
አዲስ አበባ፡– የተሟላ ነጻነትና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የሥራ ባህልን ማዳበር ይገባል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት “የሥራ ባህልና ምርታማነት ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ዘመኑ የሚጠይቀው ሉዓላዊነት በላብና በጥረት የሚረጋገጥ ነው። ከዚህ መነሻነትም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የሥራ ባህልን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
ጊዜው ከለውጥ ጋር በፍጥነት መራመድ የሚጠይቅ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኃያል ሀገር ለመገንባት ጠንካራ የሥራ ባህልን ማዳበር ያስፈልጋል። በጠንካራ የሥራ ባህል ኃያል ሀገር መገንባት ካልተቻለ የትኛውም ሀገር ተነስቶ የፈለገውን የማድረግ ስልጣን ስለሚኖረው የሀገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ይወድቃል ሲሉ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአባቶች አጥንትና ደም ነጻነቷን አስከብራ የቀጠለች ሀገር ብትሆንም፤ የኢኮኖሚ ነጻነቷን እስካላረጋገጠች ድረስ ነጻነቷ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀርም ያሉት ሚኒስትሯ፤ ምክንያቱም ያልተሟላ ነጻነት ይዞ በኩራት መሄድ እንደማይቻል አመልክተዋል።
ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ የተሟላ ነጻነት ከተፈለገ በላብና በጥረት የተለወጠች ሀገር መገንባት ያስፈልጋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ዓመታት መልካም ዘሮች ተዘርተዋል። በተለይም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ምርታማነትን በማሳደግ ለውጥ ማምጣት ይቻላል በሚል እሳቤ፤ ውጤቱ እንደክልሎቹ የተለያየ ቢሆንም እንኳን፤ የሥራ ባህል ለውጥ ለማምጣት ማህበረሰቡን ከታች ጀምሮ የማወያየት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ማምረትን እና የተመረተን ምርት እሴት ጨምሮ መላክ የኩራት ምንጭ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ እንደዚህ አይነት ጥልቅ እሳቤዎች ፣ልምምዶች እና የሥራ ባህሎች ሙሉ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችሉም ጠቁመዋል።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ (ዶ/ር) በመነሻ ጽሁፋቸው እንደገለጹት፤ ጠንካራ የሥራ ባህል ለመገንባት ተግዳሮት ከሆኑት መካከል ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደካማ የሆነ የትምህርት እና የሙያ ስልጠና አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አብዛኛው ዜጋ የቢሮን ሥራ ብቻ እንደ ሥራ አድርጎ የመቁጠር እና ሌሎች የሥራ አይነቶችን ለመሥራት ፍላጎት ማጣት። እንዲሁም ለስደት መነሳሳት፤ በትላልቅ ከተሞች ብቻ ለመሥራት መፈለግ እና በተወሰኑ የሥራ አይነቶች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ሌላኛው ተግዳሮት ነው ብለዋል።
ጥላሁን(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚሠሩ እጆች እንደሚያበለጽጉ በማሳየት፤ ለጠንካራ የሥራ ባህል ተግዳሮት ሆኑ አመለካከቶችን እንደገና በመፈተሽ እና የተጠናከረ የሚዲያ ዘመቻ በማድረግ የባህል ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም