ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ምግብ ነው። ምግባችንን በአይነት በአይነቱ አጣፍጠን ለመመገብ ዘይት ዋነኛው ግብዓት ይሆናል። ሰሞኑን በአገራችን ዘይት መሰረታዊ ፍላጎት መሆኑ ቀርቶ የቅንጦት ምግብ ሊሆን ዳር ዳር እያለ መሆኑን እንመለከታለን።
ከሦስት መቶ ብር ቀስ በቀስ አንድ ሺህ ብር የደረሰው ዘይት ሕዝቡን እያነጋገረ ይገኛል። ስለዚህ ጉዳይ የሸማቹን ሀሳብ ለመመልከት በወጣንበት ወቅት ገበያ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፍሬህይወት አሰፋ ዘይት ከመወደዱም በላይ በየሱቁ የለም የሚባለው ነገር እያስገረማቸው መሆኑን ይናገራሉ። አገራችን የተለያዩ የቅባት እህሎች አምራች ሆና ሳለ ዘይት እንደችግር መነሳቱ አሳዝኗቸዋል። የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾች ዘይት ማምረት ትተዋል እንዴ? ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሰሜነህ ተከተል ናቸው። በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልጓም ያጣው የኑሮ ውድነት እንደሚያሳስባቸው ገልፀው አሁን ደግሞ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በእጥፍ የጨመረው የዘይት ጉዳይ እጅግ አስገርሟቸዋል።
ቀደም ሲል ከቅባት እህሎች በአነስተኛ መጠን ዘይት አምራቾች ያቀርቡ የነበሩት የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾችን ከገበያ ወጥተው ከውጪ በሚገባ ዘይት ላይ መንጠልጠላችን የአለም ኢኮኖሚ ወጣ ገባ ባለ ቁጥር አብረን እንድንዋዥቅ አድርጎናል ሲሉ ይናገራሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ቢበረታቱ መልካም ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቱን የዘይት ፍላጎት በግማሽ ይሸፍናሉ ተብለው የተከፈቱ ግዙፍ የዘይት ፋብሪካዎች አገራችን ውስጥ ኖረው ዘይት በዚህ ልክ መወደዱ ምክንያቱ ምን ይሆን ብለው ይጠይቃሉ።
ይህን ጥያቄ ይዘን ዘይት በማምረት ሥራ ላይ ከተሰማሩት ባለሃብት አንዱ ወደሆኑት የበላይነህ ክንዴ ፊቤላ ኢንዱስትያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስልክ ደውለን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ሰጠኝ እንግዳውን አነጋግረናቸዋል።
አቶ ሰጠኝ እንደሚሉት፤ ፋብሪካው ለሰባት ክልሎችና ለአንድ ከተማ አስተዳደር ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከክልል ቢሮዎች ጋር በመሆን መንግስት ባስቀመጠው ኮታ መሰረት በዝቅተኛ ዋጋ ዘይት ለገበያ እያቀረበ ነው። ምርቱንም ሠላሳ አንድ አከፋፋዮች ከፋብሪካው ተረክበው የሚያከፋፍሉ ሲሆን በየክልሉ ቁጥራቸው የሚለያይና ከአንድ እስከ ስምንት የሚደርሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ክልሎቹም ዘይቱን ከአከፋፋዮች ተቀብለው ለየወረዳው በማዳረስ ተጠቃሚው በቅናሽ ዋጋ ዘይት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ። ለሕዝቡ እየቀረበ የሚገኘው ዘይት የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር 82 ብር ከ15 ሳንቲም ሲሆን እስካሁን ድረስም ስልሳ ስድስት ሚሊዮን ሊትር ዘይት በፋብሪካው ተመርቶ ለክልሎች ተሰራጭቷል፤ አሁንም በመሰራጨት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ ።
በዘይት ዙሪያ ሰሞኑን የሚነሱ ቅሬታዎችንም እየሰሙ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰጠኝ ፋብሪካው ያመርታል የተባለውን ያህል ምርት አምርቶ የተጠቃሚውን ፍላጎት እንዳያሟላ በሙሉ አቅሙ እያመረተ አይደለም ይላሉ። ለዚህም በምክንያትነት ያቀረቡት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ለማምረት 10 ኪሎ ዋት ኃይል የሚያስፈልገው ቢሆንም አሁን ግን አራት ኪሎ ዋት ኃይል ብቻ ነው ያገኘው። ፋብሪካው በስሩ ስምንት ፋብሪካዎችን ይዞ እንደመንቀሳቀሱ የኃይል ማነስ በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ እንቅፋት እንደሆነበት አብራርተዋል። ፊቤላ ሲመሰረት በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም ቢኖረውም በኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በድፍድፍ የፓልም ዘይት ዋጋ በየጊዜው መጨመርና ሌሎች ለፋብሪካው የሚያሥፈልጉ ግብዓቶች በመወደዳቸው በአሁኑ ሰዓት ካለው የማምረት አቅም በ50 በመቶ ብቻ እያመረተ እንዲቀጥል መገደዱን ነው ያስታወቁት።
ከውጭ የሚገባውን የፓልም ዘይት ድፍድፍ ለማስገባት በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪ አለመገኘቱም ለሥራቸው ማነቆ መሆኑን አስረድተው፤ መንግስት በየዙሩ በፈቀደው የውጭ ምንዛሬ 20 ሺህ ቶን ገዝቶ በማምጣት አጣርቶ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ያስረዳሉ። ከአንድ አመት በፊት የምግብ ዘይት ማምረት የጀመረው ፋብሪካ ባሳለፍነው አንድ አመት በአምስት ዙር አንድ መቶ አምስት ሺህ /105ሺህ/ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከ66 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት አጣርቶ ለገበያ አቅርቧል።
አቶ ሰጠኝ እንዳሉት፤ ፋብሪካው ተቋቁሞ ምርት ማምረት ሲጀምር አለም ላይ የነበረው የአንድ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ዋጋ 762 ነጥብ 50 ዶላር የነበረ ሲሆን በወቅቱ በፋብሪካው የሚመረተው አንድ ሊትር ዘይት በ40 ብር ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል። ይሁንና ባለፉት ወራት አለም ላይ የድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ ምክንያት ናቸው የተባሉት ደግሞ የኮቪድ 19 መስፋፋት፣ አለም ላይ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሎጅስቲክስ አቅርቦት ችግር እንዲሁም በዩክሬንና በራሽያ መካከል ያለው ግጭት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ፋብሪካው ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት እየገዛ አጣርቶ ለገበያ ለማቅረብ በአራተኛ ዙር አንድ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት 1ሺህ362 ዶላር ገዝቶ እንደነበረ አስታውሰው በአምስተኛ ዙር አንድ ሜትሪክ ቶን የድፍድፍ ፓልም የምግብ ዘይት 1ሺህ407 ዶላር መግዛቱን ነው የተናገሩት።
ይሁንና ይህ የዋጋ ጭማሪ ፊቤላ በአራተኛ ዙር ከገዛበት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ቢሆንም በዘይት ገበያ እና በዜጎች ኑሮ ላይ ሊያሥከትል የሚችለውን ጫና በመረዳት ድርጅቱ በአራተኛ ዙር ባመጣበት ዋጋ በአምስተኛ ዙር ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ሳያደርግ ለገበያ ለማቅረብ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፈቃደኝነቱን በመግለጽ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በማሰራጨት ላይ ይገኛል።
በዚህም መሰረት የአምስተኛ ዙር የፋብሪካ ብር የመሸጫ ዋጋ ከየካቲት ወር ጀምሮ ባለ 5 ሊትር 425ብር ከ63 ሣንቲም፤ ባለ 20 ሊትር 1ሺህ 640 ብር ከ72 ሣንቲም፤ ባለ 25 ሊትር 2050 ብር ከ15 ሣንቲም መሆኑን ያብራራሉ።
ሌላው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የሱፍ ዘይት ምርት ባለማግኘቱ እስካሁን ፋብሪካዎቹ ይሄንን ማምረት እንዳልቻሉ የሚናገሩት አቶ ሰጠኝ ፓልም ላይ ያለው ሁኔታም ችግሩን መጠነ ሰፊ አድርጎታል ብለዋል። አለም ላይ በሱፍ ዘይት አምራች ዩክሬንና ሩሲያ በመሆናቸው ችግሩ እነዚህ አገራት ከገቡበት ጦርነት እስካልወጡ ድረስ መፍትሄ ሊያገኝ እንደማይችል አስታውቀዋል።
ለስድስተኛ ዙር የሚሆን ወደ 25 ሺህ ሜትሪክ ቶን የፓልም ዘይት ማምረቻ ግብዓት መገዛቱን የጠቀሱት አቶ ሰጠኝ እሱም በ10 ቀናት ውስጥ ተጓጉዞና ተጣርቶ ለገበያ ይቀርባል። ይሄ በእንዲህ እንዳለ ግን ፋብሪካው የሚያስፈልገውን ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ያደረገው እንቅስቃሴ እንዳልተሳካለት አብራርተዋል።
እንደ አቶ ሰጠኝ ገለፃ፤ ፋብሪካው ግብዓቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ራሱን ሊችል አስቦ ተንቀሳቅሶ ነበር። ሆኖም ግን በቤኒሻንጉል እያሰራው የነበረው ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል። ይሄ ለወደፊት በስፋት ሊሰራ ላሰበው ሥራ ጫና እንደሚሆንበት አስረድተዋል። የመብራት ኃይል ማጣት፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ የዓለም የፓልም ዘይት የድፍድፍ ዋጋ በየጊዜው መጨመር ፋብሪካው በራሱ አቅም እንዳያመርት ያደረጉት ምክንያቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት ።
ከኅብረተሰቡም ሆነ ከፋብሪካው የተነሱትን ሀሳብና አስተያየቶች ይዘን ያመራነው ወደ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው። ለጥያቄያችን ምላሽ የሰጡን በሚንስቴሩ የንግድና ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ መስከረም ባሕሩ እንዳሉት፤ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ፊቤላን ጨምሮ ተመሳሳይ ችግሮችን ያነሳሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር የመነጋገርና የማስተካከል ሥራዎች እየሰራን ነው። ይህ ማለት ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለማስተካከል ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ በያዝነው በጀት አመት ለዘይት ብቻ ተብሎ የተያዘው የውጭ ምንዛሪ ወደ 397 ሚሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ መካከልም 145 ነጥብ 9 ሚሊየን የሚሆነው ለፊቤላ የተመደበ ነው ።
በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚታወቅ ሲሆን ይህም በእቅድ የሚመራ መሆኑን ጠቅሰው ካለው ሀብት አንፃር በመታየት በጥናት ላይ የተመረኮዘ ድልድል የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ የተመደበው የውጭ ምንዛሬ በጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ምርቶች በወቅቱ እንዲደርስ ለማድረግ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዘረፉ ከተመደበው 397 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የፓልም ድፍድፍ ዘይት የሚያስገቡ ተብለው የተመረጡ ስድስት ፋብሪካዎች ሲሆን ከእነዚህ መካከል 154 ነጥብ 9 ለፊቤላ፤ ለሸሙ 138 ነጥብ 6 ሚሊዮን፤ ለሀማሪሳ 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን፤ ለአልምፒክስ 53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር፤ ደበሊው ኤ ለሚባል ፋብሪካ ወደ 48 ሚለዮን ዶላር መመድቡን ገልፀዋል። ግብዓት የማስመጣት ሂደቱም እንደየ ፋብሪካዎቹ በፍጥነት የሚሄድና የሚቀንስበት ሁኔታ አለ።
ፋብሪካዎቹም የተለያዩ ግብዓቶችን ከማግኘት አንፃር የራሳቸውን ጥረት ማድረግ የሚኖርባቸው መሆኑን ጠቅሰው ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚሰራበት አግባብ እንዲኖር አማራጮችን መመልከት የሚገባቸው መሆኑን አንስተዋል።
ፊቤላ አግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በራሱ ለማምረት ሞክሮ አሁን በአገሪቱ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ቢስተጓጎልበትም እንደ አገር ከተሰራ ያለምንም የውጭ ምንዛሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ማምረት የሚቻል መሆኑን ጠቁመዋል። በጣም ትልልቅ የማምረት አቅም ያላቸው ፋብሪካዎች በየክልሉ ማቆም መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ መስከረም በአጭር ጊዜ ውስጥ የቅባት እህሎች ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚመረትበት ሁኔታ ቢኖር አሁን በአገራችን ያሉ ችግሮች ሁሉ እንደማይኖሩ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም አብዛኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ስንዴ ከውጭ የሚገባ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ ግን በአገር ውስጥ የበጋ ስንዴ በብዛትና በጥራት በማምረት ከውጪ የሚገባውን የመቀነስ ሥራ ለመስራት ተችሏል። በተመሳሳይ የቅባት እህሎች ላይ በስፋት ከተሰራበት ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ ሳያስፈልጋቸው በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚቻል መሆኑን አብራርተዋል።
ሁሉንም ኃላፊነት ወደ መንግስት ከመግፋት ይልቅ ሁሉም በየደረጃው ማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች ቢሞክር በጋራ ችግሮች የሚቀረፉ መሆኑን አሳስበዋል። ቀደም ባሉ ጊዜያቶች ለጤና ተስማሚ የነበሩ የቅባት እህል ዘይቶች በአገራችን ይመሩት የነበረበትን ጊዜ በማሰብ አሁንም የውጭ ገበያ ላይ መንጠልጠላችንን አቁመን አሁን በስፋት ለተተከሉት ፋብሪካዎቻችን ግብዓት የሚሆን ምርት ወደ ማምረቱ ብንገባ በአናት በአናቱ እየተደራረበ ያለውን ችግሮቻችን ለመቅረፍ የመፍትሄ ሀሳብ ሊሆን ይችላል።
በአገር ውስጥ ለተከሰተው የዘይት ዋጋ መናርና የምርት እጥረት ዋናውና አንዱ ምክንያት በዓለም ላይ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሠራተኞች በቤታቸው በመቀመጣቸው እንዲሁም የሰው ኃይሉ በሞት በመጎዳቱ ምክንያት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ባለመቻላቸው የተፈጠረ የምርት ማነስ ነው። እንዲሁም በዓለም ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በአገር ውስጥ ካለው ሰው ሰራሽ ችግር ጋር ተዳምሮ ነው።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም