
– በሦስት ዕፅዋቶች ላይ በተደረገ ሳይንሳዊ ምርምር ጥቅማቸውን ማረጋገጡም ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የዳውሮ ማኅበረሰብን ቅርስና ባህላዊ የዕፅዋቶች ዝርያዎችን የያዘው ኢንትሮግራፊክ ሙዚየም የመጀመሪያ ዙር የዲጅታላይዜሽን ሥራው መጠናቀቁን የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በሦስት ዕፅዋቶች ላይ ባደረገው ምርምር ጥቅማቸውን ማረጋገጡን አመለከተ ።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሣሁን ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ኢንትሮግራፊክ ሙዚየሙ የዳውሮ ማኅበረሰብን ታሪክ፣ ባህልና ባህላዊ የዕፅዋቶች መድኃኒቶችን አጠቃቀም በሚገባ የሚያሳይ ነው።
ይህ የማኅበረሰቡ ቅርስና ባህላዊ የመድኃኒት አጠቃቀም በስፋት የሚታወቅ አልነበረም ያሉት ፕሮፌሰር ካሣሁን፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ሙዚየሙን ዲጂታላዝ የማድረጉ ሥራ ለኢንስትቲዩቱ በኃላፊነት ተሰጥቶት ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል።
አሁን ላይ የመጀመሪያ የዲጂታላይዜሽን ሥራው እንደተጠናቀቀ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሙዚዬሙ ቅርስን ከማስተዋወቅ ባሻገር በባህላዊ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ዕፅዋቶች በጥናት እንዲለዩና ጥቅማቸውን ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችም ተረድተው እንዲገለገሉባቸው ለማድረግ የሚያስችሉ ዕድሎች የተገኘበት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
የሙዚዬሙ ዲጂታላይዝ መሆን እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ጠቁመዋል። ለአብነት ማኅበረሰቡ ቅርሶቹን አውቆ ታሪኩን እንዲረዳ፤ ባህላዊ የሆኑ መድኃኒቶቹን በሳይንሳዊ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ከዚህ ባሻገር ቱሪስቶችን በመሳብ የተሻለ ገቢ የሚያገኝበትን አማራጭ ይፈጥራል። እንደ ሀገር ሲታይ ደግሞ ለማኅበረሰብ ጥናት አጥኚዎች፣ ለዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ለዘመናዊ ሳይንስ አጥኚዎችና ለዕፅዋቶች ሳይንስ ተመራማሪዎች እንዲሁም ለዕፅዋቶች ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ከቱሪዝም መዳረሻነት አንጻርም የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የዳውሮ ኢንትሮግራፊክ ሙዚየምን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ፤ እንደ ሀገር ለየት የሚሉ ተግባራትም በዞኑ ላይ ተሠርተውበታል የሚሉት ፕሮፌሰር ካሣሁን፣ በዳውሮ ዞን በቅርስነት እንዲቀመጡ የሚሆኑ ማኅበረሰቡ ከዚህ በፊት በባህላዊ መልኩ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሦስት የዕፅዋቶች ዝርያዎችን ጥቅሞች በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በመለየት የመጀመሪያ የጥናት ውጤቶችን ይፋ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመዋል።
ዕፅዋቶቹ ማኅበረሰቡ ተባይን ለማጥፋት፣ ባክቴሪያን ለመከላከል እንዲሁም ለከብቶች መኖና ማደለቢያ የሚገለገልባቸው እንደሆኑ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጫንቋ በሳይንሳዊ ስያሜው (Agarista salicifolia) የሚሰኘው ዕፅዋቶች ለተባይ ማጥፊያነት፣ ደልበንሳ በሳይንሳዊ ስያሜው (Pentas schimperiana) የተሰኘው ዕፅዋቶች ደግሞ ባክቴሪያዎችን ለመቆጣጠርና የከብቶች መኖ እንዲሁም ሰሳ በሳይንሳዊ ስያሜ (Dioscorea schimperiana ) የተሰኘው በጫካ የሚገኝ ድርቅ በሚመጣበት ወቅት ጥቅም ላይ የሚያውሉት ዕፅዋቶች በዋናነት በጥናቱ ተለይተው ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ ጫንቋ የተሰኘውን ዕፅዋቶች ከመርዛማነቱ አንጻርና ከአለው ጥቅም አንጻር ሲታይ ፍቱንነቱ በስፋት የታየበት ነው። ደልበልንሳም እንዲሁ ከፍተኛ የኒውትሬሽን አቅም ያለው በመሆኑ ከብት ለማደለብ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተረጋግጧል። በተጨማሪነት ባክቴሪያዎችን ለመቆጣጠርም ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በተለይ የከብቶች መኖ ሲዘጋጅ መኖ ውስጥ ሲገባ በጣም ውጤታማ ጥቅም እንዳለው ማረጋገጥ መቻሉን አስታውቀዋል።
ፕሮፌሰሩ፤ ከባህላዊ ግልጋሎቱ ባለፈ በፋብሪካ ደረጃ ቢሰናዳ እና በጥቅም ላይ ቢውል እንደ ሀገር የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አመልክተዋል። በማኅበረሰቡ አጠራር ሰሳ የተሰኘው ዕፅዋትም ምንም እንኳን በጫካ የሚገኝና የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ችግርና ድርቅ በሚያጋጥምበት ጊዜ ከጫካ አምጥቶ የሚጠቀመው ቢሆንም ሁሌም ጥቅም ላይ መዋል ቢችል ያለው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ በምርምር መለየቱን አንስተዋል።
በተለይም ለጤና ተስማሚ ከመሆን አንጻር፣ ካለው ኒውትሪሽን አኳያና መርዛማነት የሌለው መሆኑ ሲታይ ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ መገንዘብ መቻሉን አንስተዋል። በተጨማሪም ምን ምን ውሕዶች በውስጡ አሉ የሚለውን በማየት ከሌሎች ምርቶች በተሻለ ሁኔታ አቅም እንዳላቸው ማየት መቻሉን አስረድተዋል።
በምርምርና የዲጂታላይዝድ ሥራው እስካሁን በአለው እንቅስቃሴ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በመጀመሪያው ዙር ዌብሳይት ዴቨሎፕ ተደርጎ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ኢንስቲትዩቱ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እንዲታወቅ የሚያስችልን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የዲጂታላይዝድ ሥራው የአንድ ጊዜ ተግባር እንዳልሆነ፤ በየጊዜው ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ካሣሁን፣ እስካሁን ባለው መረጃ በሙዚዬሙ ውስጥ በዕፅዋቶች ደረጃ ከ420 በላይ የተለያዩ ዕፅዋቶችና 11 የባህል አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ። ይህንን ከማጠናከር አንጻር ደግሞ በቀጣይ ከዞኑ ጋር በመተባበር ማዕከል ከፍቶ ለመሥራት መታሰቡን አስረድተዋልም።
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም