እንደምን ሰነበታችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን አንባብያን፤ ሰሞኑን የብልፅግና ፓርቲ በአንደኛው ጠቅላላ ጉባኤው በ1ሺህ486 ድምፅ ዶክተር ዐቢይ አሕመድን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አድርጎ ሲመርጥ፤ በተጨማሪም አቶ አደም ፋራህን በ1ሺህ370 ድምፅ እንዲሁም አቶ ደመቀ መኮንንን በ970 ድምፅ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች አድርጎ መምረጡን. እድሜ ለቴክኖሎጂ በብዙ ሺህ ማይል እርቀት ሆኜ ተከታትያለሁ። “በሐሳብ ልዕልና ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና” የሚለው የፓርቲው መሪ ሃሳብም ትኩረቴን ስለሳበው ለዛሬው የምለውን ልበል።
“ተስፋ” ማለት ቃል የተገባልን ነገር እውነት እንደሆነ ማመን ነው! ተስፋ ሰው በሕይወቱ በፍላጎቱ ልክ የተመኙበት ለመድረስ የሚያስችለው ጠንካራ እምነት ነው። ነገር ግን የሳይንስ ሊቃውንትና የሥነ ልቦና ጠበብቶች ከሚሰጡት ፍቺ ይበልጥ ሰፊና ጥልቅ ትርጉም ያለው ተስፋ ሰዎች በዕለት-ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥማቸውን የኢኮኖሚ ጣጣ ለመወጣት የዛሬን ሳይሆን ነገን የሚኖሩበት አማራጭ የሌለው አስቤዛ አድርገውታል።
በመሠረቱ ተስፋ የሁለት ነገሮች ቅንጅት ውጤት ነው። ይኸውም አንድን ጥሩ ነገር የማግኘት ምኞት እና ያ ጥሩ ነገር እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችለውን መሠረት አካትቶ የያዘ ነው። ተስፋ በእውነታ እና በማስረጃ ላይ ፅኑ ሆኖ የተገነባ እንጂ በምኞትና በፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተም አይደለም።
ስለዚህም ከፖለቲካ ሊህቃን የምንሰማውን የተስፋ ድምፅን አምነን ብቻ መቀበል ሳይሆን፤ እንደ ዜጋ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ተገቢ ይመስለኛል። በዚህ ረገድ “ከፈተና ወደ ልዕልና የሚለው” የብልፅግና ፓርቲ መሪ ቃል በመርሕ ላይ የተመሠረተ ተስፋ ይመስለኛል።
ስለዚህ በጤና ፖሊሲ በኢኮኖሚና በትምህርት ፖሊሲ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በሕገ መንግስት መሻሻልና በአገራዊ ምክክር ምን አዲስ ነገር እንጠብቃለን? በእርግጥ ይህንን የፓርቲው የተስፋ ቃል እንዳለ ብንቀበለው እንኳን ፈጦ የመጣውን የተመፅዋችነት ብሔራዊ አደጋ ለመመከት ምን አይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው? ለምሳሌ፣ የተመረጡት ሶስቱም የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንቶች ለአለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነት ለውጡን ሲመሩ የነበሩ ናቸው፤ አሁንም በድጋሚ ተመርጠው ተመሳሳይ ኃላፊነት ተቀብለው ሊቀጥሉ ነው።
ስለዚህ ሕዝቡ የሚመኘውን ዘላቂ ሰላምና የኑሮ ዋስትና በትክክል ለማግኘት አሁንም በሪፎርም ነው የምንቀጥለው ወይንስ ሥር ነቀል የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጡልን ይችላሉ? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎችን ስናነሳ፤ ያሳለፍናቸውን አራት ዓመታት የለውጥ ጉዟችንን በወፍ በረርም ቢሆን መፈተሽ ግድ ይለናል። በመሠረቱ አንድ አገር አገር ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ መንግሥት የኢኮኖሚ መዛባት እንዳይመጣ ፖለቲካውን ማዘመንና ኢኮኖሚውን እንዳይጫነው ማድረግ ተቀዳሚ ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል። የአንድ አገር ኢኮኖሚው ጤነኛ ነው የሚባለው ፍላጎት እና አቅርቦቱ የተጣጣመ ሲሆን፤ ፖለቲካውን ዘመናዊና የተረጋጋ ያደርገዋል።
ፖለቲካው ካልተረጋጋ ደግሞ ኢኮኖሚው ተናግቶ በማኅበራዊ ዘርፉ ትልቅ ቀውስ ይፈጠራል። የአንድ አገር እድገትና ልማት መሠረታዊ ግብዓቶቹ የፖለቲካው መስከንና ሰላም አማራጭ የሌላቸው ጉዳዮች ናቸው። ሰላም ማለት ደግሞ ከሰው ልብ ውስጥ ጭንቀትና ስጋት ሲጠፋ ነው። ስጋትና ጭንቀት መፈናቀልና ጦርነት ዛሬ በአገራችን በሕዝቦች መካከል አስቸጋሪ የሕይወት ፈተና ሆኗል።
ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚ ያሳየነው እድገትን ስንፈትሽ በምግብ እንኳን እራሳችንን ለመቻል ያደረግነው ጥረት ውጤታማ ነው ብዬ አላምንም። ከማንኛውም ወቅት በከፋ ድህነት የምትገኘውን አገራችንን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት አስተዋይ ልቦና ያላቸውን ምሑራንና አገር ወዳዶችን ኢትዮጵያውያንን ይዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምከር አለባቸው። ሌላው ቢቀር በሕልውናው ጦርነት እንዳደረጉት በግብርናውም ዘርፍ ትራክተራቸውን ይዘው አረንጓዴ አሻራቸውን በማስቀመጥ ለአያሌ የልማት ጀግኖች ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለኝም።
ይሄን የምለው በግብርና ላይ የምናደርጋቸው የፖሊሲ ለውጦች ይኖራሉ አይኖሩም ብዬ ለመከራከር ሳይሆን፤ ቢያንስ አስተማማኝ የራስ የመቻል ፍላጎት ለማሟላት ቢያቅተን እንኳን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታችንን ለመቻል ጉልበታችንን፣ እውቀታችንን፣ ጊዜያችንና ሀብታችንን አስተባብረን ለጤናማ ለውጥ መዘጋጀት ይኖርብናል። አሁን የጀመርነውን የአንድነት ስሜት አጠናክረን ብሔራዊ ጠቀሜታ ባለው የልማትና የገፅታ ግንባታ ላይ መረባረብ ይጠበቅብናል።
ምክንያቱም የምስራቅ አፍሪካዋ እስትራቴጂክ አገር ኢትዮጵያ አሁን በገጠማት የብሽሽቅ ፖለቲካ ምክንያት ከምታደርገው ያልተቋጨው የሕልውና ጦርነት በተጨማሪ በውጭ መንግሥታት የታወጀባትን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻና የኢኮኖሚ ማእቀብ ማስፈራሪያ ተደማምረው ለተለያዩ የዋጋ ንረትና ለውጪ ምንዛሪ እጥረት፣ ዳርገዋታል። በተለይ የሥራ አጥነት ቁጥር መጨመር፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ የዶላርና የብር ልዩነቶች ሽቅብ ማደግ፣ ሌብነትና ዘረፋ፣ ሙሰናና ጉቦኝነት መበራከት መፈናቀልና በሽታ፣ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች፣ የኑሮ ውድነትና ድርቅ ሲደራረቡባት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ሸርሽሮ በማሳጣት ቅሬታን መፍጠር መጀመሩ አይቀሬ ነው።
እንደዚህ አይነት የማኅበራዊ ቀውሶች ሲጀምሩ ከግለሰብ አልፈው የክልል መንግሥታትን የችግሩ ሰለባ ስለሚያደርጋቸው ፍትሐዊ የበጀት ጥያቄዎችን በማንሳት ፌዴራል መንግሥቱ ጋር መፋጠጥ ይጀምራሉ። ስለዚህ ከብልጽግና ፓርቲ ምን እንጠብቅ? አሁንም በሪፎርም ባቡር እንጓዝ ወይንስ ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ እናመጣለን? ማለት ይገባል። ምክንያቱም ሳንለወጥ የምንቀጥል ከሆነ ግን ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ…. ድካማችን ሁሉ የእንቧይ ካብ …የእንቧይ ካብ እንዳሉት አባት ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም ያሳስበኛል።
እንደኔ እምነት ግን 11 ሚሊዮን አባላት የሰበሰበው የአገሪቱ ግዙፍ ፓርቲ ብልጽግና እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ እውነት የኢትዮጵያ ተስፋ ሊሆን ይችላል ወይ? የሚለው የሚሊዮኖቻችን ጥያቄ ለመመለስ ጊዜን መጠበቅ ግድ ቢሆንም፤ ጨክነን ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ። ይህንን ለማድረግ ድፍረቱ ካጣን ግን አገራችን በተስፋና በፈተና ላይ ሆና ትቀጥላለች።
ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ዋስትና የሚሰጡ ጠንካራ ተቋሞችን መገንባትና ወሳኝ አመራሮችን አፍርቶ ኃላፊነት የሚሰማው ኅብረተሰብን መፍጠር፣ የሚችል ሥርዓት መመሥረት ነው። አገርን እንደ አገር ጠብቆ ለማቆየት ከምንጠየቀው መስዋዕትነት እጅግ የበረታ ዋጋ የሚያስከፍሉንን ከሌብነትና ከዘረኝነት የፀዳ ዴሞክራሲዊ የፖለቲካ ሥርዓት ማዋለድ ነው። እነዚህን የመሰሉ የቤት ሥራዎቻችንን ከሠራን ሁላችንም አገራችን ለመገንባት የሚጠበቅብንን የዜግነት ድርሻ ማዋጣት ከቻልን በጋራ ተጋግዘን ኢትዮጵያን መለወጥ የብልጽግና ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ብሔራዊ ግዴታ ይሆናል።
ስለዚህ አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ከፈለግን መጀመሪያ እራሳችንን ከሰቀልንበት የአንቱታ ዙፋናችን ላይ ወርዶ በትኅትና ኅብረተሰቡን ዝቅ ብለን ማገልገል ከቻልን እውነትም የፓርቲው መሪ ቃል “ከፈተና ወደ ልዕልና” የሚለው ብልፅግና በመርሕ ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ግዙፍ ፓርቲ ሊደርገው ይችላል። ትናንት መደማመጥ አቅቶን በአግባቡ ለመኖር ባለመቻላችን በርካታ የሰው ሕይወትና የሀብት ውድመት ደርሶብናል።
ዛሬ ደግሞ ከትናንቱ፣ ስህተታችን ተምረን በአግባቡ መኖር ካልቻልን ሌላ የእርስ በእርስ ብጥብጥና የንፁሐን ወገኖቻችን ሕይወት ለማጥፋት የምንሞክር ከሆነ “በተስፋና ባልተቋጨ ጦርነት” ውስጥ አገራችን አስገብተን ስንዳክር እንኖራለን። ዘመኑ የተራቀቀ የቴክኖሎጂ ዓለም በመሆኑ ለአንድ አገር ጠንካራ ፓርቲ የፖለቲካ አመራር የሚሰጥ የአመለካከትና የላቀ ርእዮታዊ እውቀትና ብስለት የሚጠይቅ ጊዜ ላይ ነን። ስለዚህ ያሳለፍናቸውን የአሁኑኑም ችግሮቻችንን በአዲስ መንገድ ለመጋፈጥና ደግ ቀን ለማምጣት በመፍትሔ ፍለጋ ዙሪያ ብልጽግና ከተስፋ ወደ ልዕልና የሚደርገውን ሽግግር በሚጨበጥ በሚዳሰስና በሚታይ የተግባር ክንውኖች ያሳየናል ብለን በተስፋ እንጠብቃለን።
እኔም ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ። በሌላ ሃሳብ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን!
አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም