የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣውን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ ተከትሎ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰንጉዳይ እልባት ሳያገኝ ‹‹የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች›› ለተጠቃሚዎች በዕጣ ማስተላለፍ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡ ይህን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰንበአግባቡ ለመለየት ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህንን በተመለከተ ምሁራን የሚሉት አላቸው፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ደረጄ ተረፈ አዲስ አበባ እየሰፋች በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳዩን ዝም ብሎ ማየቱ ተገቢ አይደለም፡፡ በማለት የመግለጫውን ትክክለኝነት በመጠቆም፤ መፍትሔው በጊዜ እና በፍጥነት ወሰኑን ማስቀመጥ መሆኑን ይናገራሉ። መግለጫውን ተከትሎም በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ ምክረ ሃሳብ ለማስቀመጥ ተገቢ ነው የሚል ዕምነትም አላቸው።
ወደፊት ከተማውና ክልሉ እንዴት ተቀና ጅተው መሥራት እንዳለባቸው በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ የኮሚቴዎቹ አባላት ጉዳዩን የሚያውቁ ሲሆኑ፤ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማነጋገር እና የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ለውሳኔ የሚያግዝ የመነሻ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ መንግስቴ ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ጉዳይ ሌላ ኮሚቴ መቋቋሙን በመንቀፍ፤ በቅርቡ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንና የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ተቋቁሟል፤ ይህ የኦሮሚያን እና የአዲስ አበባ ጉዳይን አካትቶ ማየት ይችላል፡፡
እንዲያውም ኮሚሽኑ በቅድሚያ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለውን ችግር ቢፈታ፤ በሌሎችም ክልሎች አሉ የተባሉትን የፍትሐዊነት ችግሮችን ለማቃለል ጥሩ ተሞክሮ ይሆንለታል ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡ከዚህ ውጪ የባለስልጣናት ቡድን አቋቁሞ ችግሩን እፈታለሁ ማለት ተገቢነት የሌለው መሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ በኮሚቴው ውስጥ ባለሙያ አለመካተቱን ገልጸው፤ የባለስልጣናት ቡድን ጥናት ሊያጠና እንደማይችልና ጉዳዩ መታየት ያለበት በገለልተኛ ወገኖችና በባለሙያዎች እንጂ ይገባኛል አይገባኝም ብለው በሚከራከሩ ባለስልጣኖች መሆን እንዳልነበረበት በመናገር አሁንም ኮሚቴው ሥራውን ይቀጥል ቢባል እንኳን የገለልተኝነት ጉዳይ ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ‹‹ ኮሚቴው ለአንድ ወገን ያደላ ይሆናል፡፡›› ከሚለው ስጋታቸው ባሻገር የመቋቋሙ ህጋዊነት ላይም ጥያቄእንዳላቸው በመጠቆም፤ ችግሩ መፈታት ያለበት በኮሚሽኑ ብቻ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የነበሩት በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኦሮሞ ራስ መረዳጃ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ የኮሚቴውን መቋቋም ይደግፋሉ፡፡
እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለአገሪቷ መውደቅ ምክንያት በሚሆን ደረጃ ከበሮ እስከማሞቅ ከዘለቁ በራስ ላይ ቤት እንደማቃጠል ነው፤ ካሉ በኋላ ታስቦበትም ሆነ ሳይታሰብበት አዲስ አበባ ያለአግባብ ሰፍታለች፡ ፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ነገሮች እየከረሩ በስሜት እየተመራን በመሆኑ ኮሚቴ ማቋቋሙ ስሜትን ሊያረግብ ስለሚችል አካሄዱ ተገቢ ነው ፤ ወደ ፊት ግን ጉዳዩ በጥናት ይመለሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡
‹‹የግል ስሜትን ብቻ መከተል ከሃዲዱ እያፈናቀለን ነው፤ የአገሪቷ ህልውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጉዞው ገና ከመሆኑ አንጻርም አሁንም ድህነቱ፣ ሥራ አጥነቱ፣ ረሃቡ እንዳለ ነው፡ ፡ ሥራዎች ገና አልተሠሩም፡፡ ዓለም ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ቢደርስም ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ገበሬው የሚያርሰው በበሬ ነው፡፡ ከ20 እና 30 ዓመት በፊት የሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ አሁንም አሉ፡ ፡
አሁን አገርና ክልል በሚመሩ መስተዳድሮች መካከል ልዩነት እየታየ ነው፡፡›› በማለት፤ በዚያ ደረጃ ልዩነቶች መፈጠራቸው አስጨናቂ መሆኑንና ሌሎችም ያረገዙትን ችግር ማፈንዳት ሲጀምሩ ብዙ ነገሮች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ቀድሞ መፍትሔ ላይ መሥራት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ በእርሳቸው እምነት ለመደማመጥ ሁኔታዎችን መፍጠር ወሳኝ ሲሆን፤ ትልቁ መፍትሔ ግን ቆም ብሎ መደማመጥ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ፡፡ እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ገለፃ፤ መንግሥት ለመደማመጥ ኮሚቴ ማቋቋሙና ጎን ለጎንም ሥራዎችን መሥራቱ ትክክል ቢሆንም፤ ችግሮች ወዴት እያመሩና ሁኔታዎች በምን መልኩ እያደጉ ናቸው? የሚለው በደንብ መጠናት አለበት።
የሚወሰደው ዕርምጃ ማንን ያስከፋል? ማንን ያስደስታል? የሚለውን በደንብ መተንተን ይፈልጋል፡፡ ዝንባሌው ወዴት ያመራል? የሚለውን መዳሰስና ቀድሞ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከህገመንግሥት ተነስቶ አፈፃፀም ድረስ ያለውን ሁሉ ማየት ይጠይቃል፡፡ ወደ ፊትም ኢትዮጵያ አገር ሆና እንድትቀጥል ጥናቱ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱንም መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ዝናቡ ይርጋ በበኩላቸው አዲስ አበባ ዕድገቷ ከዘጠኙም ክልሎች እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ 55 አገሮች፣ ከአውሮፓና ከእስያ በአጠቃላይ ከዓለም ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መዲና በመሆኗም ተራማጅ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ሃሳብ ይዞ መምጣት የግድ ይላል። ሌሎች አገሮች እንዲህ ዓይነት ትልቅ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የእስያ መዲና ከተማን እንዴት አድርገው ነው የሚያሳደጉት ለሚለውም ተሞክሮ ማምጣት ወሳኝ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 59 «አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል ስለምትገኝ ልዩ ጥቅም ታገኛለች» ሲል የወደፊት መስፋፋቷንም ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ በመስፋቷ የሚጎዳ ስለሚኖር ልዩ ጥቅም እንደሚያስፈልግ አስቀምጧል፡፡
ስለዚህ ያንን መብት የሚከበርበትን መንገድ ማስተካከል እንጂ ከዚህ ወዲህ አዲስ አበባ አትሰፋም ብሎ መደምደሙ ትክክል አይደለም፡፡ ወሰኑ ሳይካለል የሚለው ከህገመንግሥቱ አንፃር በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ከመሆኑም በላይ ሳይንሳዊ መልሱ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ የሚያገኘው ልዩ ጥቅም ምንድን ነው የሚለውን በመለየት የጋራና የተናጥል ብሎ በማስቀመጥ ማንም ሳይጎዳ መብቶች ሳይጣሱ በእኩል ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ወሳኝ መሆኑን አቶ ዝናቡ ይናገራሉ፡፡
ለቀጣይ ተራማጅ የሆነና ብዙ እንደ አዲስ አበባ ዓይነት ከተሞችን መፍጠር መፍትሔ ነው የሚሉት አቶ ዝናቡ፤ ነገር ግን እስከዚያው ድረስ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ቋሚ ድንበር ያስፈልጋቸዋል ወይ? የሚለው ላይ ጥናት ማጥናት እና መወያየት፣ ክፍት ይሆናል ከተባለ ደግሞ በምን አግባብ የሚለውን ማስቀመጥ ያስፈልጋል ፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ኮሚቴዎቹ የተዋቀሩት ወሰን ለማስቀመጥም ሆነ ውሳኔ ለማስተላለፍ አይደለም፡፡
ለመወሰን ከሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን ይነጥቃሉ፡፡ ስለዚህ ኮሚቴዎቹ የዳሰሳ ጥናት አድርገው የመፍትሔ አቅጣጫ ማመላከት አለባቸው፡፡ ችግሮችን መለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የመንግሥት ግዴታ በመሆኑ አካሄዱ ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትልቅ ውክልና ያላቸው በመሆኑ እነርሱ ይወስናሉ፡፡ ዋናው ነገር የሚሰራው የነበረውን ፍቅርና አንድነት የቀጣዩን ትውልድ ህይወት በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በምህረት ሞገስ