አዲስ አበባ፤- ጦርነት በምንም መልኩ አማራጭ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች አሳሰቡ። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በግጭቱ የሚሳተፉ አካላት ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግርና በመደራደር ሊፈቱ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ትናንት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ላሉ አካላት የሠላም ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤- ግጭትና ጦርነት ውጤቱ የሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመትን በማድረስ የሀገርን ውስን ሀብት የሚያጠፋ፤ የልጆቻችን ተስፋ የሚያቀጭጭና ነገን የሚያጨልም ነው። ከዚህ አኳያ ግጭት በምንም መልኩ አማራጭ ሆኖ ሊቀጥል አይገባም፡፡
ካለፈው ልምዳችን ተምረን ግጭትና ጦርነት በምንም መልኩ አማራጭ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይገባ በማመን ጦርነትንና ተያይዘው የሚመጡ የሠላም ጠንቆችን በቃ ልንላቸው ይገባል ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፤ ሁሉም በግጭት ውስጥ የሚገኙ የመንፈስ ልጆቻችንና መላው ሕዝባችን ውስጣዊ ችግሮችን በሠላማዊ ድርድር ለመፍታት በፍጹም መከባበርና መደማመጥ መመካከር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ገለጻ፤ እስካሁንም እየተከሠቱ ባሉ ግጭቶች እንደ ሀገር ከፍተኛ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየደረሠ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያትም በንፁሐን ላይ ያነጣጠሩ የግድያ፤ የእገታ፣ የመፈናቀልና የዘረፋ ተግባራት ተፈጽመዋል። በቅርቡ በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ ሰላሌ አካባቢ የተፈጸመው አሰቃቂና ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ድርጊት ችግሩ የደረሠበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው።
እንደዚህ አይነት ተግባራት በየትኛውም የሃይማኖት አስተምሕሮ የሚወገዙ ፍጹም የወንጀል ድርጊቶች ናቸው ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ፤ ይህንንና ከአሁን ቀደም የተፈጸሙ መሠል ድርጊቶችን የምናወግዝ ሲሆን ለሟቾችና ተጎጂ ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን ብለዋል።
በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ካለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ፈተና ሆኗል ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፤ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ለመሥራት እየተቸገሩ ናቸው። የሀገር አቋራጭና ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በስጋት ውስጥ ሆነው ነው። የሀገር ሠላምና የዜጎች ደኅንነት የመጠበቅ ጉዳይ የአንድ ሀገር ሕዝብና መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
ግጭቱ እኛ የሃይማኖት መሪዎችን በእጅጉ እያሳሰበንና እያስጨነቀን ይገኛል ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ሁሉም ወገን ከምንም በፊት ቅድሚያ ለሠላም ሊሠጥ ይገባል። እነዚህ አካላት ጉዳዮቻቸውንም በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግርና በመደራደር ሊፈቱ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለሁሉም አባትና ሽማግሌ በመሆን ለየትኛውም ወገን ሳናዳላ ፍጹም ገለልተኛ በሆነ አግባብ ግጭት ውስጥ የምትገኙ አካላትን ለማቀራረብ፣ ለማደራደርና ለማስታረቅ ቁርጠኛና ዝግጁ ነንም ብለዋል።
በመጪው እሁድ ኅዳር ሃያ ሁለት ቀን 2017 ዓ.ም በመቄዶንያ የአረጋውያን መጦሪያ ስለ ሀገር ሠላም ሀገር አቀፍ የፀሎት መርሐ ግብር እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
በራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም