ዝክረ ግጥም፤
አንባቢያን ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ሲመለከቱ በርከት ያሉ ጥያቄዎች በአእምሯቸው ውስጥ ሊመላለሱ እንደሚችሉ እንገምታለን፡፡ ፖለቲካና ኪነ ጥበብ ምስስላቸው በአፈጣጠር ዕድሜ ነው? በይዘት ነው? በባህርይ ነው? በከዋኞቹ ወይንስ በሌላ በምን? በግልጽነት የቀረቡትም ይሁኑ “ወይስ በሌላ በምን” በሚል ውክልና በጥቅሉ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች በሙሉ ተገቢውን መልስ ለመስጠት የገጹ ውስንነት እጅግም አያወላዳም፡፡
ቢሆንም ግን ለሁለቱም ጽንሰ ሃሳቦች የጋራ መገለጫዎች እንደሚሆኑ በማሰብ ጠልቀንም ባይሆን ላይ ላዩን በመነካካት “መልስ አከል” ሃሳቦችን ለመፈነጣጠቅ ይሞከራል፡፡
በቅድሚያ ግን ከኪነ ጥበቡ ጎራ መካከል (ዝርዝራቸው በርከት ማለቱ ሳይዘነጋ) በተለይም የአንጋፋው የሥነጽሑፍ ቤተኛ የሆነውን የግጥምን ዘውግ ለውክልና በመምረጥ ጥቂት ማሕበረሰባዊ አገልግሎቶቹን ዘርዘር አድርግን ለማየት እንሞክራለን፡፡
ለሀገሬ ሰው ግጥም ከእስትንፋሱ የቀረበ የባህሉና የዕለት ተዕለት የሕይወቱ መገለጫ ነው፡፡ እናቶች ጨቅላ ሕጻናቶቻቸውን በእሹሩሩ ግጥም እያባበሉ ይሸነግሏቸዋል፡፡ ታዳጊ ወጣት ሴቶችና ወንዶች የዕንቁጣጣሽና የቡሄ በዓላቶቻቸውን የሚያደምቁትና የሚደምቁት በግጥም ነው፡፡
ሠርጋችን ያለ ዜማና ግጥም ፌዝ ብቻ ሳይሆን ትርጉም አልባም ጭምር ነው። የዛሬን አያድርገውና የቀብራችን ሥነ ሥርዓት ሳይቀር ይፈጸም የነበረው በሙሾ አቀንቃኞች የረገዳ ዜማና ግጥም ስለመሆኑ እኛን ባለ ባህሎቹን አይገርመን ይሆናል እንጂ ከውጭ ለሚያዩን ባዕዳን ግን እጃቸውን አፋቸው ላይ የሚያስጭን “ትንግርንት” ስለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
ባህሉ በከተሜው ዘንድ እየደበዘዘ ቢሄድም በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች ሙሾ ዛሬም ድረስ በአንቱታ ከብሮና ደምቆ እንደሚከወን አይዘነጋም፡፡ ዛሬም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ገበሬና በሬ የሚቃለዱትና የሚቃበጡት፤ የሚደናነቁትና የሚመሰጋገኑት “በበርዬ እሹሩሩ” ግጥሞች ነው፡፡ ባህሉ እስከወዲያው የሚጠፋ አይመስልም፡፡
የሰለጠኑት ሀገራት ግብርናቸውን የሚያቀላጥፉት በጭስ እየታጠኑና ድምጹ በሚያጓራ ትራክተር እየታገዙ መሆኑ መቼም አይጠፋንም፡፡ የእኛው “የጥማዱ ጌታ አያ በሬ” ግን የቅኔው ፏፏቴ በአርሶ አደሩ “የነፍስ አባታችን” ሲዥጎደጎድለት ምስጋናውን በአክብሮት የተቀበለ ይመስል ጉልበቱን ሳይቆጥብ በማሳው ላይ በመቦረቅ መሬቱን ይገምሳል፡፡
የመንገድ ዳር “የእኔ ብጤዎች” ሳይቀሩ ለዕለት ዳረጎታቸው የሚማጸኑን በግጥም እያሞጋገሱ መሆኑ የዕለት ውሏችን ትዕይንት ነው፡፡ ቀረርቶና ፉከራ ያልታከለበት የጦር ሜዳ ውሎ በክላሽንኮቭና በመድፍ የአረር ፉጨት ብቻ ድል ይገኛል ተብሎ አይታሰብም።ሠራዊት ወደ ሥልጠናም ሆነ ወደ ግዳጅ ሲሰማራ ሆ! እያለ አቧራውን የሚያጨሰው በግጥምና በዜማ ዐውሎ ነፋስ ስሜቱ እየጋለ ነው፡፡
በታክሲ ወይንም በሀገር አቋራጭ አውቶቡስ ውስጥ ስንጓዝ በዜማ የተለወሱ ግጥሞች ከጆሯችን ሳይናኙ ከመድረሻችን ጣቢያ አንደርስም፡፡ እረፍት ወስደንም ይሁን የጤና እክል ገጥሞን ወይንም በሌላ ምክንያት ቤት በምንውልባቸው ቀናትም ወይ ከሬዲዮ ጣቢያዎች አለያም ከቴሌቪዥን መስኮታችን ውስጥ “በድምጻዊ/ት እከሌ” በኩል የዜማና የግጥም ወይንም የድራማ ዳረጎት ሳይደርሰን አይውልም፡፡ እንዲያው በደምሳሳው ልብ ብለን አስተውለን ከሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ከራሳችን አንደበትም ይሁን ከማሕበረሰቡ ዘንድ የኑሯችንን ቱማታ ረገብ
የሚያደርግልንን አንዳች የኪነ ጥበብ ውጤት ሳናጣጥም ውለን አድረናል ብለን ለመመስከር አፍ ይይዛል፡፡ ምን ያህል ሃሳባችንን እንደሚሰበስብ ባላውቅም ተወልደን እስክናልፍ ድረስ የምንኖረው በኪነ ጥበብ ታዛ ሥር ተጠልለን ነው ማለቱ ይቀላል፡፡ ይህ ፀጋ ቢገፈፍ በዚህ ቅጥ ባጣ አኗኗራችን ውስጥ እንዴት ተረጋግተን ልንኖር እንደምንችል ማሰቡ በራሱ አዳጋች ይሆናል፡፡ በተለይም ቀኖቻችን እንደ አሁኑ ወቅት ባልሰከነ የፖለቲካ ቱማታ ሲዳምኑብንና ግራ ስንጋባ ከኪነ ጥበባቱ የምናተርፈው መጽናኛ ባይኖረን ኖሮ የሕይወታችን መልክ ገርጥቶ ስሜታችን በወየበ ነበር፡፡ ፖለቲካዊ ሽሙጥንም ቢሆን እንደምን በግጥም እየተዋዛ እንደሚቀርብ በብዙ ማሳያዎች ማመላከት ይቻላል፡፡ ግጥም ከቅልጥም መቅኒ ይልቅ የሚጥመው ለሕይወታችን ማጣፈጫ ስለሆነ ነው፡ ፡
በዜማና በግጥም ተፋቅረን እንቀራረባለን፤ ተንሰቅስቀን ብናለቅስም ኀዘናችን ይተንልናል፡፡ ግጥም (ሥነቃሉም ሆነ መደበኛው) የኑሯችን ፈርጥ፤ ለግል ሕይወታችንም ማድመቂያ እንዲሆን ፈጣሪ የለገሰንና ባህላችንም እያሸጋገረ ያወረሰን የከበረ ስጦታ ነው፡፡
እንግዲያውስ ግጥም “ነዎሩ የሚሰኝለት” የሁላችንም ጉዳይ ከሆነ ዘንዳ ጸሐፊው ለሁሉም የኪነ ጥበባት ወካይ እንዲሆን በማሰብ ከራሱ ማስታወሻ ውስጥ ከተዋሳቸው ጥቂት የግጥም ስንኞች መካከል “ሀገር ይሏት ጉድ ነገራችንን” በጥቂቱ ጎነጥ አድርገን የፖለቲከኞቻችንንና የኪነ ጥበባት ባለሙያዎችን “መንትያ ምስስል” ወደ መቃኘቱ ጉዳይ እናመራለን፡፡
#አንዳንዴ ግራ ሲገባ ነገር እንደ ወይን ያሰክራል፣
አለያም እንደ አብሾ አናት ላይ ወጥቶ ይዘፍናል፡፡
ይዘፍናል እንጂ ጎበዝ ምሬት ውስጥን ሲጓጉጥ፣
የምን ይሉኝታ ምን ይሉኝ በማይወለድ ክፉ ምጥ፡፡
በተለይማ ሀገር በሕዝቧ ላይ ስትከፋ፣
ትንፋሽ ነበልባል ያፈልቃል ገሞራ እሳት የሚተፋ፤
ብዕርም ቁጣ ያዘንባል መልአከ ሞትን ሳይፈራ፡፡
ይኼው አንገቴን ብሎ ተጋድሞ ካራ ይጠራል፣
በእስትንፋሱ ተወራርዶ ጭዳ ለመሆን ይቆርጣል፡፡
ሀገር ይሏት ጉድ ነገር በጓዳዋ ጉድ ስታዘምር፣
ቢያሻ ጃርት ይርመስመስ እንጂ፤ መሬት ያለ ሰው አይደምቅ።
ይላል በቁጭት ሲያነባ የደሙ ግለት ሲያነዝረው፣
ሀገር ሥራዬ ሆና እንደ ሾተላይ ስትወጋው፡፡
ስዘምር ዘመን ጃጀ ስፎክር ታሪክ አፈጀ፣
ኢትዮጵያ ይሏት ሀገር ተስፋም ኑሮም እያረጀ$ ፖለቲካና ኪነ ጥበብን ምን አመሳሰላቸው?
ፖለቲካ የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ፣ የሥልጣን መወጣጫ መሰላል፣ ባለ ሁለት ወገን የስለት ሰይፈኛና የይሉኝታ ቢስነት መገለጫም ነው፡፡ ፖለቲካ “እንደ ሰው በምድር እንደ ዓሳ በባህር” የሚያኖር ተውኔታዊ ሰብዕና የሚያላብስ ባህርይ እንዳለውም በፖለቲከኞች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በግላጭ እያስተዋልን ነው፡፡ ፖለቲካ መሃላንም ሆነ በአደባባይ የሚነገር ቃልን ሽምጥጥ አድርጎ ለመካድ ጉልበቱ የደደረ ነው፡፡ “ቃልማ ይከበራል” የሚል ተከራካሪ ከሞገተን መልሳችን “በአርቴፊሻል ባህርይው እንጂ በወርቅነቱ አይደለም” የሚል ነው፡፡ የፖለቲካ ቋንቋ “በሰምና በወርቅም” ሊመሰል ይችላል፡፡
የሰሙን ትርጉም ሕዝብ አሜን ብሎ ሲቀበል የወርቁን ፍቺ ደግሞ ፖለቲከኞቹ በልባቸው እየሳቁ ይፈቱታል፡፡ ከዚህ በላይ የፖለቲካን “ግለ ፍቺ” መለጠጥ አንድም “ለወፍ” አንድም “ለወንጭፍ” ሲለሚዳርግ በድርበቡ ነካክቶ ማለፉ ብልህነት ነው፡፡ ኪነ ጥበብ መፍለቂያውም ሆነ መድረሻው ስሜት ነው፡፡ ጠቢባኑም ስሜታቸው ስሱ መንፈሳቸው ልል ሰብዓዊያን መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ራሳቸው በፈጠሩት ዘፈን ራሳቸው አልቅሰው ያስለቅሳሉ፡፡
እንደ አስለቃሽ ሙሾ አሙሺ የእነርሱ እምባ ደርቆ ሌላውን አልቅሱ እያሉ አይኮረኩሩም፡፡ ሳቃቸውና ልቅሷቸው የተደበላለቀ ነው፡፡ ልክ እንደ ፖለቲከኞች ሁሉ ከንግግራቸው ውስጥ “ሕዝባችን” የሚል ቃል አይጠፋም፡፡ በሁለቱም ጎራ “የሕዝብ” ስም የአፋቸው ማሟሻ፣ የመሸንገያ ስልታቸው ነው፡፡ ሁለቱንም የሚያቆራኛቸው “ለሀገር ስንል” የሚለው ያፈጀና ያረጀ መደለያ ነው፡፡ ሁለቱም የሀገር ነገር ሲነሳ እያንዘረዘረ “በፍቅር ያስገዝፋቸዋል፡፡” በተግባር ግን “ሆድ ይፍጀው!” ፖለቲካ የታቀደውንና የተተገበረውን አድምቆና አጋኖ ሪፖርት በማቅረብ ያስጨበጭባል፡፡ የራበን ሆድ ሳይቀር ከወንበር አስነስቶ “በሃሌ ሉያ ለማዘመር” ፖለቲካ መቀስቀሻ ዘዴው የረቀቀ ነው፡፡ በአጭሩ ግነት ባህርይው ነው ማለት ነው፡፡ የኪነ ጥበቡም ባህርይ ይኼው ነው።
በምናብ የሚስላትን ሀገር፤ በዜማ ወይንም በስዕል አለያም በሥነ ጽሑፍ አዳምቆ በማሳየት ከተደራሲው እኩል ከያኒውም ራሱ እያለቀሰ ያስለቅሳል፡፡ ሁለቱም ጎራዎች አጀብና የሕዝብ ማዕበል ከኋላ በማሰለፍ “ቪቫ!” ማሰኘትን ይችሉበታል፡፡ ፖለቲካም ሆነ ኪነ ጥበብ አፈጣጠራቸው ምድር ላይ ብቻም ሳይሆን ከፍጥረታት አስቀድሞ በሰማየ ሰማያትም ላይ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ፍንጩን ይሰጠናል፡፡
የምድሩን የፖለቲካ ቅስቀሳ ሰምተን እጅ እጅ ስላለን እና ደግመን በጽሑፍ እንዳናሰለች በመስጋት እስኪ ለየት አድርገን የሰማዩን ጓዳ ጎድጓዳ ደፈር ብለን እንፈትሽ። ፖለቲካ የሥልጣን ግብ ግብ መርቻ የረቀቀ ስልት መሆኑን ቀደም ሲል ገልጸናል፡፡ ሰይጣን ከሰማየ ሰማያት የወደቀው የእግዜሩን ዙፋን ሲጋፋ ተደርሶበት እንደሆነ ነብዩ ኢሳይያስ በግልጽ ጽፎልናል፡፡ “አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ? …እንዴትስ እስከ ምድር ተቆረጥህ? አንተም በልብህ ወደ ሰማይ አርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ… ከደመናዎች ከፍታ በላይ አደርጋለሁ፤ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ …ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓድ ትወርዳለሁ?” (አሳይያስ. 14፥12-14)፡፡
በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ በሰይጣን የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት የከሸፈው ከዘፍጥረት ታሪክ በፊት ስለነበር የፖለቲካን ዕድሜ ከዚያ ጀምሮ ብናሰላ “የፖለቲካና የዲሞክራሲ ጀማሪ ባለቤቶቹ እኛ ነን” በማለት የሚኩራሩት የጥንታዊ ግሪክ ፈላስፎች እንደማይቀየሙን ተስፋ እናደርጋለን፤ በሃይማኖት ቤተሰቦች ዘንድም ቅሬታ እንደማያስከትል ተስፋችን ነው፡፡
ኪነ ጥበብም ቢሆን መነሻው እዚያው ሰማየ ሰማየት ውስጥ መሆኑን ይሄው ቅዱስ መጽሐፍ በሺህ ምንተ ሺህ ማስረጃዎች ያረጋግጥልናል፡፡ “መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ፣ ማኅተሙንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፡፡…እያሉ አዲስ ቅኔ ይዘምራሉ፡፡
መላእክቱም ቁጥራቸው አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበረ” (ራእይ. 5፥9-14)። መጻሕፍትም፣ ዝማሬም፣ ጥበባዊ ትዕይንትም በዚህ ክፍል በሚገባ እንደተገለጸ ከሙሉው ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ የኪነ ጥበብና የፖለቲካ ዕድሜ በሰው ልጆች እንደሚበየነው “የትናንት ከትናንት ወዲያ” ግኝቶች እንዳልሆኑ ማጣቀሻዎቻችን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡
እስካሁን ያልነውን ለማለት በወፍ በረር ቅኝት (ምናልባትም አከራካሪ የሆኑ ገዳዮችን ደፈር ብሎ በማንሳት ጭምር) ዳሰሳ ካደረግን ዘንዳ እኛንና ጊዜያችንን ጠቀስ በሆኑ አንገብጋቢ ጉዳዮቻችን ላይ ጥቂት ቁዘማ እናድርግ፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በሕዝብ ስም ይማሉ እንጂ አጮልቀው ሽቅብ የሚመኙት ሥልጣንን ነው።
የኪነ ጥበባቱ ባለሙያዎችም እንዲሁ “የሕዝብ ልጆች ነን” እያሉ በአደባባይ ራሳቸውን “ለሕዝብ ጉዲፈቻነት” ያቀረቡ ቢመስልም ምኞታቸው እና ሕልማቸው ዝናና ሀብት ስለመሆኑ ማንም ሊያስተባብል አይችልም፡፡ ፖለቲከኞች ነገ ከሥልጣናቸው ተንሸራተው ተራ ሰው ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰቡንም ሆነ መስማቱን የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡
የኪነ ጥበብ ሠፈርተኞችም ቢሆኑ ወርተረኛው ትውልድ ተነስቶ እነርሱ እንደሚረሱ ወይንም ዝናቸው እንደሚደበዝዝ እንኳን በውናቸው ቀርቶ በሕልማቸውም ማሰቡን አይፈልጉም፡፡ ፖለቲከኞች ይዋሻሉ፤ ሲዋሹም ቅርጥፍ አድርገው ነው፡፡ “ዐይኔን ግንባር ያድርገው” ብለው እስከ መማል ሲደርሱም ትንሽም ቢሆን አይሰቀጥጣቸውም፡፡
የኪነ ጥበቡም ሆነ የፖለቲካው መንደረተኞች ከነገ ይልቅ ዛሬ ላይ ቢያተኩሩ ይቀናቸዋል፡፡ ሁለቱም መኮፈስን በሚገባ ያውቁታል፡፡ ተራና ሰላምተኛ የነበረው ግለሰብ ልክ የሥልጣን ኮርቻውን መፈናጠጥ ሲጀምር የልቡ እብጠት ጨምሮ መሬቱንም ይሁን የተፈጠረበትን ማሕበረሰብ ለመጠየፍ አያመነታም፡፡ ብዙው የኪነ ጥበብ ሰውም እንደዚያው ነው፤ ዝናና አድናቆት ሲዥጎደጎድለት ከመሬት ከፍ ብሎ በዓየር ላይ ቢንሳፈፍ ደስታውን አይችለውም፡፡ በዚህ ሁሉ ቱማታ መካከል ግን ለህሊናቸው ዳኝነት የሚገዙ፣ ሕዝባቸውን በማገልገል ደስታን የሚጎናጸፉና ከዕለት ጥቅም የራቁ ቅሪቶች የሉም ማለት አይደለም።
ቁጥራቸው ኢምንት ቢሆንም አሉ፤ በሚገባም ይኖራሉ። ፖለቲከኞቻችን ሆይ! አትዋሹን ብለን የብረት ቀንበር ባንጭንባችሁም ቢያንስ ቢያንስ ግን ቴያትሩን ተውትና ውሸታችሁ ለከት ይኑረው። የፖለቲካ ሹመኞችም እንዲሁ፡፡
ጥቂት የማትባሉ ከያኒያንም እንዲሁ በሕዝብ ስም እየማላችሁ ሕዝብን አታሳንሱ፤ ለራሳችሁ ረክሳችሁ ሕዝቡንም አታርክሱ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግራ የተጋባንባቸው ሁለት ጉዳዮች ቢኖሩ አንዱ የፖለቲከኞቻችን ኪዳን ሰባሪነት፤ ሌላኛው የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች ነገረ ሥራ ነው፡፡
ሰው ሆናችሁ እንደ ሰው አገልግሉን፡፡ ዝናና ሥልጣን የዘላለም መስሏችሁ አትቀልዱብን፡፡ ዙሪያ ጥምጥም ያስኬደን ዋናው ዓላማ እያበገነ እንቅልፍ የነሳንን ይህንን መራራ መልዕክት ለማስተላለፍ ስለሆነ የሁለቱም ጎራ “ጌቶች ሆይ!” በአሜንታና በትሁት መንፈስ ሂሳችንን ተቀበሉ፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014