አዲስ አበባ፦ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ከ45ሺ 35 በላይ ለሚሆኑ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት አስተዳደር አመራሮች የብቃት መመዘኛ የጽሁፍ ፈተና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ ፈተናውን ለሚያልፉ የሙያ ፈቃድ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ አሰፋ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የምዘና ፈተናው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በመላው የኦሮሚያ ክልል መጋቢት 9 ቀን2011ዓም የሚሰጥ ሲሆን፤ 129 የፈተና ቦታዎች፣105 ፈታኞች፣28 ተቆጣጣሪዎች በማመቻቸት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡ ፡
በፈተናው ላይ ከሚቀመጡት ከ45ሺ 35 መምህራንና የትምህርት አስተዳደር ኃላፊዎች መካከል ከ45ሺ8 በላይ የሚሆኑት መምህራን፣ ከ1ሺ246 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የትምህርት አስተዳደር አመራሮች ናቸው፡፡ የጽሁፍ ፈተናው በተመረቀበት የትምህርት ዘርፍና በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ምዘናው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ጊዜው ከሚጠይቀው የትምህርት ዝግጅት ጋር እራሱን እያበቃ ለትምህርት ጥራት የሚተጋና በሙያው የሚተማመን መምህርና አመራር ለማፍራት እንዲሁም በመምህራኖቻቸው የሚተማመኑ ተማሪዎች እንዲኖሩ ለማስቻል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ያስረዱት አቶ ዓለማየሁ፤ ምዘናውን አልፎ የሙያ ፈቃድ ለማግኘት 70 በመቶ ውጤት ማምጣት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡
ከአጠቃላይ ውጤቱ 80 በመቶ የጽሁፍ ፈተና፤ 20 በመቶ ደግሞ በሥራ ላይ አፈጻጸማቸው እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ ምዘናው ሶስቴ እንደሚሰጥ የጠቆሙት አቶ ዓለማየሁ በመጀመሪያው አመት ፈተናውን ያለፈ ለሁለት አመት የሙያ ፈቃድ እንደሚያገኝ፣ ከሁለት አመት በኋላ ደግሞ ተመዝኖ የአምስት አመት፣ሶስተኛውን ፈተና ያለፈ ደግሞ ቋሚ የሙያ ፈቃድ እንደሚሰጠው አስረድተዋል፡፡
በእነዚህ ሂደቶች ማለፍ ያልቻለ ሰው ከሙያው ውስጥ የሚወጣበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር የምዘናው አላማ ማባረር አይደለም›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ ምዘናው ክፍተቶችን ለመለየት እንደሚረዳ፣ የመምህራኑን ክፍተት በማየት የመደገፍ ሥራ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከኮሌጆችና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መምህራንና የትምህርት አስተዳደር አመራሩን የማብቃት ተግባር እንደሚከናወን አመልክተ ዋል፡፡
ምዘናው እንደ ስጋት መታየት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡ በአሰራሩ ላይ ቅሬታ ካለ የቅሬታ አቀራረብ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ምዘናው ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው እንደሚገባ፤ ምዘናው ቀጣይነት እንዲኖረው የማበረታታት ሥራ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የተጀመረው ምዘናና የሙያ ፈቃድ የመስጠት ተግባር በሌሎችም ዘርፎች ቀጣይነት እንዳለው አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
ለምለም መንግሥቱ