ማኅበራት በ6ወር ውስጥ ቆሻሻን በመሸጥ ብቻ 49 ሚሊዮን ብር አግኝተዋል
አዲስ አበባ፡- ቆሼ ከሚገኘው 30 ሄክታር የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ውስጥ እየለማ ያለው 1 ነጥብ 5 ሄክታሩ ብቻ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። ቆሻሻን በማስወገድ ላይ የተሰማሩ ማኅበራት በ 6 ወር ውስጥ ቆሻሻን በመሸጥ 49 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውም ተጠቅሷል።
ከተማ አስተዳደሩ በ2009 ዓ.ም ቆሻሻ ተደርምሶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰበትን ሥፍራ መልሶ የማልማት የመጀመሪያ ዙር ሥራ መጠናቀቁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን እና ለተባባሪ አካላት ትናንት ገለፃ ተደርጓል። የኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ እንዳሉት፤ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራው 30 ሄክታር ሲሆን፤ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቱ በ 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ተግባራዊ ሆኗል ብለዋል።
ቀደም ሲል ቆሻሻው ተደርምሶ በሰው ህይወትናበንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰበትን አካባቢ ሥፍራ መልሶ ለማልማት የከተማ አስተዳደሩ ከተባበሩት መግሥታት ድርጅት የሠፈራ መርሐ ግብር ‹‹ዩ.ኤን ሃቢታት›› እና ከጃፓን መንግሥት ጋር በመተባበር ከአንድ ዓመት በፊት የ‹‹ፉካካ›› ዘዴ ፕሮጀክት ተቀርጾ በመተግሩ 1 ነጥብ 5 ሄክታር ማልማት መቻሉን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የተከማቸውን የቆሻሻ ከፍታ በመደርመስ ወደ ሥር የማስረግና በቆሻሻ ውስጥ የሚገኘው ፍሳሽ ወደ ወንዝ ገብቶ ጉዳት እንዳያመጣም ተጨምቆ እንዲጣራ የማድረግ ሥራም በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታው በነዋሪዎች እንዲሁም በአካባቢው ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጥርና የቆሻሻ ማከማቻ ቦታውንም በሚቆጥብ መንገድ ለመጠቀም እየተሠራ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በወቅቱ ተከስቶ ለነበረው አደጋ መፍትሔ መስጠት እንጂ የአካባቢው መልክዓ ምድር በመለወጥ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንዳልሆነም አስታውቀዋል። በሌላ በኩልም በከተማ ደረጃ ቆሻሻን በማስወገድ ሥራ ላይ የተሰማሩ 74 ማኅበራት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወር ውስጥ ቆሻሻን ሸጠው 49 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ቆሻሻን ከማስወገድ ይልቅ ወደ ሀብትነት መለወጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተማዋ እስከ 20 በመቶ የሚሆነው ቆሻሸ መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ፤ ይህ ሀብት የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ፋብሪካ ገብቶ ወደ ጥሬ ዕቃነት ተቀይሮ የውጭ ምንዛሬን መቀነስ ያስችላል እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ። ለአጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሥራ በከተማ አስተዳደሩ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በጃፓን መንግሥት ሁለት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተደርጎ እየተሠራ ሲሆን፤ ለ30 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የመጀመሪያ ደረጃ ሥራም የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይም አካባቢውን አረንጓዴ የማድረግ ሥራ ይሠራል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በቀን ከሦስት ሺ ቶን በላይ የሚመነጨውን ቆሻሻ በረጲ (ቆሼ) ስፍራ እንደሚያስወግድ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በአዲሱ ገረመው