
አዲስ አበባ፦ ከመጪው ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ (online) እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ከመጪው ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ሀገር የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በአዲስ አበባ ከተማ ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ይሰጣል። ለዚህም የሚሆን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በቢሮው ከተደረጉት የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች መካከል ፈተናውን የሚወስዱት ተማሪዎች በበይነ መረብ መፈተን የሚችሉባቸው ግብዓቶች የተሟሉላቸው የመፈተኛ ጣቢያዎች ዝግጅት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቢሮው በከተማ አስተዳደር ደረጃ ፈተናውን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችለውን ጀኔሬተርን ጨምሮ በቂ የኮምፒውተር፤ ታብሌት፣ ኢንተርኔት፣ ዋይፋይ ግብዓት የተሟላለት የመፈተኛ ጣቢያ ዝግጅት ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ ሲያከናውን መቆየቱንም አመልክተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ፤ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ፤ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በዋናነትም ትምህርት ሚኒስቴር ከቢሮው ጋር በቅንጅት የዝግጅት ሥራውን ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ፈተናውን ለ48 ሺህ 415 ተማሪዎች በአራት ዙር ለመስጠት የሚውል ግብዓት የተሟላበት የፈተና ጣቢያ ድልድል ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን አመልክተው፤ በዚህ መሠረትም እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዓድዋ ድል መታሰቢያን እንዲሁም የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎችን በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችሉ ሰርቨሮች እና ኮምፒዩተሮች የተደራጀ ግብዓት የተሟሉላቸው 111 ፈተና መስጫ ጣቢያዎች ተለይተው ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
የቢሮ ኃላፊው ዘለዓለም (ዶ/ር) ፈተናው ሰኔ 23 ቀን 2017 25ሺህ 224 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በሚወስዱት ፈተና በይፋ የሚጀመር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሄው የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የሚወስዱት የመጀመሪያ ዙር ፈተና እስከ ሰኔ 24 እና 25 የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሄው የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የሚወስዱት ሁለተኛ ዙር ፈተና ሰኔ 26፣ ሰኔ 27 ፣ እንዲሁም ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ የሚቆይ መሆኑን አመልክተዋል።
ቢሮ ኃላፊው በተጨማሪም እንደገለፁት ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የሚወስዱት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የመጀመሪያ ዙር ሐምሌ አንድ፤ ሁለት እና ሦስት ቀን 2017 ዓ.ም ይሰጣል። እንደዚሁም ይሄው የማህበራዊ ሳይንስ ሁለተኛ ዙር ፈተና ሐምሌ አራት ፤ ሰባት እና ስምንት ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ ይቆያል ብለዋል።
ተፈታኞቹ የበይነ መረብ አሰጣጥ ሂደቱ ለአጠቃቀም ቀላል እና ኩረጃን የሚቀንስ መሆኑን ተረድተው ከየትኛውም ስጋት ነፃ በመሆን እና በመረጋጋት ፈተናውን ለመውሰድ እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል። ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም