አዲስ አበባ፡- የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የደረሱበትን የዕድገት ደረጃ መሰረት ያደረገ አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ገለጸ። የብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረጊ ዮርጊስ አብረሃ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የብሮድካስት አገልግሎት አዋጁ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃ የደረሱ በትን ዕድገትና ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ እንዲሆን በአዲስ መልክ በመዘጋጀት ላይ ነው። እንደ ዳይሪክተሩ ገለጻ በሥራ ላይ ያለው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ብቸኛ በነበረበት ጊዜ የወጣ አዋጅ ነው።
በአሁኑ ወቅት በህዝብ ባለቤትነት የሚመሩ ከአሥር በላይ የራዲዮና ዘጠኝ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመኖራቸው ምንም ዓይነት የግል ብሮድካስት አገልግሎት ካልነበረበት ወቅት በመውጣት 12 የግል ሬዲዮና 18 የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም 48 የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
ስለዚህ ነባሩ የብሮድካስት አዋጅ እነዚህን ሁሉ ለማስተዳደር አመቺ ስላልሆነ ካለው ዕድገት ጋር መጣጣም አለበት።ወቅቱ ያመጣው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ለመገናኛ ብዙሃን ዕድገት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ያሉት ዳይሪክተሩ፤ ከዚህ ጋር የሚጣጣም የመገናኛ ብዙሃን ሕግና አሠራር ስለሚያስፈልግ እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ ሲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ከተወያዩበት በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በ1999 ዓ.ም. የወጣውና በሥራ ላይ ያለው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ በተለያዩ ሞገዶች አማካይነት በተለመደው መንገድ የሚያሰራጩ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ይህ አዋጅ ለብሮድካስት ባለስልጣን በኢንተ ርኔት አማካይነት ወደ ህዝብ የሚደርሱትን የራዲዮና ቴሌቪዥን ስርጭቶችንና ማህበራዊ ድረ ገጾችን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን አልሰጠውም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በየትናየት ፈሩ