«…ለምን! ለምን! ሞተ!?
ርዕሶቹን የተዋስኩት ከስልሳዎቹ ትውልድ ገናና ዝማሬዎች መካከል ከአንድ ሁለቶቹ ጥቂት ቃላትን በመዋስ ነው። ያ ቀስተኛና አብዮተኛ ትውልድ በስሜት ማዕበል እየተላጋ አቅጣጫው የጠፋበት የበጋ መብረቅ ብጤ ቢሆንም፤ ምኞቱና ትግሉ ግን የተሻለች ኢትዮጵያን ማየት ስለነበር እስከ ሞት ድረስ በመጨከን ራሱን ጭዳ ለማድረግ ወኔ የከዳው አልነበረም።
የአገሪቱን መሬት ጠቅልለው በብብታቸው ውስጥ የወሸቁት የወቅቱ ፊውዳል ገዢዎች መሬቱን ለባለ መሬቱ እንዲመልሱ «በመሬት ላራሹ» መሪ ዓላማ ከፍተኛ ትግል ያደረገው ከባህል፣ ከትምክህት፣ ከዙፋንና ከእምነት ጋር እየተፋለመ እንደነበር ማስታወሱ አግባብ ነው።
ትውልዱ የጮኸለት፣ የሞተለት፣ የአካልና የኅሊና ቁስል ያተረፈበት የትግሉ መሪ ጥያቄ ሥልጣኑን በጠብመንጃ አፈሙዝ የማረከው ወታደራዊ ደርግ አደብዝዞትም ቢሆን የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም በስር ነቅል አዋጅ «መሬቱን ለላብ አፍሳሹ አራሽ» መመለሱ አልቀረም።
«አገሩን ለባለ አገሩ» አሰኝቶ ትውልዱን ያስጮኸው በዋነኛነት በሕዝቡ ላይ ለዘመናት ተጭኖ የኖረው ይህ መሠረታዊ «መሬቴን መልሱልኝ» የባለቤትነት ጥያቄ ነበር። ከትውልዱ ፊት አውራሪ አይከኖች መካከል በዘውዳዊው ሥርዓት «ግፍ ጌጡዎች» የጭካኔ እርምጃ ደሙ ደመ ከልብ የሆነው ጥላሁን ግዛው እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ብቅ ብሎ የተሰዋ ሰሞንም «ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ!?» እየተባለ የተዘመረለት አገሩ ለባለ አገሩ እንዲመለስ እርሱ የመስዋዕት በግ መሆኑን ለመግለጽ ነበር።
ዘመን ሲደበዝዝ አብሮ ደብዝዞ ካልሆነ በስተቀር የመልዕክቱ ይዘት ቀላል የሚባል አልነበረም። ያለመታደል ሆኖ ግን ትውልዱ «አገሩን ለባለ አገሩ!» እያለ በመዘመር ውሎ አምሽቶውን አደባባይና ጎዳናዎች ላይ እያደገ ዙፋኑን ያናወጠበት ያ ዝነኛ መዝሙር የማታ ማታ ያዋለደው «ንጹሑን የወጣቱን ምኞትና ርዕዩን» ሳይሆን ጠብመንጃ አምላኪውን የደርግ ሥርዓት ነበር። «…ለምን ለምን ሞተ!?» በሚል ነዲድ ቁጣና ቁጭት ካበገነው ነበልባል እስትንፋስ የተግለበለበው ያ ዝማሬ የተጠናቀቀውም በቀይና በነጭ ቀለማት በተወከሉ ሽብሮች እርስ በእርስ በመጠፋፋት ነበር።
«ነቅናቂው ነቅንቆ ቢያነቃንቀው፣ የተነቀነቀው ነቅንቆ ጣለው።» ቋጥኝ ለመደረማመስ አገልግሎት ላይ በሚውል ድማሚት የሚመሰለው ይህ ባለ ሁለት ስንኝ ግጥም የዘመኑን ወጣቶች ትግልና የትግሉን ክሽፈት በሚገባ የሚያሳይ ብቻም ሳይሆን፤ የታሪክ ትውስታችንን ለመጠቅለልም ጭምር ጥሩ ምርጫ ስለሆነ በዚህ ቦታ እንዲጠቀስ ግድ ብሏል። ዛሬም
«አገሩን ለባለ አገሩ!?» – ያልተቋጨው ጩኸት፤
ባለ አገር ሆኖ ስለ «ባዕድ ባለ አገርነት» ማውራት ከእውነታ እንደመጋጨት ሊያስቆጥር ይችላል። ይሁን እንጂ ባዕድ ባለ አገርነት የነበረ፣ ያለና፣ ወደፊትም ላለመኖሩ ዋስትና የሚያሰጥ አይደለም። የዘመነ ፊውዳል ባላባቶች ሙሉ ኢትዮጵያን የተቃረጧት በሕግ ድጋፍ፣ በዙፋኑ «በርቱ» ባይነት መሆኑን እንደ አዲስ መተንተኑ ጉንጭ አልፋነት ነው።
ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ምድሪቱንም ጭምር ያስለቀሱት እኒያ የፊውዳል ሥርዓቱ የዙፋን በረኞች ቢያንስ ቢያንስ በብዝበዛ ሥርዓታቸው አግላይአልነበሩም።
መሬታቸው ጦም ውሎ ጦም እንዳያድርም፤ በጭሰኝነትም ሆነ በገባርነት የዕለት ጉርሻቸውን የሚያድኑ ዜጎችን ከየትኛውም ብሔርና ጎሳ እየሰበሰቡ በሥራ ላይ ያሰማሯቸው ነበር። የትኛውም የአገሪቱ ዜጋ በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን እግሩ ወደሚመራው አቅጣጫ በነፃነት እየተንቀሳቀሰ የዕለት እንጀራውን ለማሸነፍ ላቡንና ደሙን እየገበረ መኖር ይችል ነበር።
«ተኖረና ተሞተ» አባባል ሳይዘነጋ። በዚህ ጸሐፊ የታዳጊነት ዘመን አንዳንድ በሥራ እጦት የተቸገሩ ጎረምሶች ሲከፋቸው «ግፋ ቢል አዶላ፤ ጨብጥ ቢል አካፋ!» የሚል ብሂል ነበራቸው – «ምንም ይግጠመኝ ምን አዶላ ሄጄና አካፋ ጨብጬ በባህላዊ ወርቅ ፍለጋ በመሰማራት የዕለት እንጀራዬን አሸንፋለሁ።» ማለታቸው ነበር። ከዚህ አባባል ዛሬን የሚሞግቱ በርከት ያሉ ትምህርቶችን መዞ ማውጣት ይቻላል። አንድም፡- ሥራ አጡ ወጣት «ያለ ሥራ ተቀምጬስ ጊዜዬን አላጠፋም ላቤን ጠብ አድርጌ ሠርቼ እራሴን አስተዳድራለሁ» ማለቱ ነው።
ሁለትም፡- «አገሬ ሰፊ ነች በየትኛውም አቅጣጫ ተንቀሳቅሼ በነፃነት መሥራት እችላለሁ» የሚለውንም ትርጉም ተሸክሟል። እንደ ሦስተኛ የሚቆጠር ከሆነም «አካፋ መጨበጥን በሥራ ክቡርነት መገለጫነት» ልንተረጉመው እንችላለን። ዛሬ ዛሬ ባለአገርነት ብርቅ ሆኖ ለራስ አገር ባዕድ መሆን ጉልበቱ የፈረጠመበት ወቅት ይመስላል።
አገሬ ብለው በወገናቸው መካከል የሚኖሩ ባለ አገሮች በዘራቸው ምክንያት ተጨፈጨፉ፣ ተፈናቀሉ፣ ተሰደዱ … ማለት እጅግ የቀለለበት ወቅት ነው። ሰው በአገሩና በወንዙ እንዴት ባዕድ ሆኖ ይገለላል። በዘር እብደት የሰከሩና የተለከፉ እኒህን መሰል እኩያን በሚፈጽሙት የከፋ ድርጊት «አገሩን ለባለ አገሩ!» ብለን ወደ መንግሥትና ወደ ፀባዖት ለፍትሕ ፍለጋ ብንጮኽ ይፈረድብናል? ለመሆኑ በአደባባይ ለፍትሕ ሲሟገቱ በግፈኞች እርምጃ ሕይወታቸውን የተነጠቁትን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የጉራጌ፣… የወላይታ (ዝርዝሩን ላልዘልቅበት ነካካሁት መሰል) ወጣቶች «…ለምን ለምን ሞቱ!?» ብለን ብንሟገት የምናገኘው መልስ «ለዴሞክራሲ ሲሉ!» የሚል አይደለምን?።
በእነርሱ መስዋዕትነትና በሌሎችም የኢትዮጵያ ለውጥ አላሚ ልጆች ተገኘ የተባለው «የደም ዋጋ ዴሞክራሲ» ውጤቱ እንዲህ ይላሽቃል ብሎ ማን ገመተ፤ ማንስ ጠረጠረ። ሰው በአገሩ እየኖረ እንዴት ባዕድ ባለ አገር ይሆናል? ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀው ጥያቄ ነው።
ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም «የመጻተኛው አገር» በሚል ርዕስ የከተባት አንዲት ብጥሌ ግጥም አለችው። መልዕክቷ ረቀቅ መሆኑን በማስታወስ እዚህ ቦታ ተውሼ ጥቂት ልቆዝምባት። «አገር ድንኳን ትሁን ጠቅልዬ የማዝላት፤ ስገፋ እንድነቅላት ስረጋ እንድተክላት።» ገጣሚው አገርን የወከለው በድንኳን ነው።
ድንኳን ከሸራ ውጤት የሚዘጋጅ መጠለያ ብቻ አይደለም። ተራዳ አለው፣ አውታር አለው፣ ቋሚ ተሸካሚና ችካልም እንደዚሁ። ከግብጽ ለወጡት ጥንታውያኑ እሥራኤላውያን ድንኳን እንኳንስ ግብሩ ስሙ ራሱ የከበረ ነበር።
«የማደሪያው ድንኳን» በመባል የሚታወቀው የምድረበዳ ተጓዦቹ የእሥራኤላውያን ድንኳን በውስጡ ያህዌ እያሉ የሚጠሩት ፈጣሪ አምላክ በክብር የሚያርፍበትና የቃል ኪዳኑ ታቦት ጭምር የሚቀመጥበት የበረሃ ቤተመቅደስ እንደሆነ የታሪኩ ትንታኔ ይህንን እውነታ ያብራራልናል።
ዘለቅ ብለን እንተንትነው ማለቱ ለዚህ ርእሰ ጉዳይ የሸክም ያህል ስለሚከብድ በድርበቡ አስታውሶ ማለፉ ይመረጣል። ለዘመናት በዘለቀው ቀኖናዋ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓል ሲከበር ታቦታት ውጭ በድንኳን ውስጥ እንዲያድሩ የምታደርገው ይህንን ታላቅ የመንፈሳዊ ትርጉምና ትውፊት በመከተል እንደሆነ ይታመናል።
የገጣሚውን ሃሳብ በአሜንታ እንቀበልና ኢትዮጵያን በድንኳን እንመስል። ድንኳኗን አጠናክረው የሚይዙትን ተራዳዎች፣ አውታሮች፣ ቋሚዎች፣ ችካሎችና መሰል መገልገያዎች፡- በብሔር ብሔረሰቦቿ፣ በታሪኳ፣ በደማማቅ ባህሎቿ፣ በወጎቿና በማህበራዊ እሴቶቿ ወዘተ.ሊመሰሉ ይችላሉ።
ድንኳንን ድንኳን የሚያሰኘው የላይ ላዩ መክደኛ ብቻ እንዳይደለ ሁሉ አንድን ሕዝብ ሕዝብ የሚያሰኘው መገለጫዎቹም ብዙዎች ናቸው። ጉዳዩን አስፍቶ መለጠጡ ከርዕሰ ጉዳያችን እንዳያርቀን ስለሚያሰጋ ሃሳቡን ሰብሰብ ማድረጉ ይበጃል። ድንኳን በአግባቡና በወጉ ካልተደኮነ በስተቀር በቀላሉ በንፋስ ሊፈራርስ ይችላል።
አገርም እንዲሁ ሕዝቧ በግራ መጋባት ነፋስ ከግራ ቀኝ የሚላጋ ከሆነ አውሎ ነፋሱ የሚያደርሰው አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። «የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ» (ዕንባቆም 3፡7) የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ትንቢት የትኛውን ዘመንና ትውልድ እንደሚወክል ሙያችን ስላይደለ የሥነ መለኮት ምሁራን ካላገዙን በስተቀር ሥነ አፈታቱን ስለምናዛባ እንዲሁ ጥሬ ዐረፍተ ነገሩን ብቻ ጠቅሶ ማለፉ ብልህነት ነው።
በድንኳን የመሰልናት ኢትዮጵያ የተጨነቀችባቸው ጉዳዮች በታሪኳ ውስጥ ከአሁን ቀደም እንደ አሁኑ ተፈታትነዋት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ለመስጠትም ጠለቅ ያለ ምርምርና ትንተና ስለሚያስፈልግ ለጊዜው ጊዜ መስጠቱ ይበጃል።
ከሕዝቡ መከራና ስቃይ ለመረዳት እንደሚቻለው ግን እውነትም «በድንኳን የመሰልናት ኢትዮጵያችን» ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ በእጅጉ እየተጨነቀች ስለመሆኗ ያፈጠጠው እውነታችን ምስክር ነው። ለምን ልትጨነቅ ቻለች? አስጨናቂዎቿስ እነማን ናቸው? ለምንስ ሊያስጨንቋት ዘመቱባት የሚሉት አጠቃላይ ጥያቄዎች መልሳቸው በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው።
ሕወሓትና ሸኔ ድንኳኗን ሊያፈርሱ ቋምጠው ሲያስጨንቋት እያየንም አይደል? እነዚህ ሁለት የአሸባሪ ድርጅቶችና መጋለቢያ ፈረሶቻቸው በደም የሰከሩና በደም የተጨማለቁ ስለመሆናቸው ብለን ብለን የመግለጫ ቃላቶቻችንን ስለጨረስን «የዘመናችንና የወቅቱ መቅሰፍቶች» ብሎ መጠቅለሉ ይቀለናል።
የሉዓላዊ ተራዳዎቻችንንና አውታሮቻችንን ገነጣጥለው ኢትዮጵያን ለማጎሳቆልና ክብሯን ለማራከስ የሚሞክሩት የሩቅ ጎረቤቶቻችንና የቅርብ ቡና አጣጭዎቻችን አገራት በአንድ በኩል፤ የሩቆቹ ጀብደኛ መንግሥታት በሌላ ግንባር ወጥር ብለው ደንኳናችንን ለማፍረስ በሚጯጯኹ እድርተኞች ልንመስላቸው እንችላለን። እነዚህ ሁሉ ኃይላት ተልዕኳቸው የባለ አገሩን አገር ነጥቀው የራሳቸው የድብቅ አጀንዳ ማስፈጸሚ ለማድረግ እንደሆነ አይጠፋንም። እየተሞከረ ያለውም ይሄው ነው።
ኢትዮጵያዊው ባለ አገር እኔስ ፈርዶብኝ አገር አልባ እየሆንኩ ነው፤ ለመሆኑ፡- «አገሬ ራሷ አገሯ የት ነው?” (ይህንን ርዕስ ከአሁን ቀደም ለአንድ ጽሑፌ መጠቀሜን ልብ ይሏል) ብሎ በግራ መጋባት እንዲጠይቅ የተገደደባቸውን ብዙ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል።
አንዱ ትልቁ በሽታ የዘረኝነት ልክፍት የተጠናወተው የፖለቲካ ልምምዳችን ነው። ይህ ደዌ በአገር ደረጃ ያደረሰብን ስብራት እጅግ ግዙፍ ስለሆነ አቅሙን ይበልጥ አጉልተን ለማሳየት ጊዜ አናባክንም።
ቢቻል አንድም በጸሎት ወይንም በጾም አለያም ፖለቲከኞቻችን የልባቸውን ድንዳኔ ትንሽ ለስለስ ካላደረጉ በስተቀር ይህን ክፉ እባጭ በጋራ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ እንዳንነቅለው ሊፈታተነን ይችላል። ባለ አገሩ በራሱ አገርና ጓዳ ባዕድነት እንዲሰማው የሚገደድበት ሌላው ሰበብ በስዕለትም ይሁን በስለት ተቆርጦ አልጣል ያለንና የተጣባን የአገሪቱ የቢሮክራሲ ማነቆ አንዱና ትልቁ በሽታችን ነው።
በውስብስብ የመንግሥት ድርና ማግ የተተበተበው የአገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ሕዝብን ማስለቀስ ብቻም ሳይሆን በአገሩ ላይ ፊቱን አዙሮ እንዲሰደድ ጭምር ምክንያት እየሆነ ነው። የቢሮክራሲውን ጡዘት ሲያከሩ የሚውሉ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጉዳይ በትዝብት ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን፤ በትርም የሚያስፈልጋቸው እንደሆነ እንመሰክራለን። ውሏችን በሙሉ በለቅሶ የታጀበ ስለሆነ።
በዕለት ዳቦ እጦት አንድ ሌሊት ርሃብ እየሞረሞረም ቢሆን ሌሊቱን ማንጋት ይቻላል። ሲደጋገም ግን እንኳንስ የፓርቲን ወንበር ቀርቶ የነገሥታትን ዙፋንም ሊነቀንቅ እንደሚችል ሹሞቻችን ቢያውቁት አይከፋም። ከሰሞኑ ሕዝበ ኢትዮጵያን እያንጫጫ ያለው የኑሮ አቀበት ወዴት አድርሶ የት እንደሚያሳርፈን ለመገመት እየከበደ ነው።
ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ባዕድነት ከተሰማውና «አገሩን ለባለ አገሩ» እያለ መዘመር ከጀመረ ምልኪው ደግ ስላይደለ «አገሬ ሆይ!» ለራስሽ ባለ አገርነት ራስሽ እወቂበት። ሰላም ይሁን!::
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 /2014