የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ላለፉት በርካታ ዓመታት ጥሩ ከሚባሉት ኢኮኖሚዎች መካከል እንደነበር በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምስክርነት ሲሰጡ ቆይተዋል።
ይህ የኢኮኖሚ እድገት የሚጠበቀውን ያህል ዜጎች ከድህነት ማላቀቅ ያልቻለ፣ እና የሚፈለገውን ያህል የሥራ እድል መፍጠር ያልቻለ ነበር በሚል ቢተችም እድገቱ እድገት እንደነበር የሚክድ አልነበረም።የኢኮኖሚ እድገቱ በሚፈለገው ልክ የሥራ እድል መፍጠር ባለመቻሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እየኖረ ከመሆኑም ባሻገር የሥራ አጥነት ችግር መቅረፍ የአገሪቱ ዋነኛው ራስ ምታት ሆኖ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ይህ የኢኮኖሚ እድገት መቀዛቀዝ እያሳየ መምጣቱን እነዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሪፖርቶቻቸው አመላክተዋል።
አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሰላም እና መረጋጋትን እውን ከማድረግ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው። በእርግጥ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ሰላም ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።
ነገር ግን በኢኮኖሚ እድገት ያልተደገፈ ሰላም ዘላቂ ሊሆን እንደማይችልም እሙን ነው። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል የለውጡ መንግሥት አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሲያካሂድ የነበረ ቢሆንም አገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ጦርነት፣ እና የዜጎች መፈናቀል ጉዳዮች የመንግሥትን ትኩረት የሳቡ ሆነው በመቆየታቸው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት ተሰጥቷል ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም ።
በመሆኑም አገሪቱ የገባችበትን ጦርነት በሰላማዊ እና በንግግር ከመፍታት ጎን ለጎን ኢኮኖሚውን እንዴት ማገገም እንደሚቻል ሁሉም ሊያስብብት ይገባል።
ሰሞኑን 1ኛ ጉባኤውን ያካሄደው ብልጽግና ፓርቲም ኢኮኖሚ መልሶ ለማቋቋምና የአስር ዓመት ዕቅድ ትግበራ ሥራዎች ላይ ፈርጀ ብዙ ሥራ በመሥራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር በማድረግ በአጠቃላይ የሕዝቡ ኑሮ አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ ማሻሻል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል።
ገዢው ፓርቲ ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሬት ለማውረድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊረባረብ ይገባል። ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦትና የዜጎች መፈናቀል የወቅቱ የአገራችን አንገብጋቢ ችግር እንደሆነ የአደባባይ ሐቅ ነው። ነገር ግን ለዚህ ለተጋረጠብን የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የፖለቲካ ሪፎርም በማካሄድና ዴሞክራሲን በማስፈን ብቻ ከችግሩ መውጣት የማይታሰብ ነው።
ይህን ሁሉም አካል ሊገነዘበው ይገባል። የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ እጅግ ወሳኝ ነው። ያለ ኢኮኖሚ እድገት ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ቢቻል እንኳ ዘላቂ ሊሆን አይችልም።
ሰላም ለመመለስ እና መረጋጋትን ለማስፈን መንግሥት እየተጨነቀ እንዳለው ሁሉ የኢኮኖሚ ችግሮች ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህን ወሳኝ ጉዳይ መስመር ማስያዣ ስትራቴጂዎች ሊዘጋጁ የግድ ይላል።
አገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ከየአቅጣጫው የተለያዩ አካላት አማራጭ ሀሳቦችን እያቀረቡ መሆኑ የሚበረታታ ነው ። ሆኖም በዚያው ልክ ኢኮኖሚውን ማገገሚያ መፍትሔዎችንም በዚሁ መልኩ ሁሉም ሊያዋጣ ይገባል ።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው የመንግሥት አካልም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኢኮኖሚው እንዴት ማገገም እንዳለበት ሲናገሩ ብዙም አይደመጥም።
ለኢኮኖሚ ተግዳሮቶች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ መድረኮች ብዙም አይታዩም። የኢኮኖሚ ችግሮች አገሪቱ ላጋጠማት ፖለቲካዊ እና ሰላም ችግሮች አንዱ መንስኤ መሆኑ የማያጠራጥር ቢሆንም ይህን መንስኤ ወደ ጎን የተወ መፍትሔ ችግሩን በዘላቂነት አይቀርፍም።
አገሪቱ ካለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር የዕለት ዕለት እንቅስቃሴ ኢኮኖሚውን እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚል ሊሆን ይገባል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አልፎ አልፎ የሚያቀርቧቸውን ወቅታዊ ኢኮኖሚ ነክ ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ በመደበኛ ሚዲያዎች ከሚሰጥ መጠነኛ የሚዲያ ሽፋን በዘለለ ስለ ኢኮኖሚ ብዙም ትኩረት አለመሰጠቱ አገሪቱ ከነበረችበትና ካለችበት ሁኔታ አንጻር የሚጠበቅ ቢሆንም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዳይ ግን መዘንጋት ያለበት አይደለም።
የኢኮኖሚ ጉዳይ ከአሁኑ መስመር ለማስያዝ ጥረት የማይደረግ ከሆነ በቀጣይ ጊዜያት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር በመዳመር ትልቅ ራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለው የሕዝብ ቁጥር በአንድ በኩል በረከት በሌላ በኩል እርግማን የመሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው።
ይህ በበርካታ የዓለም አገራት የታየ ነው። በትምህርት፣ በስልጠና እና በመሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በየዓመቱ ለሥራ ዝግጁ እየሆነ ያለው የሰው ኃይል ምርታማነት፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መስጠት የግድ ነው።
በአጠቃላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለአገር በረከት ሊሆን የሚችለው በአግባቡ ወደ ሥራ ተሰማርቶ ራሱን እና አገሩን የሚጠቅም ፍሬያማ ሥራ ላይ መሰማራት ከቻለ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ምርታማ መሆን ካልቻለ አደጋም ነው።
የሰው ካፒታል ከሌለ፣ ጤናማ የኢኮኖሚ እድገት ወይም የወሊድ መጠን መቆጣጠር ካልተቻለ እርግማን የመሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው። በከፍተኛ ቁጥር የሚጨምረው ወጣት ካሁኑ በአግባቡ ለመያዝ ካልታሰበበት በቀጣይ የሚያስከትለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ያለመረጋጋት ስጋት ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ ሊታይ ይገባል። ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ እንዳለ የሚያውቅ ሰው አርፎ አይተኛም።
ከአሁን አሁን ሊፈነዳ ይችላል በሚል ቦምቡን በአይነ ቁራኛ ይከታተለዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የግል ዘርፎች እና የመንግሥት አካላት ከሰላም በማስከተል ለኢኮኖሚ እድገት ብዙ ሊጨነቁ ይገባል። በቀጣይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን የሚደፍን መሆን አለበት። ሁሉን አቀፍና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማትም መሆን አለበት። የኢኮኖሚ እድገትና ልማት በተጨባጭ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለውን ድህነትን ለመቀነስ እና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ አንዱ መንገድ ሊሆን ይገባል።
በአኃዝ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሊሆን ይገባል። በሌላ አነጋገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 89 ላይ እንደተገለጸው ፍትሐዊ እና ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 /2014