አዲስ አበባ፡- ከመርከቦች ግዢ ጋር ተያይዞ በሜቴክ ኃላፊዎች ላይ ዐቃቤ ህግ በመሰረተባቸው ክስ ተከሳሾች ያቀረቡት መቃወሚያ ላይ የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛው ወንጀል ችሎት ትናንት ብይን ሰጥቷል። ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ 12 የቀድሞ ሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ሁለት ግለሰቦች ከመርከቦች ግዢ፣ ጥገናና አስተዳደር ጋር ተያይዞ በተከሰሱበት ወንጀል ተከሳሾች ያቀረቡትን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ መርምሯል፡፡
ችሎቱ ተደራራቢ ክስ ሊቀርብብን አይገባም ብለው ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው እና ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል ያቀረቡትን መቃወሚያ ተቀብሎ ክሱ እንዲሻሻል ሲወስን፤ ቀሪዎቹ ህጋዊነት እንደሌላቸው ከህግና ከህጋዊ አግባቦች ጋር በማገናዘብ አስረድቶ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ ክሱ ገዝፎ ሊቀርብብን አይገባም፣ ስንሰራ የነበረው ወታደራዊ ትዕዛዝ ነው፣ ትክክል አይደለም ሲሉ የተቃወሙ ሲሆን፤ ችሎቱ በክሱ ተጠቅሶ የቀረበው 544 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የጉዳት መጠን ከፍተኛ መሆኑን እና ለጊዜው የሚታይበት ሁኔታ እንደሌለ በማብራራት እንዳልተቀበለው ጠቅሷል፡፡
ተከሳሾቹ ላይ ሶስት የተለያዩ ክሶች የቀረቡ ሲሆን፤ አንደኛው ክስ በመንግስትና በህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን በማለፍ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑ በክሱ መጠቀሱ ይታወሳል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ለመርከቦች ጥገናና አስተዳደር 544 ሚሊዮን 702ሺ 623 ብር በላይ የሚገመት ለፕሮጀክት የተመደበ ውስን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣት ለራሳቸውና ለሌሎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም በማግኘትና በማስገኘት መጠርጠራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ሊከላከሉት የሚገባቸውን የመንግስትና የህዝብ ጥቅም ያለአግባብ ጉዳት እንዳደረሱና ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው መርከቦቹ ወጪ ብቻ እያስወጡ ከቆዩ በኋላ ያለጨረታ አጭር ዝርዝር ወጥቶ እንዲሸጡ በማዘዝ መጠርጠራቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
መርከቦቹ ከተገዙበት ዋጋ 607 ሺ 432 ዶላር ከስረው እንዲሸጡ ማድረጋቸውና መንግስት ከውድድር ሊያገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳሳጡም የዘገብን ሲሆን፤ ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሶ 24 የሰውና 70 የሰነድ ምስክሮችን አቅርቧል። ዐቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎ ለሚያዝያ 13 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርብ አዟል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በዘላለም ግዛው