
በአገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ሰሞኑን የእውቅና፤ ሽልማትና ማዕረግ የማልበስ ሥነሥርዓት አካሂዷል። «እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም» በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ በምርጥ አዋጊ፣ በምርጥ ተዋጊ በአሃድና በግለሰብ፣ በውጊያ ድጋፍና የውጊያ አገልግሎት ዘርፍ፣ በስታፍ፣ በዩኒትና በግለሰብ ደረጃ 151 ግለሰቦችና ቡድኖች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። እኛም ከእነዚህ ተሸላሚዎች መካከል ጥቂቶቹን እናስተዋውቃችሁ።
1.መቶ አለቃ ዋሲሁን ፈጠነ፤ በምሥራቅ ዕዝ የ76ኛ ክፍለጦር አንደኛ ሬጅመንት የሕክምና ኃላፊ
በተለያዩ ግንባሮች ከፊት በመሰለፍ እና የቆሰሉ ጓዶች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም ማህበረሰቡን በማስተባበር እና ለቁስለኞች በፍጥነት በመለየት በአስቸኳይ እርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በአንድ ወቅት በድሬ ሮቃ አካባቢ በነበረ ውጊያ ቁስለኞችን በማከም ላይ ሳሉ በጠላት ኃይል ይከበባሉ። ነገር ግን ቁስለኛን ጥዬ ከምሄድ አብሬ እሞታለሁ በማለት ቁስለኞችን በመያዝ ለማዳን ከመዋከብ በተጨማሪ ከጠላት ጋር መሣሪያ ይዘው በመፋለም ካደሩ በኋላ በጥይት እሩምታ ውስጥ አምልጠው ቁስለኞችን ማውጣት ችለዋል።
በድሬ ሮቃ፤ ካሳጊታ፣ ሃይቅ እና ጭፍራ በነበሩ ውጊያዎች ላይ ከባድ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። ሁለት ጊዜ ቢቆስሉም ከጦርነቱ ሳይወጡ እዚያው ሕክምና በመውሰድ ጠላትን መፋለም የቻሉም ናቸው።
ሻለቃ አዛዣቸውና ምክትላቸው በቆሰሉበት ወቅት ኃላፊነቱን በመውሰድ ሻለቃዋን በመምራት ጠላት ክፍተት እንዳያገኝ የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።
በዞብል በነበረው ፈታኝ ውጊያ ከመከላከያው ጎን በመሆን ከሞራል ጀምሮ የሕክምና ድጋፍ በማድረግ የጀግንነት ሥራ ፈፅመዋል። በዚህና መሰል የጀግንነት ተግባራቸው የአንደኛ ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል።
2.ምክትል አስር አለቃ አንተነህ፡-77ኛ ክፍለጦር አንደኛ ሻለቃ ኦፕሬተር

ገና በለጋ ዕድሜው ውትድርናን የተቀላቀለው ወጣቱ ምክትል አስር አለቃ አንተነህ በተሰለፈባቸው ግንባሮች ሁሉ ከጓዶቹ ፊት በመገኘት ጠላትን ፊት ለፊት የተጋፈጠ ጀግና ነው። እኔ በሕይወት እያለሁ አገሬ በጠላት እጅ ወድቃ ማየት አልፈልግም በማለት፤ ሁለት ጊዜ ቢቆስልም ጓዶቹን ‹‹ጥዬ አልሄድም›› በማለት እዚያው ሕክምና በመውሰድ ወደጦር ግንባር የዘመተና ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ ጀብድ የፈፀመ ነው።
‹‹ለእዚህ ድል ያበቁኝ የተሰዉ ሰማእታት እና የቆሰሉ ጓዶቼ ይህ ሽልማት ይገባቸዋል ያለው›› ምክትል አስር አለቃ አንተነህ፤ ወደፊትም አገሩን በጀግንነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል።
እርሱ በመጀመሪያ የተመደበው በሬዲዮ ኦፕሬተርነት ነበር። ከዚያ የጠላት ኃይል እያየለ መምጣቱን ሲገነዘብ በሬዲዮ ማስተባበሩን በመተው ሬዲዮውን ከስሩ ለሚገኙ ጓዶች በመስጠት ከፊት ሆኖ ሊፋለም ብሬን ይዞ ጠላት መሃል ገብቷል። በዚህም በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ኪሳራ እንዲከናነቡ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ምክትል አስር አለቃ አንተነህ ቀደም ሲል የሰሜን ዕዝ ውስጥ ነበር። በወቅቱ ጠላት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈፅም በቀጥታ ወደ ኤርትራ በማፈግፈግ እና ከዚያም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመደራጀት መልሶ ማጥቃት በመሰንዘር በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ካደረሱ ጓዶች አንዱ ነው።
አዲአገራይ፣ ሰንሰለታማው የዞብል ተራራ፣ ኢዛና ተራራ እና ሌሎች አውደ ውጊያዎች ላይም በመሰለፍ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ነው።
3.ኮሎኔል አክሊሉ ጤቆ፡ በምሥራቅ ዕዝ የ76ኛ ክፍለጦር አዛዥ

ኮሎኔል አክሊሉ አሸባሪው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ የዕዙ አባል ነበሩ። ከዚያ ጁንታው በዚህ ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈጽም እነሱም ከጦራቸው ጋር ወደ ሱዳን ድንበር በማፈግፈግ ወደ ሽሬ አቅጣጫ እየተዋጉ ሄዱ። በወቅቱ የሻለቃ አዛዥ ነበሩ። ከዚያ በበረሃው ውስጥ ዳግም በመደራጀት እና ጥቃት በመሰንዘር ጠላትን ለመደምሰስ በተደረገው ውጊያ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በወቅቱ የእርሳቸው ሻለቃ በሱዳን በሁመራ አካባቢ ነበር። ጁንታውም እጃቸውን እንዲሰጡ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርግባቸው ነበር። እነርሱ ግን የወገን ጦር እስከሚደርስ ባለው ኃይል እየተከላከሉ በመዋጋት ከብዙ ፈተና በኋላ ወደ ማጥቃት ሊገቡ ችለዋል።
ከዚያ በሁመራ አካባቢ ተጨማሪ ኃይል ከተገኘ በኋላ በመጀመሪያ ወደሽራሮ፤ ከዚያ ወደሽሬ፤ ከዚያ ወደአድዋ ከዚያም ወደተምቤን እያሉ ጠላትን እግር በእግር እየተከታተሉ በማጥቃት ብዙ ጀብድ ፈጽመዋል። በተምቤን በተለይ አብአዲ በሚባል አካባቢ ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመሆን ጠላት አፍኖ የወሰዳቸውን ከአንድ ሺህ በላይ የወገን ጦር አባላት ለማስለቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ከዚያ መንግሥት ጦሩ ከትግራይ እንዲወጣ ሲያደርግ እነሱም በጭና በኩል ጥሰው በመግባት ወደ አማራ ክልል ገቡ። ከዚያም ካሳጊታ ላይ ለ22 ቀንና ሌሊት ከጠላት ጋር በመተናነቅ ከፍተኛ ጀብድ ፈጽመዋል።
በዚህ ስፍራ ጠላት ሚሌን ለመያዝ ያለ የሌለ ኃይሉን በማሰባሰብ ከፍተኛ ትግል ሲደረግ፤ ጦራቸው ከፍተኛ ትንቅንቅ አድርጓል።
ከዚያ በማጥቃት በባቲ በኩል ወደአፋር በመግባት ዞብልን ለመቆጣጠር ችለዋል። በዞብል ውጊያም ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ ጠላት ሙሉ ለሙሉ እንዲደመሰስ በማድረግ በኩል የኮሎኔል አክሊሉ አስተዋፅ ከፍተኛ ነበር።
4.ኮሎኔል ሰጥዬ አራጌ፡ የ23ኛ ክፍለጦር ዋና አዛዥ

ጁንታው የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ እሳቸው የብርጌድ አመራር ሆነው ሁመራ በሱዳንና ኤርትራ ድንበር አካባቢ በሚገኝ ስፍራ ነበሩ። በወቅቱ ጥቃት ሲፈፀም ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ በጀግንነት በመዋጋት ጦራቸውንና መሣሪያዎቻቸውን ሳያስነኩ ወደኋላ አፈግፍገዋል።
ከዚያም የተበታተኑ ሬጅመቶችን በማሰባሰብ ተመልሰው በማጥቃት ጠላት የዘረፈውን ንብረት ማስመለስ ችለዋል። በዚህ ውጊያም ለ11 ቀናት በማሽላ ማሳ እርሻ ውስጥ በመደበቅና ጥሬ ማሽላ በመብላት የወገን ጦር እስከሚደርስላቸው ድረስ ከፍተኛ ትንቅንቅ አድርገዋል።
በሽሬ አድርገው በአክሱም በመግባት በአድዋ፣ በተምቤን ጠላትን ተከታትሎ በማጥቃት አኩሪ ድል እንዲመዘገብ የመሩ አዋጊ መኮንንም ናቸው። በጁንታው ታፍነው የነበሩ 1536 ከፍተኛና መካከለኛ ወታደሮች ከጁንታው ማስለቀቅ በተቻለበት ውጊያም የእርሳቸው ሚና የላቀ ነበር። ጭና በነበረው ውጊያ እንዲሁ ጀብድ ፈፅመዋል።
ጁንታው በአፋር በኩል ሚሌን ለመቁረጥ በካሳጊታ ግንባር ባደረገው እልህ አስጨራሽ ውጊያ ለ22 ቀናት ቀንና ሌሊት ያለበቂ ውሃና ምግብ ጠላትን በመፋለም በጠላት ላይ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የጦር መሪም ናቸው።
እሳቸው የሚመሩት 23ኛ ክፍለጦር በወቅቱ በብርጋዴር ጄኔራል ሻምበል በየነ ይመራ ነበር። ኮሎኔል ሰጥዬ በርካታ ጀግና የጦር መኮንኖችንም በማፍራት ስኬታማ ነበሩ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም
ወርቁ ማሩ