መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አንድ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ።በእለቱ፤ የአገሪቱ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ጣቢያዎች በሙሉ መደበኛ ስርጭታቸውን ለጊዜው ገታ አድርገዋል።
ይልቁንም በይዘቱ ለየት ያለ ትልቅ፣ ትንሹን፣ የወንድ፣ ሴቱን፣ የተማረውን፣ ያልተማረውን፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን፣ የከተሜውን የባላገሩን በአጠቃላይ የሁሉንም ማኅበረሰብ ልብ ሰቅዞ የሚይዝና የሚያሞቅ ፕሮግራም በሁሉም የቴሌቪዥን መስኮቶች እና ሬዲዮ ጣቢያዎች እየተላለፈ ነበር።
ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት፣ ባለሃብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ ተሰባስበዋል።
በእዚያ ቦታ መሰባሰባቸው ያለምክንያት አልነበረም።የዜጎች የዘመናት ቁጭት እና ህልም የሆነውን አባይን ለመገደብ ጊዜውና ቦታው ያኔ እና እዛ በመሆኑ ነበር። በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ በቦታው ለተሰበሰቡት እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ስርጭት ለዘመናት በተስፋ ሲጠባበቁት የነበረውን ብስራት አበሰሩ።
እግረመንገዳቸውንም ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲህ ሲሉ መልዕክት አስተላለፉ ‘‘በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በገንዘባቸው፣ በንብረታቸው፣ በእውቀታቸው የሚገነቡት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ግድብ በመሆኑ የህዳሴ ግድባችን መሀንዲሶች እኛው፣ ግንበኞችና ሠራተኞች እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዟችን ባለቤቶች እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው።
ለልማት ቆርጦ የተነሳው ሕዝባችን የሚሳነው ነገር የለም።ድህነትና ውርደትን ያለ አንዳች ጥርጥር ታሪክ እናደርጋለን።’’ በእርግጥ ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ተብሎ የሚታወጀው የውጭ ወራሪ ሲመጣ ወይም ሌላ የአገርንና ሕዝብን ህልውና የሚፈታተን ነገር ሲያጋጥም መሆኑ የማያጠያይቅ ሀቅ ነው።በጊዜው ግን ወራሪም ሆነ ወረርሽኝ በአገር ላይ አልነበረም።
አገርም እንደወትሮው እንደታፈረችና እንደተከበረች ነበረች።ያንን መሰሉን አዋጅ እንዲያስተላልፉ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ያስገደዳቸው ምክንያቶች የሉም ብሎ መደምደምም አይቻልም።ብዙ ገፊ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል።ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
1ኛ. ከማህጸኗ ፈልቆ በመንገዱ ያገኛቸውን ወንዞች ሁሉ እያስገበረ የሚጓዘው እንደ ስሙ ትልቅነት በግብሩ እናት አገሩንና ሕዝቡን ያልጠቀመውን ይልቁንም ውሸታም የሆነውን ተፈጥሮ የለገሰቻትን አንጡራ ሀብቷን ለመገደብና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፤
2ኛ. ኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ከድህነት ለመውጣት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየት ስትጀምር የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አባዜ እስከ ዛሬም ድረስ የተጠናወታቸው ታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም ስጡኝን እንጂ እንካችሁን የማታውቀውን ግብፅን የዘመናት እኔ ብቻ ልጠቀም እራስ ወዳድነት ጫና ለመቋቋም፤
3ኛ. ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት ስትነሳ ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት በብድር፣ ወይም ከለጋሽ አካላት በልገሳ እንዳታገኝ በተለያየ አጋጣሚ ግብፅ አስቀድማ ሰርታ ስለነበር ያን መሰሉን አዋጅ ወይም ጥሪ ከማስተላለፍ ውጭ በሌላ አማራጭ ኢትዮጵያ ለመገንባት ያሰበችውን ግዙፍ ግድብ እውን የምታደርግበት አማራጭ ስላልነበራት፤
4ኛ. ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ከተያያዝንና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነን ከሠራን የማንችለው አንዳችም ነገር አለመኖሩን ለመላው ዓለም ለማሳየትና የማንንም ጣልቃ ገብነት በፍጹም የማንፈልግና የማንታገስ መሆኑን በአጽንኦት ለመግለጽና ሌሎችንም በርካታ ምክንያቶች መደርደር ይቻላል።
እዚህ ላይ የግብፅ ሴራ ፍሬ አላፈራላትም ብሎ መደምደም አይቻልም፤ በከፊልም ቢሆን ተሳክቶላት፤ ፍሬያማ ሆናለች።ለዚህ ማሳያው ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ በብድርም ሆነ በልገሳ እንዳናገኝ ያደረገችው ጥረት ተሳክቶላት ወዳጅ ያልናቸው አገራት ሳይቀሩ ጀርባቸውን ሰጥተውናል።
ይህ ክስተት ሁሉን ለእኔ ለምትለው ግብፅ ሰርግና ምላሽ ሳይሆንላት የቀረ አይመስለኝም።ምክንያቱም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አይነቱን አይደለም በኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር ተወዳዳሪ የማይገኝለትን ግዙፍ እና ውስብስብ ፕሮጀክት ያለውጭ እርዳታና ድጋፍ በኢትዮጵያውያን አቅም ብቻ ለመስራት መሞከርም ሆነ ማሰብ እብደት ነው ብላ ስለምታስብ።
እዚህ ጋር ነው የራስ ወዳዷ ግብፅም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን በወጉ ካለማወቅና ታሪክን ካለመረዳት የተነሳ ስህተታቸው የሚጀምረው። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያንና ምስማር በተ መቱ ቁጥር እየጠነከሩ እንደሚሄዱ ከራሳችን ከኢትዮጵያውያንና ከጥቂት አገራት በስተቀር የገባው ያለ አይመስልም።
ዳሩ ግን እውነታው ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን ያከበራቸውን የሚያከብሩ እንደ ማር ጣፋጮች፣ ዝቅ ብለው የሚታዘዙና ትሁቶች የመሆናቸውን ያክል ልግዛችሁ፣ ልርገጣችሁ ብሎ ላሰበ ከብረት የሚጠነክሩ፣ እንደ እሬት የሚመሩ፣ አትችሉም የሚላቸውን የበለጠ እልህ ውስጥ በመግባት ችለው ለማሳየት የማይወጡት ዳገት፣ የማይወርዱት ቁልቁለት፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።
ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህያው ምስክር ነው። በራሳችን አቅም የጀመርነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያስተናግድም እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ዛሬ ላይ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ላይ በመድረስ የሁላችንም ተስፋና ኩራት ለመሆን በቅቷል።
መንግስት ላቀረበው ጥሪ ኅብረተሰቡ ምላሽ የሰጠበት አግባብ ከወትሮው የተለየና አስገራሚ ነበር።ለወትሮው በፖለቲካ አመለካከት፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነቶችን ያስተናግድ የነበረው ኢትዮጵያዊ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ምንም አይነት ልዩነት ሳይፈጥር ለግድቡ ግንባታ አቅሙ እንደፈቀደለት ድጋፉን አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል።
ከመንግስት ጥሪ ጎን ለጎን የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ሌሎችም እንወክለዋለን፣ ይደግፈናል ወይም ተከታያችን ነው ላሉት የማኅበረሰብ ክፍል የመንግስትን ጥሪ በመቀበል የበኩሉን ድጋፍ እንዲያበረክት ያላሰለሰ ቅስቀሳ አካሂደዋል።
እዚህ ላይ አንድ የሃይማኖት አባት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ገንብቶ ማጠናቀቅ የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት የተጠቀሙበትን ቃላት በአስረጅነት ማስታወስ አስፈላጊ ይሆናል።‘‘ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ በማህፀን ካሉ ህጻናት እና በመቃብር ካሉ ሙታን በስተቀር የማይመለከተው ሰው የለም’’ በማለት ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
አንድ ሌላ አባት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የማይከፍሉት መስዋዕትነት እንደሌለ ሲገልጹም ‘‘ደማችንን የሲሚንቶ ማቡኪያ አጥንታችን ብሎኬት አድርገን ታላቁ ህዳሴ ግድባችንን ገንብተን እናጠናቅቃለን’’ በማለት ነበር የማይናወጥ አቋማቸውን የገለጹት። ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በከተማ የሚኖሩ ወላጆች ከልጆቻቸው የእለት ጉርስ ላይ በመቀነስ አርሶ አደሩም ለዘር ያስቀመጠውን እህልና የቀንበር በሬውን ሳይቀር በመሸጥ አልኝታነቱን ቦንድ በመግዛት፣ ስጦታ በመለገስ፣ ሌሎች ቁሳቁሶችን በማበርከት አሳይቷል።ከዚህ በተጨማሪም ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በከተማና በገጠር የሚኖሩ ዜጎች በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ በንቃት በመሳተፍ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የበጎ ፈቃድ ሥራ አከናውነዋል።
ረጅም ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀምራል እንደሚባለው በራሳችን አቅም መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል እናሳካዋለን ብለን ቆርጠን መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም አሀዱ ብለን የጀመርነው ግድባችን ንስር እንቁላሏን ፈልፍላ ጫጩት እስከሚሆን ለአንድ አፍታም ከእይታዋ እንደማይርቅ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ፈተና ያፀናው ፕሮጀክት!! ለአፍታም ቢሆን እይታቸውን ከግድባቸው ላይ ሳይነቅሉና ያላሰለሰ ድጋፋቸውን በማበርከት ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ችሏል።
በእርግጥ በዚህ ሂደት ውስጥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን እድገት በአይኔ ከሚያሳየኝ ሞቴን እመርጣለሁ ለሚሉ አንዳንድ ግለሰቦችና አገሮች በደስታ ያሰከረ፣ ብዙኃኑን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፋና ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉትንም በግድቡ ላይ ጥለውት የነበረውን ተስፋ አስቆርጦ ጉዟቸውን በአጭሩ እንዲቋጩ ያስገደደ ክስተት አስተናግዷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካስተናገዳቸው ፈተናዎች ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀመጠው ፕሮጀክቱ አሀዱ ተብሎ ሲጀመር በአምስት ዓመትና በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ቢባልም ስምንት ዓመታትን ቆይቶና ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ቅርጥፍ አድርጎ ከበላ በኋላ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከዛሬ ነገ ግድቡ ተጠናቆና ኃይል አመንጭቶ ምስራቅ አፍሪካን በብርሃን ያጥለቀልቃታል፣ ሻማን ለልደት ብቻ እንጠቀማለን፣ ኩራዝ ደግሞ ወደ ሙዚየም አስገብተን ለልጆቻችን ድሮ ድሮ ኩራዝ የሚባል በላምባ የሚሰራ፣ ለመብራትነት የሚያገለግል፣ ጭሱ አይን የሚያቃጥል፣ ብርሃኑ እምብዛም ያልሆነ መሳሪያ ነበር፤ ይኸው በእኛ በወላጆቻችሁ ብርታት ዓባይን ገድበን ራትም መብራትም በማድረግ ለእናንተ ለልጆቻችን አወረስናችሁ እያልን ታሪክ ሰሪም ነጋሪም እንሆናለን ብለን በጉጉት በምንጠባበቅበት ወቅት የግድቡ ግንባታ የሲቪል ሥራዎች 82 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች 25 በመቶ፣ እንዲሁም የብረታ ብረት ሥራዎች 13 በመቶ፣ በአጠቃላይ የግድቡ ሥራ አፈጻጸም ከ65 በመቶ እንዳልዘለለ እና ገንብቶ ለማጠናቀቅም ተጨማሪ ከአምስት ያላነሱ ዓመታትና ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ የሚገልፀው መርዶ ይፋ ሆነ።
ይህ ክስተት ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆጃችን ጭምር የሀዘን ማቅ ያከናነበ ክስተት ነበር። ሌላው የህዳሴ ግድብ ፈተና ሆኖ እስከዛሬም ድረስ መፍትሄ ሳያገኝ የዘለቀው የሦስትዮሽ ድርድሩ ነው።
ኢትዮጵያ 85 በመቶ ባለቤት በሆነችው የዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ገንብታ ለመጠቀም የማንንም ችሮታም ሆነ ይሁንታን የመጠየቅ ግዴታ የለባትም። ነገር ግን የራሷን ጥቅም ባስጠበቀና የሌሎችንም በማይነካ መልኩ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ አድርጋ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ለድርድር ብትጋብዝም አገራቱ በተለይም ግብፅ በአንድ በኩል የዲፕሎማሲን በሌላ በኩል የፀብ አጫሪነትን ሁለት ምርኩዞች ተደግፋ ድርድሩ መቋጫ ሳያገኝ ዓመታትን አስቆጠረ።
ይህ ችግር ለኢትዮጵያ የድርድሩን ፋይል ዘግታ ሙሉ ትኩረቷን በስራዋ ላይ እንዳታደርግ አድርጓታል። በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም አልቀረም።
ይኸውም አብዛኛው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለግድቡ ያደርጉ የነበረውን የተለያዩ ድጋፎች በመቀነስ የተወሰኑት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በማቋረጥ ለመከላከያ ሠራዊትና በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማዋላቸው ለግድቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል።
በሌላ በኩል በተለይ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ትኩረታቸው ወደ ጦርነቱ በመሆኑ ለግድቡ የሚሰጡት ሽፋን ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነበር ለማለት ያስደፍራል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችም በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያልተካተቱ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ግንባታውም ሆነ የሚደረገው ድጋፍ ለአፍታም ቢሆን ሳይገታ የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በስኬት አጠናቆ የመጀመሪያ የሙከራ ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ ሆኗል።
ዕድሜ ይስጠን እንጂ ሙከራ ብቻ ሳይሆን ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል አመንጭቶ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ራትም መብራትም የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።ቸር እንሰንብት!::
ጉጉ ከአባይ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2014