የዋጋ ንረት በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት አልሆነለትም፡፡ ይህም የኅብረተሰቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የዋጋ ንረቱ እንኳን ቅናሽ ማሳየት ይቅርና ባለበት መቀጠልም አልቻለም፡፡ አሁን ያለው የዋጋ ንረት ከእስካሁን ሁሉ የከፋ ነው፤ ነገ ደግሞ ከዛሬውም የባሰ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በአንዳንዶቹ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት ደግሞ ጠዋትና እና ከሰዓት በኋላ ሰፊ የዋጋ ልዩነት እስከማሳየት የደረሰ ነው፡፡
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች የሚሳዩትም የዋጋ ንረቱ እየተባባሰ መሄዱን ነው፡፡ እጅግ የሚያስገርመው ነገር አገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ሰማይ መድረሱ ነው፡፡
ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ አርሶ አደሮች ደጋግመው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው፡፡ አትክልትና ፍራፍሬን ለማሳያነት ያህል ጠቀስኩ እንጂ በሌሎቹ ምርቶች ላይ ያለውም የዋጋ ንረት የሚቀመስ አይደለም፡፡
መንግሥትም ለኑሮ ውድነቱ በየጊዜው የሚደረድራቸው ምክንያቶቹ ዛሬም አላለቁበትም። አንድ ጊዜ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የታየ የዋጋ ንረት … የነዳጅ ዋጋ መጨመር››፣ ሌላ ጊዜ ‹‹የስግብግብ ነጋዴዎች ድርጊት››፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ኢኮኖሚያዊ አሻጥር›› … እያለ ይናገራል፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ግን ኑሮ ናላውን ላዞረው ኅብረተሰብ ምንም ፋይዳ የላቸውም፤ አይኖራቸውምም፡፡
ሁነኛ ሰሚ ጆሮ ባያገኙም ‹‹ኑሮውን አልቻልነውም … የዋጋ ንረቱ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል …›› የሚሉና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲደመጡ የቆዩ የዜጎች ድምፆች ዛሬም እየተስተጋቡ ነው፡፡
መንግሥት ዛሬም ከዚህ ቀደም ሲናገራቸው የነበሩ ምክንያቶችን እየነገረን ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሰሞኑን ለተከሰተው የምግብ ዘይት እጥረትም ‹‹የስግብግብ ነጋዴዎች ድርጊት›› የሚለው ምክንያት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ‹‹ስግብግብ›› የሚባሉት ነጋዴዎች የማይታዩ/የማይታወቁ ፍጡራን ናቸው? እንዲህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉትስ ብቻቸውን ነው? መልሶቹ ቀላል ናቸው … ነጋዴዎቹ ይታወቃሉ! ድርጊቱን የሚፈፅሙትም ብቻቸውን አይደለም!
መንግሥት ‹‹ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሬ ያደረጉ ሱቆች ታሸጉ›› ይላል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ እርምጃስ ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል? የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር ተጨማሪ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር አያደርግም? ሱቆችን ማሸግ/መዝጋት አዋጭነቱ ምን ያህል እንደሆነም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሱቆች ሲታሸጉ የሚታሸገው ምርት/ሸቀጥ በአቅርቦት ላይ የሚፈጥረው የራሱ ጫና ይኖራል፡፡
ይህ እርምጃ የአቅርቦት ሰንሰለቱን እንደሚጎዳው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ እንዲያውም የዋጋ ንረትን ሊያባብስ የሚችልበት እድል አለ፡፡ በተጨማሪም ሱቆችን ማሸግ የመጨረሻ አማራጭ ሆነው ከሚጠቀሱ እርምጃዎች መካከል አንዱ በመሆኑ የመጨረሻ አማራጮችን ከመተግባር አስቀድሞ ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ነጋዴው እንደሆነ ሱቁ ለተወሰነ ጊዜ ቢታሸግበትም በየጊዜው ዋጋ እየጨመረ የሰበሰበው ትርፍ ሱቁ ተዘግቶ በቆየባቸው ቀናት ያልሸጠውን ያካክስለታል፡፡
ሱቆች ሲታሸጉ በሚፈጠረው የአቅርቦት እጥረት የሚጎዳው ሸማቹ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መሐል ደግሞ በንግድ ሰንሰለት ውስጥ የሚፈጠርና በኅብረተሰቡ በተለይም ደግሞ በሸማቹ ላይ የተጋረጠ እጅግ አደገኛ ነቀርሳ አለ፡፡
ይህ ነቀርሳ ውስብስቡ የደላሎች ሰንሰለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በደላሎች ተፅዕኖ ስር ያልወደቀ የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም፡፡ ደላላ በመሐል ሲገባ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ተመን ከመፈጠሩም ባሻገር የግዥና ሽያጭ ስርዓቱ የተበላሸ ይሆናል፡፡
[እዚህ ላይ ግዥና ሽያጭን የሚያቀላጥፉና ሂደቱን የሚያቃልሉ ሕጋዊና የሰለጠኑ ደላላዎችን እንዳልዘነጋኋቸውና ክብር እንዳልነፈግኋቸው ማስታወስ እፈልጋለሁ] የሆነው ሆኖ የትኛውም ዓይነት ምክንያት ቢደረደር በእያንዳንዱ እቃ ላይ የሚጨመረው እያንዳንዱ ዋጋ ተጠራቅሞ የሚያርፈው በሸማቹ ኅብረተሰብ ትከሻ ላይ ነው፡፡
የመንግሥት ምክንያት ድርደራና የፌስቡክ ማኅበረሰብ ቀልድ በኑሮ ለጎበጠው ሕዝብ ምኑ ነው? ለመሆኑ መንግሥትስ እስከመቼ ድረስ ነው ‹‹ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን›› በምክንያትነት እያቀረበ የሚዘልቀው?! እዚህ ላይ ከሳምንታት በፊት ‹‹መንግሥት ‹ችግሩን እየፈጠሩ ያሉት ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው› ብሏል፡፡
እርስዎስ ምን ይላሉ?›› ተብለው የተጠየቁ አንድ ባለሙያ የሰጡትን ምላሽ ላስታውስ ‹‹ … ስግብግብ የሚባሉት ነጋዴዎች የመንግሥት ሸሪክ/Partners ናቸው››! ከዓመት ዓመት መጨመር እንጂ መቀነስ ለማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መንስዔዎቹ መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ሀብት መዋቅሮች አለመስተካከል፣ የምርት አቅርቦት እየቀነሰ መምጣት እንዲሁም የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ እንደሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ተደራርበው የኑሮ ውድነትን ማክበዳቸውንም ይገልጻሉ።
የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ለበርካታ የአገሪቱ ችግሮች መነሻ የሆነው የሰላምና መረጋጋት መደፍረስ ዋነኛ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡ በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን ክፉኛ ጎድቶታል፡፡
የአገሪቱ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ሄዷል። ሰላም ካልሰፈነ ማረስ፣ መነገድ፣ አምርቶ ወደ ውጭ መላክ፣ ኢንቨስትመንት … ፈፅሞ የማይታሰቡ ናቸው። ሰላምን ለማስፈን ዜጎችም አስተዋፆኦ እንዳላቸው ባይካድም ዋነኛው ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡
የማንኛውም መንግሥት መሰረታዊው (የመጀመሪያውና ትንሹ) ኃላፊነቱ ሰላምና ፀጥታን ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በአገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ ከቀጠለ አገሪቷን ውስብስብ ወደሆነ ችግር ሊመራት እንደሚችልና መንግሥትም ሰላምን በማስፈን ለኑሮ ውድነቱ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ማበጀት እንዳለበት ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
[ከዚህ የባሰ ውስብስብ ችግር ምን እንደሆነ ግን በውል አልተገለጠልኝም] ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች እንኳንስ ከመንግሥት፣ ከግለሰቦችም የተሰወሩ ተዓምራዊ ነገሮች አይደሉም፡፡
መፍትሄያቸውም በግልጽ የሚታወቅ ነው። በሹማምንትና በነጋዴዎች (ደላላዎችን ይጨምራል) መካከል ያለው የጥቅም ትስስር ግን ችግሮቹም ሆነ መፍትሄያቸው የማይታወቅ አስመስሎታል፡፡ ችግሩ ከራስ ጥቅም ይልቅ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችል ፍላጎትና ድፍረት ማጣት ነው፡፡
‹‹ሹማምንት ‹ስግብግብ› በተባሉት ነጋዴዎቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም ከነጋዴዎቹ ጋር ያላቸውን ህገ ወጥ ትስስር ለማቆም የሚያስችል ፍላጎት አላቸው?›› ብሎ መጠየቅ ‹‹ሞኝ›› አልያም ‹‹ስም አጥፊ›› አያስብልም፡፡ ሰላምን ለማስፈን፣ በሕገ ወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ፣ መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ፣ ከፖለቲካ ሴራ ለመላቀቅ … የሚስችል ቁርጠኛነት ከሌለ የኑሮ ውድነቱም ሆነ ሌሎች ችግሮች መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም፡፡
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 /2014