በአገራችን ፖለቲከኝነት ብዙ ትርጉም ይሰጠዋል። በተለይም ብዙዎች የሚስማሙበት መሟገትን ትርጉም አልባ ያደረገ ነው ይሉታል።ምክንያቱም ሙግት ለማን የሚለው አልተለየበትም።ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚያነሱት ብዙዎች ሙግታቸው ስልጣናቸው እንጂ ሰው አልሆነም የሚለው ነው። ሙግታቸው ግለሰባዊ ጥቅም እንጂ አገርን አስቀድሞም አያውቅም።ፖለቲካውን ሰበብ አድርገው ፖለቲ ከኞች ስልጣን የሰጣቸውን አካልም ሲያከ ብሩትም አልታዩም።እንደውም ይባስ ብለው ሲያሰቃዩትና ሲያሳድዱት ይስተዋላል።ይህ ግን በሞራል ልዕልና እና በአስተሳሰብ ብቃት ካልተገራ መቼም ትርጉሙ ላይ እንደማይደርስ ይስማማሉ። ሰላማዊ መንገዶችን መርጦ ለአንድ ሕዝብና አገር ቁርጠኛ ሆኖ ካልተሰራበት፤ ለተጎዱ እና ለተገፉ ሰዎች ተቆርቋሪ ሆኖ መቆም ካልተቻለበት ሀሳቡ መሬት አይወርድምም ይላሉ።
እራስን ከማስቀደም አባዜ ነጻ መሆን ከተቻለና ለሌሎች ተገቢውን ክብር እና ትህትና ማሳየት ልምድ ከሆነ ሁሉም ትርጉሙን ያገኛል።በተለይም ታማኝነትን በመንፈስ ልዕልና ደግፎ የተናገሩትን በሥራ ከተረጎሙት የማይለወጥ ነገር እንደሌለ ሁሉም ያምናሉ።ፖለቲካው የጎደለው ጽናት፣ ሚዛናዊነት እና ለፍትህ ተቆርቋሪነት እንዲሁም ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች በመሆናቸው እነዚህን አስተባብረው ፖለቲከኞች መከወን ከቻሉ ፖለቲከኛነት መደበላለቁን ያቆማል፤ ትርጉሙን አግኝቶ የመፍትሄ አካል ይሆናል የሚለውን ሀሳብ ከሚጋሩት መካከል ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ ያደረግናቸው አቶ ተስፋሁን አለምነህ አንዱ ናቸው።እርሳቸው ካላቸው የሕይወት ልምድ አንጻር ብዙ የሚያስተምሩ ነገሮችንም ያነሳሉ።እናም ከተሞክሯቸው ተማሩ ስንል ለዛሬ እርሳቸውን ለንባብ ጋበዝንላችሁ።መልካም ንባብም ተመኘን።
የበኩር ልጁ ኃላፊነት
ተወልደው ያደጉት ከባህርዳር ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ራቅ ብላ በምትገኘው አዴት ከተማ ነው።ቤተሰባቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በተለይ የአባታቸው ጫና ቀላል የሚባል አልነበረም። እናት ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው። በዚህም ሁሉም ነገር ከእጅ ወዳፍ አድርገው እንዲኖሩ ተገደዋል። ልጆች አደግ ሲሉ ግን ብዙ ነገሮች ተቀየሩ።ሌላ መተዳደሪያቸውን ፈጥረው ችግራቸውን በብዙ መንገድ እንዲፈቱ ሆኑ።ምክንያቱ ደግሞ ግብርናው ላይ በስፋት መሥራታቸው ነው። በተለይም ከብት ርባታ ብዙ ጎዶሏቸውን ሞልቶ ላቸው ነበር።
እንግዳችን የበኩር ልጅ ሲሆኑ፤ በብዙ መልኩ የሥራ ጫና ይኖርባቸዋል፤ ኃላፊነትም እንዲሁ፤ ዋናው የበታቾቻቸውን ማገዝና መንከባከብ ነበር። በተለይም የኑሮ ደረጃ ዝቅ ሲል የበታቹንም የበላዩንም ማገዝ ግዴታ ሊሆን ይችላል።ማለትም አባት እናት ጭምር የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማድረግ ብዙ ሥራ መሥራት የእርሱ ግዴታ ሊሆን ይችላል።ማንም ልጅ አባቱና እናቱ እየሠሩ እርሱ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም።እናም የቻለውን ሁሉ ለማድረግ ይጣራል።ባለታሪካችንም ሲያደርጉ የቆዩት ይህንኑ ነው።በተለይ ከብት ማገዱና ወተት ለመሸጥ ከተማ ድረስ ተሸክሞ መጓዙ በዋናነት የሚተገብሩት ሥራቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ።
