሚ ሆኗል። የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ስቱዲዮም ቪዥን ኢንተርቴይንመንት በመሆን ሽልማት አግኝቷል።
በፊልም ዘርፍ
ከኦዳ ሽልማት በፊት በአፋን ኦሮሞ የፊልም ሥራዎች ቁጥር አነስተኛ የነበረ ሲሆን፣ ሽልማቱ በፈጠረው መነቃቃት በርከት ያሉ ሥራዎች በይዘትና በጥራት ለሕዝብ መቅረባቸው መቀጠሉ ተጠቁሟል።
በዚህ በዓመቱ ውስጥ የተለያዩ የፊልም ሥራዎች ለሕዝብ የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ፊልሞች መካከል ኦዳ አዋርድ ምርጥ ፊልሞችና የፊልም ባለሙያዎች ተሸልመዋል። በፊልም ዘርፍ በአመቱ ከተሠሩ የፊልም ሥራዎች ዕጩ ሆነው በዓመቱ ምርጥ ፊልምነት የቀረቡት ለፋፍ ለፌ፣ ሞኣና መልኪ ሲሆኑ፣ በምርጥ የዓመቱ ፊልም ተመራጭ የሆነው ለፋፍ ለፌ የተሰኘው ፊልም በመሆን ሽልማት ተቀዳጅቷል።
የዓመቱ ምርጥ ወንድ ተዋናይ በሚል ለዕጩነት የቀረቡት ታምራት ከበደ፣ ጳውሎስ ልዑልና ውብሸት ገብረሚካኤል ናቸው። ምርጥ የፊልም ስክሪፕት ጸሐፊ ጂማ ገለታ፣ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር ገመቺስ ጥላሁን፣ ምርጥ ቪዲዮ ኤዲተር ቶላ ዲንገታ፣ ምርጥ ዳይሬክተር፣ ጂማ ገለታ በመሆን ሽልማት ተቀዳጅተዋል። በምርጥ ሴት ተዋናይት ዘርፍ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ሀባቦ ወርቅነህ፣ ሜቲ አዳሙና ህልፋ አለማየሁ ሲሆኑ፣ ተዋናይት ሀባቦ ወርቅነህ አሸናፊ በመሆን ተሸልማለች።
በአፋን ኦሮሞ የኪነጥበብ ዘርፍ ባበረከተው አስተዋፅኦ አርቲስት ኢብራሂም ሀጅ አሊ ቦሩ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሲሆን፤ በዚሁ ዘርፍ በዘንድሮው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ከአፋርና ከሲዳማ ለኪነጥበብ ባበረከቱት አስተዋፅኦ የሕይወት ዘመን ሽልማት የተበረከተላቸውም አሉ፤ እነሱም በአፋርኛ አርቲስት አሉ ያዬ፣ ባሩሌ ሲሆኑ በሲዳምኛ ደግሞ አዱኛ ዱጋ ናቸው።
በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ በዓመቱ ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ከታተሙ መጽሐፍት በግጥምና በልቦለድ ተለይተው ምርጥ የተሰኙት ሽልማት ተቀዳጅተዋል፤ በግጥም መጽሐፍት ዘርፍ ሃመርሰን ተስፋዬና በምርጥ ልቦለድ መጽሐፍ ቆሪቾ ሹፌራ ተመርጠው የዓመቱ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ባለቤት ሆነዋል። በሽልማቱ ላይ ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎችም በሽልማት ቀርበው የሽልማት መርሀግብሩን አድምቀውታል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 /2014