ለአንድ ዓመት ያህል በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ስራ ለመወዳደር የትምህርት ማስረጃዋን አሰራጭታለች፡፡ ከዛሬ ነገ እቀጠራለሁ አሊያም መስሪያ ቤቶቹ ይጠሩኛል የሚል ድምዳሜ ላይ ባለመድረሷ የመንግስትን እጅ ሳትጠብቅ ሁለት ጓደኞቿን ይዛ በግል የኮንስትራክሽን ዘርፍ በመደራጀት የነገዋን ተስፋ እየተጠባበቀች ትገኛለች፡፡
ወጣት ፍቅርተ ሀይሉ፡፡ በ2010ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሲቪል ምህንድስና ምሩቅ የሆነችዋ ወጣት ፍቅርተ ሠሞኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ባዘጋጀው የስራ እድል ፈጠራ ክህሎትን ሊያጎለብት የሚችል ስልጠና ላይ በመሳተፍ ‹‹ከመቀጠር ሥራን መፍጠር›› የሚለውን አማራጭ ተቀብላለች፡፡
በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ያለምንም መነሻ ገንዘብ ሥራን መፍጠር ከባድ ቢሆንም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ስላልሆነ ከቀላል ነገር መጀመር እንደሚቻልም ትመክራለች ። ወጣት ፍቅርተ እንደምትለው፤ ወጣቶች ሥራን ፈጥሮ መስራት በሚለው አመለካከት ላይ የግንዛቤ ውስንነት ስላለባቸው ብዙ ጊዜ ይህንን መንገድ ሲከተሉ አይስተዋልም፡ ፡ ግንዛቤያቸው ጠባቂነት ላይ ነው፡፡ አብዛኛው ወጣት ከዚህ አስተሳሰብ የወጣ አይደለም፡፡
ተምሮ የተመረቀ ሁሉም ሥራን ያገኛል የሚል ተስፋ ስለማይኖርና ቅጥር ቢፈጸም እንኳን አድሎአዊ አሰራሮች ስላሉ የራስን አዲስ የፈጠራ ሀሳብ አመንጭቶ ሥራን መፍጠር እንግልትን ይቀንሳል፡፡ ችግሩን ለማቅለል ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ የሆነ ሥልጠና መስጠት አለባቸው፡፡ ወጣቷ « በአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አማካኝነት የተሰጠው የስራ እድል ፈጠራ ክህሎትን ሊያጎለብት የሚችለው ሥልጠና ከተለምዷዊው የስልጠና መርህ ወጣ ባለ መልኩ ወጣቶች ያላቸውን ውስጣዊ አቅምእንዲጠቀሙበት የሚያስችል ሲሆን ነው» ትላለች፡፡
ሥልጠናውን የማወደሷ ምክንያት ደግሞ በእያንዳንዱ የስልጠና ሂደት ተግባራዊ ልምዶችና የመስክ ሥራዎች ስለነበሩ በተለያዩ አካባቢዎች ምን አይነት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ የሚያስተምር መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ተቀምጦ ከማድመጥ ይልቅ ምልከታ ማድረግ አዲስ የስራ ሀሳቦችን ለማፍለቅ ይረዳል» ትላለች፡፡ ካገኘችው ሥልጠና ከዚህ ቀደም ከነበረው ሥራ የመፍጠር ተነሳሽነት አንዳች ሀይል እንደጨመረላት በመናገር ራሷን የተሻለ ቦታ ለማድረስ እንምትታተርም ገልጻለች፡፡
ወጣት ደግሰው መንግስት እንደ ፍቀርተ ሁሉ ሥራን ከመጠበቅ ሥራ ፈጣሪነት ዋጋው ከፍ ያለ መሆኑን የሚያምን ነው፡፡ በ2009ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ተመርቆ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከገኘ በኋላ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ግንባታ ጣቢያዎች ላይ በመዘዋወር ከሙያው ዝቅ ብሎ በመስራት ራሱን መለወጥ ችሏል፡ ፡ ይህም የሆነው በራሱ ጥረት እንጂ በማንም አጋዥነት እንዳልነበር ወጣቱ ይናገራል፡፡
በመዲናዋ የስራ ማስታወቂያ በሚለጠፉባቸው የተጨናነቁ ቦታዎች ላይ ተዘዋውሮ ሥራ ለመፈልግ ዓላማ ያልነበረው ወጣት ደግሰው፤ ትኩረቱ ሥራን መፍጠር ብቻ እንደነበር ይናገራል፡፡ በተለይ ‹‹ውድድር በበዛበት ዘመን ላይ የተለመደ ነገርን ማድረግ ከምንፈልገውና ከምንመኘው ነገር ያግደናል›› የሚል የህይወት መመሪያ እንዳለው በመናገር፤ በራሱ አማራጭ ህግን በመከተል አቋራጭ መንገድን መጠቀም አዋጭ እንደሆነ ነው የሚገልጸው፡፡
«በራስ የፈጠራ ሥራ ሀሳብ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ተግባቦት ትልቅ ቦታ አለው» የሚለው ወጣት ደግሰው፤ ባለው የተግባቦት ክህሎትም ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሀሳቡን እውን በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የስራ ፈጠራ ስልጠናዎችን በተደጋጋሚ መውሰዱንና አሁን ቢሮው ከሰጠው ሥልጠና ባገኘው ተጨማሪ ክህሎት አዳዲስ አካሄዶችን ለመቅሰም እንደረዳውም ይገልጻል፡፡
እገዛዎች በተለያዩ መንገዶች ሊገኙ ቢችሉም በራስ ጥረትና ልፋት ሰርቶ ራስን መለወጥ እርካታን እንደሚሰጥ የራሱ ህይወት መስካሪ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ የጥናት ፕሮጀክት አቅም ማጎልበት ቡድን መሪ አቶ ንብረት ይሁን እንደሚሉት፤ ሥልጠናው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ከተቀጣሪነት ሥሜት ተላቅቀው በራሳቸው ስራን መፍጠር የሚያስችልና በትምህርት ዓለም ቆይታቸው የተማሩትን ንድፈ ሀሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ነው፡፡ ወጣቶቹ በስልጠናው ቆይታቸው ያገኙትን ሰፊ ልምድና ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የከተማዋ ወጣቶች ተምሳሌት እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይለሰማዕት መርሀጥበብ በበሉላቸው፤ ወጣቶች በስልጠና ቆይታቸው እንዴት አዳዲስ ሀሳቦች ማመንጨትና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ መነሻ ግንዛቤ መሰጠቱንና ይህም ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ ባገኙት ስልጠና የሥራ ፈጣራ ባለቤት እንዲሆኑ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶች ያላቸውን ፀጋና ዕውቀት ለራስና ለወገን ማዋልን የመሰለ ዕርካታ ትልቅ ቦታ እንዳለው የተናገሩት አቶ ሀይለሰማዕት በስልጠና የተሳተፉት ወጣቶች የበለጠ ለውጥ ውስጥ በመግባት ማኅበረሰቡንም ጭምር ሊያገለግሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ቢሮው በወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና፣ ስራ ፈጠራና ወዳድነት ብሎም በጎ አመለካከት ከመቼውም ጊዜ በበለጠና በተግባር እንዲያረጋግጡ መሰል ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ለወጣቶች በስራ ፈጠራ ዙሪያ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመረቁ ቁጥራቸው 80 ለሚደርስ ወጣቶች ሰሞኑን ሥልጠና መስጠቱ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በአዲሱ ገረመው