አባታቸው በምንም ተአምር ሥራ እንዲያበዙ አይፈልጉም።ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ነው የሚፈልጉት።ሆኖም እርሳቸው ግን አይሆንም ብለው የቻሉትን ሁሉ ባላቸው አቅም ይሠራሉ፤ ያግዛሉም። በተለይ አባታቸው ፋታ ለመስጠት የማይቆፍሩት ድንጋይ አልነበረም።እናታቸውንም ቢሆን የሴትና የወንድ ሥራ ጭምር ሳይሉ በቻሉት ሁሉ ይደግፏቸዋል።ይህ ደግሞ ለራሳቸው ሲሉ የሚያደርጉት እንደሆነ ይሰማቸዋል።
ይህንን ተግባራቸውን ተገደው ሳይሆን በፍቅርና በደስታ ስለሚከውኑትም በብዙ ነገር እንደተጠቀሙ ይናገራሉ። የመጀመሪያው የመጀመሪያ ልጅ በመ ሆናቸው ያገኙት ሲሆን፤ ይህም ዛሬ ድረስ እንዲኖሩት ስንቅ የሆናቸው ተግባራዊ ልምምድ ነው።በዚህ የበኩር ልጅነታቸው ኃላፊነትን መሸከም ላይ ጥሩ አቅም እንዲኖራቸው ሆነዋል።ዛሬም ምንም ቦታ ቢቀመጥ የማይፈሩና ለውሳኔ ቁርጠኛ የሆኑ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከዚያም አልፈው ውሳኔያቸው ለውጥ የሚያመጣ እንጂ መሬት ጠብ የማይል እንዲሆንም አግዟቸዋል። ከምንም በላይ ሁሉን ነገር በይቻላል መንፈስ እንዲከውኑት ያስቻላቸውም ነው።በመሞከር ውስጥ መውደቅና መነሳት እንዳለም የተረዱት በዚህ የልጅነት ጊዜያቸው የነበረው የሥራ ልምምድና ጫናው እንደሆነ ያነሳሉ።
ቤተሰቦቻቸው ሲያሳድጓቸው ምንም እንኳን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮን ቢኖሩም ከሌላው አንሰው እንዲታዩ ሳያደርጉ ነው። በልጅነት አዕምሮ ከዝቅተኛ ቤተሰብ የወጣ ነው መባል በራሱ ህመም ነው።ሰዎችም የሚሰጡት ክብር እንዲሁ በርካታ የአዕምሮ ጭንቀትን ይፈጥራል። ነገር ግን ምንም ጎሎባቸው ስለማያውቅና ይህ እንዲሰማቸው ስላልሆኑ በዝቅተኛ ገቢ ያደጉ ልጅ አይመስሉም።እንደውም ሀብታም ከሚባሉት እኩል ለብሰውና ተመግበው ነው ያደጉት። በዚህ ደግሞ የአዕምሮ እርካታቸው ዛሬም ተንደላቆ እንዳደገ ልጅ የቀጠለ ነው። ለዚህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ያመሰግናሉ።
በባህሪያቸው አትንኩኝ ባይ ሲሆኑ፤ ቁጡና የፈለጉትን መጨረሻ ሳያዩ የማይተው ናቸው። አሸናፊነትን የተላበሱና ትልቅ ሰውም ቢሆን አያቅተኝም ብለው የሚያምኑ አይነት ልጅ እንደነበሩ ይናገራሉ።ቤተሰቡን አሉበት ላይ ሆነው ባይፈጽሙትም ነገ እንደሚያደርጉላቸው ያውቃሉና ሁሉን ነገር አደርግላችኋለሁ የሚሉም ናቸው። በተመሳሳይ ጥሩ ተናጋሪና በስነጽሁፉም የተካኑ ናቸው። በዚህም ትምህርት ቤት ላይ ትልልቅ ፕሮግራሞች ሲኖሩ ከእርሳቸው ውጪ መድረኩን የሚመራው የለም።እንደውም ከተናጋሪነታቸውና ከተሟጋችነታቸው አንጻር ጋዜጠኛ የመሆን ህልምም ነበራቸው። ነገር ግን እድሜያቸው ከፍ ሲል የፖለቲካው ትኩሳት ሲጋጋምና እድሜያቸው ሲገፋቸው እንዲሁም ፖለቲካ ነክ መጽሐፍትን ማንበባቸው ሃሳባቸው ወደዚያ አዘነበለ።ሌላው ስፖርት ላይም ጥሩ አቅም የነበራቸው ሲሆን፤ በማስተባበር የተዋጣላቸውና ችግሩን ለመውሰድ ምንም የማይፈሩ ልጅ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ከልጅነታቸው ሲያደርጉት የሚደሰቱበት ነገር በእርሳቸው እገዛ ሰው እፎይ ማለት ሲችል ማየት ነው። በዚህም ዛሬ ጭምር ከሁሉም ነገር በላይ ይህ ሲሆን ማየት ያረካቸዋል።ለዚህ ደግሞ መሰረታቸው ቤተሰቦቻቸውና መምህሮቻቸው ናቸው። እነርሱ በብዙ ነገር እንደገነቧቸው ያምናሉ። በተለይም በመስጠትና ደስታን መፈለግ ዙሪያ እንዲሁም ቅድሚያ ለሌላ የሚለውን ተረድተው እንዲጓዙ ብዙ ስንቅ አስቋጥረዋቸዋል። ሁሉ ነገር በሂደት እንደሚቀየርና ተስፋ ለሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነ ያስተማሯቸውም ከአዕምሯቸው አይጠፋምና የተቋጠረላቸውን ስንቅ ለሌላ ማካፈል ላይ ዋና ባህሪያቸው አድርገው እየተጓዙ እንደሆነም ነግረውናል።
ትምህርት
ትምህርታቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩት በዚያው በተወለዱበት ቀዬ አዴት ላይ ሲሆን፤ ቀለሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ይባላል።ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍልም ትምህርታቸውን ተከታትለውበታል።ከዚያ አዴት መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ገቡና ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ተማሩ። በአዴት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ደግሞ ዘጠነኛና አስረኛ ክፍልን መማር ችለዋል። ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የሆነው ደግሞ ከአዴት ወጣ ብሎ ባለው ትምህርትቤት ነው።ምክንያቱም በአዲት ከ10ኛ ክፍል በኋላ ትምህርትቤት የለም። ስለዚህም መራዊ በመሄድ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን እንዲከታተሉ ሆነዋል።
የመራዊ ቆይታቸው እጅግ ከባድ የነበረበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም ከቤተሰብ ወጥተው አያውቁም።በዚያ ላይ የቤት ኪራዩ ፣ ምግብና አንዳንድ ወጪዎችን ማብቃቃት ፈተና ነው። እናም ምንም እንኳን ላም ሸጠው በቂ ገንዘብ ሰጥተዋቸው ቢልኳቸውም አላቂነቱ የተጠበቀ ነውና እንዳይቸገር በማለት ጦም ማደር፣ ደረቅ ዳቦ መብላትን የመሳሰሉ ችግሮችን እንዲጋፈጡ ሆነዋል። ዱቄት ከቤት ስለሚወስዱም ማቡካትና መጋገሩ እንዲሁም ወጣወጥ መሥራቱ ሌላው ፈተና ነበር።በዚያ ላይ ናፍቆትም ሲጨመርበት ትንሽ ቅሬታን በውስጣቸው ይፈጥርባቸው ነበር።ይሁን እንጂ ይህንን ችግራቸውን የሚፈታ ትልቅ ኃይል ከጎናቸው እንዳለ ያስባሉ።ያም የጓደኝነት ፍቅር ነው።ከእነርሱ ጋር ሲሆኑ ችግር ገደል ግባ ይላሉ።ምክንያቱም በጓደኝነት ትስስራቸው ብዙ ከባድ ነገሮች ይፈታሉ። መብላትና መጫወቱ እንዲሁም ያለን ተካፍሎ መኖሩ በራሱ ትልቅ አቅም እንደነበር አይረሱትም። በዚህም የመራዊ ትዝታዎቻቸው ከማይረሱት መካከል እንደሆኑ ይጠቀሳሉ። ከተቸገሩበት ይልቅ የተደሰቱበት በይበልጥ የሚያስታውሱትም ለዚህ ነው። በዚህ ሁኔታም ነው የተሻለ ተማሪ ሆነው ትምህርታቸውን የቀጠሉት።
የ12ኛ ክፍል ውጤት ከመጣ በኋላ ዩኒቨርሲቲ መግቢያውን ስላመጡ ቀጥታ ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። በዚያም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መስክን መርጠው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን መያዝ ችለዋል። ከዚያ ዓመታትን በሥራና በትግል ካሳለፉ በኋላ ነው ከትምህርት ጋር የተገናኙት።ይህ የሆነው ደግሞ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እድል ሰጥቷቸው በፖለቲካል ሳይንስና ኢንተርናሽናል ሪሌሽን በሁለተኛ ዲግሪ የተማሩበት ነው።በተለያየ መልኩ በፖለቲካውና በሌሎች የትምህርት መስኮችም ልዩ ልዩ ስልጠናዎች ወስደዋል። ቀጣይም ቢሆን መማር በብዙ መንገድ እንደሚገነባ ያውቃሉና ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውናል።
ታጋዩ መምህር
የመጀመሪያ ሥራቸው የነበረው መምህርነት ሲሆን፤ ምዕራብ ጎጃም ዞን ‹‹ቋሪት›› የምትባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲመደቡ ሆነዋል።በዚያም በጣም ጎበዝ መምህርና በስነጽሁፉም የተሻለ አቅማቸውን በማሳየታቸው ሞዴል አስተማሪ ተብለውም ተሸልመዋል። ይሁን እንጂ ከአስር ወር የበለጠ አልሰሩበትም ነበር። ምክንያቱም ከልጅነታቸው ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያዳበሩት የፖለቲካ እውቀት ሥራውን ሊያሰራቸው አልቻለም።እናም ከዚህ ቀይረው ደንበጫ ላይ ከዚያም አዴት መሰናዶ ትምህርት ቤት እያሉ ተዘዋውረው ሦስት ዓመት ያህል ካስተማሩ በኋላ አገሬን ማገልገል ያለብኝ በፖለቲካው መስክ ነው ብለው ቆረጡ።
ወደ ፖለቲካው እንዲገቡ በሆኑበት ወቅት የፖለቲካ ትኩሳቱ የተጋጋመበት ጊዜ ነው። ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተፈጥረዋል። እናም እርሳቸውም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ተቀላቅለው የሕዝብ ግንኙነቱን ሥራ በመቆጣጠር በተለያየ መልኩ ስርዓቱን ታገሉ።ስለ ኢትዮጵያ አንድነትም መስበካቸውን ተያያዙት።ጊዜው ግን ትግልን ሳይሆን ዝምታን አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን ይፈልግ ነበርና ይህንን አድራጊዎችን በተለያየ መልኩ ያድናቸው ጀመር።ስርዓቱን ለመገርሰስ የምታደርጉትን ነገር አቁሙ በሚልም በድብቅ አንዳንዴም በይፋ ተግባሩን የሚፈጽሙትን አካላት በመግደል አለያም በማሰቃየት ፈተናን አበዛባቸው።ለመኖር እስኪከብዳቸው ድረስም መከራ ውስጥ ከተታቸው። በዚህም መቃረን ሊያስከፍል የሚችለውን ዋጋ ሁሉ እንዲከፍሉ አደረጓቸው።ነገሩ እርሳቸውና መሰሎ ቻቸው ሲከብዳቸውና ያሉበት ሁኔታ አገርን ባሉበት ሁኔታ መለወጥና የተሻለ ስርዓት እንዲኖራት ማድረግ እንደማይችሉ ሲሰማቸው ሌላ መንገድ መቀየስ እንዳለባቸው አመኑ፡፡
በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ መታገል እንደሚያዋጣም ወሰኑና ወደ ኤርትራ ለትግል አቀኑ።ይህም ቢሆን በችግር ላይ ችግር ተደራርቦባቸው ያሳለፉበት ነው።በሕይወት እንመለሳለን ብለው ባላሰቡት ሁኔታ ላይ ጭምር ነበር ሲኖሩ የቆዩት።እንደውም የአገራችን ችግር ይሻለናል አሰኝቷቸው እንደነበርም ይናገራሉ።በእርግጥ ከአገር ውጪ መኖር ብዙ የሚያሳጣው ነገር አለ።የመጀመሪያው ደግሞ ባለሀገር አለመሆን ነው።እናም ትግሉ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊም ኢኮኖሚያዊም እንደነበር አይረሱትም።
ኤርትራ መጀመሪያ ሲገቡ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ነው የወሰዱት። በዚህም በጣም ፈታኝ ነገር አሳልፈዋል። በትንሹ እንኳን ቢታይ የአየር ንብረት ለውጡና ባለአገር አለመሆኑ እጅግ ከባድ ነው።ከዚያ ትይዩ ተጨማሪ የፖለቲካ ድርጅታቸውን አላማ የሚያሳካ ተግባር መፈጸሙ መከራ ውስጥ ሆነው የሚከውኑት ነው።በተለይ ሌሎችን ማምጣትና ማብቃት ላይ እጅግ ውስብስብ ችግሮች እንዲያሳልፉ ያደረጋቸው ጉዳይ እንደነበር አይረሱትም።ወደ ኤርትራ ሲሄዱና ሲመለሱ የነበራቸው የሰውነት አቋም በምንም አይመሳሰልም።ምክንያቱም እንደ አገር የተቀበላቸው ማንም አልነበረም።ለመሄድ ያክል ሄዱ እንጂ በምንም ተመችቷቸው አያውቅም።እናም የአገርን ዋጋ የተረዳነው ሌላ አገር ላይ ሆነን ነው ይላሉ።የነበሩበት የጉስቁልና ኑሮ በሕዝቡ ባይደገፍና ሁሉንም ተጋፍጠው ነገሮችን በሂደት ባይቀይሩት ኖሮ ሁኔታዎች በሕይወት እንዳይመለሱ ጭምር ያደርጓቸው እንደነበር ያነሳሉ።
‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብለን አላሰብንም ነበር። ይህ መሆኑን ብናውቅ ኖሮ ከአገራችን ለመውጣትም አንፈልግም።ከአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ብዙ እንታገላለን። ሆኖም በማህበረሰቡ ብርታት፣ በኢትዮጵያውያን ጩኸትና ሥራ የዛሬው ለውጥ መጥቷል። እኛን ጨምሮ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉ የፖለቲካ ታጋዮችም በዚህ ለውጥ ትልቅ ሚና ነበራቸው። በዚህም ወደ አገራችን ተመልሰን የሰላም አየር እንድንተነፍስ ሆናነል።ለዚህ ደግሞ የለውጡ መንግሥት ምስጋና ይገባዋል። ምክንያቱም መታገል አብሮ ነው በሚል ወደ አገር ውስጥ እንድንገባ በብዙ መልኩ አመቻችቶልናል።ከገባን በኋላም አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም የምርጫ ሂደቱን ተከትሎ ሌሎች ፓርቲዎችን በአቀፈ መልኩ አገረ መንግሥቱ እንዲመሰረት አድርጓል።ይህ ደግሞ አገርን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራልና ይበል ያሰኛል›› ይላሉ።
ወደ አገር ከተመለሱና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ የፖለቲካ ትግላቸውን ዘመናዊና የጠራ ፖለቲካ እንዲሆን ወደ መሥራቱ ገቡ።አገር እንድትናወጥ ባለመፈለጋቸውም ምክንያት አዕምሯቸውን ሰፋ በማድረግ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለአገር የሚሆነውን ተግባር እንዲፈጽሙ ሆኑ።በተለይም በውይይት ነገሮችን መፍታት ላይ ጠንከር ያለ ተግባር ለመከወን ቁርጠኛ የሆኑበት ጊዜ እንደነበርም ያስታውሳሉ።ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ግለሰባዊ አጀንዳን ማስተናገድ ሳይሆን ሕዝባዊ አጀንዳዎችና መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲረጋገጥና ስርዓት እንዲይዙ ማድረግ ላይ ያለመ ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹ወደ አገር ስንገባ ብዙ ደስታ ነው የተሰማን። የሚወደን፣ የሚደግፈን ሰውን በስፋት አግኝተናል። የምንሞትለትንና የምንታገልለትን ሰው በቅርብ እያየን መታገል ደግሞ ስሜቱ ዋጋ የሚተመንለት አይሆንም፡፡›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ አገር ተወረረች ሲባል በቀጥታ ወደ ዳግመኛው ትግላቸው እንደገቡ ያስረዳሉ።በዚያም ብዙ ተግባራትን ፈጽመዋል።
‹‹የሕልውናው ጦርነት እንዲከሰት ያደረገው የሥርዓቱ አለመስተካከል ነው። እኛም የወጣነው ስርዓቱ አላሰራ ስላለን ነው። ስለዚህም ያንን የማያሰራ አገር ጠል አካል ከእኛ ውጪ ሊዋጋው የሚፈልግ አይኖርም። ስለሆነም ማቄን ጨርቄን ሳልል ልፋለመው ገብቻለሁ። የቻልኩትን ሁሉም አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ። ወደፊትም ቢሆን ይህንኑ ከማድረግ ወደኋላ አልልም። ምክንያቱም በዚህ ጦርነት ላይ መሳተፍ ታሪካዊ ሰው መሆን ነው። ለአገር የሚተረክ ሥራ መስራትም እንደሆነ ይሰማኛል፡፡›› ብለውናል።
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ፍትሀዊና እኩልነትን ያረጋገጠ እንዲሆን በድርጅትም ውስጥ በመግባት ሳገለግል የኖርኩት ነው። ወያኔ ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነት እንዳለሁ የሚል ድርጅት ነው።የተነሳውም በዲሞክራሲ ስም እኩልነትን መናድ ነው።ስለሆነም አገር ተረጋግታ እንዳትቀመጥ ብዙ ተግባራትን ሲፈጽም ቆየ፤ አሁንም ለመፈጸም ተንጠራራና ብዙዎች ላይ ጉዳት አደረሰ።ንብረትንም ሆነ ሰውን አጠፋ።ስለሆነም ያንን ታግሎ ማስቆም ስላልተቻለ መኖርም፣ መስራትም አዳጋች ነው። እናም ትግሉን እንድቀላቀልም ሆኛለሁ።መንግሥት የሚሰጠኝንም ተልዕኮ ከፖለቲካ ባለፈ አገርን ማዳን በሚል በልዩ አገራዊ ፍቅር ስንቀሳቀስ ቆይቻለሁ።ይህ ደግሞ ሁሌም የምረካበት ነው ይላሉ።
አቶ ተስፋሁን፤ በራሳቸው ወደ ግንባር ሄደው ዘምተው የቻሉትን ካደረጉ በኋላ አዲሱ መንግሥት ሲመሰረት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአካተተ መልኩ እንዲሰራ በታሰበበት ሁኔታ በአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ ተመድበው እንዲያገለግሉ ተደረጉ። ይህ ሲሆን ደግሞ ድርብ ኃላፊነት ወስደው አሁንም ወደ ግንባር በመሄድ ዘመቻው የተዋጣለት እንዲሆን በብዙ መንገድ አግዘዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪክም ተሸንፎ አያውቅምና በእነርሱ አመራር ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ታጋይነትም ጭምር ነገሮች መስመር እንዲይዙ ሆነዋል።ይህ ደግሞ ሁሌም የሚደሰቱበት እንደነበርና እግዚአብሔርንም የሚያመሰግኑበት መሆኑን ይገልጻሉ።
አቶ ተስፋሁን እንደሚሉት፤ ጦርነት አውዳሚ ነው፤ አስከፊና ዳግም ውጣውረዶችን እንድናልፍ የሚያደርግ ነው።ነገር ግን ሰላም ሆኖ ለመኖር ደግሞ የመጣውን ችግር ፈጣሪ መመለስ ግድ ነው።ለዚህ ደግሞ በውይይት ካልተቻለ በጦርነቱ ማድረግ አስፈላጊ ነው።አሁንም የሆነው ይህ በመሆኑ ተደስተውበት አድርገውታል።የወጣትነት ዘመናቸውን የገበሩለትን ትግል ለማሳካትም እንዳገዛቸው ይሰማቸዋል።ስለዚህም ይህ የትግል ጊዜ ባለታሪክ የሆኑበት ስለሆነ መቼም የማይረሱት ትዝታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹ታሪክ የአገር ጀግኖችን እንጂ ራስ ወዳድና ብልጦችን አያስታውስም፡፡›› የሚሉት እንግዳችን፤ በሕልውና ዘመቻው መንግሥት መድቧቸው ሚኒሻውን በማስተባበርና በመምራት እንዲሁም ሌላ ኃይል እንዲፈጠር በማደራጀትና በመዋጋት ያገለግላሉ። ሎጂስቲኩን በማሟላትና ባስ ባለበት ቦታ ላይ ደግሞ የሚቆረጡ ሰዎችን በማውጣት ከፍተኛ ትግል አድርገዋል።ከደቡብ ወሎ ጀምሮ እስከ ጋሸና ያለውን የጸጥታ አካል መከላከያ እንዳለ ሆኖ ሲደግፉ ቆይተዋልም።
እያንዳንዱ ሥራቸው ጦርነቱ እየተካሄደ ከጥይት ጋር ተጋፍጠው እንደነበርም ያብራራሉ። እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ የማይረሱት ገጠመኝ የመቄት ወረዳ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ የሚተኮሰውን ቦታ እንዲፈልግ ታዘዘና ተመትቶ ሞተ። እናም አጋጣሚዎች እኛ ላይ አልተፈጠሩም እንጂ በሕይወት የመኖራችን ጉዳይ አጠያያቂ ነው።ቢሆንም ማንም ይከፋል የሚል እምነት የለኝም።ምክንያቱም ለአገር መሰዋዕት መሆን በጦርነት ውስጥ ግድ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ ጠጠር ወርዋሪ ያደርጋቸዋልና የታሪኩ አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው እድል ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም በእኛ ዘመን ይህንን አድርገናል የሚሉት ነገር አላቸውና።
እርሳቸው በፖለቲካው መስክ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ከማገዝ አኳያም ብዙ የሠሯቸው ተግባራት አሏቸው።አንዱና ዋነኛው ደግሞ በግላቸው መምህር እያሉ ለተማሪዎች ይበጃል ብለው የከፈቱት ‹‹ኦሮማይ›› የተሰኘ ቤተ መጽሐፍት አንዱ ነው።ይህ ቤተ መጽሐፍት ለአካባቢው ማህበረሰብም የጠቀመና ራሳቸውን ዘና እንዲያደርጉ እድል የሰጠ ነው።ሌላው አንባብያን ጋር ያደረሱት የግጥም መድብል ሲሆን፤ ‹‹አመፅ በማህፀን›› ይሰኛል።ሥራቸውን ስናነሳ አሁን ላይ ደግሞ በአማራ ክልል የአዲሱ ካቢኔ አባል ሲሆኑ፤ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄን በሊቀመንበርነት ይመራሉ።የአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢም ናቸው።እንዲሁም የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።
የሕይወት ፍልስፍና
ትግል የማይፈታውም ማንኛውም ችግር የለም። በዚህ ውስጥ ግን እምነትና አቋም ሊኖሩ ይገባል።ማሰብና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ማወቅም ግድ እንደሆነ ያምናሉ። በተመሳሳይ የሆነውን ተቀብለን ለቀጣይ መሥራትን ሁልጊዜ ልምድ ማድረግ ይገባል የሚለውም ሌላው የሕይወት መርሃቸው ነው። ታሪክ ሰሪ እንጂ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን መትጋት ሌላው የሕይወት ፍልስፍናቸው ነው።
መልእክተ ተስፋሁን
አገር ሰላም ትሆናለች፤ ትረጋጋለች ብቻ በማለት አገር ልትረጋጋ አትችልም።ይህ የሚሆነው በልጆቿ የነቃ አመራር፤ የበቃ ዜጋ ሲፈጠር ነው።ያንን ማድረግ ላይ ደግሞ በየደረጃው ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የተቀመጡ ሰዎች ከፍተኛ ትግል ማድረግ አለባቸው።የሕዝብን አደራ መወጣት ላይ ሊሰሩ ይገባል።በተለይም ፖለቲከኞች ይህንን ነገር በስፋት መመልከት ይኖርብናል።እኛ በምናደርገው የተሳሳተ መስመር አገር ዋጋ እንድትከፍል እየሆነች ነው።ስለዚህም ማስተዋልና አርአያ መሆን እንዲሁም ለአገር ማሰብ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት።ለስርዓት መታገል ያለ ነው፤ የነበረ ነው ወደፊትም ይኖራል።ነገር ግን ጥቃቅን ልዩነቶችን አጉልቶ በማውጣት የአገርን ተስፋ ማጨለም አይገባም።የፖለቲካ ጥያቄውን ሲያነሳ አገሩን ቀድሞ አስቦ መሆን አለበት የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ግለሰቦችን ምን አልባት ሊጠቅሙ ይችሉ ይሆናል።የሆኑ ቡድኖች ሊያተርፉ ይችላሉ። ነገር ግን ስላልተረዱት እንጂ እነርሱም ድርጊቱ አይጠቅማቸውም።ምክንያቱም መብላት እንኳን የሚችሉት አገር ሰላም ውላ ስታድር ብቻ ነው። ስለሆነም አገር ከግጭትና ጦርነት የምታተርፈው ነገር አይኖርምና እያንዳንዱ ግለሰብ ይህንን አስቦ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።አገርን ወደ ኋላ ለመመለስ ዋጋ ለሌለው ጉዳይ መጋጨትም የለበትም ሌላው መልእክታቸው ነው።
መሪነት በተግባር የምንፈተንበት ነው። መሪነት እድል ሰጪና ለታሪክ ቅርብ መሆንም ነው።ሕብረተሰብን ለመቀየርም የተሻለ አማራጭ የሚገኝበት ነው።ስለሆነም ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ የተሳተፉ መሪዎች ተስፋ የተጣለባቸውን ያህል ሊሰሩ ይገባል።በተለይም ልዩነቶችን ማጥበብ ላይ ትልቅ ሥራ ሰርተው አገር ከአለችበት ችግር እንድትላቀቅ ማድረግ አለባቸው።ምክንያቱም አሁን ላይ የደረስነው አንድነታችን ተሸርሽሮ ልዩነታችን ጎልቶ በመሰበኩ ነው።የተሳሳቱ ትርክቶች ትውልዱ ላይ እንዲያድጉና ቂም እንዲያረግዙ ስለሆነ ነው።ልዩነቶች የብጥብጥ እርሾ እንዲሆኑ በየጊዜው በመሰበካቸውም ምክንያት ነው።እናም ያንን አይቶ በጥናትና በጥበብ መፍታት ከምንም በላይ ያስፈልጋል ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
በመጨረሻ ያስተላለፉት መልክት ፖለቲከኞች ነገን ማየት እንዳለባቸው ያነሱት ነው። በፖለቲከኞች ቁማር፣ ሴራና አሻጥር ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት መቀጠፍ የለበትም።በፖለቲከኞች የነቃ ተሳትፎ፣ አስተዋይነትና ሩቅ አሳቢነት እንዲሁም ተባብሮ መሥራት የማህበረሰባችን የኑሮ ደረጃ መሻሻል ነው ያለበት። በተለይም ሰላምና መረጋጋት በእነዚህ ሕብረቶች መምጣት ይኖርባቸዋልና ልብ ብለን እንንቀሳቀስ ይላሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም