
ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ እና ሂሳብ እንደቀድሞው ተማሪ በተናጠል እና በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻቸውን የሚያጠናቸው ትምህርቶች ሆነው አልተገኙም፡፡ አሁን ላይ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአንድ ሳንቲም ሦስት ገጽታዎች ለመሆን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የደረሰበት ምጥቀት አስገድዷቸዋል፡፡ እንዴት ቢባል ፊዚክስ ተመርቄያለሁ ብሎ የሚቀመጥ ተማሪ፤ ፊዚክስን ያለ ቴክኖሎጂ የትም ሊወስደው አይችልም፡፡ ኬሚስትሪ ተመርቄያለሁ የሚልም ያለ ቴክኖሎጂ ያለ ኢንጅነር እና ሂሳብ እውቀት የትም አያደርሰውም፡፡ ደግሞም በብርቱ በሥነ-ጥበብ መታገዝ አለበት፡፡ ተማሪው የሚሠራቸው የሳይንስ ሥራዎች በሳይንስ የሚፈጥራቸው ሁሉ ለሰው ጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ወይም ሰው ሰው የሚሸቱ እንዲሆኑ በሥነ- ጥበብ መታገዝ አለባቸው፡፡
መምህሩ ተማሪዎችን ሲያስተምር ጎንበስ ቀና ማለት፣ በሳቢና ማራኪ ስዕል አስደግፎ ለተማሪው ማስተማር አለበት፡፡ ይሄ ዓይነቱ የማስተማር ዘዴ ሳይንሳዊ ሥነ -ጥበብ የታከለበትም ነው፡፡ ጥበቡ ባህልን ወግን፣ አክብሮ የሚያስከብር ፣ከባሕልና ከሥርዓት የሚወጣበትን የሚያስቀር በደምሳሳው ሰው ሰው የሚሸት ነው፡፡
በመሆኑም እነዚህ ትምህርት መስኮች ለየትኛውም ዓይነት የማህበረሰብ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ መሠረት መሆናቸውን ተረድቷል፡፡ በየመስኩ ውጤታማ የልማት ተግባራት ለማከናወን ዓይነተኛ መፍትሔ ከመሆናቸው አንፃር በተለይ ከለውጡ ጀምሮ እንደ ሀገር በመንግሥትም ትኩረት ተሰጥቶ በልዩ ሁኔታ እየሠራባቸው ይገኛል። ከእዚሁ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባለው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያዋ የስቴም ማዕከል እስከ መመስረት የደረሰች ሀገር ስለመሆኗ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካም የሂሳብ ሳይንስና ሥነ ጥበባት በእንግሊዝኛው STEM power መስራች እና አባል ሀገርም ናት›› የሚሉት በትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብ ሳይንስ እና ሥነ ጥበባት ማበልፀጊያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ታደሰ ተሬሳ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን ችግር ፈቺና ፈጠራ ያለው ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ተግባር ባላት ራዕይ መሠረት ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ማራኪ እና ሳቢ ከሆነው ከኪነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብ ጋር በማዋደድ በሀገር አቀፍ የትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አቀናጅታ እየሠራችበት ስለመገኘቷ ያስረዳሉ። ተግባሩ አስደሳች አዲስ የመማር ፣ ማስተማር ልምድ የሚቀሰምበት እንደመሆኑ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እና አነቃቂ የመማሪያ አካባቢን ስለመሻቱም ያብራራሉ፡፡
አቶ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ዴስኩ ከሚሠራቸው መሠረታዊ ሥራዎች መካከል አንዱ መምህራንን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ማብቃት ነው፡፡ መምህራን ሳይንሱን ከቴክኖሎጂ ጋር በተግባር ማስተማር እንዲችሉ ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ የክህሎት ስልጠና ይሰጣል፡፡ ቴክኖሎጂውም ሆነ ሳይንሱ በሥነ-ጥበብ የተደገፈ ነው፡፡
ቤተ ሙከራቸው ሕይወት ያለው ሥራ የሚሠራ እንዲሆን ከፌዴራል እስከ ትምህርት ቤት ያለ ቡድን አደራጅቶ ይሠራል፡፡ ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች በማስወገድ አዳዲስ ኬሚካሎች በቤተ ሙከራዎች እንዲሟሉም ያደርጋል፡፡ ጊዜ ያላለፈባቸውን ኬሚካሎችም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርጉ ስልጠናዎች ይሰጣል፤ ቤተ ሙከራዎችን ያደራጃል፡፡ ምርምርና ጥናት የሚደረግበት፤ የስልጠና ሞጅሎች እና ስልጠናም የሚዘጋጅበት ነው፡፡
ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ በቅርቡ በተሠራ ጥናት መምህራን መጠነኛ ክፍተቶች እንደሚታይባቸው ተለይቷል፡፡ በጥናቱ ከተለዩት አንዱ የተግባር ቤተ ሙከራ ፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ችግር መኖሩ ነው፡፡ እንደ ፕሮጀክት ፔዳ ጎጂ የትምህርት ዓይነት ላይ ችግር አለ፡፡ እንደ ዴስክ በእነዚህ እና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን፤ ለስልጠናው ትምህርት ሚኒስቴር ከጃፓን ምሁራን ጋር ሆኖ የሠራው ሞጁል አለ። ሞጁሉ አምስት ክፍሎች አለው፡፡ አንደኛው ተማሪ ተኮር የማስተማር ሥነ ዘዴው ላይ ትኩረት የሚያደርግ ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ሁለተኛው የተማሪ አያያዝ፣ ፈተና አሰጣጥ ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ሌላኛው ማድመጥ ላይ የሚያጠነጥን ወይም በኢንግሊዝኛው (ሌሰን ፕላን) ከሚባለው ጋር የተሰናሰለ ሲሆን፤ መምህራን በጋራ አቅደው በጋራ የሚያስተምሩበትን ሁኔታዎችን የሚያመቻች እና በተግባርም የሚያሳካ ነው፡፡
በእዚህ ውስጥ የሚሠሩ ክፍሎች እንዴት ስቴምን ይመራሉ፤ ያስተባብራሉ የሚሉ የስልጠና ሰነዶች ከሚያዘጋጃቸው ይጠቀሳል፡፡ በትምህርት ቤት፣ በክላስተር ከዛም በወረዳ ፣ በዞን በክልል፣ በፌዴራል ደግሞ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ይደረጋል፡፡ የተማሪ እና የመምህራን የፈጠራ ሥራ ውድድርም በየዓመቱ አለ፡፡ በየዓመቱ የፈጠራ ሥራ ውድድር የሚያደርግ ሲሆን፤ የዘንድሮን ጨምሮ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተካሂዷል፡፡ መሪ ቃሉ በየዓመቱ ቢለዋወጥም ‹‹የዓለም የሳይንስ ቀን ለልማት እና ለሰላም›› በሚል ዘንድሮ የተደረገው በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡ ዘንድሮ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ተማሪዎች በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡ እንደ ሀገር አሸናፊ የሆኑትም ካገኙት ሽልማት ባሻገር በተሰጣቸው ነፃ የትምህርት እድል ወደ በተለያዩ ሀገሮች እንዲሄዱ የተመቻቸበት አለ። ውድድሩ ለቀጣይ ዓመትም እንዲሁ ጥቅምት 30 ይደረጋል፡፡ ይሄን ውድድር የሚያስተባብረው እና የሚመራውም ዴስኩ ነው፡፡ የፈጠራ ሥራዎችን ማስተዋወቅ መምራት አጠቃላይ ተማሪዎች፣ መምህራን በስቴም የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም የዴስኩ ኃላፊነት እና ተግባር መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዴስኩ ራሱ በማእከል ደረጃ የተቋቋመና አሜሪካ ኤምባሲ አካባቢ ራሱን የቻለ ቢሮ እንደነበረው ያስታወሱት ኃላፊው፤ ማዕከሉም የተደራጀ ቤተ ሙከራ እንደነበረውም ያስረዳሉ፡፡ ቤተ ሙከራው አሁን ላይ በቢሮ ጥበት ምክንያት ተዘግቶ መገኘቱንም ይጠቅሳሉ። እንደ ሀገር በመንግሥት ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው።
የሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርት ‹‹ስቴም ፓውር›› በአሜሪካዊው የፈጠራ ባለሙያ እና በጎ አድራጊ ማርክ ጌልፋንድ የተቋቋመ ሕጻናት እና ወጣቶችን በሳይንስ፣ቴክኖሎጂ ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ዘርፎች ለማነጽ ያለመ ተቋም ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም በእዚህ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀት መጋቢው ‹‹ስቴም ፓዋር›› እንደ ዴስክ ከሥርዓተ-ትምህርቱ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮች ተካሂደዋል። ከእነዚህም አንዱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት የተካሄደው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ ጥናት መሆኑን ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡
አቶ ታደሰ እንደሚሉት፤ ጾታን ያማከለ የሂሳብ ፣ የሳይንስ እና የሥነ ጥበባት ማበልፀጊያ ትምህርቶች ብዙ ጊዜ ሴቶችን፣ አንዳንዶች ደግሞ ወንዶችን ከሳይንስ የሚያገሉ ‹‹አንተ/አንቺ ለሳይንስ አልተፈጠርክም፤አልተፈጠርሽም ሳይንስ አትስሪ አትሰራም›› የሚል አግላይ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች አስተሳሰብ ሰብሯል፡፡
‹‹እነዚህ ሰዎች እነሱ ባላሰቡት መንገድ በቅተው ሲያገኝዋቸው እና በተለይም መምህራን ጥያቄ መልሰው ሲጨርሱ፤ ወንዱን ወንድነሽ እኮ ይላሉ፤ ሴቷንም ወንድነሽ ይላሉ›› ይሄ የተሳሳተ አስተሳሰባቸው ስር የሰደደ ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡ ይሄ ለሳይንስ የተፈጠረው ወንድ ነው ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ የሚወስድ ስለሆነ አስተሳሰቡን ለመስበር ጭምር ለመምህራን ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የሚሰጥበት እንዳለ ሳያነሱ አላለፉም፡፡ መምህራን ስላወቁ ብቻ ለውጥ አይመጣምና መምህራኑ ከሰለጠኑ በኋላ የሚያስተባብሩ፣ የሚመሩ፣ በጀት የሚመድቡትን ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች፣ የወረዳ ትምህርት ባለሙያዎች፣ የክልል የዞን እና ወረዳ ትምህርት ባለሙያዎችን በእዚሁ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ውይይትም ይደረጋል ከክልሎች ጋር በጋራም ይሠራል፡፡
ስልጠናው ከመምህራን እስከ ተማሪዎች የሚሠሩት ሥራ እንዲሁም የቤተ – ሙከራ ግብዓቶቻቸው በአካባቢያቸው ከሚገኙ ቁሳቁሶች እንዲያመርቱ የሚረዳ ስለመሆኑም ነው የሚናገሩት። ይሄ የቤተሙከራ ቁሳቁሶች ወይም ግብዓቶች ውድ ከመሆናቸው አንፃርም ወጪን ከመቆጠብ ረገድ አስተዋጽኦው መጉላቱንም ይጠቅሳሉ። ሳይንሱንም ከአካባቢው ጋር ለማገናኘት በብርቱ እገዛ ያደርጋል። በሀገር ደረጃ የሚሰጠውም ስልጠና ይሄንኑ እሳቤ ማእከል ያደረገ ነው፡፡
የሰለጠኑትን ሥራ ላይ አውለዋል ወይ? የእኛ ስልጠና ምን ለውጥ አመጥቷል? የሚለውን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ወርዶ ያያል፡፡ በስተመጨረሻ የክትትል እና ድጋፍ ጥናት ይሠራና ምርጥ ተሞክሮዎችን ይቀምራል። አሁንም ይሄንኑ ኢትዮጵያ ቀዳሚ የሆነችበትን ተግባር ወደ የሚመጥነው የሚሻገርበትን ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎችም ጋር በትኩረት እየሠራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ላይም ሆነ የትኛውም ሥፍራ ሥራው የሚሠራው በተበታተነ መልኩ ነው፡፡ እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ማዕከል ወደ ዴስክ የወረደው በሲቪል ሰርቪስ እና ጥናቱን ባጠኑት ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥም ባሉ ባለሙያዎች ስለመሆኑም በቁጭት ያነሳሉ፡፡
አሁን እንደ ትምህርት ሚኒስቴር እየተሠራ ባለው ሥራ ወደ ቀድሞው ማዕከልነቱ የሚመለስበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚልም ተስፋ አላቸው። እንደእሳቸው ምክረ ሃሳብ ይሄም ወደፊት መስተካከል ያለበት ነው፡፡ ከተስተካከለ እና ወጥነት ባለው መልኩ በዩኒቨርሲቲዎች ጭምር እንደ ሀገር ከተሠራ ኢትዮጵያ እቅዷን የማታሳካበት፣በችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ድህነትን አሸንፋም ወደ ብልፅግና የማትሻገርበት ምክንያት አይኖርም፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በእዚሁ መልክ መስኩን እየደገፉ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ያሬድ በቃሉ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ባህልን ለማዳበር እየተሠራ ስለመገኘቱ ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው ትምህርት ቤቶች የሚማሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሳይንስ ባህልን አዳብረው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ የሚገኘውም በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ሳይንስ ምህንድስ፣ ሂሳብ እና ከተማ የሚባለውን ያጣመረ ትምህርት ይሰጣል፡፡
ትምህርቱ ከመሠረታዊ ሳይንስ ጀምሮ ክህሎት በሚያዳብሩበት ተግባር ተኮር ስልጠና የታገዘ ነው፡፡ ይሄም የሳይንስና ባሕል ግንባታ ከሚማሩት የተግባር ትምህርት በተጨማሪ የተግባር ትምህርትን አዳብረው በራሳቸው ትልቅ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ፤ ለሀገራቸው ደግሞ ችግሯን መፍታት እንዲችሉ እንደሚያደርግም ያስረዳሉ፡፡ በእዚህ የስልጠና መርሃ ግብር አልፈው በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የደረሱ መኖራቸውንም ይገልፃሉ፡፡ የራሳቸውን ካንፓኒ ከከፈቱት ተማሪዎች ውስጥ ቴክፕላስ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ ስልጠናውን መምህራንም እንዲወስዱ እንደሚደረግ የሚያነሱት ኃላፊው ዓላማው ተማሪዎች የሚሠሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች እውቀትን መሠረት አድርገው እንዲያግዙ፤ በሌላ በኩልም ተማሪዎችን እንዲያበረታቱ ስለመሆኑም ያብራራሉ፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም