አቶ አማን ይኹን ረዳ የንግድ፤ ምጣኔ ሃብት እና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ሙያዊ ሃሳቦችን በመስጠት የሚታወቁ ናቸው፡፡ በዛሬው ዕትማችን የዋጋ ንረት፣ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ትስስር፣ በቀጣይ ኢኮኖሚውን ለመታደግ እንደ ሀገር መሠራት ስለሚገቡ አንኳር ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት መነሻው ምንድን ነው?
አቶ አማን ይኹን፡- ምክንያቱ ዋጋ፣ ምርትና አገልግሎት እንዴት ይወሰናል የሚለው ነው፡፡ ይህን ደግሞ የሚወስነው ገበያው ነው፡፡ ገበያ አቅርቦት እና ፍላጎት የሚገናኝበት ነው፡፡ ፍላጎት እና አቅርቦት ከተመጣጠነ ገበያው የተረጋጋ ይሆናል፡፡ አቅርቦት፣ ምርት ሆነ አገልግሎት ከፍላጎት የበለጠ ከሆነ የዋጋ ማሽቆልቆል ይከሰታል፡፡ የምርትና አገልግሎት መጠን ከፍላጎት በሚያንስበት ሰዓት ደግሞ የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡ ይህ ጥቅል እሳቤው ሲሆን ወደ ዝርዝር ስንገባ ፍላጎትን የሚጨምሩ እና አቅርቦትን እንዳይጨምር የሚያደርጉ ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት 10 ሚሊዮን በላይ ዜጋ ተፈጥሯ፡፡ የዶክተር አብይ አስተዳደር ወደ ስልጣን ሲመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 109 ሚሊዮን አካባቢ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን 120 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በዓመት ውስጥ 3 ነጥብ7 ሚሊዮን ህዝብ ተወልዷል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት የሞተው 750 ሺ ነው፡፡ ይህ ማለት በአንድ ዓመት ውስጥ የህዝብ ቁጥራችን በ 2 ነጥብ 95 ሚሊዮን አድጓል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ በአራት ዓመት 11 ሚሊዮን ተጨማሪ ህዝብ ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም ይህን ተጨማሪ ህዝብ ለመቀለብ የግብርና ምርት፣ የኢንዱስትሪ ምርት አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ ምርቱስ ገበያ ላይ አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ በቂ ምርት አልተመረተም፡፡ በመሆኑም ይህን ፍላጎት ለማሟላት ከውጭ መግባት አለበት፡፡ ይህን ምርት ከውጭ ለማስገባት ምርት ደግሞ በቂ የውጭ ምንዛሪ አለ ወይ ብለን ስንጠይቅ ኢትዮጵያ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም ምርት ከውጭ እንደፍላጎታችን ለማስገባት ተቸግረናል፡፡
በተጨማሪም አቅርቦት ትርጉም ባለው መልኩ ሳይጨምር፣ በአንድ በኩል ደግሞ በግብርና ምርታማነት ውስንነት በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደልብ ምርት ማስገባት አልተቻለም፤ የህዝብ ቁጥር ደግሞ ጨመረ ማለት ፍላጎት አብሮት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ የእነዚህ አለመጣጣም የዋጋ መናር ያመጣል፤ ኑሮ ይወደዳል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ መጣጣም ቢችሉ እንኳን የኑሮ ውድነት ሊከሰትበት የሚችልበት እድል አለ። አንደኛው የግብርና ግብዓቶችና የአፈር ማዳበሪያ የሚገባው ከውጭ ነው ፤ ዋጋውም በጣም ጨምሯል። የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ በጣም ጨምሯል፡፡ አንድ በርሜል ነዳጅ ከአራት ዓመት በፊት ዓማካይ ዋጋ ከ50 እስከ 60 ዶላር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ120 ዶላር በላይ እየተሸጠ ነው፡፡ በመርከብ ለማጓጓዣም ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ወይም ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ገንዘብ 82 በመቶ የመግዛት አቅም አጥቷል፡፡ አንድ ዶላር የምንዛሪ ተመኑ የዛሬ አራት ዓመት 29 ብር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ምንዛሪው 52 ብር ደርሷል፡፡
የፓልም ኦይል ድፍድፍ ዘይት ከአራት ዓመት በፊት የዓለም አቀፍ ገበያው አንድ ቶን ድፍድፍ ዘይት 760 ዶላር ወደ 1 ሺህ 420 ዶላር ገብቷል፡፡ ይህም 95 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው የንግድ ጦርነት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በራሺያ እና ዩክሬን መካከል የተፈጠረው ጦርነት እንዲሁም በምዕራባውያንና በራሺያ መካከል የሚስተዋለው አለመግባባት እና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ፍጥጫ ምርት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግና ችግር በመፈጠሩ ትልቅ የዋጋ ንረት እየተከሰተ ነው፡፡ ከፍተኛ ስጋትም ደቅኗል። ሌሎች ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡
በዩክሬን በተነሳው ጦርነት በአጭር ጊዜ ነዳጅ 25 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ የኮረና ቫይረስ ሥርጭት በዓለም ደረጃ የምርት አቅርቦት ሠንሠለት ላይ ከፍተኛ አደጋና መናጋት ፈጥሯል፡፡ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ከቤታቸው እንዳይወጡ ሲያደርጉ ስለነበር የምርት ሂደቱ ቀንሷል፡፡ ፍላጎት አድጓል በዓለም ደረጃ ምርት ቀንሷል፡፡ በኮረና ቫይረስ የተነሳ የኮንቴነር ዋጋ እና ምርትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ለመርከቦች የሚከፈለው የማጓጓዣ ዋጋ በጣም ጨምሯል፡፡
አንድ ኮንቴነር እቃ ከቻይና ኢትዮጵያ ለማስመጣት ከሁለት ዓመት በፊት በዓማካይ 2ሺህ 500 ዶላር ይከፈል የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዓማካይ 11ሺ ዶላር ይከፈላል፡፡ በአጠቃላይ በሀገር ቤት የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል የግብርና ምርት የለም። የቆላ ስንዴ በመስኖ እርሻ ማምረት፣ ጉታገጠም ሆነ በሌላው ዘርፍ ግብርናውን ለማሳደግ የተሄደበት ርቀት በቂ አይደለም፤ በቂ ምርት የለም ስር ነቀል ለውጥም አልመጣም ብዙ ይቀራል፡፡ ስለዚህ የግብርና ማነቆችን መፍታት ይገባል፡፡ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አሁንም በቂ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የህዝብ ቁጥር በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላችን ከውጭ ምርት እንዳናስገባ የዶላር እጥረት ገጥሞናል፤ የገንዘባችን የመግዛት አቅምም በጣም ተዳክሟል፡፡ የምዕራቡና የምስራቁ ፍጥጫ፣ የአሜሪካ እና ራሺያ መካከል ያለው ድብቅ ፍጥጫ እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓለም ገበያ ላይ የማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ ብረት እና ሌሎች ምርቶች ዋጋቸው በጣም ጨምሯል፡፡
መታወቅ ያለበት ራሺያ እና ዩክሬን የዓለምን 40 ከመቶ ስንዴ ያመርታሉ፡፡ ማዳበሪያ እና ነዳጅ ብሎም ብረት በከፍተኛ ደረጃ ከራሺያ ይመጣል፡፡ ከዓለማችን 11 ከመቶ የሚሸፍነው የራሺያ ግዛት በዓለም ላይ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ በዚህ ላይ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት አላቸው፡፡ ራሺያ ጦርነት ላይ በመግባቷ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መናጋት ይፈጠራል፡፡ በአጠቃላይ ሀገራችን ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት የሚፈትነው የኑሮ ውድነት አሜሪካን ጨምሮ የዓለም ሀገራትን በእጅጉ እየፈተነ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኑሮ ውድነቱ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ይህን ያክል ተፅዕኖ አለው?
አቶ አማን ይኹን፡- የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም ማስረዳት ማለት በአጭር መንገድ ፍላጎት ማለት የህዝብ ቁጥር ማለት ነው፡፡ ህዝብ እያደገ ሲመጣ ፍላጎቱን ማሟላት አለመቻል ፈተና ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ብዛትና ምርቷ ለኑሮ ውድነቱ ሥጋት ሊሆን ይችላል?
አቶ አማን ይኹን፡- ምርት የለማ! ምርት ሲኖር እኮ ነው፡፡ ምርት አልበቃ ያለን በላተኛ ስለበዛ ነው። በአንድ በኩል ገበያውም ጭምር ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የሚፈጥር፤ ግብር የሚከፍል፣ ሠራተኛ የሚፈጥር፤ ኢኮኖሚውን የሚያዘምን አምራች መኖር አለበት፡፡ ግን ይህ ህዝብ በትክክል እንዲያመርት የሚያስችል የኢኮኖሚ ሥርዓት መከተልና ግብርናው፣ አገልግሎት ዘርፍ፣ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ብዙ ሠራተኛ መቅጠር የሚችል ኢኮኖሚ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ ይህ አልተፈጠረም፡፡ በርካታ ሰዎች ተመርቀው ሥራ የላቸውም፤ ስለዚህ ኢኮኖሚው ይህን ጥያቄ በአግባቡ እየመለሰ አይደለም፡፡ ሰውን ምርታማ እያደረግነው አይደለም፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚመራበት ሥርዓት መስተካከል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ የህዝብ ቁጥር መጨመር ስጋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ቻይና የአንድ ልጅ ፖሊሲ ያመጣችው አቅርቦትና ፍላጎት በወቅቱ ባለመጣጣሙ ነበር፡፡
በ1966 ዓ.ም የተማሪዎች ንቅናቄ ሲፈነዳ የህዝብ ብዛት 24 ሚሊዮን ነበር፡፡ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በ1983 ዓ.ም ሲረከብ የህዝብ ብዛቱ 49 ሚሊዮን ነበር። በ1987 ዓ.ም ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ የህዝቡ ብዛት 54 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነበር፡፡ የፓርላማው ወንበር 547 የተደረገው ለዚህም ነበር፡፡ አንድ የምክር ቤት 100ሺህ ዜጎችን እንዲወክል የተደረገውም በወቅቱ በነበረው የህዝብ ብዛት በመነሳት ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር ብዛት 70 ሚሊዮን ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ስለዚህ ግብርናችን አዘምነን፣ ኢንዱስትሪ ዕድገታችንን አፋጥነን፣ ከተማ ልማት በደንብ አሳድገን፣ ግብርና እና ኢንዱስትሪውን አስተሳስረን ስንሄድ መልካም ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ፋይናንስ ተቋማት ግብርናን ለማዘመንና ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የተቃኙ ናቸው?
አቶ አማን ይኹን፡- በአግባቡ የተሳሰሩ አይደሉም፡፡ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን መፍታት ነው፡፡ ግጭት፤ ዜጎችን ለመፈናቀል የሚዳ ረጉ እና እንደ ሀገር ያልተግባባንባቸውን እና አሁንም ለአመፅና ለችግር የሚያጋልጡንን ብሎም መወያየት በሚያስፈልግን ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እስክንስማማ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት አለብን፡፡ እኛ አሁን ይህን ማድረግ አልቻልንም፡፡ መንግሥት ሙሉ ትኩረቱ ለወጣት ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ለዜጎች ሥራ መፍጠርና ኢኮኖሚውን ማሳደግ ላይ መሆን አለበት፡፡ ሕዝብ ተምሮ ሥራ ካላገኘ፣ ነገሮች ካልተሟላለት ምን ይሆናል ብሎ ማሰብ ይገባል። ኢኮኖሚያችን ላይ ትልቅ ችግር አለ፡፡ በጣም ልናስብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ የተካው ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የመጣ መሠረታዊ ለውጥ የለም?
አቶ አማን ይኹን፡- ምንም የመጣ ሥር ነቀል ለውጥ የለም፡፡ የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ከመጣ በኋላ ብዙ ተስፋዎች ነበሩ፡፡ ተስፋዎቻችን ግን ‹‹ጉም መዝገን›› ሆነውብናል፡፡ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተዘንግተዋል፡፡ በኢኮኖሚው ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እኔ የሚታይኝ ግብርና ላይ አትኩሮ መሥራት ነው፡፡ 80 ከመቶ ህዝባችን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖር ነው፡፡ በከተማ ሆነ በገጠር ያለው ህዝባችን መሰረታዊ ፍላጎት ያልተሟላለት ነው፡፡ ምርት እንደልብ እንዲገኝ፣ ህዝባችን በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆን፣ የዋጋ ንረት እንዳይኖር፣ ህዝቡ ቀለብ እንዳይቸገር እና ዜጎች ሥራ እንደልብ እንዲያገኙ አሁንም ወደግብርና መመልከት አለብን፡፡
ግብርናው እንዳያድግ ደግሞ ቀፍድደው የያዙ ፖሊሲዎች አሉ፡፡ ከመሬት ባለቤትነት ይጀምራል። መሬት በባለቤትነት የአርሶ አደሩ አይደለም፡፡ አሁን አርሶ አደሩ እያረሰ ያለው መሬት ተከራይቶ ነው። ይህ የግብርና ምርታማነት እንዳይጨምር ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ለግብርና ዘርፍ የሚመደበው በጀት፣ ወደ ግብርናው ዘርፍ በባንኮች ዓማካይነት የሚገባ የብር መጠን፣ የግብርናውን ዘርፍ ከፌዴራል እስከ ወረዳ የሚመሩ ሰዎች እውቀት፣ ልምድና ብቃት ማነስ፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎች ምን ያክል በተመጣጣኝና በጤናማ የውድድር ሥርዓት የሚያቀርቡት፣ ግብርናውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ማሽነሪዎችና ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ እንደልብ አለማግኘቱ ፈታኝ ችግር ነው፡፡
ግብርናው በብዙ መንገድ የተተበተበ ነው፡፡ ግብርናው ከኢንዱስትሪ ጋር መተሳሰርና መመጋገብ አለበት፡፡ ግብርናው ሲያድግ ለዜጎች በቂ ቀለብና ለኢንዱስትሪው በቂ ጥሬ ዕቃ፣ ወደ ውጭ በመላክ በቂ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ስለሆነ ግብርናው ብቻውን የሚቆም አይደለም፡፡ ግብርናው ከኢንዱስትሪ፣ ከከተማ ልማት፣ ከኤክስፖርት ዘርፍና ከመሳሰሉት ጋር ተሳስሮ ማደግ አለበት፡፡
ግብርናው እንዲያድግ መንግሥት የሚበጅተው በጀት፣ ባንኮች የሚመድቡት ገንዘብ፣ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር በቀጥታ ግንኙነት አለው፡፡ ‹‹የታክስ ሥርዓቱ ባለሃብቶች ከተማ ውስጥ ፎቅ ከመሥራት ገጠር ገብተው እንዲያርሱ የሚበረታታ መሆን አለበት።›› ይህ ከአጠቃላይ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮችን በአስተማማኝ ከመፍታት በላይ የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን ወደ ግብርናው ለመግባት ያበረታታል ወይ? የሚለው መታየት አለበት፡፡
እውነት አዲስ አበባ ይህ ሁሉ ፎቅ ያስፈልጋታል? ባለሃብቱ ለምን ገጠር ገብቶ አያርስም? ለኢንዱስትሪ ለምን ጥሬ ዕቃ አያመርትም? ሲባል አበረታች አይደለም፡፡ ኢኮኖሚክስ የሚሰራው በማበረታቻ ነው። ማበረታቻ በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንደኛው በገንዘብ ዝቅተኛ ወለድ የሚከፈልበት ብድር እሰጣለሁ የሚለው ነው፡፡ ሌላኛው ግብርና ላይ ለሚሰማራ አካልና ምግብ በሚገባ ለሚያመርት ለተወሰኑ ዓመታት ከግብር ነፃ ማድረግና ሌሎች ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ግብርና ጥንቃቄ የሚፈልግና ውድ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ግብግብ መግጠምን ይጠይቃል፡፡ እሳት አደጋ፣ ጎርፍ፣ የወፍና ዝንጀሮ መንጋ፣ ተምች፣ ጦርነት፣ መሬት መንሸራተትና የመሳሰሉት ንብረት ሊወድምባቸው ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ አደጋ ተቀብሎ ወደ ግብርና ለሚመጡ ባለሃብቶች ማበረታታት ይገባል፡፡ በአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ይደጎማሉ፡፡ እኛ እንደነዚህ ሀገራት ያላደግንና ሃብታም ባንሆንም፤ በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነት ተነጥሎ መታየት የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የመስኖና የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የኤሌክትሪክ ግድቦች ላይ በማተኮር እየሰራ ነው። እነዚህ በተፈለገው መጠን ለውጥ እያመጡ ነው?
አቶ አማን ይኹን፡- የተፈለገው ለውጥ ቢኖርማ አሁን የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት በዚህ ደረጃ አይሆንም፡፡ አሁን ባለው መንግሥት የተጀመሩ ግድቦችንና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስጨረስ ነው። የተጀመሩት ማለቅ አለባቸው፡፡ ኢኮኖሚ ሲባል ቀዳዳው ብዙ ነው፡፡ የትኛውን ከየትኛው ላስቀድም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ ሲሞላ ሌላው ይጎድላል። የዚህ ሀገር ኢኮኖሚ ለረጅም ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ጥያቄዎች አሉበት፡፡ በላይ በላዩም አዳዲስ ነገሮች ይከማቻሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ተደራራቢ ችግሮችን ለማቃለል በጣም ፈታኝ ነው፡፡ አሁን አስተያየት እንደምሰጥህ ቀላል አይደለም፡፡ መንግሥት ሆነህ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ ግን መንግሥት ሆኖ ለሁሉም መሠረት በሆነው ሠላም ላይ ማተኮርና ግጭትን በፍጥነት መፍታት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን በማድረግ የሀገሪቱን አቅም ወደ ኢኮኖሚው ማዞር ይገባል፡፡ ኢኮኖሚው ከተንቀሳቀሰ በርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ ዜጎችም የኑሮ ውድነት ቢኖር እንኳን የመክፈል አቅም ይፈጥራሉ፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ ደግሞ ኢንዱስትሪና ግብርና ትልቅ አቅም አላቸው፡፡ በመሆኑ ከተማ ውስጥ ያሉ ሪል ስቴቶችና ብልጭልጭ ነገሮች የረባ የሥራ ዕድል አይፈጥሩም፡፡ በተጨማሪም ሥራው ምርት አልተጨመረበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመንግሥት ሪፖርት ግን በቀዳሚነት ሥራ ዕድል ከሚፈጥሩት ውስጥ ኮንስትራክሽን ቀዳሚው ነው፡፡ ሃሳብዎት ከዚህ አይጋጭም?
አቶ አማን ይኹን፡- ልክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተገነባ ነገር ስላለ በስፋት እየገነባን እንደመሆናችን ኮንስትራክሽን ዘርፉ በጣም ሥራ ይፈጥራል፡፡ ግን አሁንም ቢሆን የሥራ ፈጠራ ዘርፋችን ግብርና እና ኢንዱስትሪ ላይ የበለጠ ማተኮር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ግብርና መር ኢኮኖሚ በሚል ለዓመታት ሲመራበት ነበር፡፡ ለምን ከችግሩ መውጣት አልተቻለም?
አቶ አማን ይኹን፡- መንግሥት ግብርና መር የሚለው ውሸትና ማጭበርበር ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ በትክክል የግብርናው ዘርፍ ችግር መቅርፍ የፖሊስ ለውጥ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ መሬት ለአራሹ ብሎ አርሶ አደሩን የመሬት ባለቤት ያደረገውን የደርግ ህግ ኢህአዴግ ሲመጣ በህገመንግሥት ሽሮታል። ስለዚህ አርሶ አደሩ በትክክል የመሬት ባለቤትና ባለመብት መሆን አለበት፡፡ በባለቤትነት እንደልቡ እንዲያርስና ምርቱን እንዲያሳድግ ማድረግ ይገባል። ግብርናውን የሚያሳድግ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ሌሎች ግብዓቶችን በገበያ መስፈርት በውድድር እንዲሁም በድጎማ ጭምር ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ይገባል፡፡
ኢህአዴግ ግን ለፓርቲ የንግድ ድርጅቶች አርሶ አደሩን መበዝበዣ ያመቻቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኢህአዴግ ድርጅቶችን ሃብታም ከማድረግ ውጭ ግብርናውንና አርሶ አደሩን አላሳደገም፡፡ ለግብርናው ሲበጀት የነበረውና ባንኮች ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጡት የብድር መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ኢህአዴግ የምከተለው ግብርና መር ነው ሲል የነበረው ለይስሙላ ነው፡፡ 80 ከመቶ የሆነውን የገጠሩን ማህበረሰብ ይዣለሁ ሁሌ እምርጣለሁ በሚል እና አርሶ አደሩን ከመሬት ጋር አስሮ ለማስቀመጥ ነው፡፡
አርሶ አደሩ በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳይችል እና ግብርናው አልተመቸኝም ቢል መሬቱን ሸጦ በሌላ ዘርፍ እንዳይሰማራ ያደረገ ሲሆን አርሶ አደሩን መብት አልባ እና ጭሰኛ ያደረገ ሥርዓት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህን ማስተካከል ብለን ለመንግሥት ሙያዊ ምክረ ብናቀርብም ህገ መንግሥቱ ሲሻሻል ወደፊት እናያለን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ማስተካከል አልችልም የሚል ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያን ግብርና ማሳደግ ከተፈለገ የግብርናውን ማነቆ መፍታት ከታሰበበት የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ሳይፈታ በዘርፉ የምርት መጨመር እምብዛም አይሆንም፡፡
አርሶ አደሩ መሬቱን አስይዞ ከባንክ መበደር አይችልም፡፡ መበደር የሚለው ከኢህአዴግ የቁጠባ ድርጅቶች ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ ከፍተኛ ወለድ ያስከፍላሉ፡፡ አርሶ አደሩ እየተንገላታ ያለው ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ብዝበዛ ሂደት ውስጥ ነው፡፡ ወደ ኢንዱስትሪው ስንመጣ አብዛኛው ጥሬ ዕቃ ከሀገር ውስጥ ስለማያገኝ ከውጭ ነው የሚያስገቡት፡፡ ዘይት ፋብሪካዎች እና ድቄት ፋብሪካዎች ጭምር ጥሬ እቃ የሚያስገቡት ከውጭ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ መጠናቸው አነስተኛ ቢሆንም 500 የዱቄት ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱም 50 ከመቶ የአቅማቸውን እየተጠቀሙ አይደለም፡፡ ይህም የሆነው በጥሬ ዕቃ እጥረት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት፣ መለዋወጫ ችግር ሲከሰት እንደልብ አለማግኘት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የመሳሰሉት ተደራራቢ ችግሮች የሚያጋጥማቸው በመሆኑ ነው። በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪያችን ሊቀርፍ የሚችል በጣም የታሰበበት የተሻለ ስትራቴጂ መነደፍ አለበት፡፡ እስከዛሬ የመጣንበት ብዙ ርቀት አላስኬደንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገር ደረጃ ለገጠመን የዋጋ ንረት የረጅም ጊዜ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁናዊ መፍትሄዎች ምንድን ናቸው?
አቶ አማን ይኹን፡- መንግሥት ሊወስድ የሚችለው ትኩረት ሰጥቶ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል መሥራትና ከውጭ ምርት ማስገባት ይገባል። ከጎረቤት ሀገርም ቢሆን የሚቻሉ አማራጮችን መሞከር ተገቢ ነው፡፡ የገበያ ሥርዓት ላይም አሉ የሚባሉ ግድፈቶችን ማስተካከል ይገባል፡፡ በትራንስፖርት፣ በስርጭት መስተጓጎል የሚፈጥሩትን ማስተካከል ይገባል፡፡ ትልቁና መጠንቀቅ የሚገባው ለኑሮ ውድነት ነጋዴን ተጠያቂ ማድረግ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ነጋዴ ማለት ገበያ ነው፡፡ ገበያ አቅርቦትና ፍላጎት የሚገናኙበት ነው፡፡ ነጋዴ ገበያ ላይ አንዱ ተዋናይ ነው፡፡ የምርት እጥረት ከሌለ በስተቀር ገበያ ላይ እጥረት አይከሰትም፡፡
የአንዳንድ ነጋዴዎች ስግብግብነት የችግሩን መሰረታዊ ምክንያት የሚገልጽ አይደለም፡፡ ነጋዴዎች የራሳቸው ሚና የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ አጠቃላይ ገበያው ዘመናዊና ለውድድር ክፍት ካልሆነ፣ መንግሥት ዘመናዊ የገበያ ሥርዓት በመላ ሀገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግ ካልቻለ ምርት እያለ እጥረት ሊከሰት ይችላል። ገዥ እያለ አቅርቦት ሊስተጓጎል ይችላል፡፡ ገበያ እያለ በሎጅስቲክስ፣ ሰው ሠራሽ የተፈጥሮ አደጋዎች ሊስተጓጎልም ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሩን የሚፈጥሩ ሳይሆን ችግሩን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ ችግር አባባሽ እና ችግር ፈጣሪው መለየት አለበት፡፡ ስለዚህ ዋናው ቁልፍ ችግር የምርት እጥረት ሲሆን ከውጭ ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመር የሚያመጣው ችግርም ነው፡፡ በመሆኑም ይህንንም መቆጣጠር ይገባል፡፡ መፍጠር ያለብን የተፈጥሮ ሃብታችንን መሸከም የሚችል ህዝብ ነው። ምርት ሊያሳድጉ የሚችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይገባል፡፡ ህገመንግሥቱ መሻሻል ካለበትም መሻሻል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ንረቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ምን ዓይነት ቢሆኖች ሊኖሩ ይችላሉ?
አቶ አማን ይኹን፡- ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ሱዳን ውስጥ ፕሬዚዳንት አልበሽር ከስልጣን የወረዱት የዳቦ ዋጋ በተወሰነ ደረጃ ጨምሮ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግብጽ ውስጥ አለመረጋጋት አለ። የዳቦ ስንዴ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ከራሺያ ታስገባለች። እኛ ሀገር ህዝብ በጣም የተረጋጋ እና አስተዋይ ነው። በሌላ ሀገር ቢሆን ከፍተኛ ቀውስ ያመጣል። 1966 ዓ.ም የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት ከስልጣን ለመውረድ ቅጽበታዊ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ በአረብና እስራኤል መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ነዳጅ ዋጋው ሲወደድ ታክሲ ሹፌሮች አመፅ ጀመሩ። የአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮች አመፅ መቱ፤ ነገሮች እየተቀጣጠሉ ሄዱ፡፡ በውስጥ ብዙ የተከማቸና ሲብላላ የቆየ ችግር የነበረ ቢሆንም ለዚህ መነሻው የዋጋ ንረት ነበር፡፡ ወንጀል እንዳይበራከትና ቀውስ እንዳይከሰትም በሚገባ ሌት ተቀን መሥራት ይገባል፡፡ በተቻለ መጠን አቅምን አሟጦ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ በመሆን ሙያዊ ሃሳብ ስለሰጡን አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አማን ይኹን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም