አገራችን፣ ሕዝባችንና መንግስት በታሪክ እንዳለፉት ጥቂት አመታት ተፈትነው አያውቁም። ይሄ ፈተና የመጨረሻ እንዲሆንና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር ደግሞ ከብልጽግና ጉባኤ የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን ይጠብቃሉ ።
1ኛ. በአገሪቱ ህልውና፣ ሰላም ፣ ደህንነትና ጸጥታ ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን በማያዳግም መንገድ የሚፈታና የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባትና በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ መስራት ስጋት የማይሆንበት አስተማማኝ አገራዊ ድባብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ውሳኔዎችንና የመተግበሪያ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
2ኛ. ዜጋውን ለከፋ ምሬት እየዳረገ ያለውን የኑሮ ውድነት፤ የዋጋ ግሽበት፣ ስርዓት አልባና አጉራ ዘለል የግብይት ስርዓት፣ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ስራ አጥነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ይመላክታሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
3ኛ. አካታች አገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር በማንነት በልዩነትና በጥላቻ የተጎነቆለውን ፖለቲካችንን እልባት የሚሰጥ፤ አገረ መንግስቱን ከተቀለሰበት ድቡሽት አንስቶ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያንጽ፤ ትውልዶች ለዘመናት ሲያነሷቸው ሲታገሉላቸውና መስዋዕት ሲከፍሉላቸው የኖሩ ጥያቄዎችን በማያዳግም ሁኔታ የሚመልስ ፤ የጋራ አገር፣ የጋራ ሕልም፣ የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ሰንደቅ አላማ፣ የጋራ ጀግና፣ የጋራ ታሪክ ፣ ወዘተረፈ እንዲኖረን የሚያግዝ ስለሆነ ለተግባራዊነቱ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
4ኛ. የህልውናችንና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን አደጋ እየሆነ የመጣውን የገነገነ ሙስና ለመከላከልና የተጀመሩ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል ተብሎ በጉጉት ይጠበቃል ። ይህን ካልን በኋላ ዛሬ ላይ የተደረሰው በብዙ ውጣውረድና ፈተና ታልፎነውና የብልጽግና ፓርቲን መንገድና የአገሪቱን የፖለቲካ ታሪክ በወፍ በረር እንቃኝ ።
የብልጽግና ፓርቲ አመሰራረት ክራሞት / chronology/፦ የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ እና የኢህአዴግ መክሰም ሂደት፤
ከመስከረም 23-25 ቀን 2011 ዓ.ም በሀዋሳ በተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ የዘገየው የፓርቲ ውሕደት በፍጥነት እንዲጠና ወሰነ ፤ ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰብስቦ ውሕደቱን በ27 አብላጫና በ6 የተቃውሞ ድምፅ አጸደቀ፤ ኅዳር 7 ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በውህድ ፓርቲው ረቂቅ ፕሮግራም ላይ ተወያይቶ ረቂቁን ለኢህአዴግ ም/ቤት መራ፤ ኅዳር 9 የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ “ብልፅግና ፓርቲ” የሚለው ስያሜ ለኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ ከስምምነት ላይ ደረሰ፤ ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ምክር ቤት (ከሕወሓት ውጭ) ውሕደቱን በሙሉ ድምፅ አጸደቀ፤ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የአዲሱን ፓርቲ የወደፊት አቅጣጫ ያመለከተ መግለጫ ወጣ፡፡ ከዚህ በኋላ እህትና አጋር ድርጅቶች (ከሕወሓት ውጭ) ተራ በተራ የብልጽግና ፓርቲን መዋሀዳቸውን ይፋ አደረጉ። በዚህም መሰረት ኅዳር 14 የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል ወሰነ፤ ኅዳር 15 የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የተጀመረውን ውህደት በመደገፍ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ ።ኅዳር 16 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ቤጉህዴፓ እና የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/የሶዴፓ/ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ ወሰኑ።ኅዳር 17 የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ/አዴፓ/እና የኦሮሞ ዴሞክራሲ ፓርቲ/ኦዲፒ/ ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባዔ ብልጽግናን ለመቀላቀል በሙሉ ድምፅ መወሰናቸው ተነገረ።የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሃብሊ) በ11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔው ብልጽግናን መቀላቀሉ በይፋ አስታወቀ።ህዳር 18 የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ ደኢህዴን/ ብልጽግናን ለመቀላቀል ወሰነ፡፡
በዚሁ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ውህደቱ ህግና ስርዓትን ጠብቆ መፈፀሙን አስታወቁ።ኅዳር 20 ውህድ ፓርቲውን የተቀላቀሉ ፓርቲዎች ፅ/ቤት ሃላፊዎች በተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ስብሰባ ተካሄደ።ኅዳር 21 የብልጽግና ፓርቲን የተቀላቀሉ ድርጅቶች ይፋዊ የስምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ አካሄዱ (ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሰረተ)።
ኅዳር 24 ብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ እውቅና እንዲሰጠው ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ።ከዚያ ወዲህ ከፍተኛ አመራሮቹ በፓርቲው ፕሮግራሞች ዙሪያ መወያየት ጀምረዋል።የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተመለከተም አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሱማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች ለስራ ቋንቋነት የተመረጡ ሲሆን፣ ፓርቲው በአገሪቱ ለሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና መስጠቱም ተገልጿል።
የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ በርካታ ሺህ አመታትን ወደኋላ ቢመልሰንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙ ፈቀቅ ያላለ ነው። ይሁንና በሰራተኛ ማህበር፣ በሙያ ማህበራት፣ በተማሪዎች ማህበራት፣ በመረዳጃ ማህበር፣ በልማት ማህበር፣ በተወላጆች ማህበር፣ ወዘተረፈ ስም የፍትሐዊነት፣ የተጠቃሚነት፣ የውክልና፣ የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የመብት ጥያቄዎች ላይ መምከርና መወያየት የተለመደ ነው።
በነጻነት የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ስላልነበር እነዚህ ማህበራዊ አደረጃጀቶች ለፖለቲካዊ ትግል ሽፋን በመሆን አገልግለዋል። በ1960ዎቹ እንደ እንጉዳይ የፈሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እርሾ በመሆንም አገልግለዋል።
ሜጫና ቱለማ መረዳጃ ለኦነግ / ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር / ፤ የአገር ቤትና የውጭ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለኢህአፓ/ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ / ፤ ለመኢሶን/ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ/ ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) ለሕወሓት/ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ መመስረት ጥንስስ ሆነው አገልግለዋል። ሕወሓት/ትህነግ ደግሞ ኢህአዴግን ጠፍጥፎ ሰራው።
ትህነግ በተለይ ከ1980 ወዲህ ባልጠበቀው ፍጥነት በጦር ውሎው በለስ እየቀናው ግዳይ እየጣለ ሲመጣ ያዝ ለቀቅ ያደርገው የነበረውን “ግንባር” የመፈጠር ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ጀመረ።
ትግራይን የመገንጠል ዕቅዱን እና የማርክሲስት ሌኒኒስት ማንፌስቶዎን ወደ መደርደሪያው መልሶ በሕልሙም በእውኑም ሳያሰበው አገር የመምራት ጉዳይ እጁ ላይ ሲወድቅ ፊቱን ግንባር ወደ መመስረት አዞረ ፡፡ ግንባር መፍጠር የፈለገው በእሱ ቋንቋ ‘ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስልጣን ለማጋራት ‘ ወይም ለአገር አስቦ ሳይሆን ቅቡልነትን ለማግኘት የቀየሰው አቋራጭ መንገድ እንጂ የኦሮሞን፣ የአማራን፣ የደቡብ፣ ወዘተ . ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ አይደለም።
የድርጅቱ መስራችና የቀድሞው ስራ አስፈጻሚ አይተ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚለው መፅሐፋቸው ገፅ 141 ላይ ይሄን ጥሬ ሀቅ አረጋግጠውልናል ።” …ግንባር ለመፍጠር ሌት ተቀን እንሰራ ነበር።ይህን ያደረግንበት ምክንያት ሕወሓት ብቻውን አገር ለመምራት ተቀባይነት (legitimacy) ስለማይኖረው ነበር ።”ኢህዴንን በ1981፣ ኦህዴድን በ1982 በመጨረሻም በ1984 ዓ.ም ደኢህዴግን የኢህአዴግ አባል አደረገ።በግንባሩ የምስረታ ሒደትም ሕወሓት በኵር ሆኖ ወጣ፡፡
ትህነግን ጨምሮ የአገራችን ፖለቲካ ድርጅቶች ለምን ይከሽፋሉ ? ይወድቃሉ ? የሚለው ጥያቄ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ይህን ጥያቄ ባንሰላሰልሁ ቁጥር ሶስት ገዥ ነጥቦች ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ። የታላቋ ብሪታኒያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብለየር እንደ ሌበር፣ ቶሪ / ኮንሰርቫቲቭ ፣ ዴሞክራት ፣ ሪፐብሊካን ፣ ክርስቲያን ዴሞክራት፣ ሶሻል ዴሞክራት ወዘተ . ያሉ ዴሞክራሲያዊ የምዕራባውያን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንኳ ያለውን፣ የነበረውን ሁኔታ (status quo) ማስቀጠል ብቻ የሚፈልጉ ከሆነ ቁሞ ቀሮች ፣ ተቸካዮች እንጂ ዘመኑን የሚዋጁ ትውልዱን የሚመጥኑ ሊሆኑ አይችሉም ብለዋል ፡፡
ብሌየር እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት ከመነጠል ጋር ተያይዞ የገባችበትን ቅርቃር እና ፓርቲያቸው ሌበር ከፊቱ የተደቀነበትን ተስፋና ስጋት አስመልክቶ ከተወዳጁ የCNN Global Public Square (GPS) አዘጋጅ እና የ Washington Post አምደኛ ፋሪድ ዘካሪያ ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሌበር ስልጣን መያዝ ከፈለገ ከኢኮኖሚያዊ ግራ ዘመምነት ወደ መሀል ወይም ማህበራዊ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን የፕሮግራሙ ማዳወሪያ ወደ ማድረግ ሊሸጋገር ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ሌበር ዛሬ ድረስ ለመመስረቱ መግፍኤ የሆኑትን ማለትም ለሰራተኛው አስተማማኝ የስራ ዋስትናን ማንበር፣ የስራ ላይ ደህንነቱን ማረጋገጥ፣ ዝቅተኛ የምንዳ መነሻውን (minimum wage) ማስወሰን እና በቀጣይ ጥቅማጥቅሙን ማስከበር የሙጥኝ ብሎ ቀጥሏል። የሌበር ሕዝባዊ መሰረት በዋነኝነት ሰራተኛው ነው ማለት ይቻላል፡፡
በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታላቋ ብሪታኒያ ፖለቲካዊ መልክዓ ከሉዓላዊነት ወደ ብሔርተኝነት፣ ወግ አጥባቂነት፣ ቀኝ ዘመምነት፣ ቀኝ አክራሪነት ወዘተ . እያዘነበለ ስለሆነ ነው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርቲያቸው ሌበር ከዚህ አዲስ አሰላለፍ አኳይ እራሱን መፈተሽ አለበት ሲሉ ምክር የለገሱት ።
የቀደመውን ፣ ነባሩን ፣ ያለውን status quo ይዞ መቀጠል ዘመኑን አይዋጅም ያሉት ።ይህን ነባራዊ እይታ prgmatic view የቻይናው ኮምኒስት ፓርቲ በከፊል ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ከፊል ገበያ መር በመቀየር ፣ የአሜሪካዊ ሪፐብሊካን በትራምፕ ጎታችነት ወደ ቀኝ አክራሪነት በመጎተት ተግብረውታል፡፡
በተመሳሳይ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ ያሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት የአሰላለፍ ሽግሽግ አድርገዋል። ዘመን ተሻጋሪው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አነስታይን ከታላላቅ ግኝቶቹ ከአንጻራዊ እይታ፣ ለአቶሚክ ቦንብ መገኘት ፈር ቀዳጅ ከሆነው ቀመርና ከሌሎች ፈጠራዎቹ ባልተናነሰ እኩል የሚታወሱለት ድንቃ ድንቅ አባባሎች አሉት።ከእነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስለት” ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ፤ ችግር መፍታት አይቻልም።” የሚለው ነው ፡፡
ብልጽግና በዚህ 1ኛ ጉባኤው ፤ የአነስታይንን ዘመን ተሻጋሪ አባባል እና ” ቁሞ ቀር ” ርዕዮት ጠል የሆነውን የብሌየርን ምክረ ሀሳብ ምርኩዝ አድርጎ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።ኢህአዴግን ለውድቀት ከዳረጉ ችግሮች ጋርም ይቆራረጣል ተብሎ ይታሰባል። በታላቁ መፅሐፍ የማቲዎስ ወንጌል 9 ÷ 17 ላይ ” በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም።
ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል።ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።” እንደሚለው አዲሱን የወይን ጠጅ ማለትም ብልጽግናን ከአረጀው አቁማዳ አውጥቶ ወደ አዲሱ አቁማዳ ያጋባል ተብሎ ይጠበቃል። አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 /2014