የኢትዮጵያ አሁናዊ እውነት ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊዮኖች በረሃብ የሚያልቁበት እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

በኢትዮጵያ በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ተቀንቅኖ ድጋፍ የተሰበሰበበት ‘Do they know its Christmas?’ ሙዚቃ አሁን ላይ ዳግም መለቀቁ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመለከቱ። አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊዮኖች የሚያልቁበት የረሃብ ታሪክ እንዳልሆነም አስታወቁ።

“ዘ ታይምስ” ጋዜጣ የሙዚቃውን አሁን ላይ ዳግም መለቀቅ አስመልክቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሰጡትን አስተያየት ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የሙዚቃው 40ኛ ዓመት ሲዘከር ሙዚቃው ዳግም እንዲለቀቅ መደረጉ፤ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን፤ የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ጉዞ ያላገናዘበ፤ ገጽታን የሚያበላሽ ተረክ ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሙዚቃው ላይ እንደተገለጸችው ሳትሆን በፈጣን እድገት ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ገልጸው፤ ሙዚቀኞቹ በወቅቱ የሠሩት ሥራ የሚያስመሰግናቸው ነው። ሙዚቃው ዛሬ ላይ ከጊዜው ጋር አብሮ አለመሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ

ያመዝናል፤ የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያቃለለና ሰዋዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተረክ የያዘ ነው ብለዋል ። ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ የኢኮኖሚ ባለቤት፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎቿ ከሚጎበኙ ሥፍራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ያለች ሀገር ሆና ብትታወቅ ይጠቅም እንደነበር አመልክተዋል።

ሙዚቃው አሁን እኛ ለምንፈልገው ኢንቨስትመንት የሚጠቅም አይደለም፤ ድርቅ አሁን ላይ እኛን እንደ አሕጉርም ሆነ እንደ ሀገር አይገልጸንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በረሃብ ልትታወቅ አትችልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እና በሌሎች መስኮች እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች ዳግም ረሃብ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውንም አመልክተው፤ በስንዴ ራሷን ችላለች፤ ሌሎች ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት አቅም ፈጥራለች ። ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል የግብርና ዘርፍ አብዮት እያካሄደች መሆኑንም አመልክተዋል።

ሙዚቃው የተለያዩ ወቀሳዎች እየደረሰበት መሆኑን የዘገበው “ዘ ታይምስ” ጋዜጣ፤ በፈረንጆቹ 2014 እንደ አዲስ ሲሠራ እውቁ እንግሊዛዊ ኢድ ሺራን በሙዚቃው ከተሳተፉ አርቲስቶች መካከል አንዱ እንደነበር አስነብቧል። ይሁንና አሁን ላይ ሙዚቃው

የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ እንደማይገልጽ በሚሰነዘርበት ወቀሳ በወቅቱ በሙዚቃው ተሳትፎ ባላደረኩ እስከማለት መደረሱም አስነብቧል ።

በመድረክ ስሙ ፉስ ኦ ዲ ጂ የተሰኘው የጋና ሙዚቀኛ፤ ሙዚቃው የተጠቀማቸው የግጥም ስንኞች አፍሪካን በተመለከተ አሉታዊ መልዕክት እንዳላቸው ገልጿል። ይህም የአፍሪካን ልማት፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እድገት እንደሚያቀጭጨው አመልክቷል። ይህንን መልዕክቱን በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራ ሲሆን እውቁ ሙዚቀኛ ኢድ ሺራንም ይህንን መልዕክት ተጋርቶታል።

በኢትዮጵያ በ1977 የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ሰፊ ጉዳት ተከትሎ አየርላንዳዊው ሙዚቀኛ ቦብ ጊልዶፍና መሰል እውቅ ሙዚቀኞች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ‘Do they know its Christmas?’ የሚል ሙዚቃ አቀንቅነው ከፍተኛ ድጋፍ ማሰባሰባቸው ይታወሳል ። የዚህ የሙዚቃ 40ኛ ዓመት ዘንድሮ የተከበረ ሲሆን÷ በወቅቱ የተሠራው ሙዚቃ ዳግም ተለቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

Recommended For You