ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውና በርካታ መራጮች ድምፅ የሰጡበትን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን ተከትሎ ብልፅግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረትና ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የሚያስችለውን ድምፅ ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡
ፓርቲው ታሪካዊ ያለውን የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔውንም ‹‹ከፈተና ወደ ልዕልና›› በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም አካሂዷል።በጠቅላላ ጉባዔውም የፓርቲው ጠንካራና ደካማ ጎኖች በጥልቀት መገምገማቸው ተሰምቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ለመሆኑ የፓርቲው ስኬታማ ተግባራት እንዴት ይገለፃሉ ? ድክመቱስ እንዲሁም ቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ አበይት የቤት ሥራዎች ምንድን ናቸው የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የተለያዩ ምሁራንን አነጋግሯል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራ፣ ፓርቲው ከሁሉ በላይ አካታችነት ባህልን ማስተዋወቁ የሚደነቅበት ጠንካራ ጎኑ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ላለፉት 27 አመታት በመንበረ ስልጣን የነበረው ኢህአዴግ አራት ብሔራዊ ድርጅቶችን ብቻ በማሳተፍ ሌሎችን ‹‹አጋር›› በሚል በአገር ጉዳይ የዳር ተመልካች በማድረግ አንዱን ቤተኛ ሌላውን ባይተዋር ያደረገ የፖለቲካ ትግበራን ይከተል እንደነበር ያስታውሳሉ።‹‹አጋር›› የተባሉት ድርጅቶችም ሕገ-መንግስቱን ሙሉ በሙሉ በሚጣረስ መልኩ በአገሪቱ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ምንም አይነት ሚና ሳይኖራቸው መቆየታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጀምሮ አሰራሩን በመቀየር በፓርቲው ውስጥ በሚነሱ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነቱን ዕድል ሁሉም ክልል እንዲያገኝ መደረጉን የሚያመላክቱት አቶ ሰለሞን፤ ‹‹በዚህም ፓርቲው ሁሉን አሳታፊና አካታች መሆኑን በተግባር አሳይቷል፤ ይህ ለአገራችን የፖለቲካ ሥርዓትና ምህዳሩ መስፋት እጅግ ተስፋ ሰጪና እንደ ጠንካራ ጎን የሚወሰድ ነው›› ይላሉ፡፡
የብልፅግና ፓርቲን ጉዞና ውሳኔ በሚመለከት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ከቀናት በፊት ቆይታ ያደረጉ የክልል መሪዎችም፤ ‹‹አሸባሪው ሕወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት አጋር በሚል የተገፋን ፓርቲዎች ጉባዔዎችን ሳይቀር እንዳንሳተፍ ስንገለል ቆይተናል፣ አሁን ግን በውህድ ፓርቲው ብልጽግና ዘመን ከመገለል ወጥተን በተግባር በእያንዳንዱ ጉዳይ የሃሳብና የውሳኔ ሰጪነት ዕድል አግኝተናል ነው›› ያሉት፡፡
ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በፊት ብልፅግና ፓርቲ ምርጫውን ማሸነፍ ከቻለ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በመንግስቱ መዋቅር ውስጥ የተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ሰጥቶ እንደሚያሳትፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፓርቲው ሥልጣን በያዘ ማግስት ካከናወናቸው ተግባራትና ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ጠንካራ ተብሎ የሚወሰደው የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከመግፋት ይልቅ አብሮ መሥራትና አንዳንዶቹም በመንግስት አስተዳደር መዋቅር ውስጥ ማካተት ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው።
ይህን እሳቤ የሚደግፉት አቶ ሰለሞንም፤‹‹ፓርቲዎቹ የተለያየ እሳቤ ሊኖራቸው ቢችልም፤ በምንወዳደርበት ቦታ እንወዳደራለን፣ በምንተባበርበት ቦታ እንተባበራለን በሚል ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማቀፍ በሥልጣን መዋቅር ውስጥ ተሳታፊ በማድረጉ አገርን በጋራ ማስተዳደር ማስመልከቱ እጅግ በጣም የሚያስደንቀው ነው›› ይላሉ፡፡
አቶ ሰለሞን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ከመስራት ባሻገር አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር የመፍታት እርምጃ በተጨማሪ ሊደነቅ የሚገባው ተግባር መሆኑን ያነሳሉ።
ይህን ማድረግ ጥቅሙ ከግለሰብና ከፓርቲ አንጻር የሚታይ ሊሆን እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።በተለይም አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት ግቡን እንዲመታ ወሳኝ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ምክክር ለማድረግ ዋዜማ ላይ መሆኗንና ምክክሩም ኢትዮጵያን ለማሻገርና የተሻለች አገር ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር የሚገልፁት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ፣ የፖለቲካ አመራሮችና ግለሰቦች ከእስር መፍታትም ምክክሩ ሙሉና ውጤታማ እንደሚያደርገው ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ሌሎች አገራትም በብሄራዊ ምክክር መግባባት ለመፍጠር የቻሉት በመሰል ተግባር ነው›› ይላሉ፡፡ የተለያዩ ምሁራን ፓርቲው በሕዝብ አስተዳደር ሚናው በተለይም የዲሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር ረገድ የሚደነቅ ሥራ መስራቱን ሲናገሩ ይደመጣል።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሰለሞን ተፈራም፤ በዚህ እሳቤ ላይ ክርክር የላቸውም፡፡ ለአብነት ምርጫ ቦርድና የፍትህ ተቋማት ተስፋ ሰጪ በሆነ መልኩ በገለልተኛነት ሥራን የሚጠየቅና የሚሞገት መሆን መጀመሩንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአሁን መንግስትን በተደጋጋሚ ሲከስ ማስተዋላቸውን የሚጠቁሙት አቶ ሰለሞን፤ ‹‹ይህ ቀደም ሲል የማይታሰብ ነበር አሁን ተለውጦ ተመልክተናል።በቂ ነው ማለት ባይሆንም ሊበረታታ የሚገባው መልካምና ተስፋ ሰጭ ለውጥ ነው›› ይላሉ፡፡
ከፖለቲካ ምህዳሩ ባሻገር ‹‹በፓርቲው አመራርና በመላው ኢትዮጵያዊያን ትብብር በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻም ከስኬታማ ተግባራት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው›› የሚሉ በርካቶች ናቸው።የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኪያ ጸጋዬም፤ ፓርቲው ሕግን በማስከበር ረገድ በተለይ የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን እኩይ ተግባር በመቀልበስ ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት ከሁሉ ቀድሞ ሊደነቅለት የሚገባ ክንውኑ ያደርጉታል፡፡
የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት እጅግ በጣም ዘግናኝና አገርን ለብተና መዳረግን አላማው ያደረገ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ኪያ፤ ‹‹ይሁንና መንግስት የአሸባሪ ቡድኑን የአጥፊነት አላማ በማክሸፍና በመቀልበስ አገርን ከመፍረስ በመታደግ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል፣ ይህም በእጅጉ የሚደነቅ ነው›› ይላሉ፡፡ይህ ማለት ግን የሕወሓት ስጋትነት አሁንም ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
የአሻባሪው የሕወሓት ቡድን እኩይ ተግባር ከአገር ህልውና ፈተናነቱ ባሻገር ፓርቲው ባለፉት አመታት ውጥኑን በሚፈለገው ፍጥነትና ልኬት እንዳያስኬድ በእጅጉ ስለመገዳደሩ የሚያመላክቱት የሕግ ባለሙያው፣ በዚህ ሂደት ውስጥም የተለያዩ የሕግ ማሻሻያና ለውጦችን ማስተዋወቅ መቻሉን ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ኪያ ጸጋዬ ገለጻም፤ ፓርቲው አገር ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት አመታት ከ10 እና ከ20 አመታት በላይ በይደር የቆዩ ሕጎች ተሻሽለዋል፤ ተለውጠዋል።ለአብነትም ስድስት አስርት አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ተሻሽሎ እንዲፀድቅ ተደርጓል።
የአስተዳደር አዋጅ፣ የግልግል ዳኝነት አዋጅ፣ የኢንቨስትመንት አዋጅ፣ በተለይ በጥብቅና ረገድ ላለፉት 20 አመታት ሲንከባበል የነበረው የፌዴራል የጠበቆች አስተዳዳር አዋጅ ወጥቷል።የሲቪክ ማኅበራት አዋጅ እንዲሁም የምርጫ ሕግና ደንብና መመሪያ ወጥቷል።የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት አዋጅ ወጥቷል፡፡
‹‹አፈፃፀሙ ተከታይ ቢሆኑም ሕጉ መሻሻል ብሎም መለወጥ በራሱ ትልቅና ወሳኝ እምርታ ነው›› የሚሉት አቶ ኪያ፣ እነዚህን ሕጎች ወደ ተግባር ማውረድና በአግባቡ መተግበር የፓርቲው ቀጣይ ወሳኝ የቤት ሥራ ስለመሆኑም አፅንኦት ይሰጡታል፡፡
ከሕግ ለውጥና ማሻሻያዎች ባሻገር የባለሙያዎች ነፃነትን በሚመለከት ውጤታማ ተግባራት ስለመከናወናቸው የሚጠቁሙት አቶ ኪያ፣ ፍርድ ቤቶችና ባለሙያዎች ነጻ ፈቃድ ማግኘታቸውን፣ የጠበቆች ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ መቋቋሙና ቀደም ሲል ባልተለመደ መልኩ የፍትህ ሚኒስቴር ከፓርቲ ነጻ በሆነ መልኩ መምጣቱን በጠንካራነት ከሚገመገሙ ተግባራት መካካል በዋቢነት የሚመደቡ መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ ስለ ሕግ አፈፃፀም ሲነሳ መንግስት የሚወስዳቸው የክስ ማቋረጥ ሂደቶች በአድናቆት የሚመለከት እንዳለ ሁሉ የሚነቅፉም በርካቶች ናቸው፡፡
አቶ ኪያ ደግሞ ውሳኔን ከአሉታዊ ይልቅ አዎንታዊ ጎኑ ከሚመለከቱት ወገን ናቸው።‹‹መጀመሪያ ላይ ውሳኔውን ለመቀበል የሚከብድ ነው፤ ይሁንና ውሳኔውን ከሕግ አግባብ ብቻ መመልከት በቂ አይደለም።በሌሎች አገራትም ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ሲባል መሰል ውሳኔ ይወሰናል›› ይላሉ።
ውሳኔው የተመለከታቸው እንዳሉ ሆነው አሁንም ጉዳያቸው በሕግ ሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውንም ታሳቢ ማድረግ ምስሉን ሙሉ እንደሚያደርገው የሚጠቁሙት የሕግ ባለሙያው፤ ውሳኔውን ተከትሎ በተለይ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ሴራን ከመቀልበስ ጀምሮ የተገኙ የተለያዩ ድሎች እርምጃው ውጤታማ እንደነበር በቂ ምስክር የሚሰጥ ስለመሆኑም አፅንኦት ይሰጡታል፡፡
ፓርቲው በሕግ አፈጻጸምና ቁጥጥር ረገድ ጠንካራ ጎኖች የማስመልከቱን ያህል ደካማ የሆነባቸውም በርካታ ማሳያዎች አሉ ሲሉ የሚሞግቱ አሉ፡፡ለዚህ እሳቤያቸው አንዱ ማሳያ አድርገው የሚጠቅሱት ደግሞ ቅጥ ያጣ የሙስና ወንጀልን ነው፡፡
በዚህ ረገድ አስተያየታቸውን የሚያጋሩት አቶ ኪያም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ሌብነት የብሄራዊ ደህንነት ዋነኛ አደጋና ስጋት ነው ማለታቸው ያስታውሳሉ።በአሁን ወቅት በታክስ፣ በመሬት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በፕሮጀክት አሰጣጥና በተለያዩ ሴክተሮች ሌብነትና ሙስና እጅጉን ስር ሰዶ እንደሚስተዋል ያመላክታሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ወቅት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሌቦችና የአገርን ህልውና ለአደጋ የሚያጋልጡ አጭበርባሪዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን የሚጠቁሙት የሕግ ምሁሩ፤ እነዚህ ኮሎምቢያና ሜክሲኮ በመሳሰሉ አገራት እንደሚስተዋለው አይነት በትልልቅ ሌብነት ላይ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች በቀላሉ የሚታዩ እንዳልሆኑም ይስረዳሉ።
እንደእነዚህ አይነት ሌቦች አቅም ያላቸው፣ የታጠቁ የተደራጁና ከመንግስት ውስጥ ሰው ያላቸው ስለሚሆኑ በሕግ ተፈላጊ ቢሆኑ እንኳን በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ ሊከፍቱ የሚችሉ ስለመሆናቸውንም ያስገነዛባሉ፡፡ ‹‹የሌብነት ተግባር በዚህ ከቀጠለ አገሪቱ በጥቂት ባለሃብቶች ቁጥጥር ስር መሆኗ አይቀርም።
በውጤቱም መንግስት ሽባ ይሆናል፣ አገርም ይፈርሳል፣ በዚህ ወንጀል ብዙ አገራትም ፈርሰዋል›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ አስከፊው ሳይመጣ የችግሩን ጥልቀት በመረዳት ከወዲሁ ጠንካራ ተግባራትን ማከናወን የግድ እንደሚልም አጽንኦት ይሰጡታል፡፡
ፓርቲው ፀረ ሌብነት መሆኑን ከቃል በላይ በተግባር ማስመልከት እንደሚገባም የሚያስገነዝቡት አቶ ኪያ፤ ‹‹ሌላው ቀርቶ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ባለሥልጣን ሃብት አስመዝግቡ ተብለው ሲለመኑ አመታት ተቆጥረዋል።መንግስት ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል ቁርጠኛ ከሆነ መሰል እርምጃዎችን በአደባባይ ተራምዶ ማስመልከት የግድ ይለዋል።
ሁሉም ሊጀምር የሚገባው ከላይ ነውም›› ይላሉ።ከዚህ ጉባኤ ማግስት ሊሆን የሚገባውም ይሕ ስለመሆኑ አጽንኦት ይሰጡታል። ከዚህ ባሻገር ፓርቲው የሕግ ትግበራውን ግልፅ የማድረግ ችግር እንዳለበት የሚጠቁሙት አቶ ኪያ ‹‹ሌላው ቀርቶ ከተማናና ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መልኩ የተደበቀ ዘይት በቁጥጥር ስራ ዋለ ሲባል በዜና እንሰማለን እናያለን ይሁንና ዘይቱን የደበቀው ማነው፣ ፍርድ ቤት መቼ ቀረበ፣ ክስ ተመስርቶበትስ ምን ውሳኔ ተላለፈበት የሚል ዜና አናሰማም አናይም፤ ባለፉት አመታት አንድም ለፍርድ የቀረበና የተፈረደበት ሕገ ወጥና ስግብግብ ነጋዴ አላየንም›› ይላሉ።
ፓርቲው ሕግን በአግባቡ ለመተግበራን ለማስፈፀም ቁርጠኛ ከሆነ መሰል አስተማሪ ውሳኔዎችንም በአደባባይ ሊያሳውቅ እንደሚገባም ያሰምሩበታል፡፡ ፓርቲው በቀጣይ ምን ማድረግ አለበት በሚለው ላይም አስተያየት ሰጪዎቹ የሚሉት አላቸው።‹‹ከመቶ ሚሊየን በላይ ሕዝብና ታላቅ አገር የመምራት ኃላፊነት የተረከበና የሕዝብ አደራ ያለበት ፓርቲ ነው።ይህ እንደመሆኑም ራሱን በተቀበለው ኃላፊነት ልክ ማተለቅ አለበት›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬ፤ አመራሮቹም በዚህ ልክ የበቁ መሆን እንዳለባቸውም ያሰምሩበታል፡፡
በተለይ እርስ በእርስ የመጋተትና ዋልታ ረገጥ ሃሳቦች ፓርቲውን ሲያምሱት እንደሚስተዋል የሚገልጹት አቶ ኪያ፣ ፓርቲው በመጪዎቹ አመታት አላማና ግቡን ለማሳካትና በህዝብ ዘንድ ተመራጭ ሆኖ ለመቀጠል በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮቹን የግድ ማረምና ልባቸው ለሁለት የተከፈለ፣ አዝማሚያ የሚጠብቁ፣ በትክክልና በሚገባው ልክ ለፓርቲው ቁርጠኛ ያልሆኑ አመራሮችን ማጥራት እንዳለበትም አጽንኦት ሳይሰጡት አላለፉም፡፡ እንደ አቶ ኪያ ገለፃም በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት ነጋዴዎች አሉ።
ግጭትን በማነሳሳሳትና በማፋፋም ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚታትሩ አሉ።በዚህ ረገድ በቂ የሆነ የክትትልና የግምገማ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።በአሁን ወቅት ሸኔ ከዋና ከተማዋ በቅርብ ርቀት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፤ ይህ ፈጣን እልባት የማይሰጠው ከሆነና ወደ ሰላማዊ መንገድ ካልሆነም ወደ ሕግ የሚመጡበት አግባብ እስካልተፈጠረ አደጋው እጅጉን ከፍተኛ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ሰላምና ጸጥታን በማስከበር ረገድ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ ስለመሆናቸው ያመላከቱት የሕግ ምሁሩ፣ ለዚህ ደግሞ የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት ትብብርና መናበብ ብሎም ጠንካራ የሆነ የሕግ አስከባሪ ሰራዊት መገንባት የግድ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በሕግ አፈጻጸም ረገድ ግለሰቦች ተገምግመው ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ የብሄር መታወቂያቸውን የሚያወጡና የሚሸሸጉበት አካሄድ ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባና ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደህንነት ሲባል በተለያዩ ክልሎች ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ የታጠቁና የሚንቀሳቀሱ ሃይሎን አደብ ማስገዛት አለበት ነው ያሉት። በተለይ ሌብነትን በመከላከል ረገድ መገናኛ ብዙኃንም የምርመራ ጋዜጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ የግድ እናደሚላቸው ሳይጠቁሙም አላለፉም፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሰለሞን ተረፈ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በሚፈለገው ልክ የፖለቲካ አመራሮች በየጊዜው ገምግሞ አስቸካይ እርምት ሊወስድ እንደሚገባው በተለይም ቀደም ሲል በነበረ አመለካካት ሁለት ሃሳብ የሆኑ ተቸክለው የቀሩ አመራሮቹን ማጥራትና አዲስ ትውልድን ወደ አመራር ማምጣትና የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት ነው አፅንኦት የሰጡት፡፡
አስተያየታቸው የሰጡን ምሁራን ሚሊዮኖች በተፈናቀሉበትና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተባባሱ በመጡበት በዚህ ወቅት የገዥውፓርቲ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ መግባት፣ በሕይወት የመኖር ዋስትና፣ የመንቀሳቀስ፣ ሃብትና ንብረት አፍርቶ የመኖር መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ የቤት ሥራ እንዳለበትም ጠቁመዋል። በኢኮኖሚ ረገድም ገዥው ፓርቲ ብልጽግና በተለይም በኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በመቆጣጠርና በመከላከል ረገድ ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ የግድ እንደሚለው አስምረውበታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2014