“ብልፅግና የርዕዮተ ዓለም እሥረኛ አይደለም” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ ፦ ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ላይ በመመሥረት፣ ከሌሎች ሐሳቦች በመማር፣ በገቢር ነበብ መንገድ የሚጓዝ እንጂ የርዕዮተ ዓለም እሥረኛ እንዳልሆነ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። ፓርቲው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመለየትና ለማስከበር ስትከተል የነበረውን የዓይን አፋርነት አካሄድ መለወጡን አመለከቱ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት እንዳስታወቁት፤ ፓርቲው በኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ላይ በመመሥረት፣ ከሌሎች ሐሳቦች በመማር፣ በገቢር ነበብ መንገድ ይጓዛል እንጂ የርዕዮተ ዓለም እሥረኛ አይደለም። ለአንድ አካባቢ ወይም ብሔር የቆመ ሳይሆን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያለው የሐሳብ ፓርቲ ነው። ይሄም የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዓ ምድር የለወጠ የለውጥ ፍሬ ነው።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ንቃት በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲፈጠር አድርገዋል። የፖለቲካ አደረጃጀቶችን አምጥተዋል። የሕዝብ ጥያቄዎችን ቅርጽና መልክ ሰጥተዋል። የፖለቲካ ትግል ስልቶችንም አስተዋውቀዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግልና የፖለቲካ ትግል እንዲቀላቀል፤ የጥላቻ ፖለቲካ እንዲነግሥ፣  በብሔር፣ በርዕዮተ ዓለምና በትግል ስልት መፈራረጅ እንዲበረታ በማድረግ ለዘመናዊ የፖለቲካ ጉዟችን ሳንካዎችን አኑረዋል። ብልፅግና ፓርቲ ነባሮቹን ፖለቲካዊ እሴቶች በሚያጎለብትና የፖለቲካ ስብራቶቻችንን በሚጠግን መልኩ መመሥረቱን ጠቁመዋል።

የብልፅግና መመሥረት የዳርና የመሐል፤ ዋና እና አጋር፣ አርብቶ አደርና አርሶ አደር፤ ተራማጅና አድኃሪ፤ ጠላትና ወዳጅ፣ ወዘተ. የሚባሉትን ግንቦች በማፍረስ በሐሳብ ላይ ብቻ የተመሠረተ የፖለቲካ አደረጃጀትን መሆኑን ጠቁመው፤ የሃሳብ ልዩነቶችን እንደ ጌጥና እሴት በመውሰድ ተፎካካሪዎቹን በጠላትነት እንደማይፈርጅም አመልክተዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ አንዱ ስብራት የኋላ ቀርነት ፈተና ነው። በሁሉም ዓይነት ዘርፎች ኋላ ቀርነት በመንሰራፋቱ የተነሣ ኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት እድሜዋን ያህል አላደገችም። ለውጡ ከመጣባቸው ገፊ ምክንያቶች አንዱም ይሄው የኋላ ቀርነት ስብራት ነው። በለውጡ ዘመን ኋላ ቀርነትን ቀርፎ ኢትዮጵያን ለማዘመን አያሌ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለውጥም አምጥተዋል።

የግብርና ኋላ ቀርነትን ቀርፎ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሠራው ሥራ የባሕልም የውጤትም ለውጥ መጥቷል። ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅት ብቻ ይጠብቅ የነበረው የግብርና ባሕል መስኖን በመጠቀም፣ በኩታ ገጠም እርሻና መሬት ጦም እንዳያድር በተሠራው ሥራ፣ ዓመቱን ሙሉ የሚመረትበት ባሕል እያመጣ ነው።

ስንዴን፣ ሩዝን፣ ገብስን፣ በቆሎንና የፍራፍሬ ምርቶችን ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። ስንዴን ከውጭ ማስመጣትም አቁማለች። በአትክልትና በፍራፍሬ ዘርፍም የወጪ ምርት መጠናችን ጨምሯል።

ኢትዮጵያን ለማዘመን በተሠራው የኢንዱስትሪ ምርታማነት ሥራ አያሌ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተቻለ ነው። ከዚህ በፊት ከውጪ የሚገቡትን የቢራ ብቅል፣ የምግብ ዘይት፣ ፓስታና አልሚ ምግቦች፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የፀጥታ አባላት የደንብ ልብስ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች (ፖል፣ገመድና ትራንስፎርመር) በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሥራ ውጤት እያሳየ እንደሚገኝም አመልክተዋል ።

ለውጡ እንዲመጣ ከገፉት ሀገራዊ ስብራቶች አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱ ሀገሪቱን ከአቅሟ በላይ ለሆነ ዕዳ የዳረገ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛነፍን ያስከተለ፣ የዋጋ ውድነትንና ግሽበትን ያመጣ ስብራት ነው። ይሄንን ስብራት ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመዘርጋት ሁሉን አቀፍ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል ።

በዚህ ማሻሻያ አማካኝነትም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም፣ ሀገራዊ ገቢን በሀገራዊ ምርት ልክ የማድረግ ሪፎርም፣ ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ሪፎርም፣ የባንኮች የውጭ ምንዛሪን ከሌሎች ገበያዎች ጋር የማጣጣም ሪፎርም፣ የዕዳ ቅነሳና ሽግሽግ የማድረግ ሪፎርም፣ የመንግሥትን የመበደር ሁኔታና መጠን የማስተካከል ሪፎርም፣ ተከናውነዋል ብለዋል።

በዚህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት የምናገኘው ብድርና ድጋፍ ጨምሯል። የዕዳ ሽግሽግና ቅነሳ ውይይቶች ወደ ውጤት ቀርበዋል። የሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ክምችት አድጓል። የሀገር ውስጥ ገቢን የማሰባሰብ አቅሞችም ከፍ ማለታቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመለየትና ለማስከበር የምትከተለው የዓይን አፋርነት አካሄድ ነበር። ይሄም በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር የሚያስችል ገቢራዊ አካሄድ እንዳንጓዝ አድርጎን ኖሯል። ለውጡ ይሄን አካሄድ ቀይሯል። ሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር ግልጽና ጉልሕ የሆነ መንገድን መከተል ጀምራለች። ባለፉት ዘመናት የተከሠተውን የባሕር በር የማጣት ስብራት ለመጠገንም ይሄንኑ መንገድ መከተል አስፈላጊ ነበር ብለዋል ።

በዚህም የተነሣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ዓለም በብዛት እንዲቀበለው ለማድረግ ተችሏል። በዓለም አቀፍ መድረኮችም ብሔራዊ ጥቅሞቿን ሊያስከብሩ በሚችሉ የሁለትዮሽና ባለ ብዙ ዘር ትብብሮች ላይ በጉልሕ ትሳተፋለች። እንደ ብሪክስ ባሉ ማሕቀፎች ላይ ያደረገቸው የአባላነት ተሳትፎም የዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

Recommended For You