
እስልምና በአምስት መሠረቶች ላይ የቆመ ነው። እነዚህም ፈጣሪን በብቸኝነት ማምለክ፤ ሰላትን መስገድ፤ የረመዳንን ጾም መጾም፤ ዘካ (ምጽዋት) ማውጣት፤ እና ሀጅ (ኃይማኖታዊ ጉዞ )መፈጸም የሚሉት ናቸው። ሙስሊሞች ከእነዚህ አምስት የእስልምና መሠረቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የሮመዳን ጾምን ጾመው ጨርሰዋል። የርህራሔ ፣ የደግነት ፣ የመረዳዳት እና የፍቅር ወር የሆነውን የሮመዳንን የጾም ጊዜ ሲጨርሱ የኢድ በአል ቦታውን ይረከባል። ኢድ የሮመዳን ጾም የፍቺ በዓል ነው፡፡
ሙስሊሞች ለአንድ ወር ያህል በትጋት ሲያከናውኑት የነበረውን የጾም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው። በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል። ዛሬ የሚከበረውም 1446ኛውን የኢድ በዓል እነዚህን እሴቶች ተላብሶ የሚከበር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የኢድ አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በጸጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች። ኢድን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት በክርስትና በዓላት ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ ኢትዮጵያዊ መገለጫችን ነው። ይኸው ልዩ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች በዘንድሮው 1446ኛው የኢድ በዓል ላይ ተጠናክረው የሚታዩ ይሆናል፡፡
ኢድ የስጦታ እና የመረዳዳት በዓል ነው። የኢድ በዓል ሲከበር ሰዎች ስጦታ በመለዋወጥ ፍቅርና አክብሮታቸውን ይገልጻሉ። እንኳን አደረሳችሁ ይባባላሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው። የእስልምና እምነት በኢድ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ለተቸገሩ ወጎኖች የሚደረግ ድጋፍ ዘካተል ፊጥር ይባላል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች በጋራ የሰላት ሥነሥርዓት ወደ ሚያካሂዱበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ለተቸገሩ ወገኖች የዘካተል ፊጥር ርዳታ ማድረግ ግዴታቸው ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በችግር ላይ ያሉ ወገኖች የኢድን በዓል እንደሌሎች ወገኖቻቸው ሁሉ በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው ነው፡፡
የኢድ እሴቶች ከሆኑት ውስጥ ሁሉም አማኝ በእኩል ስሜት በደስታ በዓሉን እንዲያሳልፍ ማስቻል ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይኸው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ሁኔታ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ነው ፤ በዛሬው የኢድ በዓልም ይኸው ተጠናክሮ ይቀጥላል። አሁን ባለው ሁኔታም ይህ የመረዳዳት ባህል እየተጠናከረ መጥቷል። የዘንድሮውም 1446ኛ ኢድ አልፈጥር በዓል እነዚህ እስላማዊ እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት ወቅት ይሆናል፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም 1446ኛውን ኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ከሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ጋር ቆይታ አድርጓል። እንደሚከተለው አቀናብረነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የረመዳን የጾም ወቅት እንዴት አለፈ ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- የዘንድሮ ረመዳን ለየት ያለ ነበር። ለየት ያደረገውም ሰላም የሰፈነበት አንድነትን ያጠናከረ ፣ በግጭት ውስጥ የነበሩ ክልልች ወደ ሰላም የመጡበት ወር ነው። የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች ለዘመናት እርስ በእርስ ሲጋጩ የቆዩ ናቸው። በዚህም የበርካቶች ደም ፈሷል፤ ሕይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረት ወድሟል። ይህ ታሪክ ግን በዚህ ረመዳን ተቋጭቷል፡፡
የጥላቻ ደመና ተገፎ የፍቅር፤ የአንድነት እና የወንድማማችነት በር ተከፍቷል። በዚህ ረመዳን አፋሮች ወደ ሶማሌ ክልል ሄደው አፍጥረዋል። በተመሳሳይም ሶማሌዎችም ፕሬዚደንታቸውን ጨምረው፤ ሱልጣኖች፣ ኡጋዞች ኡለማዎች ወደ አፋር ክልል በመሄድ አብረው አፍጥረዋል። ረመዳንን በጋራ አሳልፈዋል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ክልሎች ሰላም ሰፍኗል። ይህ እንግዲህ ከረመዳን በረከቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ወደ ኃይማኖታዊ ክንውኑ ስንመጣ ደግሞ በረመዳን መስጂዶቻችን ደምቀው ጾሙን አሳልፈዋል። አቅም ያላቸው አቅም ለሌላቸው ሲያስፈጥሩ እና ያላቸውን ሲያካፍሉ የቆዩበት ወቅት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢድ ማለት ምን ማለት ነው ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- -ኢድ ማለት በዓረብኛ ተመላላሽ ማለት ነው። በየአመቱ ተመላልሶ የሚመጣ ማለት ነው። ኢድ የተከበረ ቀን ነው፣ በየአመቱም ተመላልሶ ይመጣል። ይሄ ቀን ታሪክ አለው። ነብዩ መሃመድ መዲና ሲገቡ እምነት አልባ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ እምነት አልባ ሰዎች በአመት ውስጥ ሁለት በዓላትን ያከብሩ ነበር። እነዚህ የክብረ በዓላት ቀናት ለጨዋታ እና ለጭፈራ ብቻ ነበር የሚያውሏቸው። ከጨዋታ እና ጭፈራ ውጭ ቁም ነገር አልነበራቸውም፡፡
ነብዩ መሃመድ መዲና ሲገቡ አላህ በራሱ ፈቃድ በቁርዓን አማካኝነት ትዕዛዝ አስተላልፎላቸው ነበር። እነዚህ በጭፈራ እና በዳንኪራ ያልፉ የነበሩ በዓላትን ወደ ምስጋና እና ኃይማኖታዊ በዓል እንዲለወጡ አላህ በመፍቀዱ ኢድ አልፈጥር እና ኢድ አልአድሃ በሚል ሁለት በእስልምና የተከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት ለመሆን ቻሉ። እነዚህም በአላት የፍቅር፣ የአንድነት ፣ የአብሮነት እና የመረዳዳት በዓላት በመሆን ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል፡፡
ኢድ የደስታ በዓል ነው። ኢድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል በመሆኑ በጾም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለስበትና ይህንኑም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው።
እኔም ለመላው ሙስሊሞች 1446ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የሰላም፣ አንድነት፣ የደስታ እና የፍቅር እንዲሆንላቸው እመኛለሁ። በዓሉን ስናከብርም አቅም ያጡ ወገኖችን በመደገፍ፣ ወላጅ አልባ ህጻናትን በማልበስ፣ ታመው ሆስፒታል የተኙ ዜጎችን በመጎብኘት ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ በአጠቃላይ መልካም ነገሮችን በመፈጸም ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢድ በዓል አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ የተለያዩ ምጽዋቶች ይሰጣሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ማብራርያ ቢሰጡን ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- በረመዳን እና በኢድ ወቅት አቅም የሌላቸው ወገኞች እንዳይቸገሩ በማሰብ የሚፈጸሙ ሁለት አይነት የምጽዋት አይነቶች አሉ። ዘካተል ፊጥር እና ዘካለተል ማል በመባል ይታወቃሉ፡፡
ዘካተል ፊጥር ማለት ማንኛውም ሙስሊም የረመዷንን ወር ደርሶ የዒድ ሌሊትን ያገኘ የሆነ ሰው ለድሆች ሊሰጠው የሚገባ የተመጠነ የምግብ አይነት ነው። ዑመር ዘካተል ፊጥር በረመዳን ወቅት ፆመኞች ፆመው ከማጠናቀቃቸው በፊት የሚሰጥ ነው። ዘካተል ፊጥር አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ በፆም ወቅት ፆሙን የሚያጎሉበት ስህተት ቢፈጽም ያን ስህተት ለማስፋቅ እና ጾሙን ሙሉ ለማድረግ የሚሰጥ ስጦታ ነው። ሥጦታው ደግሞ ለምስኪኖች እና ለጾም አዳሪዎች ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰው ካለው ነገር ላይ እንዲሠጥ ተወስኗል። የስጦታው መጠንም በመካከለኛ እድሜ ባለ ሰው እፍኝ አምስት ወይም ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ነገር እንዲሰጥ የነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ተከታዮች ወስነዋል። ዘካ ግዴታ ነው፤ ማንኛውም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ሊያወጣው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
ዘካተል ፊጥር እንደሚሰጠው ስጦታ የሚሠጥበት ቀን ይለያያል። የሚሠጠው ነገር ወደ ምግብነት ያልተቀየረ ከሆነ ተቀባዩ የተቀበለውን ነገር ወደ ምግብነት ቀይሮ እንዲጠቀም ከአንድና ከሁለት ቀን ቀድሞ መሠጠት አለበት። የሚሠጠው ደግሞ የኢድ ሶላት ተሰግዶ ከማለቁ በፊት ነው። ከዚህ ካለፈ ምጽዋት ተደርጎ የሚቆጠር ይሆናል። ዘካተል ፊጥር ተሚር፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘቢብ እና ሌሎች ለምግብነት የሚያገለግሉ የእህል ዘሮች ሊሆኑ ይችላል። የእህል ዓይነት መስጠት ያልቻለ በገንዘብ ተምኖ መስጠት ይችላል፡፡
ሁለተኛው አይነት ምጽዋት ደግሞ ዘካተል ማል ይባላል። ዘካተል ማል በዓመት አንድ ጊዜ የሚሰጥ አቅም
ያላቸው ሰዎች የሚሰጡት ምጽዋት ነው። አቅም ያላቸው ወገኖች ከፍ ያለ ገንዘብ ለድሆች የሚያከፋፍሉበት ሥርዓት ሲሆን ይህም ሰዎች ከተራዘመ ተመጽዋችነት ወጥተው ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው። ይህ ደግሞ ተረጂነትን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል ነው። ስለዚህም የዘንድሮውን 1446ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ስናከብር እነዚህን ኢድ እሴቶች ከግምት ውስጥ በማስባት ሊሆን ይገባል፡፡
በተጨማሪም ማኅበረሰቡ በበዓል ወቅት ከመረዳዳት ባሻገር ሀገራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በጋራ መቆምም ይጠበቅበታል። ሰዎች በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲራቡና ሲጠሙ ዝም ብሎ መመልከት ከእስልምና አስተምሮ አንጻር የሚያስጠይቅ ነው፡፡
በተለይም ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት በአንዳንድ አካካቢዎች ባሉ ግጭቶች ለችግር የተዳረጉ ዜጎች በርካቶች ናቸው። በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህም የኢድ አልፈጥርን በዓልን ስናከብር እነዚህን ወገኖች በመጎብኝነትና ወገናዊ ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል፡፡
አሁን አሁን የድሆችን ቤት በማደስ፣ ማዕድ በማጋራት የተጀመሩ ሥራዎች የሚያስደስቱ ናቸው። እስልምና በጣም የሚደግፋቸውና አብዝቶም የሚሠራባቸው ናቸው። ወቅቱ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ መረዳዳት የሚያስፈልግበት በመሆኑ ለተቸገሩ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎች ማድረስ የግድ ይላል፡፡
በእርግጥ በአሁኑ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና የድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው። በየአመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው፡፡
በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው። በተለይም በበዓላት ወቅት አቅመ ደካሞች በዓላትን በእኩል ተደስተው እንዲሳልፉ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በበዓላት ወቅት ኢትዮጵያውያን ኃይማኖት ሳይገድባቸው አንድነታቸው ጠንክሮ ይታያል። ዘንድሮስ ምን ይመስላል?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፣ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የተላበሱ ሕዝቦች ናቸው። በርሃብም ሆነ በድርቅ፣ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ። የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፣ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፣ በልማት ይሳተፋሉ፣ ሀገራቸው ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ዘር ፣ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፣ የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባሕር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው፣ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሃመድ ተከታዮችንና ቤተሰቦችን ተቀብላ በማስተናገድና በማኖር የጎላ ታሪክ ያላትና ለእስልምና ኃይማኖትም ባለውለታ ተደርጋ የምትቆጠር ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህ አኩሪ ታሪክ ሺህ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተቀብላ በእንክብካቤ የምታስተናግድ ሀገር ነች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የኢፍጣር (ጾመኞችን የማብላት) መርሃ ግብሮችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱና ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የሶማሌ፣ የሶርያ፣ የየመንና የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግሥታቸው ድረስ ጠርተው አስፈጥረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ቤተመንግሥት ድረስ ጋብዞ ማስፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ በጎ ተግባር ነው። በዚህ ተግባራቸውም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን እንግዶችን የመቀበል ታሪክ አስቀጥለዋል፡፡
ከ98 በመቶ በላይ አማኝ የሆነው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን በማካፈል ያምናል። ሰዎች ሲቸገሩ የሚጨክን አንጀት የለውም። ከመሶቡ ቆርሶ፤ ከኪሱ ቀንሶ ያለውን ይሰጣል። የእርሱ ቤት ደምቆ የጎረቤቱ እንዲቀዘቅዝ አይፈቅድም። ይህም አኩሪ ባህል ኢትዮጵያውያን በችግር እንዳይንበረከኩና ችግርን ድል አድርገው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡
ይህ የመተሳሰብ ፣የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴትም በዘንድሮው የኢድ በዓል ዋዜማዎች ጀምሮ በጉልህ ታይቷል። የክርስትና እምነት ተከታዮች የመስገጃ ቦታዎችን በማጽዳት አብሮነታቸውን አሳይተዋል። በተመሳሳይም ሙስሊሞች የክርስትና እምነት በአላት ሲመጡ አደባባዮችን በማጽዳት ጭምር አጋርነታቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል። ይህ አኩሪ ታሪክ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በመከባበር እየኖሩ ነው። ሁሉም ዜጋ መብቱ ተከብሮለት ፣ አንዱ አንዱን እምነት፣ ባህል እና እሴት በማክበር አንድነታቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖቶችን ተቀብላ ያስተናገደችና ለዘመናትም በመከባበር ላይ እንዲኖሩ ያደረገች ሀገር ናት። በዚህ ረገድ እርስዎ ምን ይላሉ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፣ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የተላበሱ ሕዝቦች ናቸው። በርሃብም ሆነ በድርቅ፣ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ። የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፣ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፣ በልማት ይሳተፋሉ፣ ሀገራቸው ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ዘር ፣ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፣ የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባሕር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው፣ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሃመድ ተከታዮችንና ቤተሰቦችን ተቀብላ በማስተናገድና በማኖርና የጎላ ታሪክ ያላትና ለእስልምና ኃይማኖትም ባለውለታ ተደርጋ የምትቆጠር ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህ አኩሪ ታሪክ ሺህ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተቀብላ በእንክብካቤ የምታስተናግድ ሀገር ነች፡፡
ሀገሪቱ ውስጥ አይሁድ ነበሩ አሁንም አሉ ይባላል፤ ክርስትናም ቀድሞ የነበረ ሲሆን እስላም ደግሞ ከአንድ ሺህ አራት መቶ አርባ አራት አመተ ሂጀራ በፊት ነበረ የመጣው። እንግዲህ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ሃይማኖቶች አብረው ኖረዋል። በእርግጥ አብረው ይኑሩ እንጂ የሚበላለጡ ነገሮች ነበሩ። መንግሥታት ሲቀያየሩ ከፍና ዝቅ የሚያስበሉ ነገሮች ነበሩ። ሕዝብ እንደ ሕዝብ ግን በአብሮነት ተቻችሎ ተከባብሮ አብሮ መአድ ቆርሰው አብረው ኖረዋል። አሁን ግን በሀገራችን ሃይማኖቶች እኩል መብት አግኝተዋል ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም በጋራ በመሆን የሃይማኖቶች ጉባኤ ላይ አብረን እየሠራን ነው።
ሕዝቡ የእስልምና ሃይማኖት በዓል ሲመጣ እንደ አንድ ሰው ሆኖ በአብሮነት ተከባብሮ ተደጋግፎ መአድ የሚቆርስበት ሁኔታ ነው ያለው። ሀገራችን በዚህ ረገድ የዓለም ምሳሌ የምትሆን ሀገር ናት። ሕዝቡ ውስጥ ያለው መከባበርና መቻቻል በየትኛውም ሀገር የሚታይ አይደለም። ሕዝቡ ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ ማስቀጠል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- የቀደሙ የሀገር እሴቶችን አስከብሮ ከማስቀጠል አንፃር ከሕዝበ ሙስሊሙ ምን ይጠበቃል?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- እኛ ለሕዝበ ሙስሊሙ እያስተላለፍን ያለው መልእክት ሀገራችን በተለይም በዚህ ጊዜ ሁሉም የሃይማኖት አባል ችግሩንም ደስታውን በጋራ እየተቀበለበት ያለበት ሁኔታ መኖሩን ነው። ሁላችንም የግል ሃይማኖት ቢኖረንም ሀገራችን ግን አንድ ናት፤ ይህችን ሀገር ደግሞ ሰላሟን መጠበቅ፤ ልማቷን ማስቀጠል፤ ከዚህ በፊት ይዘነው የመጣነውን የአብሮነት ባህል ማሳደግ ይኖርብናል።
ከበፊቱ የበለጠ መቻቻል ከሚለው እሳቤ ወጥተን መደጋገፍና መተባበር መፈቃቀር ሕዝቡ መገለጫው እንዲሆን መሥራት ይኖርብናል። የነበረንን እሴት አሳድገን እጅ ለእጅ ተያይዘን ማደግ ማለፍ ይኖርብናል። በዓሉ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ያለው ለሌለው ያካፍልበታል፤ ያግዝበታል፤ የፈጣሪውን ትዕዛዝ ይፈጽምበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ስለሰላም እና አንድነት የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- እንደ ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፕሬዚደንትነቴ ማስተላለፍ የምፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ሙስሊሙ ህብረተሰብ አንድነቱን ጠብቆ እና ከሌሎች የኃይማኖት ተከታዮች ካር ተከባብሮ እና ተዋዶ እንዲኖር በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር እንደመሆኗ ሰላሟንም መጠበቅ ያለብን ሁላችንም ነን። በዚህ ረገድ እንደምክር ቤት እየሠራናቸው ያሉ ሥራዎች አሉ፣ ውጤትም እየተገኘባቸው ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እምነቱ ተከብሮለት እና ባህሉ ታውቆለት በሰላም እየኖረ ነው። በኃይማኖቶች መካከል መከባበር ይታያል፣ የጋራ ሀገራችንን በጋራ የማልማት እና የመተባበር ባህል ዳብሯል። ይሄንን አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል፡፡
ሌላኛው የማስተላልፈው መልዕክት ስሰላም ሁሉም ዜጋ ሊገነዘብ ይገባል። ሰላም ሲኖር ነው ሁሉም ነገር መኖር የሚችለው። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት የሰላምን ጉዳይ ዋነኛ ሥራው አድርጎ ይዞታል። ስለሰላም መስበክ ብቻ ሳይሆን ሰላም እንዲረጋገጥም የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው። በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ወርደን ሰላም ለማምጣት እየሠራን ነው።
ችግር በአለበት ቦታ ሁሉ በጀት መድበን እየተንቀሳቀስን ነው። በዚህም ከላይ እንደጠቀስኩት ለዓመታት በግጭጥ ውስጥ የነበሩትን የአፋር እና ሱማሌ ክልሎችን በማስማማት ወደ ሰላም መልሰናል። ይሄ ደግሞ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፡፡
በመጨረሻ የማስተላልፈው ቁም ነገር ሙስሊሙ ህብረተሰብም ሆነ የሌሎች እምነት ተከታዮች የሀገራቸውን ሰላም እንዲጠብቁ አደራ እላለሁ። አብሮ መኖርም ሆነ ኃይማኖትን በአግባቡ ማከናወን የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ሰላማችንን ከጠበቅን ሀገራችንን ማሳደግ እና ልማታችንን ማፋጠን እንችላለን፡ ሁሉም ዜጋ ሀገሩን ሰላም እንዲጠብቅ አደራ እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም