‹‹ኢትዮጵውያን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን እና ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በመምረጣቸው የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲባል በተለያዩ ጊዜ በውጭ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች የተቃጣባቸውን አደጋ በጋራ መመከት ችለዋል›› ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ሄኖክ ስዩም ‹‹በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት እድሎችና ፈተናዎች በሚለው ጥናታዊ ጽሁፋቸው።
ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተለየ መልኩ ነጻነቷንና አንድነቷን ጠብቃ መቆየት የመቻሏ አንዱ ምስጢር ዜጎቿ በትውልድ ቅብብሎሽ ባልደበዘዘው የአገር ወዳድነት ስሜት በክፉም በደጉም በአንድነት አብሮ በመቆማቸው እንደሆነም ያወሳሉ። ጥናቱን መነሻ በማድረግ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት እድሎች ፈተናዎችና መፍትሄዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ቅኝት ምሁራን እንደሚከተለው ያብራራሉ። በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሻለሙ ስዩም ‹‹ወደ ኋላ መለስ ተብሎ የአገሪቷ ታሪክ ሲታወስ፤ አገሪቷን አንድ ሊያደርጉና ወደ ፊትም ጥሩ ተስፋ ሊያመጡ የሚችሉ እድሎች ታይተዋል›› ይላሉ የነበሩትን የአንድነት መንፈስ የሚያጎለብቱ እድሎችን በማንሳት።
እርሳቸው እንደሚያብራሩት፤ የአገር ግንባታ አሊያም ምስረታው ሲቃኝ እንደ ታሪክነቱና ዓለም አቀፍ ትንታኔዎች እንደሚያሳዩት አንድ አገር በተለያየ መንገድ ልትመሰረት ትችላለች። ኢትዮጵያም በዚህ ውስጥ አልፋለች። ኢትዮጵያ ያላት ታሪክና የተለያዩ እሴቶች ለግንባታው መሰረት በመሆን እዚህ ለመድረሷ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከዚህም ውስጥ ለአብነት አጼ ቴዎድሮስ ዘመናዊነትንና አንድነትን ለማምጣት ያደረገው ጥረት ይነሳል። በተለይ ባልተማከለ መንግስት ትተዳደር የነበረችው አገር ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚጠራው ወቅት አንድ ሆና እንድትተዳደር ስንቅ የጣለ ነው። ይህ እያደገ መጥቶ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስትም ተግባራዊ ሆነ።
ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር ምን ትመስላለች የሚለውም በተማከለው ሥልጣን በማዕከላዊ መንግስቱ ብቻ ውስጥ የተዳደረችውን አገር በትውልድ ቅብብሎሽ ህብረ ብሔራዊነቷን አቅፋ ዛሬ ላይ እናገኛታለን። አንድ አገር እንደ አገር ለመቀጠል በተለይ በዚያች አገር የሚኖሩ ሁሉም ዜጎች ሊኖራቸው ስለሚገባ የጋራ እሴት ወይም አገራዊ ማንነት ላይ መስራት አለባቸው የሚሉት አቶ ሻለሙ፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እንደ አገር ብትመሰረትም አሁን ባለንበት ደረጃ አገራዊ ማንነት በትክክል መገንባትእንዳልተቻለ ይናገራሉ። ከዚህ አንጻር አገራዊ መግባባትን እንዴት መመስረት ይቻላል የሚል እሳቤ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ይመክራሉ። አቶ ሻለሙ ‹‹አገራዊ አንድነት ወይም አገራዊ ማንነት ስለተዘፈነለት ብቻ የሚመጣ አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ አገራዊ ማንነት በልጽጓል አሊያም ዳብሯል ሲባል ዜጎች አገራዊ ማንነትን አምነው መቀበል ሲችሉ ነው።
በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ ሁሉም በቆመበት ‹‹የዳቦ ፖለቲካ›› ላይ ገብቷል። ይህ ማለት ሰዎች ስንት አተርፋለሁ እንጂ አገሪቷ እንዴት ትመራ ምን አይነት ፍላጎት አላት የሚለው አስተሳሰብ ደካማ ነው›› ይላሉ የአንድነትን ጽንሰ ሃሳብ በጎ ተጽእኖና አሁናዊውን የኢትዮጵያ ገጽታ በመዳሰስ። እንደ አቶ ሻለሙ ማብራሪያ፤ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ሲጀመር ቋሚ የሆነና ሊነቀነቅ የማይችል መሠረት ያለው ‹‹የጋራ ጥቅም›› ሊኖር ይገባል። ወይም የአንድ አገር ቀዳሚ ጥቅም መረጋገጥ አለበት። ሌላው አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ነኝ ካለ በኢትዮጵያ ውስጥ በዞረበት ቦታ ሁሉ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ሊሰማው ይገባል። ይህ ካልሆነ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ እሳቤው ሊያድግ አይችልም። ‹‹አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንገንባ ሲባል የይስሙላ ሳይሆን የጋራ ባህልን በማበልጸግ ፍጹም የሆነ ውህደት ማምጣት ያስፈልጋል። በጋራ ፍላጎት ላይ ስምምነት ከሌለ አንድ ላይ መኖሩ ትርጉም የለውም። ውህደት የሚባለውም የጋራ ጥቅሙን መሠረት ያደረገ ነው።
በአገሪቱ ጥቅም ላይ ተሳታፊ የሆነ ዜጋ መፍጠር ይገባል። እነዚህ የጋራ ባህሎች እስካሁን ላለው አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በዚህ መነሻነት ፖለቲከኛው ከንግግር በዘለለ ምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ አንድነት መመስረት የሚያስችል ተግባር ማሳየት አለበት›› ይላሉ አቶ ሻለሙ። ሚዛናዊነቱን ለማስጠበቅ በአገሪቷ ማዕከላዊ ቦታ ያሉና ከማዕከላዊ ስፍራ ርቀው የሚገኙ ማኅበረሰቦች እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸውና ጦርነትን በጋራ በመዝመት አገርን ከጠላት መከላከል ከሚያወሱ ታሪኮች ቀጥሎ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የጋራ መሰረተ ልማቶች አብሮነትን ለማጠናከር አይነተኛ እድሎች እንደሆኑም ይጠቁማሉ።
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ግርማ ተሾመ በበኩላቸው፤ እንደ አገር አንድ የኢኮኖሚ አሊያም የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ህዝቦች በጋራ የሚኖሩበትና ተንቀሳቅሰው ሀብት ማፍራትና መጠቀም ሲችሉ፤ እንዲሁም በወደፊት እጣ ፈንታቸው የጋራ መዳረሻ ሲኖራቸው ነው ይላሉ። ‹‹ህዝቡ ከዚህ በፊት ለረጅም ዓመታት አብሮ ሲኖር የነበረ በመሆኑ የገነባቸው በርካታ የጋራ እሴቶች አሉ። ይህም ሁሉም በፈለገበት ቦታ ተዘዋውሮ የሚሰራበት ሁኔታዎችን ፈጥሯል›› በማለት በአገር ግንባታ ሂደት ያሉትን መልካም ዕድሎች ይጠቁማሉ። የነበረው የጋራ ባህል፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ትስስሩ ለረጅም ጊዜ ተጠብቆ የቆየ መሆኑን፤ እንደ አገርም የውጭ ወራሪ ሲመጣ በአንድነት መንፈስ በመተባበር ጠላትን የመመከት ሁኔታዎች በሙሉ ለአንድነቱ ምቹ እንደነበሩ፤ እነዚህ እድሎች አሁንም ተጠብቀው ከቆዩና በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ወደ ፊት አብሮ የመኖርና አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚቻል ዶክተር ግርማ ይናገራሉ። አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እድሎች እንዳሉ ሁሉ ፈተናዎችም ያጋጥማሉ የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ አንድነትን እንዲያጎለብቱ ተልዕኮ የተሰጣቸው ተቋማት ለመምራት ደካማ መሆን፣ የፌዴራል ሥርዓቱንም ሆነ የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ አለመቻል፣ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ለመገንባት የተመሰረቱት ተቋማት ብቁ አለመሆናቸው አንዱ ፈተና መሆኑንም ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በታሪክ ትምህርት ውስጥ የሚቀርቡ የተለያዩ ትርክቶች በህብረተሰቡ መሀል አንዱ አንዱን ሊቃረን በሚችል መልኩ የኋላ ታሪኮችን የማንሳት ሁኔታዎች መኖራቸውና ይህም አሁን ያለው ህዝብ በጋራ በሚያደርጋው እንቅስቃሴዎች ላይ አለመተማመን የሚፈጥር እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህ አይነቱ አሉታዊ ሂደት ደግሞ ለወደፊቱ የአብሮነት እሳቤዎች ተግዳሮት እንደሚሆን ያብራራሉ። ዶክተር ግርማ ለአንድነቱ ግንባታ ፈተና ይሆናል ብለው የሚያቀርቡት ሌላው ምክንያት አገሪቷ በኢኮኖሚ ድሃ መሆኗን ነው።
የድሃ ኢኮኖሚ ማራመድ በራሱ በትንሽ ነገር እርስ በእርስ የመጠላላት አዝማሚያ እንደሚኖረውና በዚህ ረገድ የጋራ ሀብትን እኩል በመጠቀም ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸው አንድነትን ያላላል ይላሉ። በሌላ በኩል የጋራ እሴት ከመገንባትና የወደ ፊት ራዕይን ከማሳየት አኳያ በትውልዱ ላይ ትምህርትና ግንዛቤን መፍጠር እንዳልተቻለና የሚሰጡት ግንዛቤዎችም የተሳኩ አለመሆናቸውን እንደ ችግር ያነሳሉ። በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ቡድን የሚፈጸሙ አድሎዎችና በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ህብረተሰቡን ማርካት አለመቻልም የአገር ግንባታን የሚፈታተን ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ‹‹ብዝኃነትን በአንድነት ውስጥ የማስተናገድ ፍልስፍና ግቡ ህብረ ብሄራዊ ዴሞክራያዊ የሆነ አንድነትን መገንባት በመሆኑ፤ ብዝኃነትን ውበት አድርጎ በመቀበል በመቻቻል የጋራ አገር ለመገንባት የጋራ ጉዳይ መኖር አለበት›› ሲሉ ዶክተር ግርማ ይመክራሉ። ዶክተር ሔኖክ በጥናታቸው ንድፈ ሃሳባዊ ቅኝትና ተዘማች ጽሁፎችን ዋቢ አድርገው እንደሚያስቀምጡት፤ ኢትዮጵያውያን በአገር ጉዳይ ላይ አንድነታቸው ከብረት የጠነከረ ቢሆንም፤ በውስጣቸው ግን ብዙ ቡድኖችን የያዘ ብዝኃነት አላቸው።
በኢትዮጵያ ከነበረው የማኅበራዊና የፖለቲካ ልዩነቶች እና መስተጋብሮች ምክንያት የታሪክ፣ የባህል፣ የሃይማኖት የቋንቋ፣ እና የብሄር ልዩነቶች ስለምትታወቅ በአንዳንዶች ‹‹የህዝብ ሙዚየም›› ተብላ ትጠራለች። እንደ አገር ይህን ብዝኃነት በአንድነት ውስጥ የምታስተናግድበት ፍልስፍና እና አተገባበር በሂደት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብን ስኬታማነት ይወስናል። በአገሪቱ በአንድነት አብሮ መኖር ስልት፣ የታሪክ አገነዛዘብ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶች አተገባበር፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንና ሌሎችን መሰረት በማድረግ የሚነሱ የውስጥ ችግሮች የአገር አንድነት ግንባታ ላይ ጥቁር ጥላ አጠልሽቶባታል።
የአገር አንድነትን እየተፈታተኑ ያሉ የወል ታሪክ ትርክቶችና የአረዳድ ልዩነት፣ የብሄራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነት እይታዎች የተዛባ መሆን፤ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የአሳታፊነት ችግሮች የህዝቦች የእርስ በእርስ መጠራጠርን እና የመገለል ስሜቶችን መፍጠር፤ ከአገር አንድነት ግንባታ አንጻር የተቋማት ሚና አናሳ መሆን የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እሴቶች አለመጎልበት ዋና ተጠቃሾች ናቸው። ‹‹ኢትዮጵያዊነት እንደ አንድ አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት እንዲያስተሳስር ከተፈለገ ከሚለያይ ይልቅ በሚያስተሳሰር ጉዳይ ላይ ማተኮር›› እንደሚገባ አጽንኦት የሚሰጠው የዶክተር ሄኖክ ጥናት፤ አንድነትን በብዝኃነት ውስጥ ማስተናገድ፣ በወል ታሪክ በመንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች ዙሪያ መግባባት በመፍጠር የጋራ ማድረግ፣ አንድነትን ለማጠናከር የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከር እንዲሁም የወጣቶች አገራዊ የሰብዕና ግንባታ አስመልክቶ በእቅድና በዓላማ መስራት እንደሚያስፈልግ ጥቁምታ ሰጥቷል።
የህብረ ብሄራዊ አገር ግንባታ ምንነት በጥናታዊ ጽሁፉ ጽንሰ ሃሳብ እንደሰፈረው፤ ህብረ ብሄራዊ የአገር ግንባታ መንግስት የማስፈጸም የስራ ኃላፊነቱን በመጠቀም የብሄራዊ ማንነትን በማዋቀር ወይም በማቀናጀት የሚፈጸመው ነው። ዓላማውም በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ህዝቦችን በአንድነት አስተሳስሮ ጠንካራ እና የተረጋጋች አገር ለመፍጠር ማገዝ ነው። የአገር ግንባታ ስኬት እና ስራዎች እንደየአገሩ የታሪክ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና በሌሎች የልዩነት ዓይነቶች እና ጥልቀት የሚለያይ ቢሆንም ጠንካራና የተቀናጀ ሥራ የሚፈልግ የስራ ሂደት ያለው ነው።
‹‹ኢትዮጵያ ለዘመናት መንግስት መስርተው ነጻነታቸውን ጠብቀው ከኖሩ የዓለማችን አገራት ተጠቃሽ ብትሆንም የተሳካ የአገር ብሄር ግንባታ ግን በማካሄድ አንድነቷን በጠንካራ መሰረት ላይ ማቆም አልቻለችም። በህዝቦቿ መካከል እንደ ጸጋ ሊታዩ የሚችሉ የብሄር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት የኑሮ ዘይቤ እና ሌሎች ልዩነቶች ያሉ ቢሆንም ይህ ሳያራርቃቸው የጋራ እጣ ፈንታቸውን ለመገንባት በጋብቻ፣ በንግድና በእምነት በመሰናሰል በርካታ የጋራ አኩሪ አገራዊና አካባቢያዊ ታሪኮችን በመፈጸም አብሮነታውን አረጋግጠዋል። ህዝቦቿ በበጎዎቹ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ችግሮች፣ ስቃዮችና ውድቀቶችንም ሲጋሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት አገሪቷን ያስተዳደሯት ጠንካራ አንድነት በዘላቂነት ከመገንባት ይልቅ ለቆሙለት የግልና የቡድን ፍላጎት ለማሟላት በሚረዳ መልኩ አገሪቷን ሲቀርጹ ቆይተዋል›› በኢትዮጵያ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ምስረታ ሙከራዎችን ዳራዊ ታሪክ ጥናቱ ጠቅሷል። በአሁኑ ወቅት የብሄርና የአንድነት ሀይሎች መካከል ላይ መሳሳቦች ይታያሉ። አንዳንዶች ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት በሚለው ላይ ብቻ በማተኮር የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ማንነት መገለጫዎችን የማይቀበሉ ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ሌሎች ለብሄርተኝነት ቅድሚያ በመስጠታቸው አገር ግንባታን አስመልክቶ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አንዱ ወገን የሌላውን ባለመቀበል ምክንያት ውስብስብ እና ውጤታማ እንዳይሆን እያደረገው ይገኛል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ለዘላቂ አንድነት ግንባታ የሚያግዙ ተገቢ ለውጦችና ማሻሻያዎች ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም በአገሪቷ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደቶች ወሳኝ ሚና ያላቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መጤን ስለሚገባቸው እና ከዚህ አንጻር የወል ታሪክ አተረጓጎም፣ የልህቃን/ኤሊቶች/ ሚና፣ እና የብዝኃነት አያያዝ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባው ነው የዶክተር ሄኖክ ጥናት የሚጠቁመው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በአዲሱ ገረመው