«ከፈተና ወደ ልዕልና፤» እንዴት… !?
የብልጽግናም ሆነ የሌሎች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠናክሮ መውጣት ፋይዳው ለአገርና ለሕዝብ ሲሆን፤ በተቃራኒው የጠራ መስመር ከሌላቸው፣ በብልሹ አሠራር ከተተበተቡ፣ ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ የግል ወይም የቡድን ጥቅም የሚያስቀድሙ ከሆነ፤ በኢዴሞክራሲያዊነት፣ በስሜትና በግዕብታዊነት የሚነዱ ከሆነ እንደ ሕወሓት/ኢህአዴግ፣ ኢሰፓ፣ ኢህአፓና ሌሎች አገርን ለሁለንተናዊ አደጋ ስለሚዳርጉ በቅርብ በመከታተል ሲጠናከሩ ማበረታታት፤ ሲደክሙ ደግሞ ችግራቸውን ነቅሶ ማሳየትና መደገፍ ለአባላቱ ብቻ የሚተው ጉዳይ መሆን ስለሌለበት ከታዛቢነት ወይም ከዳር ቆሞ ተመልካችነት ወጥቶ በንቃት መሳተፍ ይገባል። የእኔም ትችት ማለትም በአዎንታም በአሉታም ከዚህ ቅን ሀሳብ የመነጨ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ። ወደ ሰሞነኛው የብልጽግና 1ኛ ጉባኤ ልመለስ፡-
አገራችን በዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እየተፍገመገመች ትገኛለች። ለዚያውም በታሪኳ አይታቸውም ሆነ ሰምታቸው በማታውቃቸው ፈተናዎች። ላለፉት 50 አመታት ሲቀነቀን የኖረው የማንነት ፖለቲካ ያነበረው ጥላቻ፣ ልዩነት፣ መጠራጠር፣ አክራሪ ጎሰኝነት፣ የደባ ፖለቲካ፣ የተፈጥሮ ሀብት ብሔርተኝነት /resource nationalism/ የመጀመሪያው ሲሆን፤ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባትና በመረጡት አካባቢ ተዘዋውሮ ሰርቶና ሀብት አፍርቶ የመኖር መብት መጣሱ ዜጎችን ለሞት ለመፈናቀልና ለዘረፋ መዳረጉ ሌላው ፈተና ነው። ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ቡችሎቻቸው (ሕወሓት፣ ሸኔና ሌሎችም) በአገራችን ህልውና ላይ የደቀኑት አደጋ ሦስተኛው ፈተና ነው። ከወረዳ እስከ ፌዴራል የተንሰራፋው ስር የሰደደና የገነገነ ሙስናም ሌላው ትልቁ የአገር ህልውና ፈተና ነው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ከኢኮኖሚያዊ ችግር አልፎ ወደ ደህንነትና የጸጥታ ችግርነት የማደግ አደጋ መኖሩ ከባድ ፈተና ነው። በግብይት ሥርዓቱ የሚስተዋለው ሥርዓት አልበኝነት በአናቱ ተጨምሮ ወደለየለት ቀውስ እያንደረደረው ይገኛል። ከአገሪቱ ሕዝብ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት በሆነበት አገር የሥራ አጥነት ችግር የብልጽግናም የአገርም ፈተና ነው። እየተሰራፋ የመጣው ድህነትና የነፍስ ወከፍ ገቢ ባለበት መርገጥና በድሃው ሕዝብ ማዕድና ኑሮ አለመገለጡ ሌላው አሳሳቢ ፈተና ነው። ከታላቁ የህዳሴ ግድብና ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ የተከፈተው ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲሁ አገራዊ ፈተና ነው። እንግዲህ ገዢው ፓርቲ ብልጽግና እነዚህንና ሌሎች እንደ አሸዋ የበዙና ሲንከባለሉ የመጡ ፈተናዎችን ነው ወደ ልዕልና እቀይራለሁ ያለው።
ልብ አድርጉ ፈተናዎችን አልፋለሁ ወይም እሻገራለሁ ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ከፍታና የላቀ ስኬት እለውጣቸዋለሁ በማለት ነው 1ኛ ጉባኤውን በማካሄድ የተጠናቀቀው። ከፈተና ወደ ልዕልና ለመሸጋገር ግልጽ ፍኖተ ካርታ መቅረጽና በአባላቱ መካከል ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። አብዛኛዎቹ እነዚህ ፈተናዎች ሲከሰቱ ወይም የኢህአዴግ ባለዕዳ በመሆን ብልጽግና በሽግግርና በገዥ ፓርቲነት ለአራት አመታት ሥልጣን ላይ ነበር። በመሆኑም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ ደረጃው ይብዛም ይነስም፤ በተከሰቱ ፈተናዎች እጁ አለበት። እንግዲህ እነዚህን ፈተናዎችን በፈጠረ ተመሳሳይ አመራር፣ መዋቅር፣ ተቋምና አደረጃጀት መፍትሔ ማምጣት አይቻልም።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ዘመን ተሻጋሪው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አነስታይን ከታላላቅ ግኝቶቹ ከአንጻራዊ እይታ፣ ለአቶሚክ ቦንብ መገኘት ፈር ቀዳጅ ከሆነው ቀመርና ከሌሎች ፈጠራዎቹ ባልተናነሰ እኩል የሚታወሱለት ድንቃ ድንቅ አባባሎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስለት «ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ፤ ችግሩን መፍታት አይቻልም።» የሚለው ይገኝበታል። ጥያቄው ከዚህ አንጻር ብልጽግና ራሱን ፈትሾ አስተካክሏል ወይ !? የሚል ነው።
ሰሞነኛው የብልጽግና 1ኛ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት በዋዜማው፤ በታላቁ መፅሐፍ የማቲዎስ ወንጌል 9 ÷ 17 ላይ እንደተገለጸው፤ «በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም። ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል። ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።» እንደሚለው አዲሱን የወይን ጠጅ ማለትም ብልጽግናን ከአረጀው አቁማዳ አውጥቶ ወደ አዲሱ አቁማዳ ያጋባል ተብሎ ይጠበቃል ብዬ ነበር።
በእርግጥ በአንድ ጀንበር ይሄን ለውጥ ማምጣት ባይቻልም በዚህ ጉባኤ አበረታች ለውጦችን ተመልክተናል። ጉባኤው የተመራበት ግልጽነትና ዴሞክራሲያዊነት ይበል የሚያሰኝ ነው። ከሞላ ጎደል ውይይቱንና ምርጫውን በአገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በቀጥታ ተላልፏል። አጋር በሚል አፓርታይዳዊና የሞግዚት አገዛዝ የበይ ተመልካች የነበሩ ፓርቲዎች አባል ሆነው በጉባኤው ውክልና አግኝተው ከመሳተፋቸው ባሻገር፤ አቶ አደም ፋራህ ከሱማሌ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። በአጋር ስም ተገልለው ከኖሩ ክልሎች የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተሰይመዋል። በዚህም የአገራቸው ጉዳይ እንደሚመለከታቸውና እንደሚያገባቸው ተረጋግጧል።
በጉባኤው ዋዜማ ያነሳሁት ሌላው ማሳሰቢያ፤ ኢህአዴግን ለውድቀት ከዳረጉት በርካታ ድክመቶች አንዱ ቁሞ ቀርነትና ተቸካይነት ስለሆነ ብልጽግና ከዚህ ተምሮ ራሱን ያስተካክላል ይሆን? የሚል ነበር። በዚህ ጉባኤ ብልጽግና በሒደት የሚለወጥና ተቸካይ ፓርቲ አለመሆኑን በተግባር አሳይቶናል። ከፍ ብዬ ከዘረዘርኋቸው ማሻሻያዎች በተጨማሪ በርካታ ተስፋ ሰጪ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል። ቀደም ሲል ይካሄዱ የነበሩ የኢህአዴግ ጉባኤዎች የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ሕጋዊ ሰውነት ማስገኛ መድረኮች እንጂ ነፃና ገለልተኛ አልነበሩም። ይህ ጉባኤ ግን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ከመሆኑ ባሻገር ድርጅታዊ ውስጠ ዴሞክራሲንም ሲለማመድ ተመልክተናል። ኢህአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያም ሆነ የመሬት ፖሊሲው የሚቀየረው በመቃብሬ ላይ ነው ይል የነበረው ቁሞ ቀር አስተሳሰብ በብልጽግና ቦታ እንደሌለው በዚህ ጉባኤ ተመልክተናል።
ሕገ መንግሥቱ እንደ ቅዱስ ቁራን፣ መጽሐፍ ቅዱስና ሃይማኖታዊ ቀኖና ሳይሆን በሕዝብ ውሳኔ ሊሻሻል እንደሚችል በፓርቲው ፕሬዚዳንት አማካኝነት ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያዊነት ከፍ ሲልም ሰው መሆንና መደመር የፓርቲው መልህቅ መሆናቸውን በመግለጽ ልዩነት፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነትና ግለኝነት የትም እንደማያድረስ አጽንኦት ተሰጥቶታል። ሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የተጠያቂነት ችግሮች በፓርቲው ቦታ እንደሌላቸውና ፓርቲው የግለሰብ ወይም የአንድ ቡድን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበሪያ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን በፍትሐዊነትና በእኩልነት ማገልገያ መሆኑን ማወጁ ከኢህአዴግ ይለየዋል። ቃሉን በተግባር ማረጋገጡን ወደ ፊት ሁላችንም የምናየው ሆኖ፤ ፓርቲው የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማወጁ በሒደት ከማንነት ወደ ዜግነት ፖለቲካ የመለወጥ ተስፋ እንደሰነቀ ያመላክታል።
ኢህአዴግ ብሔራዊ ምክክርና እርቅ እንዲካሄድ ሲጠየቅ ማን ከማን ጋርነው የሚታረቀው፤ የተጣላ የለም እያለ ሲያጣጥለው የኖረው አገራዊ ምክክር በብልጽግና ተቀባይነት ከማግኘቱ ባሻገር ለተግባራዊነቱና ለስኬታማነቱ የድርሻውን እንደሚወጣ ቃል መግባቱ ፓርቲው ዘመኑን የዋጀ ሆኖ ለመውጣት የቆረጠ መሆኑን ያመላክታል። ደጋግሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አካታች አገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር በማንነት በልዩነትና በጥላቻ የተጎነቆለውን ፖለቲካችንን እልባት የሚሰጥ፤ አገረ መንግሥቱን ከተቀለሰበት አሸዋ አንስቶ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያንጽ፤ ትውልዶች ለዘመናት ሲያነሷቸው ሲታገሉላቸውና መስዋዕት ሲከፍሉላቸው የኖሩ ጥያቄዎችን በማያዳግም ሁኔታ የሚመልስ፤ የጋራ አገር፣ የጋራ ሕልም፣ የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ሰንደቅ አላማ፣ የጋራ ጀግና፣ የጋራ ታሪክ፣ ወዘተረፈ እንዲኖረን የሚያግዝ ስለሆነ በገዥው ፓርቲ ትኩረት ማግኘቱ ተስፋን ያጭራል።
ሆኖም የገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠንካራ ሆኖ መውጣት ለሁሉም ይበጃል በሚል ቅን እምነት የፓርቲ ፖለቲካን ለውድቀት የሚዳርጉ ቀይ ስህተቶችን ላስታውስ፡-
1ኛ. ፖለቲካዊ ትንተናው በአመክንዮና በተጠየቅ ሳይሆን በስሜትና በግዕብታዊነት የተቃኘ መሆኑ፦ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ / መኢሶን /መስራች አባል አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በ«አርትስ» ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው «ትናንትም ሆነ ዛሬ እንደ አገር እንደ ሕዝብ የገጠሙንን ፈተናዎች ለመሻገር ሳይንሳዊ ጥልቅ ትንተና ያስፈልጋል። ትንተናው ግን በግዕብታዊነትና በስሜት ሊሆን አይገባም» ብለዋል። ዛሬ ለምንገኝበት ውርክብ የዳረገን የ60ዎቹ ትውልድም ሆነ እሱን ተከትለው የተቀፈቀፉ ነፃ አውጭ ፓርቲዎች በስሜትና በደም ፍላት ተመስርቶ የተደረገ ትንተናና የደረሱበት የተሳሳተ ድምዳሜ ነው ማለት ይቻላል። በተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ተንጠልጥሎ የሚሰጥ የመፍትሔ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ለውጥ ውጤቱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። የመደብ ትግልን በማንነት ጥያቄ አሳክሮ የተወጠነው ዘውጌ’ዊ ፌዴራሊዝምም ሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከተዘፈቅንበት አዘቅት ሊያወጣን ይቅርና ለከፋ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ዳርጎን አርፎታል። ስለሆነም ትንተናችን ሳይንሳዊና አመክኖአዊ ይሁን።
2ኛ. ለችግሮች አገረኛ መፍትሔ አለመሻት ፦ ላለፉት 50 ዓመታት እንደ መስኖ ውሃ እነ ሌኒን፣ ስታሊን፣ ማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ማኦ፣ ማኪያቬሊ፣ ወዘተ. በቀደዱልን የርዕዮተ ዓለም ቦይ መፍሰሳችን አልያም ሲገድቡን መገደባችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ሆኖም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዛሬም ጥያቄዎቻችን አለመመለሳቸው ችግሮቻችን አለመፈታታቸው ሳያንስ ይበልጥ ተወሳስበው ውላቸው ጠፍቷል። ለዚህ ነው ለአንደኛው ችግር መፍትሔ ስናበጅ ሌላው እንደ እንቧይ ካብ ከጎን የሚናደው። ከሌኒን ኮርጀን የብሔር ጥያቄን እንደፈታን ስናስመስል አገራዊ ሕልውና አደጋ ላይ የወደቀው። ከሶቪየት ገልብጠን የዕዝ ኢኮኖሚን ስንተገብር ነው ፈጠራ የኮሰመነውና ኢኮኖሚውም የደቀቀው። ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓንና ከቻይና እንዳለ ቀድተን ልማታዊ መንግሥት ስናነብር ነው አገር የጥቂቶች ሲሳይ ሆና ያረፈችው። ለነገሩ ጠንካራ አገራዊ አንድነትና ተቋማት በሌሉበት ልማታዊ መንግሥት አይታሰብም።
እነዚህ ማሳያዎች ችግሮቻችንን በተናጠል እና በተኮረጀ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖሊሲ ለመፍታት ያደረግነው ሙከራ መክሸፉን ያሳጣሉ። ለዚህ ነው አገር በቀል ወደ ሆነና ዙሪያ መለስ እይታ ማተኮር የሚያስፈልገው። ለዚህ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ «መደመር» ቁጥራቸው ቀላል ባልሆነ ልሒቃን አገርን፣ ትውልድንና ዘመንን የዋጀ ምላሽ ተደርጎ የተወሰደው። ፅንሰ ሀሳቡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በ«ቲንክ ታንክስ»፣ በሙያ ማህበራት፣ በዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ወዘተ . ሲተች ሲሔስ ደግሞ ይበልጥ የጋራ አካፋይ ሆኖ ሊወጣ ይችላል ተብሎ የታመነው።
3ኛ. የተረክና የታሪክ ምርኮኛ መሆን ፦ሰለሞን ሥዩም የተባሉ ፀሐፊ በፍ-ት-ሕ መፅሔት ከአንድ አመት በፊት ባስነበቡት መጣጥፍ ታሪካችን ሦስት የትርክት ዘውጎችን መፍጠሩን ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡን ጠቅሰው አትተዋል። አክሱማዊ ፣ ሴም ኦሪየንታላዊ እና ስር _ ነቀላዊ ናቸው። ሦስተኛው የስድሳዎቹ ትውልድ የፈጠረው ነው። የታሪኩንም የፖለቲካውን ትርክት ከስሩ ለመቀየር፣ ለመንቀልና ለመፈንቀል ነው የሠራው። ትርክት ቀድሞ በተቀመጠ ድምዳሜና ብያኔ ላይ የሚዋቀር መሆኑ የውርክቡ መግፍኤ ነው። የዚህ ትውልድ ቅርሻ የሆኑ «ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጪዎች» በተለይ ባለፉት 30 አመታት ታሪክን በሸውራራ ትርክት ለመቀየር ያደረጉት ጥረት በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸው ነበር ማለት ይቻላል።
በእነዚህ የፈጠራ ትርክቶች በዜጎች መካከል ጥላቻን፣ መጠራጠርንና ልዩነትን ጎንቁለው በማሳደግ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ችለዋል። በተዛባ ትርክት ለቆሙ የጥላቻ ጣኦታት እንድንሰግድ መስዋዕት እንድንገብር አድርገዋል። ላለፉት በርካታ አመታት በተለይ ለውጡ ከባ’ተ ወዲህ ሰሞነኛውን ጨምሮ የተስፋዋን ምድር ወደ አኬልዳማ ቀይረው በተደጋጋሚ ቅስማችንን ሰብረው አንገታችንን አስደፍተውናል። ሆኖም ዛሬም ከዚህ የጥላቻ አዙሪት ለመውጣት ተረካችንን እንደገና መበየን እና ቂም በቀል የሚያወርሱ ጣኦቶቻችንን ከአእምሮ ጓዳችን አውጥተን ማንከባለል በየከተሞች ያቆምናቸውን የጥላቻ ሐውልቶች እንደገና ስለፍቅር ስለይቅርታ መቅረፅ አለብን። ከዚህ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን ሳይሸራረፍ የማረጋገጥ ጉዳይ አጠናክሮ የመቀጠል ግዴታም አለብን። የሰላም ሚኒስቴርና የታሪክ ልሒቃን ታሪካችንን መቧቀሻ ጓንት ከማድረግ ይልቅ የወይራ ዝንጣፊ መያዥያ እንዲሁም የሰላምና የመግባቢያ ድልድይ መገንቢያ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው።
ከመስከረም 23-25 ቀን 2011 ዓ.ም በሀዋሳ የተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ «አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና» በሚል መሪ ቃል ነበር የተካሄደው። ከሦስት አመታት በኋላ ዛሬ ገለልተኛ የክዋኔ ወይም የፖለቲካ ኦዲተር ብንልክበት መሪ ቃሉን ምን ያህል ተግብሮታል!? መልሱን ለእናንተ ልተወውና፤ ከሦስት አመታት በኋላ በሚካሄደው 2ኛው ጉባኤ ደግሞ የብልጽግና 1ኛ ጉባኤን መሪ ቃል ማለትም «ከፈተና ወደ ልዕልና፤»ን ኦዲት ለማድረግ ያብቃን።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም