ዓድዋ፤ ኢትዮጵያዊያን በኩራት የሚናገሩት እንደ ክፍለ ዘመን ተሻግሮም ሀያል ተጋድሎ የሆነ፣ በጥቁሮች የተመዘገበ ድንቅ ታሪካዊ ክስተት ነው፤ ይህ ክስተት በእዚህ ትውልድም በተለያየ መልክ መዘከሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ባለሙያዎች ይህን ታላቅ ታሪክ በሙዚቃ፣ በስዕል በፊልምና በቲያትር እያጣቀሱ ሲያወሱት ኖረዋል::
ዛሬም የዓድዋን ታላቅነት የሚዘክሩ፣ ድሉን በብርቱ የሚስቡ የኪነ ጥበብ ስራዎች ለሕዝብ መቅረባቸው ቀጥሏል:: በዚህ ዓመት በጉዞ ዓድዋ የተዘጋጀው ለየት ባለ መልኩ የተሰራው ሙዚቃዊ ተውኔትም ከእነዚህ ስራዎች መካከል ተጠቃሹ በመሆን የዘንድሮው የዓድዋ በዓል ልዩ ድምቀት ሆኖ አልፏል::
ጉዞ ዓድዋዎች ለተከታታይ 8 ዓመታት ዓድዋ ድረስ የእግር ጉዞ በማድረግ የዓድዋን ታሪካዊ ቦታዎችን፣ ሁነቶችንና የዘማቾችን ልዩ ልዩ ሁናቴን በሚያመላክት መልኩ ከመነሻው እስከ ዓድዋ በመጓዝ ሲዘክሩ፣ ታሪካዊነቱን በተግባር ሲያመላክቱን ቆይተዋል:: ዘንድሮ ደግሞ በጉዞ ዓድዋ መስራቹ ያሬድ ሹመቴ ተደርሶ በቀረበ ተውኔት ዓድዋን በዚህ ዘመን እይታ፣ ለዚህ ዘመን ሰው በሚገባ መልኩ ጥበብን ምርኩዝ አድርገው “ዓድዋስ” ብለው ሰይመው ለመድረክ አብቅተውታል:: ትያትሩን ያዘጋጀው ደግሞ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተመራማሪና መምህር ተስፋዬ እሸቱ ነው::
የዓድዋን ታላቅ ገድል በሚከበርበት ቀን ዋዜማ ለሕዝብ የቀረበው ይህ ሙዚቃዊ ተውኔት ዓድዋ በዚህ ዘመን ትውልድ እንዴት ይገለፃል? የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ መሰረት አድርጎ የዓድዋን ድል የዚህ ዘመን ትውልድ ዓድዋን ከራሱ መልክና ቁመና ጋር እንዲያይ የሚያደርግ የድሉን ሀያልነትና የዚያ ዘመን ኢትዮጵያዊያንን ተጋድሎና አንድነት የሚያወርስ ጥበባዊ ኩሸት ነው::
በሁኔታዎች ምቹ አለመሆን የተቋረጠው የጉዞ ዓድዋ የእግር ጉዞ ይህንን ታላቅ የኪነጥበብ ስራ ለማስገኘት ሰበብ ሆኗል:: ያንን ታላቅ ታሪክ የሚዘክር የእግር ጉዞ ሲያሰናዳ የነበረው “ጉዞ ዓድዋ” በኪነጥበብ ዓድዋን ሊያመላክተን የወጠነው ውጥኑ ተሳክቶ ታሪካዊው ሁነት መድረክ ላይ በዛሬ ተለክቶ በጥበበኞች ተሰናስሎ በኢትዮጵያ ልጆች ተበጅቶ በድንቅ ሙዚቃዊ ተውኔት ታይቷል::
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በዓድዋ ድል በዓል ዋዜማ ምሽት በወዳጅነት ፓርክ ለእይታ የበቃው ይህ ሙዚቃዊ ተውኔት የዓድዋን ታሪክና ምንነት በዛሬ መነፅር ውስጥ ያኔ የሆነውን እየጠቀሰ ዛሬን ማሳየት የቻለ በአዘገጃጀትና በሀሳቡ አዲስ የሆነ ድንቅ ትያትር ነው::
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ ታላቁ የአፍሪካዊያን ድል ዓድዋ በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያዊያን የተመዘገበ አንፀባራቂ ድል እንደመሆኑ የድሉን ያህል ባይሆንም ሁነቱን የመዘከር ያህል በመጠኑ ለመዳሰስ ተሞክሯል:: “ዓድዋስ” የተሰኘው ይህ ሙዚቃዊ ተውኔት ግን ከቀደሙት ስራዎች ይለያል::
የሙዚቃዊ ተውኔቱ ይዘት
ጥበብ የሩቁን አቅርቦ የማሳየት እንዲሁም ያለፈውን የማስመልከት ልዩ አቅም አለውና “ዓድዋስ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ተውኔት ትናንት የሆነውን ገድል ወደ ዛሬ አምጥቶ አሳይቶናል:: ይህ ተውኔት መድረክ ላይ ቀርቦ ሲታይ ምን ይነግራል? መልዕክቱስ ምን ላይ ነው? ለሚለው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል::
ዓድዋ ትናንት አባቶች የከፈሉት ትልቅ መስዋዕትነት ያስገኘው ድል ሲሆን፣ የዛሬው ትውልድ ዓድዋን በምን መልክ ይገልፀዋል? ትውልዱስ በዓድዋ እንዴት ይገለፃል? ዓድዋ ለዛሬ ዘመን ሰው አልያም ለአሁኑ ትውልድ ምን ትርጓሜን ይሰጣል? አልያም ዓድዋ በዛሬ ትውልድ ውስጥ እንዴት እና በምን መልክ ሊታይ ይችላል? ለሚሉት ጥያቄዎች በገፀ ባህሪያቱ ሁነት፣ በሙዚቃዊ ክዋኔውና በዳንስ ታጅቦ በልዩ ቀለም ባሸበረቀው መድረክ ምላሽ ይሰጣል::
ዓድዋ በዚህ ትውልድ እንዴት ይገለፃል? የሚለው የዚህ ሙዚቃዊ ተውኔት ዋንኛ ማጠንጠኛ ጉዳይ ሲሆን፣ በዚያ ዘመን የተከፈለውን ታላቅ መስዋዕትነት ለአገር ተብሎ የሆነውን ሁሉ አውቆ ዛሬ እኔ ስለዚህች አገር ከራሴ በላይ ምን እያደረኩ ነው? ወደፊትስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? በሚል ተመልካች ራሱን እንዲጠይቅ የሚያደርግ ታላቅ እሳቤን ያዘለ ሙዚቃዊ ተውኔት ነው:: ዓድዋስ ይህን ትውልድ በዓድዋ እንዴት እንደሚገለፅ በጥበብ ታግዞ ድንቅ በሆነ መንገድ ማሳየትም ችሏል::
ከመነሻው ጀምሮ ዓድዋን የሚያህል ታላቅ ገድል በምን መልክ ይነገር? እንዴት በመድረክ ተውኔት ያንን ታላቅ የሆነ ታሪክ በጥበባዊ መልኩ እንዲዘከር ተደርጎ ይቅረብ? የሚሉት ትላልቅ ፈተናዎች ፤ ተውኔቱን ለማዘጋጀት ሲታሰብ ካዘገጃጀቱ ጀምሮ ብዙ የታሰበበት እንደነበር ትያትሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በተሰጠበት ወቅት የዚህ ሙዚቃዊ ተውኔት አዘጋጅ ረ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ ተናግሯል:: ዓድዋን ከሀያልነቱ አንፃር ምኑን ላሳይ? ብሎ ማሰብና እንዴት ልግለፀው? ብሎ መግለጫ መንገድ መፈለጉ ትልቁ ጉዳይ እንደነበር የዝግጅት ጅማሮውን አዘጋጁ ያስታውሳል::
በእርግጥም አዘጋጁ ስለዓድዋ ተፅፎ የቀረበው የያሬድ ሹመቴ ጽሁፍ አይቶ እና ወዶ መስራት እንደሚችል አሳይቶበታል፤ አምኖበት ሰርቶ ስኬትን ተቆናጦበታል:: ረ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ ዓድዋን የመሰለ ታላቅ ታሪክ በኪነጥበብ ረገድ ብዙ እንደሚያሰራ ገልጾ፣ ይህን “ዓድዋስ” የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔት ሲያዘጋጅ ከታሪኩ ግዝፈት አንፃር ገምግሞና የተለየ አተያዩንና ሀሳቡን ወዶት እንደሆነ ይናገራል::
ተውኔቱ በህብረ ተሳትፏዊ አቀራረብ (collective approach/ensamble) ስልት የተዘጋጀ ነው የሚለው አዘጋጁ “ህብረ ተሳትፏዊ አቀራረብን የመረጥነው ዓድዋ ከሚለው ሃሳብ ከራሱ ላይ ስለምንነሳ ነው›› ሲል የቀረበበት መንገድ መምረጫ ምክንያታቸው አስረድቷል።
ዓድዋን በተመለከተው በዚህ ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ በአዘጋጅነት መሳተፌ እድለኛ ነኝ የሚለው ረ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ እንደ አንድ ኪነጥበብ ባለሙያ በመሰል ታሪካዊ ስራዎች ውስጥ መሳተፍ እንደሚገባ ይገልፃል:: የዓድዋ ታሪካዊ ሃሳብ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ባጎናጸፈን ዘመን ተሻጋሪ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች መሰረት እንደራሳችን መረዳት እና እንደ ዘመኑ ቃኝተን እኛኑ የሚመስል ቅርጽና ሁለንተናዊ መሰናስል በመፍጠር የተሰናዳ ነው በማለት አዘጋጁ ረ/ፕ ተስፋዬ እሸቱ ዓድዋስ የተሰኘውን ሙዚቃዊ ተውኔት ይገልፀዋል። ዓድዋን የመሰሉ ታላላቅ የኢትዮጵያ ታሪኮች በኪነጥብ ስራዎች ማሳየት እንደሚገባ የሚናገረው አዘጋጁ፣ ከተሰራ ብዙ ድንቅ ነገር ማሳየት እንደሚቻል “ዓድዋስ” ማሳያ መሆኑን ያስገነዝባል::
ያንን ታላቅ ሁነት ለመግለፅ የኪነ ጥበብ ባለሙያና የጉዞ ዓድዋ መስራች ያሬድ በልቡ ያሰበውን ለሌለው ማድረስ ፈለገና “ዓድዋስ”ን በብርሃናማው ልቡ ወለደው:: የሙዚቃዊ ተውኔቱ ደራሲ ያሬድ ሹመቴ ስለ ቲያትሩ መነሻ ሲገልጽ፣ ከዚህ በፊት ዓድዋን በታሪካዊ ቦታው ላይ በእግር ጉዞ በመገኘት ይዘክሩ እንደነበር አስታውሶ፣ የዘንድሮውን 126ኛ የዓድዋ ድል በዓል በጥበብ እና ለያት ባለ መልክ በማውሳት ታሪካዊነቱንና ከዛሬ ዘመን ጋር በምን መልክ መታረቅ እንዳለበት ለማመልከት ማሰቡን ይገልፃል:: ዓድዋ በዛሬ ትውልድ እንዴት ይገለፃል የሚለውን ሀሳቡን እና የዓድዋ ታላቅነት ለአሁኑ ትውልድ ለማሳየት ታስቦ መዘጋጀቱን የሚገልፀው ያሬድ::
በተውኔቱ የተሳተፉ ሰዎች ሁሉ የዓድዋን ልብ የታደሉ፣ ስለ ዓድዋ መልካም መናገር ያላቸውና የዓድዋ ጀግኖች ገድልን በትክክለኛ ስሜት የተረዱ፣ ሙያውንም የሚያውቁ እንደሆኑ ይናገራል:: ስራው እጅግ ባጠረ ጊዜ ትልቅ መስዋዕትነት ተከፍሎበት ለመድረክ መብቃቱንና የባለሙያዎች ትጋትና አብሮ መስራት ባህል ካለ ትልቅ ስራ በአንድ ወር ውስጥ በዚህ መልክ መስራት እንደሚቻል “ዓድዋስ” ማሳያ መሆኑን ገልጿል::
ዓድዋስ ሙዚቃዊ ተውኔት በዓድዋ የነበረውን የጀግኖች ገድል በተለየ መልኩ ማሳየቱ ሌሎች የስነ ጥበብ ባለሙያዎች እጅግ ከበረከተው ታሪክና ባህላችን ውስጥ እየቆነጠሩ ብዙ ሊያስመለክቱን እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ነው:: በሙዚቃዊ ተውኔቱ እንደ አንድ ታላቅ ታሪካዊ የሆነ ጉዳይ ላይ እንደተዘጋጀ የኪነጥበብ ስራ፤ ታሪክ በምን መልክ መገለጥ እንዳለበት ማሳየቱ፣ የዓድዋ ታሪክ ዛሬ ባለው ትውልድ እንዴት ይገለጣል የሚለውን ማንሳቱ፣ የዓድዋን ሀያልነት መግለፁ ስራው በባለሙያዎች ድንቅ ጥምረት ተበጅቶ ለተመልካች የቀረበ መሆኑን ያሳያል::
የዘርፈ ብዙ ሙያተኞች ጥምረት በ”ዓድዋስ”
ዓድዋስ ሙዚቃ ከተውኔት ጋር ተጋብቶ ታሪክን በተለየ መልክ ያሳየ የአሁኑ ትውልድ ሀላፊነትና ገፅታን ያመላከተ ከመሆኑም ባሻገር በስራው ውስጥ የተሳተፉ በርካታ የጥበብ ሰዎች ቅንጅትና አዲስ የሆነ ስራ ፈጠራ መፍጠር ያስቻላቸው ጥሩ ገጠመኝም ሆኗል:: ሙዚቃ፣ ዳንስና ትወና በአንድ መድረክ ላይ በተለያዩ አዘጋጆች ግን ደግሞ አንድነት ፈጥረው በልዩነት ውስጥ ህብር ፈጥረው የደመቁበት የጥበብ ስራም ነው::
አንጋፋዎቹን ተዋንያን አበበ ባልቻ እና ተፈሪ አለሙን ጨምሮ ከ350 በላይ ሰዎች በሙዚቃዊ ትውኔቱ ተሳትፈዋል፤ የዳንስ ትርኢት አቅራቢዎችና የመድረክ ሰዎች በተዋናይነት ተሳትፈዋል፤ በሙያው ከፍ ያለ ክብርና እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች የተለያየ በዝግጅቱ ላይ በአዘጋጅነት ተሳትፈዋል:: አጠቃላይ የተውኔት ስራውን ከመራው ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ በተጨማሪሪ በሙዚቃው ዝግጅት እዮዔል መንግስቱ፣ ኬሮግራፈር ተመስጌን መለሰ፣ በረዳት አዘጋጅነት ሰለሞን አብረሀም የተሳተፉበት ዓድዋስ የባለሙያዎቹ ቅንጅትና የጋራ ስኬትንም ክፍ አድርጎ ያሳያ ነው::
የአሁኗን ኢትዮጵያን የሚመስሉ የዳንስ እና የስርከስ ትዕይንቶች የታጀበ የቀደመውን የዓድዋ ትውፊት ትሩፋት በአዲስ መንፈስ ለመቃኘት እንዲቻል 150 ዳንስኞች እና 100የስርከስ ትርኢት ባለሙያዎች 50 የተለያዩ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎች እና የሙዚቃ ተጫዋቾች በዚሁ ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ ተሳትፈዋል::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014