ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ከዓለምና ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል። ቀዳሚ ካደረጓት መካከል በተለያዩ ዘርፎች አይረሴ ጀግኖቿ የፈፀሟቸው ገድሎችና የፃፏቸው ወርቃማ ታሪኮች ትልቅ ቦታ አላቸው። ለዚህም ብርቅዬ አትሌቶቿ ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ የስፖርት መድረኮች ያስመዘገቧቸው አይረሴ ድሎች በብዙ አጋጣሚዎች ከዓለምና ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር ሆና ስሟ በታሪክ ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ችለዋል።
በስፖርቱ ዓለም በተለይም በአትሌቲክስ የረጅም ርቀት ውድድሮች ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በበለጠ ገናና ስም እንዲኖራት ያስቻሉ በርካታ እንቁ አትሌቶች ባለቤት ናት። ለዚህ ደግሞ እንደ ዘመናችን ሁሉም ነገር ተመቻችቶላቸው ሳይሆን ከባዶ ተነስተው ፋና ወጊ በመሆን ለአሁኖቹ ከዋክብት አትሌቶች ፈር የቀደዱ ባለታሪኮች የመሰረት ድንጋይ ናቸው።
እንደ እድል ሆኖ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ማራቶን ታሪክ በወንዶች በጀግናውና ታሪካዊው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ አማካኝነት ወርቅ ያጠለቀች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር ብቻም ሳትሆን በኦሊምፒክ የሴቶች አስር ሺ ሜትር በኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የወርቅ ሜዳሊያ የተጎናፀፈች የመጀመሪያዋ አትሌት ነች። የሁለቱ ጀግኖች ዘመን የማይሽረው ገድል ዓለም ሁሌም የማይረሳው ኢትዮጵያውያንም ዘወትር የሚኮሩበት አኩሪ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሊምፒክ መድረክ የመጀመሪያ የሆኑበት ታሪክ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ሌላም ተጨማሪ የሆኑ በርካታ ገድሎች አሉ።
በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም በሳምንቱ መጀመሪያ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ ያስባላትን ታሪክ በኦሊምፒክ ስለፈፀመችውና ብዙም ስለእሷ ሲነገር የማይስተዋለውን ፈርቀዳጅ የማራቶን ጀግኒት ይዳስሳል። ይህች ታሪካዊ ኮከብ የማይረሳ አኩሪ ገድል በኦሊምፒክ መድረክ ብትፈፅምም እምብዛም ወደ መገናኛ ብዙሃን ስትቀርብ አትታይም። ተደጋግሞ መነገር የሚገባው ታሪኳም በሚገባው ልክ ሲዘከር አይታይም። ይሁን እንጂ በቀደሙት ዓመታት የቴሌቪዥን የስፖርት ዝግጅት ሲጀምር ከሚታዩ ምስሎች መካከል እሷ አኩሪውን ታሪክ ስትፅፍ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል።
ይህች የማራቶን ባለ ታሪክ ፋጡማ ሮባ ስለመሆኗ መገመት አይከብድም። እኤአ በ1996 አትላንታ ኦሊምፒክ ላይ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በ10 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ፣ በ10 ሺ ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያውን እንቁዋ አትሌት ጌጤ ዋሚ ስታጠልቅ በሴቶች ማራቶን ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ለአሁኖች የርቀቱ ፈርጦች ፈርቀዳጃ በመሆን መላውን የጥቁር ሕዝብ ጮቤ አስረግጣለች ።
ፋጡማ ትልቁን ታሪክ ለመስራትና ለበርካታ አፍሪካውያን ሴት አትሌቶች ምሳሌና የይቻላል ምልክት ለመሆን ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋለች። ከአትላንታ ኦሊምፒክ አንድ ዓመት በፊት 1995 እኤአ ስዊድን ላይ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አገሯን ወክላ ተሳታፊ ብትሆንም 19 ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። ይሁን እንጂ ይህ ጥሩ የማይባል ውጤት ትልቅ ታሪክ ከመስራት ተስፋ አላስቆረጣትም። በቀጣይ ዓመት ኦሊምፒክን እንድትሳተፍ የሚያደርግ ድል በጣልያን የሮም ማራቶን አሸንፋ ወደ አትላንታ በማቅናት አይረሴውንና ታሪካዊውን ድል ለማኖር በቅታለች።
ከአትላንታ ጣፋጭ የኦሊምፒክ ድል ቀጥሎ ባሉ ዓመታትም ከ1997 እስከ 1999 ድረስ በቦስተን ማራቶን ለሶስት ተከታታይ ዓመት በማሸነፍ ዛሬ ላይ መኖሪያዋን ካደረገችባት የአሜሪካ ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ የማትረሳ ኮከብ ለመሆን በቃች። በዚህም የከተማው ሰው(የቦስተን) ነዋሪዎችም ‹‹our lady›› የእኛ እምቤት እያለ ይጠሯታል።
የኦሊምፒክ ድሏ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሴቶች ማራቶን ቀዳሚ የሆነችውን የፋጡማን ታሪክ ለመድገም ኢትዮጵያ አሥራ ስድስት ዓመታትን ጠብቃለች። የፋጡማ የኦሊምፒክ ድል በማራቶን ከ16 ዓመት በኋላ ቲኪ ገላና እኤአ በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ደግማለች።
እንቁዋ አትሌት ለኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰለፈችው በ1988 እኤአ ላይ በግማሽ ማራቶን ውድድር በመሳተፍ ነበር። በሁለት የዓለም የግማሽ ማራቶን ቻምፒዮናዎች ላይም እስከ 10 ባለው ደረጃ ለመግባት በቅታለች። በ1994 እኤአ ላይ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን በፓሪስ ማራቶን ላይ ስታደርግ በ19ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰችው።
ከዚያ በኋላ የመጀመሪያ የማራቶን ድሏን ደግሞ በሞሮኮ ማራኬሽ ላይ ያስመዘገበች ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ በሮም ማራቶን በድጋሚ ለማሸነፍ በቅታለች። በ1996 እኤአ ላይ በአትላንታ በተካሄደው ኦሎምፒክ በኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ለመሰለፍ የበቃችው ከዚህ ውጤቷ በኋላ ነው። በወቅቱ የኦሊምፒክ ማራቶኑን 2:26:05 በሆነ ሰዓት አንደኛ በመሆን ስታጠናቅቅ የሩሲያዋ ቫለንቲና ይጎሮቫና ጃፓናዊቷ ዩኩ አርሞሪ 2ኛና 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል።
ከአትላንታ ኦሊምፒክ በኋላ በቦስተን ማራቶን ከ1997 እስከ 1999 እኤአ ለሶስት ጊዜ አከታትላ ካሸነፈች በኋላም ፤ በ2000 እኤአ ላይ ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ በመጨረስ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች። በ2000 እኤአ ላይ በሲድኒ ኦሊምፒክ በማራቶን ውድድር 9ኛ ደረጃ ያገኘች ሲሆን፤ በ2001 እኤአ ላይ ደግሞ በኤድመንተን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 13ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በ2004 እኤአ ላይ በጃፓን የናጋኖ ማራቶንም አሸንፋለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2014