አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ። ምክር ቤቱ ትላንት ባደረገው የአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሃያ ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ የህገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ለማቋቋም ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ በመመርመር አዋጅ ቁጥር 1123/2011ን በሦስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
አዋጁ የህገመንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተ ምሮና ተደራሽነትን በማስፋት ህገ መንግሥታዊ መርሆዎችንና እሴቶችን ለማስገንዘብ ሰፊ ዕድል የሚሰጥ፤ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ሁለንተናዊ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ የሚችል ዜጋና ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል፣ ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር የሚራመድና ህግና ስርዓቶችን የሚያከብር ትውልድ ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተጠቅሷል።
ከምክር ቤቱ አባላት “በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስር ይህን ሥራ የሚሠራ ራሱን የቻለ አካል እያለ እንደገና ሌላ ተቋም ማቋቋም ለምን አስፈለገ? “በሚል ለቀረበው ጥያቄ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳ ቢዋ ክብርት ወይዘሮ ፎዚያ አሚድ “የህገ መንግሥት ጥሰቶች፣ አለመግባባቶችና ግጭቶች እየተስተዋሉ ያሉት ህብረተሰቡ በህገ መንግሥቱ ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ምክንያት ለህገ መንግሥት ስርጸት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈልጓል” ብለዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በየትናየት ፈሩ