“መሸምደድ የሚባል ነገር አልወድም። ሽምደዳን በጣም እጠላለሁ” – ተማሪ ናታኒም በላይ
“ዛሬ” ዛሬ ነው፤ ምናልባትም ከጊዜ አጠቃቀም አኳያ “አሁን” የምንለው። ያም ሆነ ይህ፣ “ዛሬ”ም እንበለው “አሁን” በ”ትናንት” እና በ”ነገ”፤ ወይም፣ በ”ቅድም” እና “በኋላ” መካከል ያለ ወሳኝ የጊዜ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ከተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ አኳያ ግን ለ”ነገ” ቀዳሚውን ትኩረት ሰጥተነዋልና ምህዋራችን፣ የምንሽከረከርበት ኦርቢት እሱ ይሆናል ማለት ነው (የዘርፉ ሊቃውንትም ይረዱናል ብለን እናስባለን)። ለዚህ ደግሞ ዐቢይ ምክንያቱ እውቁ የትውልድ ሥነ ምግባር ቀራፂ አባባ ተስፋዬ (ተስፋዬ ሣህሉ) “ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች!!!” ማለታቸውን ማስታወሳችን ነውና አንባቢ ይህንን ዘመን ተሻጋሪ አባባል በአእምሮው ጓዳ ይዞ አብሮን ይዘልቅ ዘንድ እንጠይቃለን። ፍልስፍናው “shaping the world of tomorrow with Futurism” እንዲል፣ ብሩህ ተመኚ ፊውቸሪስቶች ከተባልንም ጥሩ። (ጣሊያናዊው ባለቅኔ ፊሊፖ ቶማሶ ማሪኔቲ (22 ዲሴምበር 1876 – 2 ዲሴምበርr 1944) እንዴት ነህ፣ ሰላም ነህ?)
ዛሬ በዚህ አምድ ላይ የሚኖረን ቆይታ ከእንግዶች ጋር ነው። እንግዶቹም “ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች!!!” (“ፍሬዎች” የሚለው “መሪዎች” ከሚለው ጋር በተለዋዋጭነት እንዲታይ ያስፈልጋል) በሚለው ወርቃማ አባባል ሊገለፁ የሚችሉ፤ ወይም፣ የሚገባቸው ናቸው። በመሀል 4 ኪሎ በሚገኘው “የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ” (ትምህርት ቤቱንና አጠቃላይ የትምህርት አሰጣጡን … በተመለከተ ባለፈው ሳምንት በዚሁ አምድ ላይ “የመጪው ዘመን ሳይንቲስቶችን ከቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ” በሚል ርእስ ያሰፈርነውን ጽሑፍ ይመለከቷል) ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ፤ መለየት አይቀርምና በ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ምክንያት ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከሚወዱት ትምህርት ቤት፣ መምህራን፣ “አብሮ አደጎቻቸው”ና የተቋሙ ማህበረሰብ የተለዩ ብርቅዬ ተማሪዎች ናቸው።
አላዛር ተካ እና ናታኒም በላይ ይባላሉ። ሁለቱም በወሰዱት የማትሪክ ፈተና (የ2013 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና) “ሰቃይ” ሲሆኑ፤ ከራሳቸውም ባለፈ ለትምህርት ቤቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ነጥብ ያስቆጠር ዘንድ ምክንያት የሆኑ ተማሪዎች ናቸው። በዚህ ምክንያትም የዛሬው እንግዳችን ሆነዋልና እንደሚከተለው እናወጋለን። ወጋችንንም ከአንደበተ ርቱኡና ከመላ አገሪቱ አቻዎቹ 1ኛ ከወጣው አላዛር ተካ እንጀምር።
ተማሪ አላዛር ተካ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪ ነው፤ ወይም ነበር። ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና እስከወሰደበት ጊዜ ማለት ነው። አላዛር ከትምህርት ቤቱ ኮከብ ተማሪዎች መካከልም አንዱና ቀዳሚው እንደ ነበር መምህራኑና ጓደኞቹ ይመሰክሩለታል። ይህ ብቻም አይደለም፣ በዘንድሮው የማትሪክ ፈተናም ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት ከራሱም አልፎ ትምህርት ቤቱንም በአገር አቀፍ ደረጃ የሪኮርድ ባለቤት ለማድረግ የበቃ የዓመቱ ኮኮብ ነው።
አላዛር በአጠቃላይ ከ700 አጠቃላይ ድምር ውጤት 659 በማምጣት በአገር አቀፍ ደረጃ የመሪነቱን ቦታ የጨበጠ የዓመቱ ኮኮብ ሲሆን ይህ ከኋላ ታሪኩ ጋርም የሚገናኝ ሆኖ መገኘቱን (የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ውጤቱ 99.9 ፐርሰንታይል ወይም 93 ከ100 ነው) ስናስብ “ከጥንት ነው ከመሰረቱ ….” እንድንል የሚያስገድደን ተማሪ ነው። (እዚህ ላይ የሲቪክ ትምህርት ውጤት ግሽበት ገጥሞታል በሚል የተያዘ መሆኑን፣ እሱ ከተቀነሰ የአላዛር ውጤት 563 ከ600 ሊሆን እንደሚችል ነግሮናል።)
“ውጤት እንዴት ነው?” ላልነው “በጣም አስደሳች ነው።” በማለት የመለሰልን አላዛር ለዚህ ውጤት መምጣት የትምህርት ቤቱ መምህራን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው፣ “አብሮ አደጎች ነን” ከሚላቸውና የነበራቸውን የአራት አመት ቆይታ መቼም እንደማይረሳው ከሚናገርላቸው የክፍልና የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር የነበረው አብሮ የመስራት ሁኔታ፣ የትምህርት ቤቱ አደረጃጀት (ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ …)፤ እንዲሁም በቤተሰቡ በኩል የፈለገው ሁሉ ይሟላለት የነበረ መሆኑን በሚገርም ትህትና ይናገራል።
በመምህራን በኩል ይሰጠን የነበረው ነፃነት፣ የፈለግነውንና ያልገባንን እንድንጠይቅ ማበራታታቸው፣ አንድን ርእስ ጉዳይ (ቶፒክ) እስከ መጨረሻው፣ እስኪገባን ድረስ ዘልቀው የማስረዳት ብቃትና ፍላጎታቸው፣ በምንከታተለው የትምህርት ዘርፍ የበለጠ እንድናውቅ የሚያደርጉት ጥረት፤ እንዳንፈራ፣ እንዳንጨነቅ ማድረጋቸው ለእኛ ለተማሪዎቻቸው ትልቅ አቅም ነበር የሚለው አላዛር የዚህ ሁሉ ድምርና የራሱ ያልተቋረጠ ጥረት ለዚህ እንዳበቃው ይናገራል።
አላዛር ተካ የዋዛ ተማሪ አይደለም። በውይይታችን ወቅት እንደነገረን ከሆነ መረዳት በፈለገው ጉዳይ ላይ ሰፊ ጊዜ ወስዶ ይሰራል፤ እንደውም ከመስራቱ በፊት አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን አጋዥ ቁሶች (ከመጻሕፍት ጀምሮ ማለት ነው) ያሰባስባል፤ በቃ ከዛ በኋላ ያ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ካልገባውና ስለ ጉዳዩ አጠናቅቆ ካልተረዳ መላቀቅ የለም። ሙሉ ቅዳሜና እሁድን ሁሉ ያሳልፍበታል። የበላይነቱ የሱ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው ከያዘው ርእሰ ጉዳይ ጋር እሚላቀቀው። ይህ ልምዱም ለዛሬው ውጤቱ እንዳበቃው ነው የሚናገረው። “ለወደፊቱ፣ ለዩኒቨርሲቲም በዚሁ መሰረት ነው እየተዘጋጀሁ ያለሁት” ሲልም ያክላል።
ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በቀላሉ ለመግባት ይቻል ዘንድ የሚያዘጋጀውን መግቢያ ፈተና (እንግሊዝኛ እና ሂሳብ) ወስዶ ከ1600 አጠቃላይ ውጤት 1580 ማምጣቱን የነገረን አላዛር ለውጤት ለመብቃት መንገዱ አንድ ብቻ እንደሆነም ይናገራል – ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ጠንክሮ መስራት።
እንደ ሳይንስ ተማሪነቱ ስለ ዝንባሌው ጠይቀነው ሀሳቡን ያጋራን አላዛር “በፊት ለፊዚክስ ነበር ከፍተኛ ፍላጎትና ፍቅር የነበረኝ። በሂደት ግን፣ የበለጠ በትምህርት ደረጃዬ ከፍ እያልኩና የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን በዝርዝር እየተዋወቅሁ፣ ችግሮችን እየለየሁ … ስመጣ ፍላጎቴና ዝንባላዬ ወደ ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ተቀየረ። አሁን በዚሁ መስክ ነው መቀጠል የምፈልገው” በማለት ነግሮናል። “በዚሁ መሰረትም መረጃዎችን እያሰባሰብኩ ነው፤ አስፈላጊውን ዝግጅትም ከወዲሁ ጀምሬአለሁ። የተለያዩ ጥያቄዎችንም እየሰራሁ ነው። ይህን ማድረጌ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬን በቀላሉ እንዳልፈው ያደርገዋል ብዬ አስባለሁም” ነው ያለን።
“በትምህርት ዓለም ላሉ ተማሪዎች ምን የምታስተላልፈው መልእክት፣ የምታካፍለው ልምድ አለ?” ብለነውም “አንድ ተማሪ ምንድነው ማወቅ የምፈልገው፣ ወደፊት ምን አይነት ቴክኖሎጂ ተፈጥሮና ስራ ላይ ውሎ ነው ማየት የምሻው፣ ምን ምን ችግሮች አሉ፣ እንዴት ነው ችግሮቹን ልንፈታ፣ ልናቀል፣ ልናስተካክል የምንችለው፤ አጠቃላይ መፍትሄውስ ምንድን ነው? እና የመሳሰሉት በአእምሯችን ሊመላለሱ ይገባል። በእነዚህ አይነቱ ፍቅር ስንያዝ በሁሉም ነገር መቅደም ይቻላል ማለት ነው። መዘናጋት የለብንም። በጉዳዩ ላይ ሙሉ ግንዛቤ እስኪያዝ ድረስ መስራት ያስፈልጋል።” ሲል ከፍ ባለና ራእይን በሚያመለክት አገላለፅ መልሶልናል።
ሌላዋና የዓመቱ የውጤት ሰገነት ላይ በመቆም ከፍ ብለው ከታዩት አንዷ ተማሪ ናታኒም በላይ ስትሆን፤ እሷም የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪና የአላዛርና ጓደኞቹ “አብሮ አደግ” ነች። በተገኘው ውጤትና ስሜቷ ዙሪያ አነጋግረናት ቀለል ባለ ስሜት የሚከተለውን አጫውታናለች።
ተማሪ ናታኒም ውጤቷን አስመልክታ “አዎ፣ ውጤት ጥሩ ነው። ከዚህ በላይ የጠበቅሁ ቢሆንም ጥሩ ነው፤ ደስ ብሎኛል።” ያለች ሲሆን ለዚህ ውጤት፣ 651 ከ700 ለማምጣቷ ምክንያቱንም “ከክፍልና ቤት ስራ ጀምሮ ማንኛውንም አይነት፣ ከትምህርት ጋር የተያያዙ ስራዎችን መስራት፣ በተለይ ትምህርት ቤቱ የልዩ (ስፔሻል) ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከመሆኑ አኳያ በከፍተኛ ደረጃ ውድድር የሚታይበት መሆኑና በዛው ልክ መስራት የሚገባ በመሆኑ ያንን ማድረግ፣ ከክፍል ጓደኞች ጋር መረዳዳት፣ አብሮ ማጥናትና መስራት፣ የመምህራኑ ቀናነትና ሙሉ ድጋፍ” መሆኑን ትናገራለች።
ናታኒም በ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናም ከአላዛር ጋር ተመሳሳይ (99.9 ፐርሰንታይል፣ ማለትም 93 ከ100 ነው) ውጤት ያመጣች ሲሆን፣ በዛን ጊዜም በተማረችበት ት/ቤት (ክሩዛ) ጥሩ ጥሩ መምህራን እንዳስተማሯትና ለጥሩ ውጤት እንደበቃች የምትናገር ሲሆን፤ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ መምህራንም ከማበረታታት ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ ያደረጉላት መሆናቸውን፤ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ፍርሀት ብሎ ነገር እንደ ሌለ፤ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር መማር በራሱ ትልቅ እድል እንደሆነና ሁሉም ተማሪ ቀድሞ፣ ጎበዝ ሆኖ ለመገኘት እንደሚሰራ፤ የቤተሰብ ድጋፍ … ለዛሬዋ ብቻ ሳይሆን ለነገዋም ትልቅ መሰረት እንደሚሆናት ደስ እያላት ታስረዳለች።
ተማሪ ናታኒም እንደ ነገረችን ከሆነ ቤተሰቦቿ ምንም አይነት ተፅእኖ ፈጣሪዎች አይደሉም። አስፈላጊውን እገዛ ከማድረግና ማሟላት ባሻገር፣ በማንኛውም እሷን በሚመለከት ጉዳይ ከማማከር ያለፈ ውሳኔ ላይ የሚደርሱት ነገር የለም። ይህንንም “አስፈላጊውን ሀሳብ ከሰጡኝ በኋላ ውሳኔውን እራሴ እንድወስን ነው የሚያደርጉት። ምንጊዜም የመጨረሻው ውሳኔ የእኔ የራሴ ነው። ያለ ምንም ተፅእኖ ነው በራሴ ጉዳይ ላይ ራሴ የምወስነው። እንደዚህ ነው ያሳደጉኝ። ያ ሁሉ አግዞኛል።” ስትል ትገልጸዋለች። “ወደዚህ ትምህርት ቤት እንድገባ እንኳን አማከሩኝ እንጂ እነሱ አልወሰኑም። እኔ ነኝ መግባት አለብኝ ብዬ የወሰንኩት” በማለትም ሀሳቧን ታጠናክረዋለች።
እንደ ሳይንስ ተማሪነትዋ ዝንባሌዋን፤ ማጥናትና መሆን የምትፈልገውንም ጠይቀናት ነበር። “መጀመሪያ ፍላጎቴ ባዮሎጂ ነበር፤ ባዮሎጂ በማጥናት ወደ ህክምና ሙያ መግባት። በሂደት ደግሞ ፍላጎቴ ወደ ፊዚክስ ሄደ። ከተወሰነ በኋላ ደግሞ ተመልሶ ወደ ሜዲሲኑ መጣ። አሁን በእሱው መቀጠል ነው የምፈልገው። ቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ ለመግባት የሚያስችለውን የመግቢያ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነኝ። እያጠናሁ ነው።” በማለት ነበር የመለሰችልን።
የአጠናን ስልቷን በተመለከተም “እኔ ሳይገባኝ የምተወው አንድም ነገር የለም። ሲገባኝ፣ እርግጠኛ ስሆን ብቻ ነው አቁሜ ወደ ሌላ የምሄደው። ጥናትን በተመለከተ አስቀድሞ መዘጋጀት እንጂ እኔ ሁሉን ነገር መሸምደድ ያስፈልጋል ብዬ አላምንም። አስቀድመህ ባደረከው ዝግጅት ሁሉም ነገር እንዴት እንደመጣ ካወቅህ ድንገት ብትረሳው እንኳን እንደገና ማስታወስ ትችላለህ። መሸምደድ የሚባል ነገር አልወድም። ሽምደዳን በጣም እጠላለሁ። አስቀድሜ ነው የምሰራው። ከወራት በፊት ነው የማጠናው። ለእኔ የፈተና ወቅት ደረሰ ማለት የማጥኛ ጊዜ ደረሰ ማለት ሳይሆን የክለሳ ጊዜ ነው። ይህ ለሌሎች ላይመች ይችላል። ለእኔ ግን ትክክለኛውና ተገቢው የአጠናን ዘዴ (ስርአት) ነው።” በማለት ነው የገለፀችልን።
“ናታኒም አንቺ ከላይ በነገርሽን አሰራርሽ ውጤታማ ሆነሻል። ለሌሎች ተማሪዎች የምትመክሪው፤ የምታካፍይው ልምድ ካለሽ?” ለሚለው ጥያቄያችንም “ከሁሉም በላይ ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ ነው፤ ከጎበዝና ተባባሪ ተማሪዎች ጋር በጋራ መስራት ይገባል፤ ለፈተና ብቻ ተብሎ ሳይሆን ለማወቅ ተብሎ ማጥናት ተገቢ ነው፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው። ይህንን ሁሉም በትምህርት ዓለም ያለ ሰው ሁሉ ሊያውቀው፤ አውቆም ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል። ይህ ከተደረገ ውጤት የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም።” የሚል ኮስተር ያለ መልስ ሰጥታናለች።
በአጠቃላይ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎቹ አላዛር ተካ እና ናታኒም በላይን፣ ቤተሰቦቻቸውንን መምህራኖቻቸውን፤ እንዲሁም መላው የትምህርት ባለድርሻ አካላትን በድጋሚ “እንኳን ደስ አላችሁ!!!” እያልን፤ ለአላዛርና ናታኒም፤ እንዲሁም ለመላው ወደ ዩኒቨርሲቲ ገቢ ተማሪዎችም መልካም የትምህርትና ውጤት ዘመን እንዲሆንላቸው ስንመኝ በሌላ የሕይወት ምእራፍ ዳግም እንደምንገናኝ በመተማመን ነውና መልካም የትምህርት ዘመን!!!
(ባለፈው ሳምንት ወደ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በመሄድ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና የካምፓሱ ርእሰ ፕሪንሲፓል ከሆኑት አቶ አቤል ጫላ ጋር ባደረግነው ቆይታ ወደዚህ ካምፓስ ለመግባት ከ8ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት በተጨማሪ በርካታ መስፈርቶች እንደሚያስፈልጉ፣ ከሥነ ምግባር ጀምሮ ያሉት ሁሉ እንደሚታዩ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ካምፓሱ የሚያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ የግድ መሆኑን፤ እነዚህን (መግቢያ ፈተና 75%፣ የሚኒስትሪ ውጤት 15%፣ ቃለ-መጠይቅ 10%) ያሟላ ተማሪ ብቻ ወደዚህ ተቋም እንደሚገባ፤ ካምፓሱ በሳይንስ ዘርፍ ከአገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶችን ማፍራትን ግብ አድርጎ እየሰራ መሆኑን መነጋገራችን ይታወሳል።)
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም