አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የተካሄደው አሕጉር አቀፍ የሠላም ኮንፈረንስ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋማት የሪፎርም ሥራዎችን እንዲገነዘቡ ዕድል መፍጠሩን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የኮንፈረሱን ማጠቃለያ በማስመለከት እንደገለጹት፣ ኮንፍረንሱ የአፍሪካ ሀገራት በኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋማት የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች ላይ ልምድ እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
አሕጉር አቀፍ የሠላም ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ በሠላም ጉዳዮች ላይ ኮንፍረንስን የማዘጋጀት አቋሟን ያሳየችበት ነው ያሉት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ ኮንፍረንሱ የአፍሪካ ሀገራት በኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋማት የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎችን እንዲገነዘቡ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
አሕጉራዊ የሠላም፣ የብልፅግናና የልማት ኮንፍረንስ ሠላማዊና የበለፀገች አፍሪካን እንገንባ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት መካሄዱን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እህትና ወንድሞችን በመጥራት በሠላም ጉዳይ ላይ እንዲወያዩ፣ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ የሚያስችል መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ሩዋንዳ ከዘር ማጥፋት ግጭቷ በኋላ እንዴት ግጭቷን እንደፈታች ያላትን ልምድ ማቅረቧን በመግለጽ፣ ደቡብ አፍሪካም ከድኅረ አፓርታይድ በመውጣት እንዴት ችግሮችን እንደፈታች ያላትን ልምድ ማቅረቧን ተናግረዋል።
ኢጋድም ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ያለው ልምድ አቅርቧል ያሉት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያም በልማት፣ አየር ንብረትን፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯን፣ ሠላም ግንባታ ሂደቶችን፣ ቁርሾዎችን በሽግግር ፍትሕና በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት እየሠራች ያለችውን ሂደት አቅርባለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል መሆኗና ሁለተኛ ከፍተኛ ሕዝብ የያዘች ሀገር እንደሆነች ጠቅሰው፣ በሠላም ግንባታ ሂደት ያደረገችውን አስተዋፅዖ ለሌሎች ሀገራት የምታጋራና በውስጥ የገጠሟትን ችግሮች በምክክር ለመፍታት እየሠራች ያለች ሀገር እንደሆነች ገልጸዋል።
መድረኩ ኢትዮጵያ ልምዷን ለሌላው ዓለም ሀገራት እንድታቀርብ ዕድል ሰጥቷል ያሉት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ ተደማጭነቷን፣ ተቀባይነቷንና አቅሟን ሌሎች እንዲገነዘቡ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
መድረኩ እንደሀገር በቀጣይ በሠላም ጉዳዮች ላይ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተጨባጭ ውጤት እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከኮሪያው ጦርነት እስከ ሩዋንዳና ሶማሊያ በተለያዩ በ11 የዓለም ሀገራት 142 ሺህ በላይ ሠላም አስከባሪ ሠራዊቷን አሰማርታ መሳተፏን በመግለጽ፣ ለአካባቢው፣ ለቀጣናው፣ ለዓለም ሠላም አስተዋፅዖ ያደረገችና እያደረገች ያለች ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የሀገርንና የቀጣናውን ሠላምን ለማረጋገጥ እየወሰደች ባለው የሪፎርም ሥራዎች ሀገራት እምነት እንዲጥሉባት ያደረገ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ልክ እንደትላንቱ በአካባቢው፣ በቀጣናውና በዓለም ሠላም ላይ ያላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
22 ሀገራት የተሳተፉበት ሃሳብ አሕጉር አቀፍ የሠላም ኮንፈረንስ የበለፀገችና ሠላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም