
ዜና ሀተታ
ጊዜው 1999 ዓ.ም ነው። በዚህ ጊዜ የ 19 ዓመቱ ተማሪ ባንታለም ጉግሳ በትምህርት ቤት የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ክበብ አባል ይሆናል። ከዚያም ወደ ቀይ መስቀል ተቋም በመሄድ እንዴት የመጀመሪያ ርዳታ መስጠት እንደሚቻል ከጓደኞቹ ጋር ስልጠና ይወስዳል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ባንታለም እና ጓደኞቹ ስልጠናቸውን አጠናቀው ሲወጡ፤ እድሜያቸው ጠና ያለ ባልና ሚስቶች ቆመው ሲያለቅሱ ያስተውላሉ።
ሁለቱን ሰዎች አይቶ ለማለፍ ልባቸው ስላልፈቀደ ጠጋ ብለው አናገሯቸው። ባልና ሚስት ሲያለቅሱ የነበረበት ምክንያት ልጃቸው ልትወልድ ሆስፒታል ገብታ ደም ስላስፈለጋት፤ ደም ለመግዛት ደላሎችን አናግረው የጠየቋቸው ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው ነው።
ያቺ አጋጣሚ ነበረች የደሴ ከተማውን ባንታለም ጉግሳ ደም ወደ መለገስ በጎ ተግባር ያስገባችው። ከዚህ በኋላ ደም መለገስን የምን ጊዜም ሰናይ ተግባሩ በማድረግ ቀጠለበት። ይህ መልካም ተግባሩም ለመሸለም አብቅቶት 21ኛው ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በሚከበርበት ወቅት ለ65ኛ ጊዜ ደም በመለገስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመሸለም በቅቷል።
“እኔ መለገስ በጀመርኩበት ወቅት የደም ሽያጭ እንጂ መተካት አልተጀመረም ነበር” የሚለው ባንታለም፤ “ሰዎቹን አናግረን ጭንቀታቸውን ከሰማን በኋላ ትቶ መሄድ ስለከበደኝ ተመልሼ መጥቼ ልለግስ አልኳቸው። ከዚያም ምርመራ ተደረገልኝ እና መለገስ እንደምችል ስለተነገረኝ ለገስኩ።” ይላል።
“ደም በመለገሴ በቀላል ነገር ሰዎችን ማስደሰት እንደሚቻል ተማርኩኝ ። በአጋጣሚ በህመም ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ልግስናዬን አቋረጥኩ እንጂ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መለገስ አላቆምኩም። ደም መለገስ የሰው ሕይወት መታደግ ስለሆነ ሌሎች ሰዎችም ሊፈሩ አይገባም ።” ሲል ሃሳቡን ይገልጻል።
ለ54ኛ ጊዜ ደም በመለገስ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ የተሸለመው ሰለሞን ከታ ለስድስተኛ ጊዜ የሚለግሰውን ጓደኛውን አጅቦ የሄደባት አጋጣሚ ነበረች እሱንም ገና በ17 ዓመቱ ደም መለገስ እንዲጀምር ያደረገችው።
“ከጓደኛዬ ጋር የሄድኩት ለመለገስ አልነበረም ግን እሱ ሲለግስ ለምን አትሞክርም አለኝ። የመጀመሪያዬ በመሆኑ ፍርሃት ቢኖርብኝም አደፋፈረኝና እሺ ብዬ ለገስኩኝ። ከዚያን በኋላ እንዲያውም ሶስት ወር ሳይሞላን ሁሉ እየሄድን እንለግስ ነበር።” ይላል።
“ሕይወት ማዳን በጣም ደስ የሚል ነገር ነው።” የሚለው ወጣት ሰለሞን፤ ለሶስተኛ ጊዜ ሲለግስ አጋጣሚ የእሱ ደም ለታካሚዋ ሲደርስ ለመመልከት ችሎ ነበር። በዚህም ታካሚዋ ደም ከማግኘቷ በፊት የነበራትን ስቃይ እና እሱ በለገሰው ደም ሕይወቷ ሲተርፍ ማየቱ በበጎ ተግባሩ እንዲቀጥልበት እንዳስገደደው ይናገራል።
ደም የመለገስ ባህል እንደ ሀገር ደካማ መሆኑን በማንሳት፤ “በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ነገር እንዲህ ሲል ያስታውሳል። ‹‹በአንድ ወቅት አንድ ሰውዬ ሚስቱ ልትወልድ ሆስፒታል ገብታ በአጋጣሚ ደም አስፈለጋት። ነገር ግን ባለቤቷ እራሱ ከመለገስ ይልቅ ሆስፒታል በር ላይ ደም በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዎች ጋር ለመግዛት ሲደራደር አገኘሁት። ይህንንም ለደም ባንኩ ባለሙያዎች በማሳወቅ ሰውየው ወደ ማረሚያ እንዲገባ ተደረገ፤ እኔም ለሴትየዋ በመለገስ ሕይወቷ እንዲተርፍ ምክንያት ሆኛታለሁ።” ሲል ይገልጻል።
ደም የመለገስ ልምዱ ጤናውን ከማስጠበቁም በላይ፤ በምንም የማይተካው የሰው ሕይወት እንዲተርፍ ምክንያት አድርጎታል። ሁሉም ሰው በደቂቃ ውስጥ ምን እንደሚገጥመው አያውቅም የሚለው ወጣቱ ደም መለገስ ደግሞ ዓላማው የተቸገሩትን መርዳት ስለሆነ፤ በመስጠታችን ምንም በማንጎዳው ደም የሰው ሕይወት እናትርፍ ሲል መልክቱን ያስተላልፋል።
ሌላው ለ29ኛ ጊዜ ደም በመለገስ ተሸላሚ የሆነው የሐረር ከተማው ወጣት ቅዱስ ያሬድ ነው። ቅዱስ 15 ዓመት ሊሞላው አካባቢ ነበር በ2008 ዓ.ም ደም መለገስ የጀመረው። “የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የደም ባንክ ባለሙያዎች ከትምህርት ቤታችን አቅራቢያ መጥተው ሰዎች ደም እንዲለግሱ ሲጠይቋቸው ፈቃደኛ እየሆኑ ሲለግሱ ሳይ ደስ ብሎኝ እኔም ለገስኩ።” ይላል።
በወቅቱ ከእድሜው አንጻር የማይፈቀድ ቢሆንም፤ ሰውነቱ ግዙፍ ስለነበር ለመለገስ መቻሉን የሚናገረው ቅዱስ፤ ባጋጠመው ኀዘን እና ንቅሳት በመነቀሱ ምክንያት መኃል ላይ ለተወሰኑ ጊዜያት ቢያቋርጥም፤ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል መለገሱን ይገልጻል።
ደም በመለገሱ የማይተካውን የሰው ልጅ ሕይወት በማትረፉ የአዕምሮ ሰላም ማግኘቱንም ይገልጻል “አንዳንድ ጓደኞቼን አምጥቼ እንዲለግሱ አደርጋለሁ። ነገር ግን አንዳንዶቹ ግንዛቤው ቢኖራቸውም ደም ይሸጣል በሚል ለመለገስ አይፈልጉም ይላል። ›› ዓላማው ከአንድም ሶስት ሰው ለማትረፍ እስከሆነ ድረስ ለግሶ የሰውን ሕይወት ማትረፍ ያለው የመንፈስ ርካታና ደስታ ትልቅ ነው።” ይላል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም