እንደ ጃፓን፣ ታይላንድና ቻይና የመሳሰሉ ሀገራት በሳይንስና ምርምር አሁን ለደረሱበት የእድገት ደረጃ መሰረታቸው ሀገር በቀል እውቀቶች መሆናቸው ይነገራል።ኢትዮጵያም የበርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤት ብትሆንም ሀገር በቀል እውቀቶችን በመንከባከብና በተገቢ መንገድ በማጥናት ለሀገር ልማትና ለማህበረሰብ ግንባታ በመጠቀም በኩል ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉም ይጠቀሳል።
ተመራማሪዎች መነሻቸውን አጠገባቸው ያለውን ዕውቀት ከማድረግ ይልቅ በውጭ ዕውቀቶች ላይ የማተኮር እና እነዛን ገልብጦ የማምጣት አዝማሚያም እንደሚታይባቸው ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያትም በርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች ባሉበት አካባቢ ብቻ ተቀብረው ቀርተዋል። በአገር በቀል እውቀት ጥናት ማዕከላት፣በቴክኖሎጂ ሥነ-ምግባር ጥናት፣በትምህርቱና በፍልስፍናው ዓለም ባህላዊ እና ዘመናዊ እውቀት እንዴት መዋሃድ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚሰጠው ጥያቄ ከሆነም ሰነባብቷል።
በተለይም ከሀገር በቀል እውቀቶች መካከል የባህል ህክምና ትኩረት ከተነፈጋቸው መካከል መሆኑ ይጠቀሳል። በሃገራችን የባህል ህክምና ጥበብ ከሁሉም የዓለም ሀገሮች በፊት የተጀመረና ዓለም ሰልጥኖ ዘመናዊ ህክምና ከመጀመሩ በፊት ነው። በዘርፉ የተሰማሩ ጠበብት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሁሉንም አይነት በሽታ የሚፈውሱበት መድሃኒት የተለያዩ ዕጽዋትን በመመራመርና በመቀመም ለታማሚው መጥኖ በመስጠት ነበር። የባህል ህክምናን በሀገራችን በሰፊው ይጠቀሙበት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።
እንደ አለመታደል ሆኖ ዓለም በህክምናው ዘርፍ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ቢደርስም እኛ ግን የውጭውን ሥልጣኔ ተመልካች በመሆናችን ሀገር በቀል ለሆነው ባህላዊ እውቀት በአግባቡ ባለመረከባችን ቀደምት የሆነው የባህል ህክምና ተንቆና ተረስቶ እንዲኖር ፈርደንበታል።ለዛሬም ይህን ማጠየቂያ የሚያረጋግጥ አንድ ብዙ ያልተወራለት የመስኩ ምሁራንም ትኩረት ስለ ነፈጉት ባህላዊ መዋቢያና ህክምና ልናነሳ ወደናል።
የወሎ የወይባ ጢስ ሳሎን ባለቤት ሃና ብርሃኑ ትባላለች፤ደሴ ተወልዳ አድጋለች፤እቴጌ መነንና ሆጤ ትምህርት ቤቶች ተምራለች፤በወይዘሮ ስህን ቢዝነስና ስራ አመራር ኮሌጅም በሴክሬታሪያል ሳይንስ በዲፕሎማ ተመርቃለች፤ እንደማንኛውም የአካባቢው ወጣት የተሻለ ኑሮን በመመኘት ስደትን እንደ አማራጭ ወስዳለች። ለሶስት ዓመታት በዱባይ ሰርታለች። ነገሮች እንደጠበቀቻቸው ባለመሆናቸው ጊዜዋን አላባከነችም። ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ የተለያዩ ሥራዎችን ሞክራለች ። በእጇ ላይ የነበረው እውቀትን መንዝሮ መጠቀም እንዳለባት ስታምን ደግሞ የሥራና የእንጀራ መንገዷን በአደገችበት ባህላዊ እውቀት የወሎን ወይባ መርጣለች።
የሃና አያቶች ከባህሉ መፍለቂያ ባቲ አካባቢ የሚኖሩ በመሆናቸው ከነሱ የወሰደችውን ሀገር በቀል እውቀት ልታዘምነው ወዳለች። ያኔ ልጅ እያለች ወደ ባቲ አያቶቿን ለመጠየቅ ስትሄድ በአካባቢው የሚዘወተረው የወይባ ጢስ ባህላዊ ሥርዓቱን ብታይም ጥቅሙን ለመጠየቅ እንዳልደፈረች ታስታውሳለች።
በባቲ ከተማና አካባቢው እድሜዋ ለእቅመ ሂዋን የደረሰች ሴት የወይባ ጢስ መሞቅ የዘወትር ክዋኔዋ መሆኑን አረጋግጣለች። ለዚህ ይሆን “ውበት ሲለካ ባቲ ነው ለካ” የተባለው? ስትልም ራሷን ጠይቃለች።ከውበት መጠበቂያነት ባለፈም የወገብ ህመም ያለባቸው ሴቶች ደግሞ ይበልጥ እንደሚጠቀሙበት ስትሰማ ይበልጥ ለማወቅ ጓጉታለች።ባህላዊ ሥርዓቱን ስትከታተልም የተለየ ፋይዳ እንደሚኖረው በመረዳት ክትትሏን አጠናከረች።
የወይባ ጢስና በባህላዊ ሥርዓቱ
የወይባ ዛፍ በተወሰኑ የሀገራችን አካባቢዎች ብቻ የሚገኝ ዛፍ ነው። ዛፉ ለመሞቅ እስኪደርስ ድረስ ለተወሰኑ ዓመታት ይጠበቃል።ለአቅመ መሞቅ ሲደርስ ከዛፉ ላይ ቅርንጫፎቹ እየተቆረጡ ነው ለጢስነት የሚያዘጋጁት።
የወይባ ዛፍ ወደ ቢጫ የተጠጋ ቀለም አለው። ከሚሴ፣ ባቲና ወደ ራያ ቆላማው አካባቢ በብዛት ይበቅላል። ገበሬዎቹ ቆራርጠው ለገበያ ፤ነጋዴዎቹ ደግሞ ለተጠቃሚው በሚያመች መልኩ አዘጋጅተው ያቀርቡታል። እንጨቱ ሳይላጥ እርጥበቱን እንደ ጠበቀ ሲሆን ይበልጥ ይመረጣል የምትለው ሀና እርጥበቱ ከበዛና የመሻገት ምልክት የሚያሳይ ከሆነ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት መታጠብና መጽዳት እንዳለበት ትናገራለች። እንጨቱ የሚፈላለጠውም ለመሞቅ ዝግጁ ሲኮን ብቻ ነው።
በባቲና በአካባቢው የወይባ ጢስ የሚሞቁ ሴቶች በየቤታቸው የወይባ ጢስ መሞቂያ ጉድጓድና ልዩልዩ መጠቀሚያ አላቸው። በባህሉ መሰረት አንዲት ሴት ወይባ ለመሞቅ ስትዘጋጅ ማሟላት ያለባት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። በዛ ያለ ቅቤ አናቷን መቀባት ይኖርባታል፤ የወይባው ጢስ ጉድጓዱ ውስጥ ከተደረገ በኋላ ማንኛውንም ወይም ያዘቦት ልብስ መልበስ ትችላለች። ጢሱ ወደውጭ እንዳይወጣ ግን ቆዳ ወይም ብርድልብስ ከላይ መደረብ የግድ ይላል።
በጢሱ ሙቀት እንደ ዘመናዊው ስቲም ቅቤው እየቀለጠ በሰውነታቸው ላይ ሲፈስ የሰውነታቸውን ቆዳ እንደሚያጠራው የምትናገረው ሀና የጢሱ ጠረንም የሚወደድ በመሆኑ አካባቢውን እንደሚያውደው ታስታ ውሳለች። ወይባ ጢስ የምትሞቅ ሴት የምትመገበውም የተለየ ነው። ወይባ ለመሞቅ ከመግባቷ በፊት የዘንጋዳ ንፍሮ ይቀቀላል። እንደንፍሮ ብዙም አይበስልም፤ ውሃውም ሳይጠነፈፍም፤ከተገኘ በማር ታሽቶ ይዘጋጃል። ወይባ ሲሞቅ የምግብ ፍላጎት በእጅጉ ስለሚጨምር እየተሞቀ ወይም ስትጨርስ የተዘጋጀውን የዘንጋዳ ንፍሮ ወይም ገንፎ መመገብ የግድ ይላል ። በተለይ በቅርብ የወለደች እናት ከሆነች ወገቧን በማጽናትና ማህጸኗንም እንደሚጠግነው ስለምታምን በደምብ መመገብ ይኖርባታል።
ዘመንኛው የወይባ ጢስ
የወይባ ጢስ ወደ ከተማ ሲመጣ የተወሰኑ ማሻሻያዎች እንደተደረገበት የምትናገረው ሃና የገጠሩን ወይም ባህላዊውን እንዳለ ወደ ከተማ ለማምጣት ከማይቻለባቸው ነገሮች መካከል የቦታው ሁኔታ መሆኑን ታስታውሳለች። በገጠር አካባቢ ጉድጓድ ተቆፍሮ የሚጠቀሙትን ከተማ ላይ ለማምጣት አስቸጋሪ በመሆኑ ለዚሁ ተግባር የሚያመች ወንበር አዘጋጅታለች። ወንበሩ መቀመጫው ላይ ቀዳዳ ይደረግበትና ከስሩ እሳት የሚቀመጥበትን ሸክላ የሚይዝ በቀላሉ የሚከፈትና የሚዘጋ ቦታ በልዩ ይዘጋጅለታል።
ሃና ወሎ የወይባ ጢስ ድርጅትን በህጋዊ ፈቃድ ሥራ ከጀመረች ሁለት ዓመት ቢሆናትም፤ እርሷ በቋሚነት መሞቅ ከጀመረች ከሰባት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ስትሞቅም ይበልጥ እንደሚያዝናናት፤በራስ መተማመኗ እንደሚጨምርና ሁልጊዜም ንጹህ እንደሆነች እንደሚሰማት ትናገራለች።
ሃና በእርሷ ድርጅት ያለውን የወይባጢስ አጠቃቀምን እንዲህ ታብራራለች።“የከተማው የወይባ ጢስ አሟሟቅ ለየት እንዲልና ይበልጥ ምቾት እንዲኖረው ይደረጋል። ሴቶቹ ሙሉ ሰውነታቸውን ቅቤ ይቀባሉ፤አናታቸው ላይም በዛ ያለ ቅቤ ይደረጋል።ፊታቸውን ደግሞ ተፈ ጥሮአዊ የሆነው የውበት መጠበቂያ እርድና የወይራ ዘይት ይቀባሉ። እርድና የወይራ ዘይቱም የፊታቸውን ቆዳ ያጠራዋል። ጢሱ እጅና እግርን ስለሚያቀላ እጃቸውና እግራቸው በፌስታል እሸፍናለሁ”። ትላለች።
የወይባ ጢስ እየተሞቀ ምንም አይነት ኬሚካል ያለው መዋቢያ መጠቀም አይቻልም የምትለው ሃና ሁሉም ነገር ተፈጥራዊ መሆን እንደሚገባው ትመክራለች። “ለዚሁ ተግባር የተዘጋጀና ከጥጥ የተሰራ ንጹህ ነጭ ልብስ ይለብሳሉ። ጢሱ ወደ ውጭ እንዳይወጣ በካባ መልክ ከሲንቴቲክ የተዘጋጀ ሙቀትና ጢሱን የማያስወጣ ልብስ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ መደረቢያ ስለሚኖር እሱን በማልበስ ለአንድ ሰዓት ያህል የወይባውን ጢስ እንዲሞቁ አደርጋለሁ። እየሞቁም ሆነ ሙቀው ሲጨርሱ ተልባ፣ ጁስ፣ቡላና የመሳሰሉት ምግብ ይቀርብላቸዋል።ከአንድ ሰዓት ወይባ ጢስ ከተሞቅ በኋላ የቅቤውን ሽታ ለማስወገድ ራቁታቸውን ይሆኑና በተፈጨ ቡና፤ ከወይራ ዘይትና ከቀስል በተዘጋጀ መታሻ ይታሻሉ። ቡናው ያልደቀቀ በመሆኑና ሽታን የማጥፋት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ስላለው የቅቤውን ሽታም ያጠፋዋል፤ ሰውነታቸውን ለማነቃቃት ተመራጭ ይሆናል።ከታሹ በኋላ ገላቸውን ይታጠባሉ።” በማለት ዘመናዊውን አሰራር ታስረዳለች።
የሃና አብዛኛዎቹ ደምበኞች ያገቡና የወለዱ ሴቶች ሲሆኑ ስለወይባ ጢስ መረጃውን ከሰዎች ሰምተው የሚመጡም እንዳሉ ትናገራለች ። በቋሚነት የሚጠቀሙ ደምበኞችም አሏት።የወይባ ጢስ ከሚሞቁ ደምበኞቿ እንደተረዳችውም የወገብ ህመምን ከመፈወሱ በተጨማሪ ለወለዱ እናቶች የማህጸን ጤናን ይጠብቃል፤ እርጅናን ይከላከል፤ በተለይም የቆዳ መሸብሸብን በእጅጉ እንደሚያስወግድ ታስረዳለች። ቋሚ ደምበኞች በሳምንት ሁለት ቀን የሚጠቀሙ ሲኖሩ አልፎ አለፎም በየሁለት ቀኑ የሚጠቀሙ ደምበኞች አሏት። በተለይም አራሶች ከወለዱ ከሳምንት በኋላ ቢሞቁት ብዙ የጤና በረከቶች እንደሚያገኙ ትናገራለች።
አዲስ አበባ ላይ ተፈላጊነቱ እንደጨመረና በየቀኑ እስከ አስር ሰው የሚጠቀምበት አጋጣሚ አለው። በአዲስ አበባ ከ10 በላይ አስጠቃሚዎች አሉ። ከእነዚህ ጋር በማህበር ለመደራጀት ብታስብም አልተሳካላትም።በማህበር ቢሰባ ሰቡ የአጠቃቀም መመሪያ ለማዘጋጀት እንደሚቻል ታስባለች።
አንዳንድ ቦታዎች የወይባ እንጨት እጥረት በመኖሩ ሌላ እንጨትን አመሳስለው እንዳይጠቀሙ ትመክራለች። መለያውም እንጨቱ ቢጫ ቀለም ያለው መሆኑ ሲጨስም ከጥሩ ጠረን ውጭ የማይከረክር መሆኑን ማረጋገጫ ነው ትላለች። ሁሉም የወይባ እንጨት ጥቅም ላይ አይውልም፤ በተለይ ትል የበላውና የጠቆረ ነገር ካለው መሞቅ የለበትም።ተጠቃሚዎችም ይህን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ትመክራለች።
ብዙ እናቶች ዋጋውን በመፍራት ብቻ እየፈለጉ መጠቀም እንደማይችሉ አረጋግጣለች። የመስሪያ ቦታና ሌሎች ድጋፎች ቢደረጉላት ለሁሉም እናቶች በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ በባህላዊ መንገድ ጤናን ማዳረስና መዝናኛ እንዲሆን ታስባለች። ብዙ ሴቶች ድካም ስለሚበዛባቸው አስበውና ፈልገው የሚመጡበት አንድ ማዕከል ቢዘጋጅ እግረመንገዳቸውን እየተዝናኑ ጤናቸውን የሚጠብቁበት ሁኔታ ለማመቻቸትም ትፈልጋለች።
በአንድ ቀን እስከ አስር ሰው የማስተናገድ አቅም አላት ፤ በአንድ ጊዜ ሶስት ሴቶችን ማስጠቀም ትችላለች። ሁሉም ሰው በእውቀት ቢሰራው መልካም እንደሆነ የምትናገረው ሃና ሰዎች ውጤቱን ወዲያውኑ የሚያዩበት በመሆኑ ተጠቃሚዎች ደስተኞች መሆናቸውን በተግባር አረጋግጣለች።
የወለዱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሴቶች ቢጠቀሙት ከመዋብ ባለፈ ፋይዳው ብዙ መሆኑን የምትናገረው ሃና፤ የተወሰኑም ቢሆኑ ሚስቶቻቸውን አምጥተው የወይባ ጢስ የሚያስሞቁ በመኖራቸው እንደምትደሰትና ሁሉም ወንዶች ሚስቶቻቸውን ቢያበረቷቸው በራስ መተማመናቸው ይጨምራል። እነሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ወደ ተፈጥሮ መመለስ መሆኑንም ትመክራለች።
ወይባን ማን ያጥናው?
የወይባ ጢስ ማህበረሰቡ በሀገር በቀል እውቀቱ ያመጣው፤ ጥቅሙንም በተግባር ፈትኖ ያረጋገጠው ቢሆንም እስካሁን ድረስ በጥናት የተደገፈ መረጃ ባለመውጣቱ ሰዎች በማየትና በመሞከር የሚያረጋግጡት በመሆኑ ትኩረታቸውን በሀገር በቀል እውቀት ላይ ያደረጉ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የበለጠ ጥናት ቢያደርጉበት ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም የወይባ ጢስ ባለሙያዋ ሃና ታስረዳለች።
ንግድ ፈቃድ ለማውጣት እንኳን በውበት መጠበቂያ ስም የሚካተት በመሆኑ ለጤና የሚሰጠው በረከት እየተዋወቀ አለመሆኑም ያሳስባታል።ከውበት መጠበቂያነት አልፎ ለጤና ያለው በረከት በጥናት ቢደገፍ ብዙ ሴቶች ሊጠቀሙበት እንደሚችልም ታስባለች።
“እኔ አቅም ቢኖረኝ ላስጠናው እፈልጋለሁ” የምትለው ሃና ሰዎች በስሚ ስሚ ከሚመጡ በጥናት የተደገፈ ውጤት ቢኖረው ኢንተርኔት ላይ ጥቅሙን አይተው እንዲጠቀሙበት ለማድረግ እንደሚቻል ታስረዳለች። ወይባ የሀገሪቱ በስፋት ያልተጠቀምንበት አንድ ሀብት ነው። እስካሁን በጉዳት የሚጠቀስ ምንም ነገር ባይኖርም በተለይም መጠቀም የሌለባቸው ሰዎችን ለመለየት የሚያስችል በሳይንሳዊ ዘዴ የተደገፈ የብቃት ማረጋገጫ ቢኖረው ከሀገራችን አልፎ ሌሎችም እንዲጠቀሙበት የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ጭምር ራስንና ሀገርን ለማስተዋወቅ መልካም ይሆናል የሚል እምነት አላት ።
ብሩንዲ የምትኖር ደንበኛዋ ጥናት ለማድረግ ጀምራ እንደነበር የምታስታውሰው ሃና ከሷ ብዙ መረጃዎችን በመውሰዷ ውጤቱ ምን እንደደረሰ ለማወቁ በጉጉት ላይ መሆኗን ትናገራለች።ይሁን እንጂ የወይባ ጭስ ሀገር በቀል በመሆኑ በሀገራችን ተመራማሪዎች ጥናት ቢደረግበት መልካም ነው ። በተለይም መሰረቱ ከወሎ አካባቢ በመሆኑ እዛ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናትና ምርምር ቢያደርጉ ከመዋቢያ ባለፈም ያለውን ፈዋሽነት በማጥናት ሀገርም ህዝብም ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ታምናለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም